በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

ተወዳጁ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና “የቃሊቲው መንግስት” በሚል ርዕስ በፃፈው መፅሐፍ እስረኞች በቃሊቲው ማረሚያ ቤት የሚኖራቸውን የህይወት ገፅታ ጨርፎ አሳይቶናል፡፡  ጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን ደግሞ “የቃሊቲ ሚስጥሮች” በተሰኘው መፅሐፉ የቅንጅት አመራሮች በቃሊቲ እስር ቤት በታሰሩ ወቅት እርስ በእርስ ምን እየተባባሉ እንደሚጎናነጡ እንዲሁ ጨርፎልናል፡፡  መቼም የቃሊቲ ጉድ በእነዚህ ሁለት መጽሐፍት ብቻ የሚገደብ እንዳልሆነ ለደቂቃም ቢሆን ግቢውን የረገጠ ይገባዋል፡፡  እናም በአርኪዎሎጂ ጥበብ ከተገኙ ጥንታዊ ከተሞች አንዱን የመሰለ ገፅታ በተላበሰው እስር ቤት ከየትኛውም ብሔር እና የሀገሪቱ ድንበር ያልተወከለ የለም- በእስረኝነት ማለቴ ነው፡፡  አይንህ ኢትዮጵያዊ እስረኛ ማየት ቢደብረው የጃማይካ፤ የስዊድን፤ የስዊዘርላንድ፤ የአሜሪካ፤ የናይጄሪያ፤ የታንዛንያ፤ የኬንያ፤ የሶማሊያ፤ የኤርትራ… ሰዎችን እንደልብህ ታያለህ፡፡  ሌላው በቃሊቲ በመኖርህ የምታገኘው ጥቅም ምን መሰለህ? ዘባተሎ የለበሰ ፈረንጅ እስረኛ በብር ከስሙኒ ብቻ የሚሸጠውን የግቢውን ሻይ እንድትጋብዘው ይጠይቅሃል፤ ይህን ጊዜም ኩራትህ ተራራን ያክላል፤ ቃሊቲ ባትታሰር ግን ይህንን እድል አታገኝም፤ ምንአልባትም ይህንኑ ፈረንጅ አንተው ራስህ ደንበል ሕንፃ ጋ ቆመህ “ሚስተር…” እያልክ ገንዘብ ልትለምነው ትችል ነበር፡፡  ማን ያውቃል? እንግዲህ እነዚህ ሁሉ የተለያየ ታሪክ እና ወንጀል ከቃሊቲ ወንጀል ጋር የተጣቡ ናቸው፡፡

እመነኝ የቃሊቲ ታሪክ መቶ እና ሁለት መቶ መፅሐፍም ቅም የሚለው አይደለም፤ የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ፤ የፍትህ፤ የብልጠት፤ የስግብግብነት፤ የጭካኔ፤ የሀሰተኝነት… ምሽግ ነውና፡፡  በአጠቃላይ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት “እግሩ የጣለው” ወይም “ወንጀሉ የጣለው” አልያም እንደ እኔ “አቃቤ ሕግ የጣለው” ፀሐፊ ሁሉ ተርኮ የማይጨርሰው አስገራሚ፤ አስደናቂ፤ አሳዛኝ፤ አማራሪ፤ አሸፋች … ትርክት ያገኛል፡፡  እነሆም በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለስድስት ቀን ያህል በአቃቤ ሕግ በተጣልኩበት ጊዜ ያየሁት እና የሰማሁትን እነግርህ ዘንድ ወደድኩ፡፡

በቅድሚያ – የ16ኛ ወንጀል ችሎት

“ፍትህ ጋዜጣን” መስርቼ በዋና አዘጋጅነት መምራት ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ በጋዜጣዋ ላይ በሚስተናገዱ ዘገባዎች እና ነፃ ሀሳቦች የተነሳ የሀገሬ መንግስት “ደመኛው” አድርጎኛል፡፡  (አቤት በገዛ መንግስት እንደክፉ ባላጋራ መታየት እንዴት ያሳቅቃል?) በዚህም የተነሳ ከጥቃቅን እስከ ግዙፍ ማስፈራሪያዎች  ( ጥቃቅን ሲባል የመንግስት አነስተኛ የስራ ፈጠራ ዘርፍ ብቻም እንዳይመስልህ፤ ለጋዜጠኞች ተብሎ የሚዘጋጅ ጥቃቅን ሽብሮች አሉና) ወከባዎች፤ የሰላይ ጫናዎች፤ ተደራራቢ ክሶች… የዕለት ቀለቤ ሆነዋል፡፡ …ከዕለታት በአንዱ ቀንም (ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም) ከመአት ክሶቼ ሶስቱ ተመዘው በከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት ለመቅረብ ተገደድኩ፡፡

በዕለቱ ፍርድ ቤት የተገኘሁት ከሁለት ጠበቆቼ ጋር ሶስተ ሆነን ሲሆን፤ ከሳሾቼ አቃቤያን ህግም በተመሳሳይ ቁጥር ሶስት ሆነው ነው የተገኙት፡፡  ከጠዋቱ አራት ሰዓት አካባቢም ችሎቱ ተሰየመ፡፡  ዳኛውም ቦታቸውን ያዙ፡፡  አስቀድሞ አቃቤ ህግ ላቀረበው ክስም መልስ እሰጥ ዘንድ ተጠየኩ፡፡  አንደኛው ጠበቃዬ ለቀረበው ክስ መቃወሚያ ያሉትን ሀሳብ አቀረቡ፡፡  አቃቤያን ህጉም የጠበቃዬን መቃወሚያ እንደኦርኬስትራ ተቀባብለው አጣጣሉት፡፡ ዳኛውም ተደረቡ- የቀረበውን የክስ መቃወሚያም ውድቅ በማድረግ፡፡  አስከትለውም አቃቤያን ህጉ ክሱን ያብራሩ ዘንድ ጠየቁ፡፡  “ሳተናዎቹ” አቃቤያን ህግም ለሶስት እየተቀባበሉ ሶስቱን ክሶች ተገን አድርገው የሀሰት ክሶች ደረደሩ፡፡  ድርዳሬውን ሲያበቁም በዳኛው የእምነት ክህደት ቃሌን ተጠየኩ፡፡  ክሱ ውሸት እንደሆነ እና ያጠፋሁትም ሆነ የጣስኩት ህግ እንደሌለ አስረዳሁ፡፡  ጠበቃዬም ቀጠሉና ከችሎት በዋስ ተለቅቄ የክስ ሂደቱን እከታተል ዘንድ ጠየቁ፡፡   ይህን ጊዜም አቃቤያነ ህግ ተቃውሞአቸውን በእሩምታ አሰሙ፡፡  የተቃውሞ ምክንያታችን ያሉትን ሲያብራሩ “ ተከሳሹ በዚህ ጉዳይ ተከሶ ለፖሊስ ቃል ከሰጠ በኋላ አሁንም የአመጽ ቅስቀሳውን አላቋረጠም” አሉና ሐምሌ 24 ቀን 2004 ዓ.ም. ከ”ፍኖተ-ነፃነት” ጋዜጣ ጋር ያደረኩትን ቃለ-መጠይቅ እንደ ማስረጃ አቀረቡ፡፡  በጣም ደነገጥኩኝ ምክንያቱም አቃቤያን ህግ የያዙት የክስ መዝገብ ራሱ ለፖሊስ ቃል የሰጠሁት ሐምሌ 25 ቀን 2004 ዓ.ም. እንደሆነ በግልጽ ይናገራልና፡፡  ሆኖም ደፋሮቹ አቃብያን ህግ የሐሰት ክርክራቸውን ቀጠሉ፡፡  ሐምሌ 28 ቀን 2004 ዓ.ም. ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረኩት ቃለ-መጠይቅ ሐምሌ 13 ቀን 2004 ዓ.ም. የታገደውን የፍትህ ጋዜጣ ህትመት “በሲዲ ስላለኝ እለቀዋለሁ” ብሎ ዝቷል አሉ፡፡  አሁን ዳኛው ማስረጃ የፈለጉ መሰሉ፡፡  እናም “ጋዜጣው የታለ?” ሲሉ ጠየቁ፡፡  አንደኛው አቃቤ ህግ ጋዜጣውን እንዳልያዙ ተናገሩ፡፡  ይህን ጊዜም እርግጠኛ ሆንኩ፤ ዳኛው “ያለማስረጃ ውንጀላውን አንቀበልም” እንደሚሉ፡፡  ግና! ምን ዋጋ አለው፤ ያለማስረጃ ክስ ቢቀርብም ለዳኛው ምንም ማለት አልነበረምና የችሎቱ ታዳሚ እስኪታዘብ ድረስ ዳኛውና አቃቤያነ ህግ “ሰምና ወርቅ” ሆነው መስራታቸውን አደሩት፡፡  በዚህ መሀል አንደኛው አቃቤ ህግ ከስነ-ስርዓት ውጪ በሆነ መልኩ አዲስ ክስ አቀረበ፡፡  “ይህ ጉዳይ እልባት እስኪያገኝ ድረስ ፍትህ ጋዜጣ ይታገድልን” የሚል፡፡  አሁን በችሎቱ ከተገኙት ውስጥ አብዛኛው ትእግስታቸው በማለቁ ከመገረም አልፈው ማጉረምረም ጀመሩ፡፡  እናም ዳኛው “ክስ በዚህ መልኩ እንደማይቀርብ” ተናግረው አቃቤ ህጉን ይገስፃሉ ብለው የጠበቁ ነበሩ፡፡  እሳቸው እቴ! ምንተዳቸው! ይልቁኑም በመንበራቸው ተመቻቹና ከህገ ደንብ ውጭ ድንገት የእኔ ጠበቆች መልስ እንዲሰጡ ጠየቁ፡፡  (እዚህ ጋር ከኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ጋር በተያያዘ የተነገረ አንድ ቀልድ ትዝ አለኝ፡፡  ነገሩ እንዲህ ነው፤- በድህረ ምርጫ 97 የቅንጅት አመራሮች ተከሰው ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡  ከተከሳሾቹም መካከል ከምስራቅ ጎጃም ተይዘው የመጡ ይገኙበታል፡፡  መንግስትም ለነዚህ ተከሳሾች ከዛው ከምስራቅ ጎጃም የሀሰት ምስክር አምጥቶ ስለነበ ምስክሩ መስክረው ሲጨርሱ ድንገት ከተከሳሾቹ መካከል ከመንደራቸው ወደ አዲስ አበባ ከመጣ አስር አመት ያለፈውን አንድ ጋዜጠኛ ያያሉ፡፡  ጋዜጠኛው የተከሰሰው በሚሰራበት ጋዜጣ ላይ በፃፈው ፅሑፍ መሆኑን የተረዱት አርሶ አደሩ የአቃቤ ህግ ምስክር ችሎቱን እንዲህ ሲሉ በትህትና ጠየቁ “ጌታው! ያያ እከሌ ልጅም እዚህ ስላለ መንግስት ሁለት ጊዜ የአበል እና የትንስፖርት ከሚያወጣ እሱም ላይ መስክሬበት ልሂድ?”)

ከመራራው ቀልድ እንፋታና ወደችሎቱ እንመለስ፡፡  ደህና! አዲስ ለቀረበው ክስም ጠበቆቼ መልስ ሰጡ፡፡  በዚህ መሀል እኔው እራሴ መናገር እንደምፈልግ ገልጬ እንዲፈቀድልኝ ጠየኩ፡፡  ለተከሰሰ የሚሰጥ መብት ነውና ተፈቀደልኝ፡፡  ፍኖተ-ነፃነት ጋዜጣ ላይ ቃለ-መጠይቅ የሰጠሁት ለፖሊስ ቃል ከመስጠቴ አንድ ቀን በፊት እንደሆነ፤ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይም አቃቤ ህጎች “ዝቷል” ያሉት ውሸት እንደሆነና ጋዜጣው መጠቶ እንዲታይ፤ እንዲሁም አንድ ጋዜጣ የሚታገደው ለብሄራዊ ደህንነት አስጊ ዘገባ መያዙ በማስረጃ ሲረጋገጥ ብቻ እነደሆነ የፕሬስ ህጉ በግልፅ የደነገገ መሆኑን ጠቅሼ፤ መታተም ከአቆመ ከአንድ ወር በላይ የሆነ ጋዜጣ፤ ያውም ምን አይነት ዘገባ ይዞ ሊወጣ እንደሚችል ያልታወቀ ጋዜጣን አዘጋጁ ድንገት እዚህ ስለተገኘ ብቻ ይታገድልኝ ማለት “ህገ-ወጥነት” እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አስረዳሁ፡፡   በዚህ መሀል ዳኛው ተጨነቁ፡፡  ትንሽ አንሰላሰሉ እና “እየደበራቸው” መሆኑ በሚያስታውቅ መልኩ “የእገዳ ጥያቄውን ” ውድቅ አደረጉ፡፡  ነገር ግን የዋስትና ጥያቄዬን ከህግ ውጭ “ በልዩ ሁኔታ ከልክለናል” አሉ፡፡ ( ያ ልዩ ሁኔታ ምን ይሆን? ምንስ ማለት ነው?  … ብቻ በችሎት ከተገኙት ውስጥ የገባው አንድም ሰው ያለ አልመሰለኝም) ከዚህ በኋላ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሆኜ እንድከራከር ተወሰነ፡፡  ችሎቱም ለነሐሴ 28 ቀን 2004 ዓ.ም ተቀጥሮ ተበተነ፡፡  እነሆም በእንደዚህ ባለ “ሚስጥራዊ”ሁኔታ በተካሄደ ችሎት ነበር ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለስድስት ቀናት ያህል ያሰለፍኩት፡፡

ከችሎቱ ውጭ

ችሎቱ ዋስትና ከልክሎኝ በመጠናቀቁ በጥቂት ፖሊሶች ተከብቤ፤ በበርካታ የፍትህ አንባቢዎች ታጅቤ በፍርድ ቤቱ ግቢ ወደሚገኘው “አንበሳ ቤት” አመራሁ፡፡  ይህን ጊዜም ከከበቡኝ ሰዎች መሀከል የማበረታቻ ድምፅ መሰማት ጀመረ፡፡  ቀስ በቀስም ድምፁ እየበረታ፤ ጭብጨባውም እየበዛ ሄደ፡፡  ባልተጠበቀ ሁኔታ እየተፈጠረ ባለው ነገር የተደናገጡት ፖሊሶች ህዝቡ ዝም እንዲል እና እንዲመለስ በቁጣ አዘዙ፡፡  ነገር ግን በችሎቱ ድራማ እልህ የተጋባው ሕዝብ የፖሊሶቹን ማስፈራሪያ ችላ ብሎ ጭብጨባውን እና ፉጨቱን ሳያቆም “አንበሳ ቤት” ደረስኩ፡፡  በተለምዶ “አንበሳ ቤት” የሚባለው በፍርድ ቤቱ ግቢ የሚገኝ ጣሪያው ላሜራ ሆኖ ዙሪያ ገባው በብረት ፍርግርግ የተዋቀረ ነው፡፡  የቤቱ አገልግሎት አብዛኛውን ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበው ዋስትና የሚከለከሉ እና ሳይታሰሩ ሲከራከሩ ቆይተው የሚፈረድባቸው እስረኞች ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እስኪላኩ ለሰአታት የሚቆዩበት ቤት ነው፡፡  ቤቱ አንዳንዴም ከወህኒ ቤት የመጡ እስረኞች ችሎት አስኪቀርቡ ለጥበቃ አመቺ ነው በሚል እሳቤ ለማቆያነት ያገለግላል፡፡  እናም ይህ ቤት ስያሜውን ያገኘው በአሰራሩ ስድስት ኪሎ አካባቢ ከሚገኘው “አንበሳ ግቢ” ጋር ሲለሚመሳሰል ይመስላኛል – አንበሳ ቤት፡፡

እኔም ከችሎቱ በቀጥታ ወደ አንበሳ ቤት እንድገባ ከተደረገ በኋላ ከአጀቡኝ ፖሊሶች መካከል አንዱ መዝጊያውን ከውጪ በኩል ቀረቀረውና በትልቅ ጓጉንቸር ቆለፈው፡፡  አሁንም ከፖሊሶች በላይ የተቆጡት የችሎቱ ታዳሚዎች ከውጭ በኩል የአንበሳ ቤቱን ከበው ማበረታታቸውን ቀጥለዋል፡፡  የፖሊሶቹ “ዞር በሉ” ማስፈራሪያም እንዲሁ እንደቀጠለ ነው፡፡  በዚህ መሀል ድንገት በቦታው የነበሩ ጥቂት ጋዜጠኞች ረጅም ጊዜ እስር ቤት ሊቆይ ይችላል ብለው ስለሰጉ ነው መሰለኝ “የምትናገረው የመጨረሻ ንግግር ካለህ ተናገር” አሉና መቅረጸ ድምፃቸውን ለስራ አዘጋጁ፡፡  ከህዝቡ መሀከል በርከት ያሉ ወጣቶች ሞባይላቸውን ደቅነው ጋዜጠኞቹን ተቀላቀሉ፡፡  ግራ ገባኝ፡፡ የምናገረውም ጠፋኝ፡፡  ውስጤን እልህ ተናንቆታል፡፡ የአንበሳ ቤቱን የከበቡት ጋዜጠኞች እና የፍትህ አንባቢዎች ደግሞ የምለውን ለመቅዳት እየወተወቱኝ ነው፡፡ ከጥቂት ማመንታት በኋላ እንዲህ አልኩ፡፡

“የዛሬው የችሎቱ ድራማ ከአምባገነኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ህልፈት በኋላ የመጀመሪያው ነው፡፡  እናም ድራማው አስቂኝም አሳዛኝም ነው፡፡  ግና! አንድ ነገር እርግጠኛ ሁኑ፤ ይኸውም የስርአቱ ግብአተ መሬት እየተቃረበ ለመሆኑ ከምልክቶቹ አንዱ ዛሬ ያያችሁት አይን ያወጣ እና ያፈጠጠ ዳኝነት መሆኑን፡፡”

ከዚህ በኋላ ፊቴን አዙሬ በአንበሳ ቤት ውስጥ ከተደረደሩት ወንበሮች በአንዱ ላይ ጀርባዬን ከቤቱ ባሻገር ለተሰበሰቡት ሰዎች ሰጥቼ ተቀመጥኩ፡፡  ይህን ጊዜም እስካሁን ድረስ ያላስተዋልኩት አንድ እስረኛ ከእኔው ጋር በዛች ቤት መኖሩን ተረዳው፡፡  እድሜው በግምት አርባዎቹ መጨረሻ ላይ ይሆናል፡፡  ቁመቱ እንደሸንበቆ የተመዘዘ ቢሆንም ኑሮ ደህና አድርጎ እንዳጎሳቆለው ያስታውቃል፡፡  ንትብ ያለ ውሃ ሰማያዊ ጃኬት እና አዳፋም ጥቁር ሱሪ ለብሷል፡፡  ጫማውም ቢሆን ብዙ ቦታ የተጣጠፈ፤ ቀለሙ ታይቶ የማይታወቅ አሮጌ እስኒከር ነው፡፡  ቀና ብዬ አየሁት፡፡  ፈገግ አለና የአንገት ሰላምታ ሰጠኝ፡፡  በርከት ያሉ ሰዎች አብረውኝ በመምጣታቸው ግራ የተጋባ ይመስላል፡፡  ፈጠን ብዬ ሰላምታውን ሞቅ ባለ ሁኔታ መለስኩለት፡፡  በሰላምተዬ ምላሽ ተበረታቶ ነው መሰለኝ “እነዚህ ሁሉ ጓደኞችህ ናቸው ?” የሚል ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡  “አዎን” ስል መለስኩለት፡፡  “አይዞህ” አለኝ፡፡ (ይች “አይዞህ” ለእስረኛ እንዴት አይነት ስንቅ መሰለችህ?)

የሆኖ ሆኖ እኔና የአንበሳ ቤት ጓደኛዬም እንደዋዛ ወደ ጭውውት ገባን፡፡

“ምን አድርገህ ነው የመጣኸው?”  ፊቱን አጨልሞ ባለቤቱ ከስሳው እንደሆነ ነገረኝ፡፡

“ለምን ከሰሰችህ?”

“አንድ ልጅ ወልደን ተለያይተናል፡፡  እናም ልጁን ማሳደጊያ ገንዘብ አይረዳኝም ብላ ነው የከሰሰችኝ”

“አንተ ለምን አትረዳትም?”

“ስራ የለኝም ነበር በቅርቡ ነው ስራ ያገኘሁት”

“ታዲያ ስራ ከጀመርክ ለምን አትረዳትም?”

“ከደሞዜ ላይ ተቆራጭ ላደርግላት ተስማምቼ ነበር፡፡  እነሱ ግን እንድሰጣት የወሰኑብኝ ብር ከአቅሜ በላይ ነው፡፡”

“ችሎት ቀርበህ ነበር እንዴ?”

“አዎን ቅድም ቀርቤ ለከሰአት ተቀጥሬአለሁ”

“ለምን?”

“ዳኛው የወሰኑት በወር መቶ ብር እንድሰጣት ነው፡፡   እኔ ደግሞ ያንን መስጠት አልቻልኩም፡፡  እናም ፍርድ ቤቱ እንድታሰር ወስኗል፡፡”  (…እግዞ መቶ ብር የሌለው ሰው ወደ እስር ቤት የሚላክበት ሁኔታ ከዚህ ሀገር በቀር የት ይገኝ ይሆን? ኢትዮጵያ እጆቿን የምትዘረጋው ወዴት ይሆን? ወደ አሜሪካ ወይስ አረብ ሀገር?)

“እየሰራህ ከሆነ ለምንድነው መቶ ብር መስጠት ያቀተህ?”

“አልገባህም!  እኔ ስራ ከጀመርኩ ገና 18 ቀኔ ነው፡፡  እነሱ ደግሞ ዛሬውኑ ገንዘቡን መስጠት እንድጀምር ወጥረው ያዙኝ፤  ደሞዝ እስክቀበል ታገሱኝ ብል ሊሰሙኝ አልቻሉም፡፡”

ይህን ጊዜ ትንሹ ወንድሜ በርገር እና የታሸገ ውሃ ይዞ ጠራኝ፡፡  የመጀመሪያውን የእስር ቤት ስንቅ እጄን በፍርግርጉ አሾልኬ ተቀበልኩ፡፡  ከመጀመሪያው እስረኛ ጓደኛዬም ጋር ተካፍለን መመገብ ጀመርን፡፡  ተመግበን እንደጨረስንም የተለያዩ ወዳጆቼ እና የማላውቃቸው የፍትህ አንባቢዎች በፍርግርጉ በኩል እየመጡ “ሞራል እና የስንብት ቃል” መስጠታቸውን ስለጀመሩ ከእስረኛው ጓደኛዬ ጋር የጀመርኩትን ወግ መጨረስ አልቻልኩም፡፡

በእንዲህ አይነት ሁኔታም በግምት ለሁለት ሰአት ተኩል ያህል ከቆየሁ በኋላ ፖሊሶቹ ጓጉንቸሩን ከፍተው ከአንበሳ ቤቱ እንድወጣ አድርገው ወደ ዋናው የፍርድ ቤቱ በር አካባቢ ከወሰዱኝ በኋላ ፊቷን ወደ መውጫው በር አዙራ የቆመች አንዲት የደከመች የፖሊስ ነጭ ሚኒባስ ውስጥ ከተቱኝ፡፡  ይህን ጊዜም ለአንዴ እና ለመጨረሻ ስንብት ፍርድ ቤት የተሰበሰቡትን ቤተሰቦቼን፤ ጓደኞቼን፤ ባልደረቦቼን እና የፍትህ አንባቢዎችን በሚኒባሱ መስኮት እጄን አውጥቼ ሰላምታ ሰጠዋቸው፡፡

መኪናዋ መንቀሳቀስ ጀመረች፡፡  በሶስት ፖሊሶች ታጅቤም ከፍተኛውን ፍርድ ቤት ለቀቅን፡፡  ሆኖም ሚኒባሷ ከልደታ ቤተ ክርስቲያን ከፍ ብሎ ከፍርድ ቤቱ ፊት ለፊት በሚገኘው አስፓልት ቁልቁል በመውረድ ሳር ቤት ከደረስን በኋላ በአቋራጭ ቃሊቲ የሚያደርሰንን መንገድ ከመያዝ ይልቅ ወደ አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ አመራች፡፡   ከጥቂት ደቂቃዎች ጉዞ በኋላ ፖሊስ ጣቢያው በር ላይ ደረስን እና ከበር ላይ ቆምን፡፡  ጋቢናው የተቀመጠው ልጅ እግር ፖሊስም ከመኪናው ወርዶ ወደ ጣቢያው ገባ፡፡  ይህን ጊዜም በር ላይ የቆሙ የጣቢያው ፖሊሶች ለጥበቃ ካጀቡኝ ፖሊሶች ጋር የወዳጅነት ሰላምታ ተለዋወጡ፡፡  በዚህ መሀል አንዱ ፖሊስ አንገቴ ላይ በጠመጠምኩት “ስከርፍ” አማካኝነት ያወቀኝ መሰለ፡፡  ማንነቴንም ማወቁንም በፊት ገጽታው እየነገረኝ ወደ ተቀመጥኩበት ወንበር ተጠግቶ “አውቅሃለው! ተመስገን አይደለህ?” አለኝ ጓደኞቹ እንዳይሰሙት ድምጹን ዝቅ አድርጎ፤ አንገቴን በመነቅነቅ አረጋገጥኩለት፡፡  ምን አድርጌም እንደሆነ ጠየቀኝ፡፡  ወዴት እየሄድኩ እንደሆነም ገብቶታል፡፡  ነገርኩት፡፡  ጥቂት እንደመከፋት አለና ጣቱን ወደ ሰማይ ቀስሮ “አይዞህ እግዚአብሔር አለ” አለና አበረታታኝ፡፡  በዚህ መሀል ወደ ውስጥ የገባው ፖሊስ በሌሎች ሶስት ፖሊሶች የታጀቡ በግምት እድሜያቸው አሰራ ስምንት አመት የማይሞላቸውን ሶስት እስረኞችን ከእኔ ጋር ስለቀላቀሏቸው የአምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ጉዳይ እንደተጠናቀቀ የገባው ጎልማሳው የሚኒባሱ ሹፌር ሞተሩን አስናሳ፡፡  ጉዞ ወደ ቃሊቲ ሆነ፡፡

ከፊት ለፊቴ ለተቀመጠው ፖሊስ ወንድሜ ልብስ ይዞ ክራውን ሆቴል አጠገብ ስለሚጠብቀኝ ስንደርስ እንድቀበለው መኪናውን በማቆም ይተባበሩኝ እንደሆነ ጠየኩት፡፡  የጠየኩት ፖሊስ ከመመለሱ በፊት ጋቢና የተቀመጡት ሁለቱ ፖሊሶች እና ሹፌሩ ምንም ችግር እንደሌለው እና እንደሚተባበሩኝ ተደራርበው መለሱልኝ፡፡  አመስግኜ ትኩረቴን ከመኪናው ውጪ አደረግኩ፡፡  በግምት ከሰላሳ ደቂቃ በኋላም ክራውን ሆቴል ደርሰን መኪናው በሩ ላይ ቆመ፡፡  ወንድሞቼ ከእኛ ቀድመው በመድረስ ፍራሽ፤ ብርድ ልብስ እና አንሶላ ይዘው እየጠበቁኝ ስለነበር ጊዜ ሳላጠፋ ተቀብያቸው ጉዟችንን ቀጠልን፡፡  ከጥቂት ደቂቃ በኋላም ከሀገሪቱ በስፋት ተስተካካይ ወደሌለው አስቀያሚ እስር ቤት በር ላይ ደርሰን ሹፌሩ ደጋግሞ ጡሩንባ ያሰማ ጀመር፡፡  የእስር ቤቱ ዋና በርም ከውስጥ ወደ ውጭ ወለል ብሎ ተከፈተና ሚኒባሷ ገባች፡፡  ከፍርድ ቤት አጅበው ያመጡኝ ፖሊሶችም ለቃሊቲ ፖሊሶች አስረክበውኝ ሲያበቁ ርክክቡን የሚያረጋግጥ ደረሰኝ ተቀብለው ሞቅ ባለ ፈገግታ ተሰናበቱኝ፡፡

ይቀጥላል

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here