የኢትዮጵያ ሕዝብ ለኢህአዴግ ሕግጋት የሙከራ አይጥ ነው?

አባይ ሚድያ

“Think out of the box!“ የሚባል ሐረግ ሁላችሁም ሳትሰሙ አልቀራችሁም። ይሄን ወሰን የለሽ የአስተሳሰብ ግብዣ በሰዎች ንግግር መሃል፣ በውጭ ሚዲያዎችና ፊልሞች ውስጥ ደጋግመን እንሰማዋለን። ምናልባትም የቅርብ ጓደኛዎ ጠበብ አድርገው ያሰቡትን ጉዳይ “ሠፋ አድርገው” እንዲመረምሩት በመፍቀድ ግፊት አሳድረውቦት ይሆናል። ጉዳዩን በተለመደው ዓይንዎ ብቻ ማየቱን ትተው በሌሎችም ማዕዘናት እንዲያጤኑት የሚመክርዎ ሰው የአስተሳሰብ ነጻነትዎን ገደብ አልባ ያደርገዋል። ብዙዎች ለጥልቅ አስተሳሰብዎ ክብር ይሰጣሉ።

ከኢህአዴግ በቀር!

ኢህአዴግ ብቻ ነው የአስተሳሰብዎ አድማስ ሲያጥር የሚደሰተው። ኢህአዴግ ሰው በጥልቅ ዕውቀት ሲያስብ አይወድም። ኢህአዴግ ሰው ሲማር፣ ሲያውቅና ሲመራመር ምቾት አይሰማውም። ኢህአዴግ ማለት ሌላው “ኬመር ሩዥ” ነው። ኢህአዴግ ከዚህ ኬመር ሩዥ ከተባለው ፈሪ የካምቦዲያ አምባገነን በተለይ አንድ ድርጊት የወሰደ ይመስላል። ኬመር ሩዥ ነጭ መነጽር ያደረገ ዜጋ በካምቦዲያ እንዲኖር ፍላጎት የለውም። ነጭ መነጽር ያደረጉ ሁሉ የተማሩና የተመራመሩ ስለሚመስለው ያስፈሩታል፡፡ በወታደሮቹ ታድነው እንዲገደሉ በማድረግ አቻ አልተገኘለትም ነበር።

ዛሬ ለሱ አቻ የሆነ መንግስት ቢኖር ኢህአዴግ ነው። በርግጥ ኢህአዴግ የተማሩ ዜጎችን አድኖ ሕይወታቸውን አያጠፋም። ኢህአዴግ የተማረን ዜጋ ከመግደል ይልቅ አስተሳሰቡን መገደብ ላይ ነው ያተኮረው። የአስተሳሰብ ነጻነቱን ማጥፋት። ኢህአዴግ ያለውን ሁሉ ሕዝቡ እንዲያምንና እንዲደግመው በማድረግ ዜጎችን ሁሉ የጋሪ ፈረስ አድርጓቸዋል። የጋሪ ፈረስ ከአንድ አቅጣጫ ውጭ ሌሎች ማዕዘናትን የማየት ዕድል የተነፈገው ግራና ቀኙን እንዳያይ በመጋረጃ ተከልሎ ነው። ፈረስ ፈጣሪ የሰጠውን የማየት ጸጋ ሰዎች አጠበቡበት። የኢትዮጵያ ሕዝብም ፈረስ ካጣው ዙሪያውን የማየት መብት በላይ ተጥሶበታል። ዜጎች ሕጉ እንደሚሰብካቸው ዓይነት የማሰብ ነጻነት የላቸውም፤ ሕጉ መናጢ ድሃን እንደሚያማልሉ የአክሲዮን ማስታወቂያዎች ሩቅ ነው። ዜጋ ሁሉ ኢህአዴግ የመረጠለትን አቅጣጫ ብቻ ተከትሎ ነው እንዲያስብ የተፈቀደለት።

 “ማይንድ ኮንትሮል” የምትባለውን ጨዋታ ኢህአዴግ በደንብ ያውቃታል። አንድ ውሸት ደጋግሞ በመነገሩ ብቻ ወደ እውነትነት የመለወጥ ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ኢህአዴግ ያውቃል። የሚጠቀምባቸው ሚዲያዎች ሁሉ የኢህአዴግን ዲስኩሮች መደጋገም አይሰለቻቸውም። ዜጎች ደጋግመው በሰሙት ዲስኩር ተጠልፈው የመውደቅ ዕድላቸው ሠፊ ነው። ኢህአዴግ 21 ዓመታት ሙሉ ሲደጋግመው የነበረውን ዲስኩር የማምለጥ ዕድሉ ያለው ዜጋ በጣም ትንሽ ነው። ከኢህአዴግ በኋላ የተወለዱ ልጆች ግን ሙሉ በሙሉ ከመስመጥ አያመልጡም። በኢህአዴግ ዲስኩር ተጠምቀው የወጡ የእንጀራ ልጆቹ ይሆናሉ።

ሕዝቡ እንዲነቃ ኢህአዴግ ፍላጎት የለውም። ዜጎች ከነቁ መብታቸውንና ነጻታቸውን መጠየቅ ይጀምራሉ። ይሄ መሰረታዊ ጥያቄ ኢህአዴግን ከሳንባ ካንሰር በላይ ያስፈራዋል። መተንፈስ አይችልም፡፡ አንድ ዜጋ የመናገር ነጻነቱን በጠየቀ ቁጥር ኢህአዴግ ሳንባውን ትክ ትክ ይይዘዋል፡፡

ለዚህም ነው ኢህአዴግ ዜጎች የመናገር ነጻነታቸውን ረግጦ ለመያዝ ሲል በየሰበቡ ሕግጋት ማውጣት የሚያበዛው፡፡ አዳዲስ ሕግ ማውጣት ለኢህአዴግ ልክ ከግምጃ ቤት የታሸገ ደስጣ ወረቀት እንደማውጣት ቀላል ነው፡፡ ወይም ከመደርደሪያ ላይ መጽሐፍ መርጦ የማውረድ ያክል ተራ ሥራ ነው፡፡

ሰሞኑን በየዜጋው እጅ በተለይ በመንግስት ሠራተኛው አካባቢ ከተገኙ የኢህአዴግ በራሪ ወረቀቶች ውስጥ አንደኛዋ ከላይ ለመናገር የሞከርነውን ሐሳብ የምታጎላ ናት፡፡ የወረቀቱ መልዕክት ያነጣጠረው ወጣቱ የአዲስ አበባ ነዋሪ ላይ ይሁን እንጂ ጉዳዩ በተዘዋዋሪ ሁሉንም ዜጋ የሚመለከት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የወረቀቱ ጽሁፍ ሲጀምር የተወሰኑት ወጣቶች በአገሪቱ ዕድገት ተጠቃሚ ሆነዋል ይላል፡፡ ነገር ግን በሥፋት የሚገኘውን የሥራ ዕድል ተጠቅመው ራሳቸውን መለወጥ ያልፈለጉ በርካታ ወጣቶች በዓይማኖት ሽፋን በሚፈጠሩ የ”ሽብር” ተግባራት ላይ የሚንቀሳቀሱ ያክል እንደሚቆጠር ጠቆም ለማድረግ ፈልጓል፡፡

ነገሩ ያው ነው፤ የመብት ጥያቄ ያነሳ ወጣት “ሽብርተኛ” ተደርጎ ይፈረጃል ለማለት ነው፡፡ ስለዓይማኖትህ ብትከራከር “አክራሪ” ትባል ይሆናል፡፡ አክራሪ የሚለውን ስም ግን ኢህአዴግ አይሰጥህም፡፡ ኢህአዴግ “ሽብርተኛ” ነው የሚልህ፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ ሕግ ያወጣው ለሽብርተኛ እንጂ ለአክራሪ አይደለም፡፡ በርግጥ ለኢህአዴግ ስያሜህ ማንም ይሁን ማን ጉዳዩ አይደለም፡፡ ጸቡ ከስያሜህ ሳይሆን ከጥያቄህ ነው፡፡

የሰው ልጅ መብቱን አይጠይቅም፤ መብት ከሌሎች በችሮታ የሚገኝ ሳይሆን የተፈጥሮ ስጦታ ነው፡፡ የሰው ዘር ሁሉ እኩል ሐብት ነው። ስለዚህ ሕጎች ሁሉ ሰው የዜግነት መብቱን ሳይጠይቅ ለመጎናጸፍ ይችላል ይላሉ፡፡ የኢህአዴግ ሕግጋትም ይሄንን ይሉታል፡፡ ተግባራዊ ማድረግ ነው ሞታቸው፡፡

የተፈጥሮ መብታቸውን ለመጠየቅ የደፈሩ ጥቂት ዜጎች የኢህአዴግ ቁጣ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ኢህአዴግ ደም እንደጠማው ቫምፓየር ነጻነታቸውን ከውስጣቸው ጠጥቶ አንዱ ጥግ ወርውሯቸዋል፡፡ የእስከዛሬው ልምድ እንደሚያሳየን ነገ ኑሮ ከበደኝ የሚል ዜጋ ቢሰማ ኢህአዴግ አዲስ ሕግ አውጥቶ ከባድ ፍርድ ይጥልበታል፡፡

ነገ አንዲት ሴት የኢህአዴግ ባለስልጣን አስገድዶ ደፈረኝ ብትል ለአዲስ ሕግ ማሟሻ ትሆናለች፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸው ፍጹም ከክፍያ ነጻ የሆነ የትምህርት ዕድል ይሰጥልን ብለው ቢሰባሰቡ ለልጆቻቸውም የሚተርፍ አዲስ ሕግ መውጣቱ ግልጽ ነው፡፡

ከቀደመው “የአደገኛ ቦዘኔ” ሕግ ጀምሮ እስከ ቅርቡ “የአሸባሪ መቅጫ ሕግ” ድረስ የኢህአዴግ ሕግ የማውጣት ሱስ ከፍርሃት የመነጨ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ቦዘኔ ተብለው ከመርዝ ጋዝ ቀጥሎ በአደገኛነት የተፈረጁት ወጣቶች ጥያቄአቸው ምን ነበር? … በልቶ የማደር መብት ነበር!!

ከአልሸባብ ወታደሮች እኩል አሸባሪ ተብለው የተፈረጁት ወጣቶች ምንድን ነበር ጥያቄአቸው? … መንግስት በዓይማኖታዊ ጉዳያቸው ውስጥ ጣልቃ አይግባ!!

ዜጎች “መብቴን ብጠይቅ ሕግ ይረቅብኛል” እያሉ በፍራቻ ተሸማቀው የሚኖሩ ከሆነ የማሰብ ነጻነታቸው ተቀብሯል ማለት ነው፡፡ “የአንድ ሀገር ዋነኛና ትልቁ ሀብት ለም አዕምሮ ያለው ሕዝብ ነው” ብሎ የሚናገር ጠ/ሚኒስትር በተቃራኒው አስተሳሰብ ሲገድል ሰንብቷል፡፡ የሚናገረው ሁሉ የሚተረጎምብት፣ የጠየቀው ሁሉ የሚያስፈርጀው፣ … ከሆነ የሕዝብ አዕምሮ እንዴት ይለማል?

“ጠጥታችሁ አታሽከርክሩ፣ ካሽከረከራችሁ ትቀጣላችሁ!” የሚለውን ሕግ የሰለጠኑ ሀገራት ዜጎች በሙሉ አይቀበሉትም፡፡ የተወሰኑት ማስተካከያ እንዲበጅለት ይፈልጋሉ፡፡ መንግስታቸው ጠጥተው ማሽከርከር የሚችሉበት የተለየ መንገድ መስራት ግዴታው ነው ይላሉ። እነሱ ደግሞ የፈለገ ጠጪ ሰካራም ይሁኑ እንጂ እንደዜጋ ግን ግብር የመክፈል ግዴታቸውን ተወጥተዋል፡፡ ስለዚህ በነሱ አስተሳሰብ የነሱ ድርሻ ግብር መክፈልና መብታቸውን ማወጅ ሲሆን የመንግስት ድርሻ ደግሞ የዜጎችን ፍላጎት መፈጸም ነው፡፡

ያልተገደበ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የሌለው ሰው አርቆ ማሰብ አይችልም፡፡ አርቆ ማሰብ የማይችል፤ እንዲችል ተደርጎ ያልተቀረጸን ሕዝብ እየመራ የትኛውም መንግስት ከጫፍ መድረስ አይችልም፡፡ ከፋም ለማም ሕዝብ የፈለገውን የመናገርና የመጠየቅ መብት አለው፡፡ መብቱን ከጎኑ ካላገኘው መንግስት ነጥቆታል ማለት ነው፡፡ መብቱ የተነጠቀ ሕዝብ ደግሞ ተገዶ ባሪያ መሆን ጀምሯል ያስብላል፡፡

አንድ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለኢህአዴግ ግራ የተጋቡ ሕግጋት የሙከራ አይጥ መሆኑ የታከተው ጊዜስ?

አንድ ወቅት የባሪያ አብዮት የተነሳ ጊዜስ?  የወሰደውን የሕዝብ መብትና ነጻነት ከመመለስ ውጭ አማራጭ ያጣ ጊዜስ ኢህአዴግ ምን ይላል? … ለዜጎች “Think out of the box!” ብሎ ከልቡ ይፈቅዳል?

ከፈቀደ እንዲህ መባሉ አይቀርም፤ ‘’ WE DON’T NEED A BOX !!’’ /ወሰን አያስፈልገንም!!/

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here