ሕግ አስከባሪ የሌላቸው የኢህአዴግ ሕግጋት

ወንጀለኛ ዳኞች፤

Frehiwot Tadesse shot 18 times by her husband in Addis Abeba.

[አባይ ሚድያ]

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከተሰሙት አስደንጋጭ ዜናዎች መካከል አንዱ ነው፣ ሴትየዋ ላይ የዘነበው የተኩስ እሩምታ፡፡ እንደእማኞች ቃል ከሆነ ሴትየዋ እናቷን ይዛ በመኪናዋ ገዳይዋን ለማምለጥ እየበረረች ነበር፡፡ መንገዷ ላይ የገጠማትን ማንኛውንም ፖሊስ ከመልአከ ሞት እንዲያስጥላት ለመጠየቅ ነበር የምትበረው፡፡

ቢሆንም መንገዱ ሁሉ እንኳን የጥበቃ ፖሊስ ቀርቶ የትራፊክ ፖሊስም አይታይበትም፡፡ ምናልባት የፖሊስ አባላት ሁሉ ከጸሐይዋ ለመጠለል ጥላ ሥር ሸሸግ ብለው ተቀምጠው ይሆን? … በዚያ ላይ መንገዱ በተሸከርካሪ እጅግ ተጨናንቆ ስለነበር ከኋላዋ የሚከተላትን ሞት ለማምለጥ የሚያስችላት አልነበረም፡፡ የምትችለውን ሁሉ ተጣጥራ ሁለት ጎስቋላ ፖሊሶች ጋር ደረሰች አሉን እማኞች፡፡ ልክ በዛው ሰዓት ታዲያ ሞት ከኋላዋ እኩል ደረሰ፡፡

ምስኪኗ ሴትዬ ላይ 18 ጥይቶች አፈሰሰባት፤ በአደባባይ!! ፖሊሶቹ ፊት!! ከ18 ጥይቶች ውስጥ የተወሰኑትን እንኳ ለማስቀረት አልቻሉም በአካባቢው የነበሩት ሕግ አስከባሪዎች፡፡ ቀጥሎ ገዳይ ወደሟቿ እናት ተጠግቶ በአንዲት ጥይት “ብቻ” መትቶ ጣላቸው፡፡ ሌሎች ሁለት ሰዎችንም በጥይት አቆሰለ፡፡ ፖሊሶቹ እናቲቱን እንኳ ማስጣል አልቻሉም፡፡ ምናልባት ከጥይቱ ዝናብ ለመጠለል ጥላ ሥር ሸሸግ ብለው ይሆን?

ግዳይ የጣለ የመሰለው ነብሰ ገዳይ ባዶ መሣሪያውን ጥሎ እንዲህ በማለት እጁን ለአካባቢው ሰዎች ሰጠ፡፡ “የገደልኩት ሚስቴንና እናቷን ነው፤ ልጆቼን እንዳላይ ከልክለውኛል፡፡ ሞት ይገባቸዋል፡፡”

አዎ! ሕግጋት እንጂ ሕግ አስከባሪ በሌለባት ኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀለኞች ፈራጅ ቢሆኑ አይገርምም፡፡ ተራው ወንጀለኛ ቀርቶ ቱባዎቹ ወንጀለኛ ባለሥልጣናትስ እስኪፈረድባቸው ይፈርዱ የለ!?

የተበታተነ አንድ ሬሳ

ባለፈው ሰሞን ደግሞ የአንድ ግለሰብ የሰውነት አካላት በተለያየ ቦታ ተበታትነው ተገኝተው ነበር፡፡ ግለሰቡ በአውሬ ተቦጫጨቀ እንዳይባል በስለት የተቀረጣጠፈ፣ በወግ በወጉ ተቆራርጦ በየቦታው የተጣለ መሆኑን ምስክሮች ያምናሉ፡፡ ሬሳውን ለቃቅሞ እንደልጆች ጌም መሰካካቱ የተነገረለት የፖሊስ ምርመራ ክፍል /አባዲና/ አካላቱ የአንድ ሰው ናቸው ብሏል፡፡

በርግጥ ይሄ ሟች ግለሰብ የተበታተነ ሰውነቱን የሚሰበስብለት ፖሊስ አግኝቷል፡፡ ሕይወቱን ለመታደግ የቻለ ሕግ አስከባሪ ግን ሲናፍቀው ቀርቷል፡፡ ነብሰ ገዳዬች የምስኪኑን ሥጋ እንደቄራ ሥጋ ሲከፋፈሉት የኢህአዴግ የፖሊስ ኃይሎች የት ነበሩ? ሥጋውን ተሸክመው በየቦታው ሲጥሉ ያያቸው አንድ ንቁ ፖሊስ እንኳ በሥፍራው አልነበረም፡፡

ጥቅሱ ለማነው? ላኪውስ ማነው?

በተለይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተወሰዱ ጥቅሶችን በርካታ ሰዎች በየጀርባቸው አዝለው በአደባባይ ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ፡፡ “አንድ ዓይማኖት፣ አንድ ሀገር፣ አንድ ሕዝብ” የሚለው ጥቅስ ግን ከየትኛው መጽሐፍ እንደመጣ ባይታወቅም በኦርቶዶክስ ተከታዮች ዘንድ አንጋፋ መፈክር ሆኗል፡፡ ከግማሽ ዓመት በፊት የመለስ ዜናዊ ምክር ቤት “ይሄ ጥቅስ ከሕገ መንስግስታችን ጋር የሚጋጭ ነው” ሲል ተሰምቶ ነበር፡፡ ይሄን ለማለት የተገደዱት የሙስሊሙ ማኅበረሰብ የኢህአዴግን ጣልቃ ገብነት በግልጽ ዳር እስከ ዳር መቃወም በጀመረበት ጊዜ ነው፡፡ በርግጥ “ዓይማኖታዊ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም” ይበሉ እንጂ በየአደባባዩ የሚታየው ጥቅስ ግን የሙስሊሙን ማኅበረሰብ የሚያስቀይም ነው፡፡

ይህን በፎቶው ላይ የጥቅስ ቲሸርት ለብሶ የምታዩት ወጣት የመንግስትን ችላ ባይነት በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ “…ንጉስ እዝቅያስ መስገጃዎችን አስወገደ፤ ሐውልቶችንም ሰባበረ፣ የማምለኪያ ዐፀዶችንም ነቃቀለ፡፡ … “ ይላል የጀርባው ጽሑፍ፡፡ ይሄን ጠብ ያለሽ በዳቦ የሆነ ጥቅስ እያስነበበ ሕዝብ በሚሰበሰብበት ቦታ ሁሉ ሲንቀሳቀስ የሕግ ሰዎች አላዩትም? …ዓይማኖቶችን ሁሉ እኩል የሚጠብቅ ሕግ በሀገሩ ውስጥ እንዳለ ሕግ አውጪዎችና ተርጓሚዎች ይሰብኩናል፡፡ … ታዲያ ሕግ አስከባሪው ወዴት ነው ያለው? … ወይስ የኢህአዴግ መንግስት ሕግን ለጥቅስ ብቻ ይሆን የሚፈልገው?

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here