አብዶ ኑር የሱፍ (ኖርዌ)

ዛሬ ነገ ሳንል መነሳት የዜግነት ግዴታችን ነው!

ከአብዶ ኑር የሱፍ (ኖርዌይ)

ለቀድሞው  የወያኔ  ጠቅላይ ሚኒስትር  ለጊዜው ኳሷ በእሳቸው ቁጥጥር ስር  እንደሆነች  እና  የኢትዮጵያ  ህዝብን  ፍላጎት  ማክበር አለበለዚያም የኢትዮጵያ ህዝብ እና ታሪክ ጠላት ሆነው የመቀጠል ሁለት ምርጫ እንዳላቸው  በኢትዮጵያ ምሁራን  በየአቅጣጫው  ቢነገራቸውም ፤  በማን አለብኝነት ኳሷን  ባለማከፋፈል ችግር ፣ እኔ ብቻ በኳሷ  እንደፈለኩ  ከ

ምፈልገው  ወገን ጋር  ልጫወትባት ፣ ስለ ኳሷ አትጠይቁኝ ፣ ወደ ኳሷም አትጠጉ በማለት ቀይ መስመር በማስመር እና እኔ ብቻ አውቃለሁ በማለት  በ 80 ሚሊዮን ህዝብ  ራእይ  እና  ተስፋ  ላይ  እንደቀለዱ  እንዲሁም  ስልጣን  ላይ  ሙጭጭ እንዳሉ  እና  ኳሷን ያለአግባብ  በቁጥጥራቸው  ስር  በማዋል  ብሎም  የኢትዮጵያ ህዝብ  መተንፈስ እንኳን እንዳይችል  አድርገው  በፍርሃት አስረው  በማስቀመጥ  በማን አለብኝነት ጢባ ጢቦ  እየተጫዎቱ  ባሉበት ወቅት  ባልትጠበቀ ሁኔታ  ጊዜው ደርሶ  ወደ ማይመለሱበት  አለም አምልጠዋል  ፡፡ በስሩት ወንጀል  በአለም አቀፍ  ፍርድ ቤት  ሳይጠየቁ  ማምለጣቸው   ቢያስቆጭም ፡፡

በአሁኑ ሰአትስ ኳሷ የት እና  በማን ቁጥጥር  ስር  መዋል ነበረባት? የኳሷ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ  ወደ ኳሷ  መጠጋት  ለምን ፈራ ? የኢትዮጵያን ህዝብ  ነፃነት  ለመጎናፀፍ  እንነሳ  ብሎ   በሃገር ውስጥ  ለህዝቡ  የክተት  ጥሪ  የሚያቀርቡለት ጠንካራ  የተቃዋሚ  ድርጅቶች ለምን  ጠፉ ? ለሚሉት ጥያቄዎች  መልስ  አልተገኘም ፡፡ እንደ  እኔ  አመለካከት አሁንም ኳሷ በህዝቡ  ቁጥጥር ስር መዋል  እያለባት፤ ማንም  ኢትዮጵያዊ ደፍሮ ኳሳችንን አቀብሉን  የሚል ጥያቄ ባለማቅረቡ እና ማንም ወደ ኳሷ  መሄድ ባለመቻሉ አሁንም

ኳስ ጨዋታ ወደማይችለው እንዲሁም ራስ ውዳድ ወደ ሆነው የወያኔ   ቡድን በድጋሚ እና በሚያስቆጭ ሁኔታ በቁጥጥራቸው ስር ትገኛለች፡፡ በዚህ ታሪካዊ እድል ተጠቃሚ ባለመሆናችን ተጠያቂው ማን ይሆን ?

ከሰውየው ሞት በኋላ የምናያቸው እና የማናያቸው የስልጣን ሽኩቻዎች በአስገራሚ ሁኔታ እየተካሄዱ  ይገኛሉ፡፡ በተለይ በስልጣን ‘ሽግግር’ ላይ ህወሓት ባላስቡት ሁኔታ ከፊት ለፊት በመቀመጥ ሃገርን ለማተራመስ እና የነበረውን አምባገነናዊ አገዛዝ ከቆመበት ለማሰቀጠል አልቻሉም፡፡ ከፊት ያልተቀመጡት እና  የህወሓት  የቀድሞ ታጋዮች ወደ ስልጣን ያልወጡበት ምክንያት ደግሞ የኢትዮጵያን ህዝብ በመፍራት ወይም ህገ መንግስቱን በማክበር ሳይሆን  የምእራባዊያንን ተፅኖ በመፍራት  እንዲሁም ከፊት የሚቀመጡት ግለሰብ  የህወሓት  አባል ባይሆኑም  በህውሃቶች  የአእምሮ  ቅኝ  ግዛት  የተገዙ  ስለሆኑ እና  ከጀርባ  በመሆን  እንደ  አሻንጉሊት እንደ ፈለጉ ሊያሽከረክሯቸው  እንደሚችሉ እርግጠኛ  በመሆናቸው ነው፡፡

በታሪካዊ አጋጣሚ ፊት ለፊት ከተቀመጡት አሻንጉሊቶች በስተጀርባ ቀንዳም እና ነብሰ ገዳይ የሆኑት የህወሓት አውሬዎች አፈ ሙዛቸውን ደግነው በጥንቃቄ አሻንጉሊቶቹን ቀን ከሌሊት ይከታተላሉ  እንዲሁም ትእዛዝ ያስተላልፋሉ፡፡ እነዚህ ነብሰ ገዳይ የማፊያ  ቡድኖች  ስልጣኑ  ከእጃቸው እንዳይወጣ  የሚፈልጉበት ዋናው ምክንያት  ሃገር  እና  ህዝብን  በመውደድ በፍቅር ለማስተዳደር  ሳይሆን  ስልጣን  የሃብት ምንጭ  እንደሆነ ካለፉት የህወሓት ቱባ ባለስልጣኖች  ስለተማሩ እና ጠንቅቀው ስለሚያውቁት   ነው፡፡ በተጨማሪ እነዚህ ለስልጣን ያሰፈሰፉ ወንጀለኞች ከኢትዮጵያ ህዝብ ይዘረፉትን ሃብት   ላለማጣት  ብሎም  በ21 አመት ውስጥ በሰሩት ወንጀል ላለመጠየቅ  ከመድረክ  በስተጀርባ እየተባሉ   ይገኛሉ፡፡

በተለይ  ጥቂት የማይባሉ  የቀድሞ የህወሓት አባሎች አሻንጉሊቶቹ ከፊት እንደ መሪ መቀመጣቸውን አልተቀበሉትም፡፡ ለዚህም ምክንያታቸው ‘እንዴት እኛ  ስንት መስዋዕትነት ከፍለን በታንክ አዲስ አበባ  የገባን  ታጋዮች  እያለን  በህዝብ ማመላለሻ አዲስ አበባ የገቡ እና በቅርብ ድርጅቱን የተቀላቀሉ  ግለሰቦች ወደ  ስልጣን መጡ? ’ በማለት ነው፡፡ እነዚህ  የቀድሞ ታጋዮች እና አጃቢዎቻቸው የራሳቸውን ቡድን  በህወሓት ውስጥ በማዘጋጅት እና ተስፋ ባለመቁረጥ አኩርፈው  መከላከያ ሰራዊቱን  እንዲሁም በዘር  የተሳሰረውን  የደህንነት መስሪያ ቤት በበላይነት ተቆጣጥረው ሁሉንም እንቅስቃሴ  በአግባቡ ለመከታተል እየሞከሩ ይገኛሉ ፡፡

ስልጣንን  በአንድ ወገን ቁጥጥር ስር የማዋል  ድራማዎች  በሚፈፀሙበት በአሁኑ  ሰአት በአንዳንድ ተቃዋሚዎች  ዘንድ ሳይቀር እንኳን ሰላማዊ  የስልጣን ‘ሽግግር’  እንደተደረገ  እና  ለአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ  ጊዜ  ሊሰጣቸው እንደሚገባ የሚለፍፉ ግለሰቦች  በስፋት ይደመጣሉ፡፡ እኔ ግን በነዚህ ግለሰቦች  አባባል  አልስማማም፡፡ ምክንያቱም ወያኔ ከጥፋቱ የማይማር፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች እና  ታሪክ  ጠላት የሆነ፣ የሃገርን ጥቅም አሳልፎ የሚስጥ፣ የስልጣን  ሱሰኞች  የተሰበሰቡበት  እና ሃገርን  በመሸጥ ላይ ያለ የማፍያ ቡድን ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ያደርጋል ብሎ ማሰብ በራሱ የዋህነት ብቻ ሳይሆን ሞኝነትም ይመስለኛል፡፡ ወያኔ እያለ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አይኖርም፤ አብሮት ያደገው  አምባገነናዊ አመለካከቱም አይለወጥም፡፡ ስለዚህ ወያኔ ይለወጣል ብለን ጊዜአችንን ከምናባክን  ሌሎች  አማራጮችን መፈለግ የተሻለ ነው፡፡

በነገራችን ላይ ስለ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ብዙ ጥሩ ነገሮችን  የሚያሳዩ ጦማሮችን  እንዲሁም  በቃለ መጠይቅ  ምስክርነቶችን  ሰምተናል፡፡ አቶ ሃይለማርያም  ደሳለኝ  በተነገረላቸው ሰብዕና እና በህዝብ ምርጫ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆኑ ምንም ተቃዉሞ አይኖረንም ነበር ! ነገር ግን  አለመታደል  ሆኖ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የተወለዱት የኢትዮጵያን ህዝብ አፍኖ በማሰቃየት ላይ ካለው፣  በህዝብ ካልተመረጥው እና ወንጀለኛ ከሆነው ከወያኔ ቡድን በመሆናቸው እንዲሁም ካሁን በፊት ይህ ቡድን  በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በሰራው ወንጀል  በተባባሪነት  ያገለገሉ  ግለሰብ  ስለሆኑ  ምንም እንኳን የግል ሰብዕናቸው እንደተነገረን ሊሆን ቢችልም ታሪካዊዋን ኢትዮጵያን የመምራት ሞራል ሊኖራቸው አይችልም ፤ ከተጠያቂነትም  አያመልጡም ፡፡ አንድ ሰው የተማረ ፣ እምነት ያለው፣ ጥሩ የግል ስብዕና ያለው  ከሆነ እንዴት ለረጅም አመታት በወንጀል ከተሰማራ ቡድን ጋር ተባብሮ ሊሰራ ይችላል? ትላንት በፕሬዝዳንትነት ማዕረግ እና በተለያዩ  የስልጣን ቦታዎች  አገራቸውን ሲያገለግሉ የነበሩ ከዚህ መንግስት የተነኮል ስራ ጋር ላለመተባበር እና ለህሊናቸው ለመታዘዝ ስልጣን እና ክብር ሳያምራቸው  ከዚህ ቡድን እራሳቸውን ያገለሉ ብዙ የኢትዮጵያ ልጆችን አይተናል ፡፡ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝስ ወደ እራሳቸው ህሊና  የሚመለሱት መቼ ይሆን ?

አንድአንድ ግለሰቦች አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ያገኙትን ወርቃማ እድል በመጠቀም የኢትዮጵያን  ህዝብ  ወደ ስልጣን ባለቤትነት ሊያሸጋግሩት ይችላሉ የሚል ሰፊ ግምት አላቸው ፡፡ ነገር ግን እስካሁን እንዳየነው አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ  ባገኙት መድረክ እና አጋጣሚዎች ያደረጉዋቸው ንግግሮች ይህንን እንዳንጠብቅ ያደርገናል ፡፡ ለአብነት ያህል በ‘ህዝብ ተወካዮይ’ ምክር ቤት  ያደረጉት የመጀመሪያ ንግግር ማረጋገጫ ሊሆን ይችላል ፡፡ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተለያዩ ጠባሳዎችን ጥሎ ያለፈውን  እና የወያኔን  ሰይጣናዊ ርዕዮተ አለም ያጠመቁዋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር  ‘ታላቁ  መሪ ’  በማለት  ሲያሞካሹዋቸው  እንዲሁም  በንግግራቸው  መጨረሻ  ‘ዘላለማዊ ክብር  እና ሞገስ ለእግዚአብሄር በማለት ፋንታ    ‘ለታላቁ መሪያችን’  ሲሉ ለሰማ  ሰው  ሃይለማርያም ደሳለኝ  ምን  አይነት  መሪ ሊሆኑ  እንደሚችሉ እና  አማኝነታቸውንም  ጥርጣሬ  ውስጥ  እንደወደቀ  መገመት አያስቸግርም፡፡

አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ለወ/ሮ አዜብ መስፍን ማስተዛዘኛ በሚመስል መልኩ  ‘የታላቁ  መሪያቸውን  ’ ፖሊሲዎች ፣ ስትራቴጂዎች  እና ሌሎችንም  ሳይበረዙ  እንደሚቀጥሉበት ሳያቅማሙ  ነገሩን  ለዚህም  ነው  ብዙ  ኢትዮጵያዊያን  ግለሰቡን  አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ  ሳይሆን አቶ ሀይለመለስ ደሳለኝ  ሲሉ  የሚደመጡት ፡፡  በወያኔዎች  ምርጫ ወደ  ስልጣን ከመጡ ግለሰብ ተስፋ ማድረግ ወይም ጥሩ  ነገር      መጠበቅ ከየዋህነት  አልፎ  ተስፋ  መቁረጥን ሊያሳይ ይችላል ፡፡ ኧረ ለመሆኑ ለአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ  እድል በመስጠት  የኢትዮጵያን ህዝብ  እንደ  ቤተ – ሙከራ  ግብአት  መጠቀሙ የሚያበቃው  መቼ ነው ? አቶ ሃይለማርያም  ደሳለኝንስ  ምን ያህል እስኪገድሉ ፣ ምን  ያህል እስኪሳደቡ ፣ ምን  ያህል በነጻ የመናገር መብት እስኪነፍጉ ፣ ምን ያህሉን በአሸባሪንት በመወነጀል እስኪያስሩ ፣ ምን ያህሉ በርሃብ እና ቸነፈር እስኪያሰቃዩ ፣ ምን ያህል የሃገራችንን መሬት እስኪሸጡ ፣ የትኛውን ዘር እስኪጨፈጭፉ,,,,,ወዘተ ነው ፤ እድል የምንሰጣቸው ? አረ ጎበዝ በቃ በማለት እንነሳ !!!!

በመጨረሻም እንደቀበሮዋ የበሬ ብልት ይወድቅልኛል ብሎ  በየዋህነት ከመከተል እንደ ዜጋ መብታችንን  ለማስከበር እና የመብት ጥያቄዎችን  ለመጠየቅ ብሎም ህዝቡን  የስልጣን ባለቤት ለማድረግ መቃወምን  ብቻ እንደ ልማድ ከመያዝ  በመውጣት በቆራጥነት ተነስተን ኳሳችንን ወይም ነጻነታችንን  ለማስመለስ ህዝቡን  በማደራጀት ለበለጠ ትግል መነሳት ይጠበቅብናል ፡፡

ራስ ወዳዱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሞት ከተለዩ በኋላ እንደተካሄደው አይነት የይስሙላ የስልጣን  ‘ሽግግር’ ሳይሆን ትክክለኛ እና ከወያኔ ወደ ኢትዮጵያ ህዝብ በማንኛውም መንገድ የሚሸጋገርበትን ጎዳና   በቆራጥነት መከተል ይኖርብናል፡፡ ይህ ትክክለኛ የስልጣን ሽግግር ተግባራዊ  እንዲሆን  በሃገር ዉስጥም ሆነ፤ ከሃገር ዉጭ የሚገኙ ተቃዋሚዎች ሃገር ወዳድነትን ወይም ሃገርን ማዳንን መሰረት በማድረግ ፣ በመዋሃድ እና እንደ አንድ በመሆን ወደ አሰፈላጊው ትግል በመግባት፤ ህዝቡን በማቀናጀት፣ ታግሎ በማታገል ፣ በማበረታታት እንዲሁም ታላቋ ኢትዮጵያ ሃገራችን ለህዝቦችዋ አመቺ የምትሆንበትን  እና  በህዝብ የተመረጠ መሪ ወደ ስልጣን የሚመጣበትን መንገድ ለማመቻቸት በቁርጠኝነት መነሳት  ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን በመረዳት ዛሬ ነገ  ሳንል መነሳት የዜግነት ግዴታችን  ነው፡፡

ትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !

ለአስተያየቶት – abnuye2001@gmail.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here