አትነሳም ወይ?!

ከአናንያ ሶሪ

እንዲህም አትሸማቀቅ! ግራ-ቀኝህን በጥርጣሬና በፍራቻ መቃኘትም አያሻህ! እረ አትገለማመጥ! እንዲህ መርበድበድ ምንድነው?
በቅድሚያ ጽሁፉን አንብበህ ጨርስና ከዚያ በኋላ የራስህን/የራስሽን አቋም ትወስዳለህ፡፡ ጽሁፉን በሙሉ ሳታነብ ግን ቸኩለህ አትደምድም፡፡ ከስህተት ላይ ትወድቃለህና! የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳልና! የብዙዎቻችን ችግርስ ምን ሆነና?! ይኸው በወሬ እና በስሚ- ስሚ እየተፈታን ብሎም እየተነዳን አይደለ እንዴ በዘመናችን ሁሉ የተቀለደብን?! ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው! እንዲል ተረቱ፡ ፡ ስለዚህ “አንድን መጽሐፍ በሽፋኑ ብቻ አትፍረደው!” /Never Judge a book by its cover/ እንደሚባለው የፈረንጆቹ አባባል በርዕሱ ብቻ ተመርተህ የጽሑፉን ጭብጥ እንዳገኘኸው ሆኖ አይሰማህ፡፡ ርዕሱ ቁንጽል ሀይለ-ቃል ብቻ ነው፡፡ ቁም- ነገሩን በዝርዝሩ ውስጥ ነው የምታገኘው፡ ፡ “ሰይጣኑ ያለው በዝርዝሮቹ ውስጥ ነው” /The Devil is in the details/ ይላሉ ፈረንጆች ስለአንድ ጉዳይ አብጠርጥሮ ለማወቅ፤ ነገሩን በዝርዝር እና በጥሞና መመርመር እንደሚያስፈልግ ሲያስገነዝቡ፡፡ አለበለዚያ የአገራችን ቀደምት ሊቃውንት አዋቂ-መሳይ አላዋቂን እንደሚሰይሙት “ጥራዝ-ነጠቅ” መሆን ይከተላል፡፡ በጥራዝ- ነጠቅነት ደግሞ መፍትሄ አይገኝም፡ ፡ እንኳንና መፍትሄ ጉዳዩን በቅጡ መረዳትም አይኖርም፡፡ በመሆኑም ርዕስ አንጠልጥሎ ጭብጥ ጥሎ፤ የሚደረግ ውይይትና ንግግር አሊያም ገረፍ-ገረፍ ንባብ የባሰ መደናበር እና ግራ መጋባትን በማስከተል የጉዳዩን ውል ያሳጣናል፡፡ በዚህም ማናችንም አንጠቀምም፡፡

ለማንኛውም ወደ ርዕሰ-ጉዳዩ በቀጥታ ልሂድና ለማለት የፈለግኩትን ልበል፡፡ አትነሳም ወይ?! ከእንቅልፍ ነው? ከሞት ነው? ከሞት ከበረታ ድንዛዜ ነው? ፎቶ ነው? ራጂ ነው? ክርስትና ነው? …. በክፉ ነው የምትነሳው? በደግ ነው የምትነሳው? በትንሳዔ-ሙታን ነው የምትነሳው? በምንድነው የምትነሳው? ለምንድነው የምትነሳው? ወዴት ነው የምትነሳው? መቼ ነው የምትነሳው? እንዴትስ ነው የምትነሳው?

መቼም ኢትዮጵያውያን በባህላችን ብልፅግና የተነሳ አንድ ትልቅ ሰው ወይም አረጋዊ ከውጭ መጥቶ ወደቤት ውስጥ ሲገባ ከተቀመጥንበት ብድግ ብለን ተነስተን “ኖር! ኖር!” እንላለን፡፡ ምላሹም “በእግዜር!” አሊያም “እረ በልጆቻችን!” ይሆናል፡፡ ታዲያ አንተ ወንድሜስ ለእንዲህ ዓይነቱ የትልቅ ሰው አክብሮት የሚገባውን መነሳት ነው የምትነሳው? ማለቴ-ክብር ለሚገባው ክብርን ለመስጠት፡፡ አሊያስ ከወደቅህበት ረግረግ እና ረመጥ ውስጥ ነው የምትነሳው?

ወይ ኪስህ ወይ ቀኑ ጐደሎብህ፣ ወይ ርቦህ አሊያም ታመህ፣ ወይ ደክሞህ ፣ ወይ መሄጃ አጥተህ፣ ወይ ጭንቀትህን ማራገፊያ ወይ ጊዜህን ማሳለፊያ አጥተህ፣ ወይ ድህነትን አሊያም ጭቅጭቅን ሸሽተህ፣ ወይ ሰክረህ ወይ አብደህ ከየአውራ- ጐዳናዎቹ ጥጋጥግ እስከ ጫት ቤቶች ምንጣፍ እንዲሁም ከየካቲካላ ቤቶች ደጃፍ እስከምናምንቴ ‘አልጋ-ቤት’ ተብዬዎች ፍራሽ የተረፈረፍከው ወጣት አወዳደቅህ ምንኛ አሳዛኝ እና ታላቅ ኖሯል?!

ኦ ወንድሜ …. ከዚህ የበለጠ ውድቀትስ ምን አለ; በቁም ከመሞት የበለጠ ሞትስ በወዴት አለ; አደራ-አልሞትኩም ብለህ ራስህን እንዳታታልል፡፡ ሰው ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር ዓላማ የተለየ ዕለት ሞቷልና! የእግዚአብሔር ዓላማ ላንተ ደግሞ መልካምና ያማረ እንጂ የተዋረደና የረከሰ አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ዓላማ አንተ፣ እኔ፣ እሷ፣ ሁላችን በጥሩ ጤንነት፣ በረከት፣ ነፃነት እና ክብረት እየተዋደድን ብሎም እየተሳሰብን በፍቅር እንድንኖር እንጂ በአምባገነኖች እና በሱሶች ተረግጠን ከእግራቸው መረገጫ በታች አይወድቁ አወዳደቅ ወድቀን በግፍ እንድንገዛ አይደለም፡ ፡ ከቶም የእግዜአብሔር ዓላማ ይኸ ሆኖ አያውቅም! በአምሳሉ ለፈጠረን ውድ ልጆቹ እግዚአብሔር ይኼን አይመኝልንም፡፡ ይህ የጨለማው የዚህ ምድር ገዢ የክፉው ሀሳብ ነው፡፡
ከድቅድቅ ጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን ሊያወጣህ ደግሞ እነሆ የብርሃናት አምላክ የሆነው እርሱ በደጅህ ቆሞ ይጠራሃል፡፡ እውነት ያናግርሃል፤ ህይወት ኑርብኝ! እያለ ይጋብዝሃል፤ መንገድ ና! ተጓዝብኝ! ይልሃል፡፡ አዎ-አምላክህ ይጠራሃል! ፈጠን ብለህ አቤት! በለው፡ ፡ የልብህን በር ወለል አርገህ ክፈትለት፡ ፡ “ተነስተህ ሂድ! እምነትህ አድኖሃል” እንዲልህ” ሽባነትህን እንዲፈውሰው ከወደቅህበት እንዲያነሣህ ፈጥነህ ታዘዝ፡፡

አንቺስ እህቴ፡- ከወደቀው ጋር አብረሽ የምትወድቂ ውዳቂ የሆንሽው ከቶ ስለምንድነው? የወደቀውን እንደማንሳት አንቺ የቆምሽውን ሲጥልሽ መንፈስሽ የማይቆጣው ህሊናሽ የማይቆጠቁጠው በምን የተነሳ ነው? ስጋሽ እህል በራበው ቁጥር ከህሊናሽ እምነትሽን ቆርሰሽ እያበላሽው እስከመቼ ከራስሽ ጋር ተጣልተሽ ትዘልቂያለሽ? አምላክሽስ ምን ይላል? ከመብልስ ነብስ እጅጉን አይበልጥምን? ከልብስስ ሰውነት አይሻልምን? ታዲያ አስቀድመሽ ጽድቁንና መንግሥቱን አለመሻትሽ ስለምንድነው? ሌላው ሁሉ እንደሚጨመርልሽ ዘንግተሽው ነው? ለልብስና ለመብል ስትይስ እስከመቼ ነፍስሽንና ሰውነትሽን አራቁተሽ የአምላክሽን ትዕዛዝ ተላልፈሽ ትኖሪያለሽ? እኒያ ደጋግ እናቶችሽ ያወረሱሽ የመንፈስ ቅርስ ይሄ ነውን; እምነትን መብላትስ የመልካም ሴት ምግባር ነውን? ለዚች አጭር ምድራዊ ህይወትስ ዘላለማዊቷን ነፍስ መቨጥ ይገባልን? ለሚያልፍ ችግር ብለሽ ንፁህ ማንነትሽን ማጉደፍስ ተገቢ ነው? የሰውነት ክብርን ወደ ሸቀጥነት ተራ አውርዶ ለገበያ ማቅረብና ነውርን መነገድስ ለህሊና እረፍት ይሰጣል?
በሰው ውርደትና ስቃይ ሰይጣናዊ እርካታ ለማግኘት ሲባል የአምላክ ፍጡርን በገንዘብ የሚሸጥ የሚለወጥ ቁስ ደረጃ አሽቀንጥሮ ቁልቁለቱ ላይ መጣልስ ከሰብዓዊነት እና ከወንድማዊነት ይጠበቃል? የፈጠረን አምላክ በፈቀደልን መንገድ ላይ ትዕዛዙን አክብረን በጥንቃቄ ብንጓዝ ኖሮስ ከቶ ይቸግረን ነበር? ፈጣሪያችን የሰጠንንስ የሚከለክለን ማነው?

“ለምኑ ይሰጣችሁማል! ፈልጉ ታገኙማላችሁ! መዝጊያን አንኳኩ ይከፈትላችሁማል፡፡ የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና! የሚፈልገውም ያገኛል! መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል፡፡ ወይስ ከእናንተ ልጁ እንጀራ ቢለምነው ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ሰው ነው? ዓሣስ ቢለምነው እባብን ይሰጠዋልን? እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው? እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው! ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና፡፡”

ታዲያ ዛሬ እኛ፡- ሰዎች እንዲያደርጉልን የምንወደውን ነው ለሰዎች እያደረግን ያለነው? ለሰዎች ቀና ቀናውን እናስባለን? እንደግፋቸዋለን? ወይስ እንጠልፋቸዋለን? እንረማመድባቸዋለን ወይስ እናራምዳቸዋለን? በሰው ስቃይ እናዝናለን ወይስ ሀሴት እናደርጋለን? እዚህ ሁሉ የሞራል አዘቅት ውስጥ ሆነንስ የምንለምነውን መቀበል፣ የምንፈልገውን ማግኘት፣ የምናንኳኳውን ማስከፈት ከቶ ይቻለናልን? ልባችን ሳይለወጥ፣ ከአምላካችን ጋር በንስሃ ሳንታረቅ በያዝነው የመሸነጋገል እና የማታለል ብሎም እውነታውን የመካድ ጠማማ መንገድ ከቀጠልን ጉዟችን ሁሉ መጨረሻው ተያይዞ የመጥፋት ገደል ነው፡፡ እርስ በርስ ካልተዋደድን፣ ካልተዛዘንን፣ ካልተረዳዳን በምን ተዓምር ኑሯችን ሰላምና ፍቅር ይኖረዋል? በምን ተዓምርስ በሃጢያት ድካም ከወደቅንበት ትቢያ ላይ እንነሳለን?

‘እኔ ምን ጐደለብኝና? ምንስ አገባኝ? ከራስ በላይ ንፋስ!’ እያልክ እንደሰነፍ ከንቱ ሰው አትዘናጋ፡፡ አንተ ብቻህን የምትኖር ደሴት አይደለህም፡፡ ወንድም፣እህት፣ ጓደኛ፣ ጐረቤት፣ ሚስት፣ ልጅ፣ ወገን፣ ዘመድ-አዝማድ፣ የሙያ አጋር፣ የሥራ ባልደረባ ያለህ፣ የፍጥረት አቻህ የሆኑ የሰው ልጆች በሞላ የምትኖርበት ምድርን አብረው የሚጋሩህ ማህበራዊ-ፍጡር ነህ፡፡ ብቻህን ልትደሰት አትችልም፤ ስታዝንም ስትደሰትም ሰው ትሻለህ! “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለምና” ብሏል መፅሐፉም፡፡ በመሆኑም ከቤተሰብ እስከ ማህበረሰብ ድረስ በተለያዩ ውስብስብ የማህበራዊ ድርና-ማጐች (social fabric) የተሳሰርን ስንሆን፣ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአንዱ ማጣት ማዘንና መከፋት ሌሎቻችንን የሚነካን ፍጥረቶች ነን፡፡ አካባቢያችን ተተራምሶ ቤታችን የሰላም ሰገነት ሊሆን አይችልም፡፡ ስለሆነም፡- ከቤት እስከ ጐረቤት፣ ከሰፈር እስከሃገር፣ ከሃገር እስከ አህጉር፣ ከአህጉር እስከዓለም፣ ድረስ የማያገባን ጉዳይ የለም፡፡ ይመለከተናል!

የወንድምህ ጐዳና ላይ መውደቅ የአንተ ቤተሰባዊነት እና ኢትዮጵያዊነት መዋረድ ነው! የእህትህ በየባዕድ አገራቱ ጐዳና ላይ ለገበያ መቅረብ የቤተሰብህ እና የአገርህ አንገት መደፋት ነው! የአገርህ መራብ እና መረገጥ እንዲሁም እጅግ ኋላ-መቅረት እግርህ በረገጠበት የዓለሙ ዳርቻዎች ሁሉ መታወቂያህ እና ማፈሪያህ ነው!

ታዲያ አንተ ወንድሜ ራስህን እንደሰጐን አሸዋ ውስጥ ቀብረህ የእውነታውን ዓለም እያየህ እንዳላየህ ሆነህ የምትኖረው እስከመቼ ነው? እውነታው እንደሆነ አፍጥጦ አፍንጫህ ድረስ መምጣቱን አይተው! በዛች በተሸጐጥክባት ጠባብ ቢሮ ውስጥ ተወስነህ የሚከናወኑ ደባዎችን እየተመለከትህ አንደበትህን ለጉመህ፣ ህሊናህን ጠፍረህ፣ ለእንጀራህ ስትል ብቻ ዝም ማለትህ በስተመጨረሻ ላንተስ ይበጅ ይመስልሃል? የሙያ ስነ ምግባርህ የሚያዝህስ ከመቃብር የሚያስፈራ ዝምታን ነውን? እረ እልፍ በል! ያንተ ፍፃሜ ይኼ ብቻ አይደለም፡፡ ተቀጥሮ ደሞዝ ከመብላት ባለፈ በሙያህ ለማህበረሰብህ የምታበረክተው ውድ ስጦታም አለ፡፡ ወንድሜ፡- በስጋ ለመኖር ስትል በነፍስህ አትሙት! ነፍስህ ደግሞ እውነትን ማወጅ ትወዳለች! ነፃነትን ትጠማለች! ፍትህን ትናፍቃለች! ፈጠራን ታፈልቃለች! አዲስ ነገርን ትሻለች! ታዲያ አንተ ወንድሜ፡- ስለምን ነፍስህን ትጨቁናታለህ? እስከ መቼስ ነፍስህ እሆድ-ዕቃህ ውስጥ እንደወደቀች ትቀራለች? አትነሳም ወይ?!… ነፍስህ! አትነሳም ወይ?!… አንተ!

ኑሮ እጅ-እጅ ያለህ እና ያንገፈገፈህ አንተ ሥራ-አጥ ወጣትስ እስከመቼ የምስኪኗን እናትህን የመሃረብ ቋጠሮ የምታስፈለቅቅ ብኩን የወጣት-ተጧሪ ትሆናለህ? ይሄ ቀንስ መቼ ነው የሚያልፈው? 4ኪሎና ጊዮርጊስ እየተመላለስክ በየሥራ-ማስታወቂያው ግድግዳ ላይ እንጀራህን ስትፈልግ የምትንከራተተው እውነት ላንተ ሥራ ጠፍቶ ነው? የተማርክበት የትምህርት ፖሊሲ የመጨረሻ ግቡ አንተን ሥራ-ፈላጊ ተንከራታች ማድረግ ነውን? ወትሮውንስ ይህ ከሆነ ዓላማው ጊዜህን ለምን በትምህርት ቤት አሳለፍክ? አፍላውን የወጣትነት ዕድሜህን በነፃነት ለሥራ እንድትጠቀምበት ያልቻልከውስ ከምን የተነሳ ነው?

የዴሞክራሲ፣ የነጻነት፣ የእኩልነት፣ የብልጽግና፣ እንደልብ የመናገር፣ ሀሳብን የመግለፅ፣ ሠርቶ ጥሮ-ግሮ የማደግ ተስፋን በየዕለቱ እየመገቡህ እና እነዚህን ሁሉ እንደሚሰጡህ እየማሉና እየተገዘቱ ቃል የገቡልህ መሪዎችህ አንዳቸውን እንኳ በቅጡ ሳይለግሱህ ወሽመጥህን ቆርጠው እነርሱ በተደላደለ መንበራቸው ላይ ከተቀመጡ ይኸው 21 ዓመት ሆናቸው፡፡ አንተስ? አንተና አንቺ የ21 ዓመት ወጣት የሆናችሁት ብላቴኖችስ? በዚህ ዕድሜያችሁ ምን አላችሁ? ምን ጥሪት ቋጥራችኋል? ሥራ-አለሽ? ገቢ አለህ? ኑሮህ/ሽ ዋስትና ያለው ዘላቂ ነው? ወይንስ እንደቁማር የዕድል ኑሮ ነው? ‘ ባገኝ በልቼ ባጣ ተደስቼ’ የሚሉት ዓይነት ይሆን ህይወትህ? የአየር-ባየር ኑሮ የሚያዋጣው ታዲያ እስከመቼ ነው? አንተ እና አንቺ ተመልካች፤ ሌሎች ኗሪ የሆናችሁት እረ ስለምንድነው? አይበቃህም የግፍ አገዛዝ? አይበቃሽም የግፍ አገዛዝ? አልተንገሸገሻችሁም?የጉልቤ-አስተዳደር አላስመረራችሁም? አላሳደዳችሁም? አላሰደዳችሁም? በኢኮኖሚ-የዘር-ማጥፋት እና በኢኮኖሚ-አፓርታይድ እንደቅጠል አላረገፋችሁም? ወላጆች፡- የልጆቻችሁን የፍላጐት ዓይኖች በመሸሽ አልተሳቀቃችሁም? ልጆችስ፡- የወላጆቻችሁን ከቀድሞው የክብር ደረጃ መዋረድ እና መጎሳቆል ላለማየት ቤቱ አላስጠላችሁም? የጐረቤቱ ማባሪያ-የሌለው ጭቅጭቅና አለመተማመን ነብሳችሁን አላሰቀቃትም?

ንገሩኝ እስቲ እናንት የ21 ዓመት ወጣቶች? እስቲ ሳትፈሩ የልባችሁን አውጉኝ! የልጅነት ህልማችሁን በእውን እየኖራችሁት ነው? የልጅነት ህልማችሁንስ ማን ሰረቀው? ራዕያችሁን ማን ሰለበው? ትልቅ እንዳትመኙ በትናንሽ ‘ሥራዎች’ የጠመዳችሁ ማነው? እናንተስ ቻይና ሄዶ መማር፣ ዘመናዊ መኪና መንዳት፣ በምቹ ቤት ውስጥ መኖር፣ በውጭ ንግድ መሠማራት፣ አስመጭና ላኪ መሆን፣ በጥሩ አለም-አቀፍና አገር-አቀፍ መሥሪያ-ቤቶች ውስጥ በወፍራም ደሞዝ መቀጠር፣ ኑሮን ማደላደል፣ መልካም ምግብ መመገብ፣ ያማረ መልበስ፣ ከከተማ ወጣ ብሎ መዝናናት፣የንግድ ድርጅት ማቋቋም፣ በነፃነት መመራመር፣ ትዳር መያዝ፣ ልጆች ማፍራት፣ ጥሪት መቋጠር አይወድላችሁም? እናንተ የእንጀራ ልጆች ናችሁ? ለዚህ ሁሉ ክብርና ማዕረግስ ያልተገባችሁ የሰው-መናኛ የምርጦች-ትራፊ ናችሁ? እናንተ ለለቅሶ፣ለድጋፍ ሰልፍ፣ ለጦር-ግንባር አሊያም ለኮብልስቶን ብቻ የምትፈለጉ የምርጦች ጌቶች የጉልበት ሠራተኞች አሊያም የመስዕዋት በጐች ናችሁን? ከ’ዕድገቱ’ በየ’ደረጃው’ የተዋረድ የምትጠቀሙ 2ኛና 3ኛ ዜጐች ናችሁ? ኢህአዴግስ ይወዳችኋል? ወይስ ይጠቀምባችኋል? ተናገሩ እስቲ እናንተ የትናንት ‘አደገኛ-ቦዘኔዎች’ የዛሬ ‘አደገኛ-ሊጐች’ እና ‘ፎረሞች’! ተናገሩ——

የኢህአዴግ ቀለምአልባው ሽብር

በየጐዳናው ጥጋጥግ እና በየአውቶቡስ ፌርማታው ውስጥ የላስቲክ ዳስ ዘርግታችሁ የወዳደቃችሁ የኢትዮጵያ ልጆች ሆይ፡- ስለእናንተስ ግድ የሚለው ማን ይሆን? ሰብሳቢያችሁስ ከወዴት አለ? በዕቃ-መያዣ ማዳበሪያዎች ውስጥ እንደአልባሌ ግዑዝ ነገር ተወሽቃችሁ በየሱቆች ደጃፍ ከውሻ ጋር ተቃቅፋችሁ የምታድሩ ኢትዮጵያውያን የሰው ልጆችስ መጨረሻችሁ ምን ይሆን? በውድቅተ-ሌሊት እሳት አንድደውና ዙሪያውን ከበው ሲተክዙ የሚያድሩ ወንድም እና እህቶቻችንስ ሰቀቀናቸው መቼ ያበቃል? ቤንዚን እየሳቡና የሲጃራ ኩስታሪ እየለቃቀሙ ሲያጨሱ የሚውሉ የጐዳና ላይ ታዳጊ ሴት ልጆች እና ብላቴኖችስ ወገን አላቸው? ማን ከዚህ መዓት ያወጣቸዋል?

በአፍላ-ዕድሜያቸው መንታ-መንታ ጨቅላ ህፃናትን ታቅፈው ከቦታ ቦታ የሚንከራተቱ ኮረዳ-እናቶች፣ ወንድ ልጁን በጫንቃው ላይ አኑሮ እንባውን እያዘነበ የሚለምን ጐልማሳ አባት፣ ህፃናት ልጆቻቸውን አውላላ መንገድ ላይ ነስንሰው አስተኝተው ከነመላ ቤተሰባቸው የሚለምኑ አረጋዊ አባወራዎች እና እማወራዎች፣ በቆሻሻ ገንዳ ውስጥ የተጣለ ምግብ ለቃቅመው በልተው እዚያው ስር ተኝተው የሚውሉ ምስኪን እኩዬቻችን ዜጎች፣ በተበላሹ የቴሌ የስልክ ማስደወያ የብረት-ቤቶች ውስጥ የሚያድሩ የዕድሜ ታናናሾቻችን ጐዳና ተዳዳሪዎች፣ ዕድሜ ልካቸውን ክምር እንጨት እና ቅጠል ተሸካሚ ሆነው የኖሩ ጐስቋላ እናቶች እና እህቶች፡- “እረ የወገን ያለህ!?” እያሉ እየተጣሩ ነው፡፡ ከድህነት ወለል በታች ወድቀው አይዞአችሁ! የሚላቸው ጠፍቶ፣ እጁን ዘርግቶ የሚያነሳቸው የአገር-ልጅ አጥተው በዝምታ ቀስ-በቀስ እየሞቱ ነው፡፡ ወገኖቻችን ወድቀዋል! ግና ማን ያነሳቸዋል?

——- ተነሳ ተራመድ
ክንድህን አበርታ
ለሀገር ብልፅግና
ለወገን መከታ ——

አንተ እና እኔ እንዳናነሳቸው ደግሞ፡- እኛ ራሳችን በሺሻ፣ ሀሺሽ፣ ጫት፣ ሴሰኝነት፣ ልቅ-ወሲብ፣ ዳንኪራ፣ አልኮል፣ ትምባሆ፣ ወፈፌነት/ከንቱነት ነፍዘን በዚያ ላይ ጧት ማታ የኢ.ቲ.ቪን. የሀሰት ኘሮፖጋንዳ እየተጋትን አይምሮአችን ተሳክሮብን፣ እውነታው ተምታቶብን ግራ እንደተጋባን አለን፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ 22 ሰዎች ለሁለት ቡድን ተከፍለው ሲጠልዟት በሚኖሩ ኳስ ተጫዋቾች ህይወት ተማርከን ራሳችንን እና ኑሯችንን ረስተን ኮብልለናል፡፡ በአውሮፓ አገራት ስታዲየሞች ውስጥ ወድቀናል፡፡ አካባቢያችንን እንረሳ ዘንድ ኢ.ቲ.ቪ. እና ዲ.ኤስ.ቲቪ ግንባር ፈጥረው ግንባራችን ውስጥ ያለውን ማመዛዘኛ መስተሐልይ ለመስለብ ሌት-ተቀን ይደክማሉ፡፡ ማሰቢያ-አይምሮአችንም በቴሌቪዥን ሣጥን ውስጥ ተከርችሞ ተቆልፎበታል፡፡ በዚህ ዘመን ያለን ወጣቶች መብታችን ተከብሮልናልÌ አዎ- መብታችንም፡- ‘የወጣቶች የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከመሴሰን፣መስከር፣መዘሞት፣መጦዝ፣መጀዘብ፣መነሁለል’ ነው፡፡ በመቃም፣በማጤስ፣በመጠጣት፣በመዘሞት፣ አለም-አቀፍ ውድድሮች ውስጥ ተገብቶ ዋንጫና ገንዘብ ይገኝ ይመስል በየሰፈራችን እንደአሸን የፈሉ ሃጢያት መለማመጃ ቦታዎች ተኮልኩለውልናል፡፡ ከነዚህ ሁሉ የተረፍነው ደግሞ በፑል እና ጆተኒ ማጫወቻ ጠረጴዛዎች ላይ እየቆመርን በደረታችን ወድቀን የምንውል ነን፡፡ ሌሎቻችን በየሰፈሩ ስርቻዎች ውስጥ በሚገኙ ፊልም-ቤቶች ታጭቀን ልቅ የወሲብ ፊልምና የወንጀል ታሪክ ያላቸውን ሲኒማዎች ስንጋት አመሻሽተን እኩለ-ሌሊት ላይ ለወንጀል የምንሠማራ የትውልድ ማጅራት-መቺዎች ነን፡፡ ምስኪኖችን የምናጠቃ የጉድ-ትውልድ! በአካል ብቻ ሳይሆን በመንፈስም ጭምር የወደቅን! ነብሳችን በበካይ እና መራዥ ክፉ የሥጋ ምኞቶች የተተበተበ ብላሽና መርዛማ ትውልድ ነን፡፡ በሃጢአት ድካም ፣ በኑሮ ፈተና፣ በሰው እንቅፋት የወደቅን መንፈሰ-ሰባራዎች ነን፡፡ የመለኮት ህክምና የሚያሻን የነፍስ ድውያን ነን፡፡ አለባበሳችን የሰውነታችንን ጉድፍ የደበቀልን፣ አበላላችን የነፍሳችንን ገመና የጋረደልን እንደሳጥናኤል የተዋብን እንደልቡም የከፋን ሰው-መሳይ እፉኝቶችና ሻርኮች ነን፡፡ በማለዳ ቤተ-መለኰት ሄደን የምንፀልይ በእኩለ-ቀን ለጣኦት የምንሰግድ በየጥንቆላ ቤቱ ወለል ላይ ወዳድቀን የምንንደባለል አስመሳዬች እና ግብዞች ነን፡፡ ፈጣሪን ለማታለል በከንቱ ስሙን የምንጠራ ትዕቢተኞች ነን-ደግነቱ አምላክ አይዘበትበትም! ስጋውን እንጂ ነብሱን የማይጠብቅ፤ በዳያስፖራ ሴፍቲ-ኔት ታቅፎ ዶላር እና ዩሮ በመለቃቀም ራሱን የሚያኳኩል ሰው የአገሪቷን ዋና ዋና መታያ እና የሰው መገበያያ ቦታዎች ያጨናነቀባት የኃጢአት ንግድ የሚጦፍባት ሆናለች-ኢትዮጵያ!

እንዲህ ያለኸው ወንድሜ፡- ስለምን ዕለቱን የኮረዶችን ስልክ ቁጥር ከመቀበል አሊያም ከባዕድ-አገር የመጡ እንስቶችን ማጥመጃ ዘዴዎች ከማሰላሰል የዘለለ ዓላማና ግብ አትሰጠውም? ቀንህ የምትቅመውን የጫት አይነት በመጎምዥት የምታስብበት ብቻስ ለምን ይሆናል? እረ እልፍ በል! ከዚህ የተሻለ የህይወት ተልዕኮና ፍፃሜ ይኑርህ፡፡ ሰው እኮ ነህ! ፍፁም አቻ በሌለው እንከን-አልባ አምላክ አምሳል የተሰራህ!

ዝና በሚባለው ፍራሽ ላይ የተኛችሁ ከያኒያንስ የጥበብ ሰው ዋጋው ይሄ ነው? እንደቀኟችሁ የምትቀኙ የገዢ-መደብ መሣሪያ ሆናችሁ እስከመቼ? ግዴለም-ከሞራል እንቅልፋችሁ ንቁ!

……… ወገኔ
ተነስ-ተነስ-
ተነስ ባዲስ ወኔ፣
ወገኔ
ተነሽ ተነሽ ተነሽ
ባዲስ ወኔ ………

‘አዲሱም’ የኢህአዴግ አስተዳደር ድርጅቱ ከወደቀበት የአፍቅሮተ-ሥልጣን ቁልቁለት ሊነሳ ይገባዋል! ከግል-ጥቅመኝነት እና ከፍርሃት ስርቻ ውስጥ ሊነሳ ግድ ይለዋል፡፡ በየቀኑ ከሚለፍፈው ሃሳዊ-ህዳሴ ወደእውነተኛው ህዳሴ ሊሸጋገርና ሁላችንንም ሊጠቅም በሚችል ፍኖት ጉዞ ሊጀምር ብሎም የመንፈስ-ወኔን ሊያሳይ ጊዜው ደርሶበታል፡፡ ህዳሴ /Renaissance/ የሰዎችን እምቅ-ሃይል በነፃነት እንዲለቀቅ የሚያደርግ የአብርሆት/Enlightenment/ መንገድ እንጂ በሰዎች ውስጥ ያለው ብርሃን እንዲዳፈንና እንዳይገለጥ የሚያደርግ መክሊት-ቀባሪ የአምባገነንነት የጨለማ ድንብርብር አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ሆይ፡- አንተስ አትነሳም ወይ? ራስህን ከማታለል እንቅልፍ! ህዝቡ ከኔ ጋራ ነው ብለህ ስለምን ትኩራራለህ? ህዝብማ እንኳን ከአንተ ጋር ከእውነተኛው አምላክ ከኢየሱስም ጋር አልነበር! ከሙሴም ጋር እንደዚያው! ታዲያ ስለምን በሀሰት ኘሮፖጋንዳህ አቅል እየነሳህ በፍርፋሪ የሰበሰብካቸውን መንፈሰ-ደካማዎች ተማምነህ ረጅም ጉዞ ታስባለህ? ወይንስ 5ቱን እንጀራ እና 2ቱን ዳቦ በተዓምር ቀይረህ ተዓምራዊ ሊባል የሚችል ዕድገት አስመዝግበህ ሁላችንንም ታጠግበናለህ? ለማንኛውም በአሸዋ ላይ የተገነባ ቤት ዝናም ጐርፍና ነፋስ በመጣ ጊዜ እንደሚፈርስ ከቶም አትዘንጋው! ኢህአዴግ ሆይ፡- ለራስህ ስትል ጣፍጥ አሊያ ድንጋይ ነው ብለን ወደደጅ አውጥተን እንጥልሃለን!

ከህዝቡ ጫንቃ ላይ እንደመዥገር ተጣብቃችሁ የህዝቡን ደም ስትመጡ እና አጥንቱን ስትግጡ የምትኖሩ ጥገኛ-ተውሳክ ካድሬዎች ሆይ፡- ከኢኮኖሚያችን፣ ከፖለቲካችን፣ እና ከማህበራዊ-ህይወታችን ላይ ተነሱ! አሊያ ግን የህዝብ እንባና ሮሮ ጐርፍ ሆኖ ይጠራርጋችኋል-በጊዜ ንቁ!

ይቀጥላል………

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here