አጫጭር የሀገር ቤት ወሬዎች

ኢሣት ቴሌቪዥን እንዳይሠራጭ ታፈነ (ዘግይቶ የደረሰ አስደሳች ዜና፡- ኢሣት ሠራ!)

ኢሣት ቴሌቪዥን በኢትዮጵያ እንዳይሠራጭ ታፈነ

ከአንድ ዓመት ተኩል ስኬታማ አፈና በኋላ የተጣለበትን ተደጋጋሚ የአየር ሞገድ እመቃ ተቋቁሞ ላለፉት ጥቂት ሣምንታት በኢትዮጵያ ሥርጭቱን ጀምሮ የነበረው የኢሣት ቴሌቪዥንናሬዲዮ ከትናንት በስቲያ ኅዳር 4 ቀን 2005ዓ.ም ምሽት ጀምሮ ዝነኛ ሥርጭቱ መቋረጡ ታወቀ፡፡ ባለፉት የሥርጭት ጊዜያት ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የብሶት መተንፈሻና የታፈኑ የሀገር ቤት ዜናዎች ማወጃ ሆኖ መሰንበቱ የሚታወቅ ነው፡፡

ሰሞኑን ግን ኢቢኤስ የሚባለው ወያኔ-ዘመም የቴሌቪዥን ጣቢያ ከአረብሣት ወጥቶ ወደናይልሣት መግባቱን ተከትሎ የሁለቱም ሞገድ የሚተላለፍባቸው 10815 የማሰራጫ ፍሪኩየንሲ መዘጋቱ ተረጋግጧል፡፡ ይህን የማፈን ድርጊት የፈጸሙትም የወያኔው መንግሥትና የቻይና የቴክሎጂ ጠበብት እንደሆኑ ኢንሣ (INSA) ከሚባለው ከሥራ አመራር እስከጽዳትና ዘበኛ ድረስ የተመረጡ የትግሬ የጉልበትና የኢንተሊጀንስ ባለሙያዎች ብቻ ከሚሠሩበት የወያኔው መንግሥት የፀረ ድረገፅ ሚዲያ ተቋም በፌስታል ተጠቅልሎ እንዳልባሌ ከወጣ ዕቃ መረዳት ተችሏል፡፡ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት የኢቢኤስ ወደናይልሣት መግባት ከኢሣት መታፈን ጋር የቀረበ ግንኙነት አለው ተብሏል፡፡

አሁን ዘግይቶ የደረሰ አስደሳች ዜና፡- ኢሣት ሠራ!

የዚህ ዜና አቀናባሪ ዜናዎቹን ወደማጠናቀቁ ላይ ሳለ ምሣ ቢጤ ሊቀምስ ሣሎን ተቀምጦ ቲቪ ሲከፍት ኢሣት ከ24 ሰዓት መታፈን በኋላ ወደ ኢትዮጵያ አየር መመለሱን ባይኑ በብረቱ አረጋግጧል፡፡ ያላረጋገጠው እስከምን ጊዜ ሳይታፈን እንደሚቆይ መሆኑንም ለመረዳት ችላችኋል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ያ ነገረኛ ኢቢኤስ የተባለው በመለስ ሞት ደረቱን ጥሎ በአደባባይ ያለቀሰው ቲቪ ግን አሁንም አይሠራም፡፡ ለኢሣት መታፈን ጦሱ እሱ ሳይሆን እንደማይቀር ይህ ዘጋቢ ክፉኛ ሲጠራጠር መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ የኢቢኤስን የወያኔ ቤተኛነት መጠራጠር ስለማይቻል እሱን መጠንቀቅ እንደሚገባም ብዙዎች ከወዲሁ እያስጠነቀቁ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል – ኢቢኤስን በሩቅ በማለት፡፡ ኢሣቶችም ይህን ነገር አያጡትም ተብሎ ይገመታል፡፡

ኢትጵያ የሁለት ፕሬዝደንቶች ሀገር መሆኗ ተገለጸ

የወያኔው መንግሥት ቁንጮና አድራጊ ፈጣሪ የነበረው አቶ መለስ ዜናዊ በተለይ የዓለምን ማኅበረሰብ ለማሞኘት ሲል በቀየሰው ሥልት ሁሉንም ሥልጣን በእጁ ካስገባ በኋላ ለይስሙላ ሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ያላት እንዲመስልና ያም ፕሬዚዳንት ራሱን ችሎ የማይንቀሳቀስ በአካላዊ ብቃትም ሆነ በአጠቃላይ እንቅስቀሳሴው ከአሻንጉሊት ብዙም ተለይቶ የማይታይ ዕድሜ ጠገብና በእንፉቅቂት የሚሄድ አሳፋሪ ፕሬዚዳንት መሾሙ ይታወሳል፡፡ ይህ ዜና እስኪጠናቀር ድረስም ይሄው ቤት ጠባቂ ፕሬዚደንት በሰው ግፊ በምትነዳ ተሸከርካሪ እየተጓዘና ለሰላምታም በቅጡ የሚዘረጋ እጅና ሰውነት ሳይኖረው ተሹዋሚና ተሰናባች የውጭ ሀገር አምባሳደሮችን እየሸኘ ቤተ መንግሥት ውስጥ አሣፋሪ በሆነ መልክ ተጎልቶ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ምንም እንኳ ስሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢባልም በአገልግሎቱ ግን ከተጠቀሰው ዘፍዛፋ ፕሬዚደንት የማይሻል ኃይለማርያም ደሳለኝ የተባለ የወያኔ አሽከር በላይኛው ቤተ መንግሥት ከነቤተሰቡ እንዲቀመጥ ለሥልት ሲባል መፈቀዱን ከሥፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ እንደአንዳንድ ታዛቢዎች ከሆነ የሁለቱም ተግባር በስተጀርባ ተጠናቅቆ የሚሠጣቸውን ወያኔያዊ ጉዳይ መፈረም ወይም በሚዲያ መናገር በመሆኑ ሁለቱም አንድ ዓይነት የሥልጣን ደረጃ አላቸው እየተባለ ነው፡፡ ስለዚህ የሁለቱም ሥራ አንድ ነውና ሁለቱም በመቀለጃው የፕሬዚደንትነት ሥፍራ ለጊዜው ተጎልተውበት የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ከእውነተኛ ተቃዋሚዎች ጋር በመተባበር እውነተኛ ጠቅላይ ሚኒስትርና እውነተኛ ፕሬዚንደንት በአፋጣኝ በዴሞክራሲያዊ መንገድ መርጦ እንዲሾም ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ወገኖች ቁጭት በተሞላት ኩንስርና(concern/-edness) አሳስበዋል፡፡

የመለስ ፎቶ ሀገር አስለቀቀ

በኢትዮጰያ ታላቁ የሥልጣን ቁንጮ ላይ ተቀምጦ ለ21 ዓመታት ያህል ጥሬ ‹ራዕዩ›ን በሀገሪቱና በሕዝቧ ላይ ሲያራግብ/ፍ የነበረው የቤት ቀጋው የውጭ አልጋው መለስ ዜናዊ በቅርቡ ወደመጣበት ወደአፈር መመለሱን ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ ዕድሜ ጠገብ የኢሕአዴግ ባለሥልጣን ለዚህ ዘጋቢ ጠቁመዋል፡፡ ሀገር ላወቀው የዚህ የበላዔሰብ መለስ ዜናዊ ሞት ለምን ስማቸው እንዳይገለጽ እንደፈለጉ የተጠየቁት ባለሥልጣን እንደተናሩት የድርጅቱ ዲስፕሊን መረጃን መስጠት በጥብቅ ስለሚከለክልና ሬሣውን ባለማየታቸው በመረጃው ትክክለኝትም ስለማይተማመኑ የመለስ ሞት ሀሰት ሆኖ ቢገኝ ለሂስና ግለሂስ እንዳይጋለጡ በመፍራት እንደሆነ በፍርሀት እየራዱ ለዘጋቢያችን አስረድተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጋዜጠኞቻችንን በመላዋ ሀገሪቱ አሰማርተን ባገኘነው ተጨባጭና በሚታይ ማስረጃ የተደገፈ መረጃ መሠረት የአቶ መለስ ፎቶ በሁሉም ክልሎች በተለይም በትግራይ ከማጀት እስከ አደባባይ በትላልቅና በትናንሽ ቅርጾች – በፖስተሮችና በቢልቦርዶች በበራ ኤፎር ሳይዝ ወረቀቶች – ተለጥፎና ተሰቅሎ እንደሚገኝ ይሄም ሁኔታ እጅግ አሰልቺ እንደሆነባቸው በርካታ ዜጎች መጠቆማቸው ታውቋል፡፡ እነዚህን ሁሉ ፎቶዎች በዚህ በሚታየው መልክ ለማዘጋጀት የወጣው የገንዘብና የቁሣቁስ ወጪ በድምሩ ቢሰላ እስካሁን የወጣው ብቻ የሀገሪቱ የግማሽ ዓመት በጀት ሊሆን እንደሚችል ስማቸው በሽፍን እንዳይያዝ የፈለጉ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር ዶክተር አልፎአይቼው ብዙአየሁ ገልጠዋል፡፡ ዶክተሩ አያይዘውም ‹እንደዚህ ያለ መንግሥታዊ ማይምነትና የቁጭ በሉ አጭበርባሪነት በታሪክም አላነበብኩም፤ በተዘዋወርኩባቸው በርካታ የዓለም ሀገራትም አላየሁም፤ አንድ መሪ ከሞተ በኋላ ደጋፊ ነን የሚሉ ወገኖች ይህን ያህል ጥፋትና ጦም አዳሪ በበዛት ድሃ ሀገር ውስጥ እንዲህ ያለ የሀብት ውድመት ማካሄዳቸው እጅግ ያሳዝናል፡፡ ለወደፊትም ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፡፡ የሰዎቹ ስምና ማንነት ደግሞ በጉልህ ተመዝግቦ መቀመጥ አለበት›ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን እንደታዘበው መስቀል አደባባይና አካባቢው ሌሎች ማስታወቂያዎች ተነስተው ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ በተለይ የሰዎች ዐይን በቀጥታ በሚያርፍባቸው ቦታዎች የተሰቀለው ፎቶ የዚሁ የባለራዕዩ ሰውዬ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በየመሥሪያ ቤት ቢሮዎችና መተላለፊያ ኮሪደሮች፣ በየመኪናው፣ በየመዝናኛው፣ በየሆቴሉ፣ በየአሽቃባጩ ኪስና ደረት … በሁሉም ሥፍራ የዚህ መጻጉዕ ሰውዬ ፎቶ በዐዋጅ በሚመስል ግዴታ መለጠፉ የጤና እንዳልሆነ የገለጡት አንድ ተቆርቋሪ ዜጋ ‹የ300 እና 400 ብር ከልመና የማያወጣ ኮስማና ደመወዝ በአባይ ግድብ ስም በሥልጣናቸው እየዘረፉ ይልሰውንና ይቀምሰውን በማሳጣት በርዛት እያሰቃዩና በርሀብ እየገደሉ ሳለ በሌላ በኩል ደግሞ ከሞተ ለማይመለስ ሰው ለፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ሲሉ ይህን የመሰለ የሀገር ሀብት ብክነት ሲያካሂዱ አእምሮ ብሎ ነገር ስላልፈጠረባቸው ቅንጣት አያፍሩም፤ ገና ከአሁን በኋላም ለመታሰቢያው እያሉ ብዙ ሚሊዮን ማጥፋታቸው አይቀርም፤ በሰበቡም የብዙዎችን የግል ኪስ የሚያደልብ ገንዘብ ከዚህችው ድሃ ሀገር ካዝና መቦጥቦጡ የማይቀር ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በጠንካራ የጋራ ትግል በአፋጣኝ ካልተወገዱ እኛንም በኮንቴነር እያጨቁ ለሣሙና መሥሪያነት ይህን መሰል ተግናዶት(የንግድ ልውውጥ)  ለሚፈልጉ የውጪ ሀገራት ይሸጡናል…› በማለት ዐይኖቹ ዕንባ እያቀረሩ ሲናገር የተከታተለው ዘጋቢያችንም ዋና የሥራ ተልዕኮውን ዘንግቶ አብሮ አላቅሶታል፡፡ (እንድረስላቸውና ዕንባቸውን እናብስ!)

የኑሮ ውድነቱ ሕዝብን እያስለቀሰ ነው

በኢትዮጵያ ሆን ተብሎ በሚመስል ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን እየተሰቀለ የመጣው የኑሮ ውድነት የአብዛኛውን ዜጋ የሕይወት እስትንፋስ እየዘጋ መምጣቱን ዘጋቢዎቻችን ያነጋገሯቸው ታዛቢዎች ጠቆሙ፡፡

‹እህል ከቀመስኩ ሦስተኛ ቀኔ ነው› በማለት በርሀብ ምክንያት የሞት አፋፍ ላይ መድረሳቸውን ከአኳኋናቸው ማወቅ የሚቻል አንዲት አሮጊት እንደገለጹት እህል ቀምሶ ማደር ለብዙዎች የህልም ያህል መሆኑን መረዳት ተችሏል፡፡ የገንዘቡ የመግዛት አቅም በእጅጉ በመውረዱ ቀደም ሲል አምስትና አሥር ብር የያዘ ሰው እንኳን ለራሱ ለሰውም ይተርፍ እንዳልነበር ዛሬ አምሳ ብር የያዘ ሰው ከራሱ ምሣ እንደማያልፍ የጠቆመን አንድ ሊስትሮ ኦሪጂናሉ የጫማ ቀለም ዋጋ ከሦስት ብር ወደ 36 ብር ከፍ በማለቱ አንድ ጫማ ለመጥረግ በትንሹ 3 ብር ቢያስከፍልም እንኳን እንደቀደመው ጊዜ ራሱን ችሎ ለመኖር የሚያዳግተው መሆኑንና ኑሮው በእጅጉ እንደከበደው ተናገሯል፡፡ ይህ ወጣት ሊስትሮ ጨምሮ እንደገለጸው ‹እኛስ ግዴለም ብናጣ ብናጣ ለሆዳችን አናጣም፡፡ ግን ምንም ሥራ የሌላቸው ዜጎችና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው ሽማግሎችና ባልቴቶች፣ በጣም አነስተኛ ደሞዝ የሚከፈላቸው ሰዎች፣ ሕጻናትና ታዳጊዎች እንዴት ይኖራሉ? ዛሬ ጊዜ የቤት ኪራዩ ሰማይ ነው፤ አንድ ተራ ምሣ ለመብላት በሕዝብ መመገቢያ ክበባትም ሳይቀር ከ25 ብር በላይ ነው ፣ 25 ብርስ ከየት ይመጣል? ተገኘ ቢልስ በቀን አንዴ ብቻ ተበልቶ ይኖራል ወይ? ሌሎች ወጪዎችስ እንዴትና በምን ይሸፈናሉ?  ዳቦ ልብላ እንኳ ቢባል አንድ ጉርሻ የማትሆነዋ ዳቦ አንድ ብር ከሃያ ሣንቲም ናት – ሻይው ባማካይ 3 ብር ደርሷል፣ ሥጋና አትክልትማ አይታሰብም፤ ሰው እንዴት ይኖራል…› በማለት ራሱን ይዞ እየጮኸ ሮጧል ማለትም ገልጾኣል፡፡ በዚህ ሁኔታ ማኅበረሰቡ ሲገመገም አብዛኛው በምግብ ሳይሆን በንፋስ እንደሚኖር መገመት ይቻላል ተብሏል፡፡

ዘጋቢያችን ያነጋገራት አንዲት የቤት እመቤት ባሏ በሚሰጣት 1600 ብር የወር አስቤዛ ከስድስት ቤተሰቦቿ ጋር በፍጹም መኖር እንዳላስቻላት ነገር ግን ያው መኖር ስላለባት እንደምንም በተገኘው ነገር ሕይወታቸውን እየገፉ እንደሆነ ተናግራለች፡፡ እንዲያውም የርሷ አስቤዛ በጣም ከተሻሉት እንደሆነና ከዚህ ገንዘብ በእጅጉ የሚያንስ የሚያገኙ ከነጭራሹም የማያገኙ በቤተሰብ ብዛትም ከርሷ የበለጠ ያላቸው እንዳሉ ለገለጸላት ዘጋቢያችን በቁጣ እንደመለሰችለት ከሆነ ‹እንዴ! ምን ማለትህ ነው? አስበው እንጂ፤ አንድ ኪሎ ሽሮ 30 ብር ገዝቼ፣ ለኪሎ ምሥር 30 ብር አውጥቼ፣ ለኪሎ አተር ክክ 24 ብር አውጥቼ፣ ኪሎ ሥጋ 120 ብር ገዝቼ፣ ለጋዝ 300 ብር በወር አውጥቼ፣ ለመብራት 150 ብር ከፍዬ፣ ለሥልክ ሊያውም በቁጠባ 50 ብር አውጥቼ፣ ለጤፍ 850 ብር አውጥቼ፣ ለቤት ኪራይ 1000 ብር አውጥቼ፣ ለዘይት በሊትር 42 ብር አውጥቼ፣ ለተማሪ ልጆቼ … ለሕክምና…› ዘጋው ባያቋጣት የወጪው ዝርዝር የሚቆም አይመስልም፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው ግን ይህች ሴት ከነቤተሰቧ አትኖርም፡፡ በብስጭት ተነሳስታ መናገር በጀመረቻቸው የቤት ወጪዎች መሠረት የዚህች ሴት አስቤዛ ከባለቤቷ እቀበላለሁ ካለችው ወርኃዊ በጀት በዕጥፍ መብለጡን ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይሁንና ይህችን ሴት ‹ይህ የምትናገሪው ወጪ እኮ ባለቤትሽ ከሚሰጥሽ ገንዘብ ይበልጣል፡፡ ከምን አምጥተሸ ነው ቀሪውን የምታሟሊው?› ብሎ ዳግመኛ መጠየቅ ይበልጥ ሆድ ማስባስ ነውና ዘጋቢያችን አልደፈረም፡፡ መፍትሔ የሌለው ጥያቄ አንዳንዴ ጥፊ ሊያስከትል የሚችል መሆኑን የተገነዘበው ዘጋቢ አቅጣጫ ቀይሮ ከሴትዮዋ ርቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ ሥራ የሌላቸው ዜጋ  እንደተናገሩት  ‹በዚህች ሀገር ሰው የሚኖረው በኪነ ጥበቡ ወይም በጭቡ ነው› ያሉት ሚዛን የሚደፋ ሆነ ተገኝቷል፡፡ አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሉት በኪነ ጥበቡ የመባሉ ምሥጢር በባህሉ ‹እርሱ የከፈተውን ጉሮሮ ሳይዘጋው አያድርም› የሚለውን ነባር ብሂል የሚያጣቅስ ሲሆን በጭቡ የተባለው ደግሞ በማኅበረሰቡ መካከል እያጭበረበሩና እያምታቱ በሙስናና በጉቦ ወይም በእጅ መንሻ ኑሯቸውን ከአብዛኛው ሕዝብ በተሻለና በበለጠ የሚመሩ መኖራቸውን የሚጠቁም ነው፡፡ ይህም ሁኔታ ሰው ሰውን እየበላው እንዳለ የሚያስገነዝብ ነው ብለው የሚያምኑ ወገኖችን እያበራከተ መጥቷል፡፡

ይህን ዜና በማጠናቀቅ ላይ ሳለን በደረሰን ተጨማሪ መረጃ የሕይወት ድርና ማግ ውሉ የጠፋባቸው እጅግ ብዙ ዜጎች የሚያደርጉትን ሲያጡና እንዳይርባቸው በማሰብ ባለቻቸው በጣም ውሱን ሣንቲም ባህላዊ አረቂን በመሳሰሉ አደንዛዥ ነገሮች ሰውነታቸውን በማድከምና ኅሊናቸውን በማሳት ለተወሰነ ጊዜ ራሳቸውን ደብቀው ለመኖር እንደሚፈልጉ ተደርሶበታል፡፡ ከዚሁ በተያያዘ ገንዘብ ያለውም ሆነ የሌለው በደስታም ይሁን በመከፋት ሰበብ የቡና ቤቶችን ደጅ ሙጥኝ ብሎ አንጀት ጉበቱን በመጠጥ እያቃጠለ እንደሚገኝና የመኖርን ትርጉም አጥቶ የገዛ ሰውነቱን በእሳት እያጋዬ ያለው ዜጋ ቁጥርም ከጊዜ ወደጊዜ እያሻቀበ፣ ከዚህም በተያያዘ ‹ለመሆኑ በእውኑ ይህች ሀገር የማን ናት?› በሚል ጥያቄ ታዛቢን ያስደመመ ትዕይንት በከተሞች እየተንሰራፋ መምጣቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታየው የዕብዶች ቁጥርም ከጊዜ ወደጊዜ በከፍተኛ ፍጥነትና ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን፣ የአማኑኤል ሆስፒታልም ከሰውነት ተራ የሚወጡ ንኮችንና ቀውሶችን ለማስተናገድ አለመቻሉን ይልቁንም የዕብዶችን ቁጥር ለመቀነስና በሂደትም ለማጥፋት እንዲቻል  ከፈረንሳይ ሉርድ ወይም ከሸንኮራ ዮሐንስና ከሞጆ የ44ቱ ጠበሎች መካከል ክፍል ተቆጥሮ ኮከባቸው ታይቶ ለተፈጠረው ችግር አብነቶቹ መጥተው  የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ለሰባት ሰባቶች ያህል እንዲረጭ የሆስፒታሉ የዶክተሮች ቦርድ ማዘዣ ጽፎ ማስተላለፉን ነገር ግን ማዘዣው የተላከለት ክፍል ደብዳውን እስካሁን ድረስ ደብቆ መያዙን ከቦታው የደረሰን ጥቆማ ያመለክታል፡፡ እንደሚባለው ከሆነ ማዘዣውን የደበቀው የኮሚዩኒኬሽንስ ሚኒስቴር ጽ/ቤት እንደሆነና በዚህ  ቢሮ ውስጥ የመሸጉት በረከትና ሽመልስ  የሚባሉት የትልቁ ሉሲፈር ተወካዮች በቅድሚያ እንዲጠመቁ ቢደረግ የተሸለ እንደሚሆን ተጠቅሷል፡፡ (ጥያቄው ግን ማን ወንድ ያጥምቃቸው?)

የኢትዮጵያ ኤፍ ኤሞች መንግሥታዊ አደራቸውን በብቃት እየተወጡ ናቸው ተባለ

­­­­­በርካታዎቹ የኢትዮጵያ ኤፍ ኤሞች መንግሥት የጣለባቸውን ሕዝብን የማቂያቂያል አደራ እየተወጡ እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበትም ርቀትም ያላቸው ወገኖች ገለጡ፡፡ በወያኔው ፋና ሬዲዮ ሥር የሚገኘውን 98.1 በዋናነት ጨምሮ ብዙዎቹ ኤፍ ኤሞች ሕዝብን ማደንቆር የተያያዙት በስፖርትና በወሲባዊ ጉዳዮች ላይ ውይይትና እንካስላንትያ እንዲካሄድ በማድረግ እንጂ ቁም ነገር ያለው ሀገራዊ ጉዳይ ለውይይትና ለመፍትሄ ፍለጋ እንዲቀርብ በማድረግ እንዳልሆነ ምንጮቻችን ይፋ አደረጉ፡፡ እነዚህ አርቲ ቡርቲ ጣቢያዎች በመንግሥት ሀብትና ንብረት ምን ዓይነት ቆሻሻ ዝግጅቶችን እያካሄዱ እንደሆነ ከዚህ በታች አንድ አብነት በማቅረብ በጉልህ አሳይተን ይህን ዜና እንቋጫለን እንጂ ምን ይደረጋል?

ውድ አድማጮቻችን ይህ የምትከታተሉት በፋና ኮርፖሬሽን ሥር የሚሠራጨው ኤፍ ኤም ፋና 98.1 ሬዲዮ ጣቢያ ነው፡፡ በምናቀርብላችሁ ማኅበራዊ ቁም ነገር ረክታችሁ ከኛ ጋር እስከመጨረሻው እንደምተዘልቁ በመተማመን የዛሬውን የመወያያ ርዕስ ጋዜጠኛ ሔርሜላ ስብሃት ቀጥላ ታቀርብልናለች፡፡

ጥሩ፣ ውድ አድማጮቻችን ያለፈው ሳምንት የመወያያ ርዕሳችን ‹ብዙ ባቄላ የበላ ሰው ምን ይሰማዋል? ምንስ ሊገጥመው ይችላል?› የሚል እንደነበርና ብዙዎቻችሁ ‹ያስፈሳዋል› በሚለው ስትከራከሩ ሌሎቻችሁ ደግሞ ‹ቁንጣን ይይዘዋል› ማለታችሁ አይዘነጋም፡፡ በሃሳባችሁ ጣልቃ ስለማንገባ የሁላችሁንም ሃሳቦች አክብረናል፤ አስተናግደናልም፡፡ በእግረ መንገድም ብዙ ቁም ነገር እንደገበያችሁ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

የዛሬው የመወያያ ርዕሳችን ደግሞ ይህን ይመስላል፡፡ የታሪካችን መዘውር ወይዘሮ አበቅየለሽ  ትባላለች፡፡ ልታስተምራት ካገር ቤት ያመጣቻት እህቷ ከልጆቿ አባት ከባለቤቷ ጋር ስትማግጥ ያዘቻት፡፡ ዳኝነቱን ለእናንተ ሰጥታለች፡፡ ምን ታድርግ? ትፍታው? ልጅቷን ወዳገር ቤት ትመልስ? ከቤት ጠፍታ ቤቱን ለእህቷና ትወደው ለነበረው ባለቤቷ በግላጭ አስረግባ ትሂድ? ይህን ዕድል ተጠቅማችሁ… ተወያዩበት፡፡ ሁለት ሰዎች መስመር ላይ እንደገቡ ስልክ ተቀባዩ አብርሽ ምልክት እያሳየኝ ነው፡፡ እሺ ማን ልበል? ከየት ነው? እባክዎን ሬዲዮውን ያጥፉት ወይም ድምጹን በጣም ይቀንሱት …

ስሜን ነው?

አዎ፣ ስምዎን፤

የኔን?

እንዴ፣ እርስዎን አይደለም እንዴ የማናግረው?

እኮ የኔን ስም?

አዎ!

አሃ! ስሜ እንኳ ከኔው ጋር ይቀመጥ፡፡ ግን እኔ ይቺን ሴትዮ ብሆን ጥየለት ውልቅ ነበር የምለው – ምናባቱንስና፡፡ ኧረ ንሺ እቴ! የማነው ጨምላቃ፡፡ ደግሞም የገዛ እህቴን ያውም በገዛ ቤቴ፣ በዚያውም ላይ ደግሞ ብሎ ብሎ በገዛ አልጋየ ላይ …ሆሆሆ…

እንዲህ ያለ ጉድ ነው የምንሰማው፤ ዘወትር ከየኤፍ ኤሙ የሚያናፉብን ይህን መሰል ትርኪ ምርኪ ነው፡፡ የሀገር ጉዳይ ነውር ነው – አይነሳም – የዕርም ያህል፡፡ ስለኑሮ መወደድ፣ ስለአስተዳደራዊ በደል፣ ስለፍትህ ዕጦትና መዛባት፣ ስለዜጎች መሰደድና አላግባብ መታሰር፣ ስለዕውቀት መምከን፣ ስለሙስና መስፋፋት፣ ስለዘረኞች ዐይን አውጣነት፣ ጦሩ ደኅንነቱ፣ ጅምሩኩ፣ ባንኩ፣ አየር ኃይሉ፣ አየር መንገዱ፣ ፌዴራሉ፣ መከላከያው፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ ውጭ ጉዳዩ፣ ውስጥ ጉዳዩ፣ መላው የሀገሪቱ ቱባ ሥልጣንና ቱባ የጥቅም ቦታ ሁሉ በዘረኛው የወያኔ ጎሣ መያዙ እንደችግር አይነሳም፤ ስለ ድንበር፣ ስለወደብ፣ ስለመሬት ለባዕዳን ሽያጭ፣ ስለ… ብቻ ስለማንኛውም ሀገራዊ ጠቃሚ ጉዳይ በጣም ውስን ከሆኑት ጥቂቶች በስተቀር ያውም በድርበቡ በሌሎችና በብዙዎቹ ሆድ አደር ኤፍ ኤሞች  አይነሳም እየተባለ ነው፡፡ ያቺ ኤፈ ኤም ተከራይታለች የምትባለዋ ክፍታፍማ ማንናት ያቺ ማስጠሎዋማ ከዚያ ማዶ በጠባይ ብትባረር እዚህ መጥታ ሙትቻ ራዕይ አቅፋ ለምታድረው ሌላዋ ማስጠሎ ዮዲት ጉዲት ደንገጡርና ተርቲበኛ ሆናለች አሉ፡፡

የነአርሰናልና ማንቸስተር ወሬ ግን 24 ሰዓት ቢወራ አይጠገብም ብለው የሚያምኑ ወገኖች ብዙ ናቸው ይባላል፤ ለነገሩ በተለይ ወጣቱ ሁሉን ነገር ጥሎ በኳስ ሜዳ ውስጥ የመሸገ ነው የሚመስል የሚሉ ብዙ ታዛቢዎች አሉና ይህን ዜና ተጨማሪ ትንታኔ የሚሰጥበት አካል ቢኖር መልካም ነው፡፡(የአማርኛዎቹ ‹ዜናዎች› እዚህ ላይ አበቁ፤ ለአማርኞች ደህና ዋሉ ወይ እደሩ፡፡)

God Bless Ethiopia!

‘የዚህን ዜና ምንጭ’ ከፈለጉ ይህን ኢሜይል ይጠቀሙ፡- yinegal3@gmail.com

3 COMMENTS

  1. Comment:ዘረጭፋጨፍ፡ይቁም፡ካልቆመግን፡መገመትቀላልነው

    0949781805

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here