አሁንም ደግመን እንነግራችኋለን

0

አሁንም ደግመን እንነግራችኋለን

March 2015

ኢትዮጵያችን እግዚአብሔርንና ሰውን በማይፈሩ ጨካኞች እጅ ወድቃ የመከራ አገር ከሆነች ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። በህዝባችን ላይ የተመዘዘው የመከራ ሰይፍም ወደ ሰገባው የሚመለስ አልሆነም። እንዲያውም በህዝባችን ላይ ሲዘንብ የቆየው የመከራ መንፈስ እንደገና ታድሶ ገና “ልክ እናስገባችኋለን” የሚል የጣዕረ ሞት ድምፅ ከህወሃት መንደር እየተሰማ ነው።

አባይ ፀሃይ የሚባለው ወላዋይና አደር ባይ ግለሰብ በህዝቡ ላይ ሲፈፅመው በኖረው ወንጀል ገና የረካ አይመስልም። ሌላ ግዲያ፤ ሌላ ስደት፤ ሌላ የላቀ መከራ ለኢትዮጵያዊያን ደግሶላቸዋል። አባይ ፀሃይ ለአዲስ አበባ ከተማ ልቀት እርሱ ብቻ አሳቢ፤ እርሱ ብቻ ተቆርቋሪ ሁኖ ራሱን ሹሟል።የአዲስ አበባም ሆነ በአካባቢው የሚኖረው ኗሪ ህዝብ ግን አባይ ፀሃይን የሚያውቁት በእኩይ ተግባሩ እንጂ በደግ ተግባሩ እንዳለሆነ እኛ ልናስታውሰው እንወዳለን። በዚህ ግለሰብ አማካሪነት የተጀመረው ኗሪውን ህዝብ የማፈናቀል፤ ቤተሰብን የመበተን፤ የህዝቡን አብሮነት የማፍረስ ተግባር ገና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል “ገና ልክ እናስገባችኋለን” በሚል መፈክር ሥር እንደሚቀጥል ታቅዷል። አዲስ አበባን በማስፋፋት ሰበብ ብዙ ገበሬዎች ከኖሩበት መንደር ያለምንም ካሳ ተፈናቅለው የሌላ ሎሌ እንዲሆኑ መደረጉ የሚረሳ አይደለም። ይሄን የአንድን ህዝብ ማንነት የማጥፋት ድርጊትን የተቃወሙ ብዙ ወጣቶች በሞት እና በእሥራት እንደተቀጡም አረሳነውም። ትላንት የፈሰሰው ደም ሳይደርቅ፤ የፈሰሰው እንባ ሳይታበስ፤የተበተነው ሳይሰበሰብ፤ የተሰበረው ሳይጠገን እንደገና ለሌላ ዙር ጥፋት እየተዘጋጁ እንደሆነ ነግረውናል።

አባይ ፀሃይ “ልክ እናስገባችኋለን” ሲል የተማመነው ጠመንጃ ያነገተውን ኢትዮጵያዊ ወታደር እንጂ ህዝብን እንዳልሆነ እናውቃለን። ወታደር አገሩን መጠበቅ፤ ህዝቡንም ከጥፋት መታደግ፤ አጠቃላይ የአገሪቷን ህግም ማስከበር ዋናው ተልዕኮው ነበር። የአገራችን ወታደሮች ግን ዋናውን ተልእኳቸውን ትተው ኢትዮጵያን እንደ አገር እንዳትቀጥል የሚያደርጉ ቡድኖችን እድሜያቸውን ለማራዘም እየሰሩ እንደሆነ እያየን ነው።በአገራችን ጠመንጃ የታጠቁ ኃይሎች መከላከያ ኃይል አባላት፤ የፖሊስ አባላት፤ የፌዴራል ፖሊስ አባላት እና በአገራችን ታሪክ በነፍሰ ገዳይነቱ የሚታወቀው አግዓዚ የተባለው ክፍለ ጦር አባላት እና የአገር ውስጥ ደህንነት አባላት የህወሃትን ዕድሜ ለማራዘም ከልብ የመነጨ ፍላጎት አላቸው ብለን አናምንም። እነዚህ ኃይሎች የወጡበትን ጎጆ፤ ነገ ዞሮ መግቢያ የሚሆናቸውን ማህበረሰብ ወደውና ፈቅደው ያፈርሳሉ ብለን ለማሰብ ይቸግረናል።በሌላ በኩል ደግሞ ድርጊታቸው ብዙዎችን እያስከፋ እንደሆነም እናውቃለን።

አሁንም ደግመን ደጋግመን በኢትዮጵያችን ጠመንጃ ላነገቱ ኃይሎች መልዕክት መላካችንን አናቋርጥም። ጠመንጃውን ያነገቱ ኃይሎች ካነገቱት ጠመንጃ የተለዩ ናቸው። እነዚህ ኃይሎች ስሜት አሏቸው፤ ፍላጎት አሏቸው፤ ማሰብ የሚችል አዕምሮም እንዳሏቸውም የሚካድ አይደለም።የሚያዝንና የሚደሰት ስሜት፤ ለመኖር ፍላጎት፤ በጎውን ከክፉ ለመለየት የሚያስችል አዕምሮ ያሏቸው ስለሆነ ፈፅሞ እስከ ሚመሽ ድረስ መልዕክታችንን ከመስደድ አናቆምም። መልዕክታችንም አጭርና ግልፅ ነው። በዚያች አገር ውስጥ ጠመንጃ የታጠቀው ኃይል ጋር ጠላትነት የለንም።በእኛ እምነት መከላከያ ኃይል፤ ፖሊስ እና የደህንነት ሠራተኞች ጠላቶቻችን አይደሉም። እኛ ጠላት የምንለው ጠመንጃ የታጠቀውን ድሃ እና ከርታታ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን ይህን ኃይል በገዛ ወገኑ ላይ ሰይፉን እንዲመዝ እና የንፁሃንን ደም እንዲያፈስ የሚያደርገውን ኃይል ነው።የአገሪቷ መከላከያ ኃይል አሁን ባለበት ሁኔታ ለተሻለ ውጤት የሚያበቃው አማራጭ ስለሌለው ሂሊናው እየወቀሰውም ቢሆን የገዛ ወገኑን ደም እያፈሰሰ ለመቆየት የተገደደ ይመስላል። ይህን ማለታችን የድርጊቱን መፈፀም ትክክል ነው እያልን አይደለም። በማንኛውም መለኪያ የንፁህ ሰውን ደም ማፍሰስ ትክክል አይደለም። በሰማይ በእግዚአብሄር ፊት የሚያስጠይቅ፤ በምድር በሰው ዘንድም የሚያስወቅስ ክፉ ተግባር መሆኑን ሳንናገር አናልፍም።

እስከ ዛሬ የተሻለ መረጃ ስለሌለኝ፤ የተሻለ አማራጭ ስላጣሁ፤ የተሻለን መንገድ ለመፈለግ ሁኔታው ስላልፈቀደልኝ ከሂሊናየ ውጪ ሁኜ ለመኖር ተገድጄአለሁ የሚለው ምክንያት አሁን አብቅቷል። አሁን መረጃ አለ፤ ኢትዮጵያን እንደ አገር እንድትቀጥል ለማስቻል የተሻለ አማራጭም አሁን ተዘጋጅቷል። መረጃና አማራጭ መንገድ ካለ ደግሞ ከሂሊና ጋር ታርቆ እንደ ሰው ለመኖር ሁኔታው የተመቸ ሁኗል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል፤ የፖሊስ ሠራዊት አባላት፤የአገር ውስጥ የደህንነት ኃይሎች ሆይ ስሙን !

ህወሃቶች እናንተን ተገን አድርገው የገዛ ወገኖቻችሁን “ልክ እናስገባለን” ማለታቸውን ሰምታችኋል የሚል ግምት አለን። ልክ ማስገባት ማለት-ከሥራ ማባረር፤ከትውልድ ሥፍራ ማፈናቀል፤ እስር ቤት መጨመር፤ ለስደት መዳረግ እና መግደል ማለት ነው። የአባይ ፀሃይ ልክ ማስገባት ይሄን ይመስላል።ይሄን የምትፈፅሙት ደግሞ ጠመንጃ ያነገታችሁ ኃይሎች ትሆናላችሁ። ወገኖቻችሁ በህወሃቶች እጅ እንባቸውን በመዳፋቸው ሲያፍሱ ኑረዋል።በህወሃት አገዛዝ ሥር ያለች አገራችሁ ከውዳቂ አገራት ተርታ ገብታለች፤ ከዓለም አስር ፍፁም ድሃ አገሮች መካከል አንዷ ሁናለች።የአገራችሁ ወጣቶች ሞትን ፊት ለፊታቸው እያዩ ተሰደው የዓዞና የበርሃ ዕራት ሁነው ቀርተዋል። ከዚህ የተረፉትም የዓረብ መጫወቻ ሁነዋል። ይህ ሁሉ መከራ ህወሃት በተባለው ክፉ ዘረኛና ቂመኛ ቡድን ይፈፀማል። አሁን ይሄን በቃ ለማለት ግዜው ነው። ከእንግዲህ ወዲያ ታዝዤ ነው፤ ለእንጀራ ብየ ነው፤ ልጆቼን ላሳድግ ብየ ነው፤ አማራጭ አጥቼ ነው፤ የሚሉ ምክንያቶች ሚዛን የሚያነሱ ባለመሆናቸው ተቀባይነት የላቸውም።

አሁን አስተማማኝ አማራጭ አለ። የኢትዮጵያ ውረደት ያንገበገበን፤ የህዝባችን ጉስቁልና ያስቆጨን ወገኖች የአያቶቻችንን ጋሻና ጦር አንስተን ለግዳጅ ተዘጋጅተናል። ከመቸውም ግዜ በተሻለ ህዝባዊ መሠረት ላይ የቆመ ድርጅት መሥርተን ንቅናቄ ጀምረናል። ትግላችን ኢትዮጵያዊያን ከተዘፈቁበት ጭለማ ወደ ብርሃን የሚያሻግር ነው። ትግላችን ህወሃት የጫነውን የዘረኝነት ቀንበር የሚሰብር ነው። ትግላችን ህወሃት የዘረጋውን የዝርፊያ መረብ የሚበጣጥስ ነው። ትግላችን ህዝቡን በሙሉ የተጫኑ ጥቂት መንደርተኞች ሥፍራቸውን እንዲይዙ ማድረግ ነው።ትግላችን ጎጠኛ አስተሳሰብን አምክኖ ብሄራዊ ስሜትንና ውህደትን የሚፈጥር ነው። ትግላችን ዜጎች በዜግነታቸው ብቻ በኢትዮጵያ ውስጥ በማንኛውም ሥፍራ ያለ ፍርሃት የሚኖሩበትን ሁኔታ የሚፈጥር ነው። ትግላችን አብዛኛው ህዝብ በመረጠው መንግስት የሚተዳደርበት፤ ይህም መንግስት ህዝቡን ፈርቶና አክብሮ የሚሠራበት ሁኔታ የሚፈጥር ነው። ትግላችን የአገሪቷ መከላከያ ኃይል አገሩንና ህዝቡን የሚጠብቅ እንጂ የገዛ ወገኑን ደም በከንቱ የሚያፈስበት ሁኔታ እንዲያበቃ የሚያደርግ ነው።ጠመንጃውን ያንገትከው ኃይል የቀረበልህ አማራጭ መሥመር ይሄ ነው።

ደግመን እንነግርሃለን አሁን አማራጭ መንገድ አለህ። በገዛ ወገኖችህ ላይ ስይፍህን ለመምዘዝ እምቢ የማትል ከሆነና አሁንም በዚያው በጭለማ መንገድ መሄድን ከመርጥክ መጨረሻህ መልካም አይሆንም። እኛ እንድሆንን ተነስተናል። ከመንገዳችን የሚያቆመን ምዳራዊ ኃይል አይኖርም።የቃየል ልጆች ሲያጠፉን እንዲያው ዝም ብለን የምንጠፋ አይደለንም።ከእኛ ዘንድ እውነት አለ፤ ከእኛ ዘንድ የነፃነት ብርሃን አለ፤ ከእኛ ዘንድ የፍትህ ዘንግ አለ፤ከእኛ ዘንድ የእኩልነት ሚዛን አለ፤ ከእኛ ዘንድ እግዚአብሄር አለ።ይሄን ሁሉ ይዘን እናሸንፋለን እንጂ አንሸነፍም።የምናሸንፈው ለበቀል እንዳይደለ አሁንም እንነግራችኋለን። የምናሸንፈው በክፉው ላይ መልካሙን ዘር በመዝራት ነው።በጭቆና ላይ ነፃነትን፤ በአድልዎ ላይ ፍትህን፤ በህግ አልባነት ላይ የህግ የበላይነትን፤ በጎጠኛ አስተሳሰብ ላይ ብሄራዊ አስተሳሰብን ማስረፅ ስንችል ነው አሸንፈናል የምንለው። የጎሰኛነትን አጥር አፍርሰን የኢትዮጵያዊነት ስሜት ማስረፅ ስንችል ነው አሸንፈናል የምንለው። እኛ ስናሸነፍ የሚሆነው ይሄው ነው። ከእኛ ዘንድ የበቀል ስሜት የለም። ከእኛ ዘንድ ያለው ሁሉም ከህግ በታች ሁኖ ህግና ፍትህ እንዲነግሱ የሚያስችል ብርቱ ፍላጎት ነው።

ስለዚህ ጠመንጃ ያነገታችሁ ኃይሎች እኛ ከቆምንለት ቅዱስ ዓላማ ጋር እንድትተባበሩ እንጠራችኋለን።ኑና የጭለማ ኃይሎችን ምሽግ አፍርሰን የብርሃን ልጆችን አምባ አብረን እንሥራ። ኑና አብረን የወገኖቻችንን እምባ እናብስ። ኑና በግፍ ያለፍርድ የታሠሩትን እናስፈታ ።ኑና የጭቆናን ቀንበር አብረን እንስበር። ኑና አብረን አገራችንን ከፍ ከፍ እናድርጋት።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!

www.ginbot7.org

LEAVE A REPLY