397466_565476906808410_1873477712_n
PG7
ይገረም አለሙ
ወያኔዎች ለትግል በርሀ ገባን የሚሉበት ግዜ የንጉሡ ሥርዓ ፈርሶ ኢትዮጵያ ወዴት አንደምትሄድ አይደለም የት ላይ እንደቆመች እንካን ብቅጡ ያልየበት ወቅት ስለነበር ለብሶት ዳርጎ ወደ ጫካ የሚያስኬድ ቀርቶ ከተማ ተቀምጦ ለማኩረፍ የሚያበቃ በደል ነበር ለማለት አይቻልም፡፡ ስለሆነም ወያኔዎች በዛን ወቅት ለትግል የተነሱት የአጼ ዮሐንስን ቤተ መንግሥት ይዘው የትግራይን መንግሥት የመመስረት ህልማቸውን ለማሳካት መንግሥት አልባው ወቅት ምቹ ሆኖ ስለታያቸው ነበር፡፡ ቢዘገይም ካሰቡት በላይ ተሳክቶላቸዋል፡፡
ወያኔዎች ሀ ብለው ትግል ሲጀምሩ በሰነድ ያሰፈሩት ዓላማቸውም ሆነ ፤አመሰረራታቸውን፣ እድገትና ሂደታቸውን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች የሚሰጡት ምስክርነት ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያን በጥቅል እየገዙ ነጻ አውጪ የሚለውን ስማቸውን መለወጥ አለመቻላቸውና ተግባራቸው ሁሉ ጫካ የገቡበትን ዓላማም ሆነ የረዥም ግዜ ዘላቂ ግባቸውን ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ፡፡
ንጉሳዊው ሥርዓት ፈርሶ የመጪው ምንነትና እንዴትነት ባልለየበት ሰዐት አጋጣማዊ በአጭር ግዜ ዓላማችንን ለማሳካት ያስችለናል በማለት ከከተማ ተጠራርተው በረሀ ቢወርዱም የአጭር ግዜ ዓላማቸውን ለማሳካትም ሆነ ወደ ረዥሙ ግዜ ግባቸው የሚያደርሳቸውን መንገድ ለማመቻት በጥልቀት አስበውና አቅደው የተነሱ ለመሆናቸው በብልሀትም በጉልበትም የፈጸሙዋቸው ተግባሮችና አሁንም ቀሪ ዓላማቸውን ለማሳካት እየሄዱበት ያለው መንገድ ይመሰክራል፡፡ሀያ አራት አመት አናሳዎቹ ብዙኃኑን ረግጠው እየገዙ ለመዝለቅ መቻላቸውም በራሱ ከመነሻው በጠንካራ መሰረት ላይ መቆማቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
ምንም እሰጥ አገባ የማያስከትለውና እነርሱም ሊክዱት የማይችሉት አነሳሳቸው ለትግራይ መንግስትነት ነበር፡፡ ነገር ግን አጋጣሚው ለኢትዮጵያ መንግሥትነት አበቃቸው፡፡ እነርሱ ግን መነሻ ዓላማቸውም ሆነ መድረሻ ግባቸው ይህ አይደለምና ሀያ አራት አመት በሥልጣን ላይ ሆነውም የኢትዮጵያ መንግሥት ለመሆን አልቻሉም፡፡ የኢትዮጵያን መንግስትነት በመያዛቸው ምክንያት የዘገየው ግን ሊተውት ያልቻሉትና መቼ ተግባራዊ እንደሚሆን እነርሱም ርግጠኛ ያልሆኑበትን ዓላማቸውን ማመቻቸቱን ግን አንድም ቀን ችላ ብለውት አያውቁም፡፡
ያ የደደቢት ጽንስ ዓላማቸው በአስተማማኝ ተግባራዊ እንዲሆን ሁለት አበይት ነገሮችን ይፈልጋል፡፡ አንድ ለሚመሰረተው የትግራይ መንግሥት ዘላቂነትና መረጋጋት ኢትዮጵያዊነት የሚባለው የእንድነት አስተሳሰብ መጥፋትና ኢትዮጵያ የተዳከመችና የተበታተነች ሀገር መሆን፡፡ ሁለት አዲሲቱ ሀገር በሁለንተናዊ መልኳ ራሱን እንድትችል የቆዳ ስፋቷን ማስፋት፤ መሰረተ ልማቷን ማስፋፋት የህዝቡን ስነ ልቦና መለወጥ፡፡ ወያኔዎች ይህንን በብልሀትም ሆነ በጉልበት ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት ትግሉን ሀ ብለው ሲጀምሩ ነው፡፡
ገና ትግላቸው ሳይጠነክርና አቅማቸው ሳይደረጅ ሀገራዊ ዓላማና አደረጃጀት የነበራቸውን ድርጅቶች ዒላማ ማድረጋቸው በኢትዮጵያዊነት ላይ ላላቸው አመለካከት አንዱና ዋናው ማሳያ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ በቀላሉ በኢህአፓና ኢዲዩ ላይ የፈጸሙትን ማስታወስ ይበቃል፡፡ ከዛም ከኢህአፓ በወጡ እንበለው በከዱ ወይንም ለወያኔ እጅ በሰጡ ሰዎች የተመሰረተውና የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ይባል የነበረውን ፓርቲ ዓላማና ስም አስለውጠው ብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት እንዲባል ሲያደርጉት ሀገራዊ አሰተሳሰብ ፈጽሞ አንዲጠፋ ታጥቀው የሚሰሩ ለመሆናቸው በቂ ማረጋገጫ ነበር፡፡ ልብ ያለው ብዙም አልነበረም እንጂ፡፡
ብሄር ብሄረሰቦች በአለፉት ሥርዓታት የተነፈጉትን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ለማጎናጸፍ በሚል ልብ አማላይ ስብከት በየደረሱበት ምርኮኛውንም ወዶ ገቡንም እየሰበሰቡ አባልም አጋርም ያሉዋቸውን የጎሳ ድርጅቶች በመመስረት ለዓላማቸው ስኬት አንቅፋት ይሆናል ያሉትን ኢትዮጵያዊ አመለካከት የሚያጠፉበትን መንገድ ሲያመቻቹ ዓላማቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁና የመሪዎቹን እኩይ ተግባር የተረዱ ሰዎች ሊከተል የሚችለውን ጥፋት ለማመላከት ቢሞክሩም ብዙም ከቁብ የቆጠራቸው አልነበረም፡፡
ይልቁንም በየጎሳችሁ ተደራጁና የሽግግር መንግሥቱ አካል ሁኑ የሚለውን ጥሪ ተቀብለው አያሌ ኢትዮጵያውያን በአጭር ግዜ በርካታ የብሔር ብሄረሰብ /የጎሳ ድርጅቶች በመመስረት እያወቁም ይሁን ሳያውቁ የወያኔዎቹን መንገድ አመቻቹላቸው፡፡ (በደቡብ ብቻ በአንድ ግዜ ከ15 በላይ ድርጅቶች መፈጠራቸውን እናስታውሳለን፡፡) አስገራሚ የነበረው ነገር በብሄራዊ ስሜት አቀንቃኝነት በሀገራዊ መፈክር አንጋቢነት ከዛም በላይ በአለም አቀፋዊ አጀንዳ አራማጅነት ይታወቁ የነበሩ ትላልቅ የተባሉ ሰዎች ሳይቀሩ የጎሳ ድርጅት መስርተው የሽግግሩ ፓርላማ ውስጥ ለመታየት መብቃታቸው ነበር፡፡
ይህ የኢትዮጵያዊነትን ብሎኮ እየገፈፉ የየጎሳውን ነጠላ እያለበሱ የማስጨፈር መላው በብዙ መልኩ የሰመረለት ወያኔ የሚዘፍኑትን ዘፈን ግጥምና ዜማ ሳይቀር እየሰጠ ሁሉንም በተናጠል ማዘፈን ቻለ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ያለፈ ታሪክ እየመዘዘ ለእያንዳንዱ የቤት ስራ በመስጠት የኢትዮጵያ ልጆች ርስ በርስ አንዲወጋገዙና ሆድና ጀርባ እንዲሆኑ ለማድረግ ቻለ፡፡
ወያኔዎች ይህን በማድረግ ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ መሰረታቸውን ለማጠናከር ያስቻላቸውን ኢኮኖሚያዊ እቅዳቸውንም አሳክተዋል፡፡ በድርጅት ከህውኃት በክልል ከትግራይ በስተቀር ሌሎቹ በተሰጣቸው አጀንዳ ተጠምደው በጎሳ ፖለቲካ ሰክረው እንወክለዋለን የሚሉትን አካባቢ እንኳን በንቃት ማየት ባለመቻላቸው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የነበሩና የወያኔን ቀልብ ያማለሉ ንብረቶች ያለምንም ተቃውሞና ሀይ ባይ የተቻለው በቀን በጠራራ ጸሀይ ሌላው በለሊት መብራት እያጠፋ ተጓጓዘ፡፡
በወያኔ የራስን እድል በራስ መወሰን ልብ አማላይ ስብከት ተታለውም ይሁን ከመጀመሪያው በውስጣቸው የነበረው የጎሰኝነት ስሜት አመች ግዜ ሲያገኝ ፈንቅሎአቸው ይሁን ባይታወቅም ድርጅት እየመሰረቱ በወያኔ የጎሰኝነት መስመር የገቡ ሰዎች እንዳንዶቹ ብዙም ሳይቆዩ ከሰሙ፤ እስከዛሬ የዘለቁትም ቢሆኑ ለወያኔ ከመጥቀማቸው ባሻገር ይህ ነው የሚባል ያስገኙት ፋይዳ የለም፡፡
ምንም ተባለ ምንም ተደረገ ግን ኢትዮጵያዊነት እንዲህ አንደ ዋዛ የሚጠፋ ባለመሆኑ ወያኔ አጠፋሁት ብሎ እፎይ ማለት በጀመረ ማግስት መልሶ እያንሰራራ ይሄው እስከ ዛሬ እንቅልፍ እንደነሳው ይገኛል፡፡ ወያኔ ከደደቢት ሲነሳ ካነገበውና ሀያ አራት አመታትም ለተግባራዊነቱ እየሰራ ካለው ዘላቂና የረዥም ግዜ ግቡ አንጻር ከኢትዮጵያዊነት ጋር ሊታረቅ የሚችል አይደለም፡፡ ኢትዮጵዊነትም በየዘመናቱ ከውስጥም ከውጪም የተቃጣበትን አደጋ ሁሉ ተቋቁሞ ለመዝለቅ የቻለ መቼም ሆነ በማን የሚጠፋ አይደለ እንደመሆኑ መቼም ሆነ በማን የሚጠፋ አይደለም፡፡ ይህም ሆኖ ወያኔ በበርሀ ታጋይነቱም ሆነ በከተማ መንግሥትነቱ ዘመን የፈጸማቸው ተግባራት ሁሉ ኢትጵያዊነትን ማጥፋት እንዳላስቻሉት ከራሱ ተሞክሮ ትምህርት አግኝቶ ከእኩይ ተግባሩ ሊገታ አልቻለም፡፡ በመሆኑም ግዜ እየጠበቀ ለደደቢቱ ዓላማው ስኬት ሲል በብልሀትም በጉልበትም በሚፈጸመው ተግባር ሕዝብ እየተጎዳ ነው፡፡ ከዚህ የማያባራ ጉዳት ለመዳን የ ህዝቡ ምርጫ የሌለው አማራጭ አንድ ነው፡፡ እሱም ከወያኔ አገዛዝ መገላገል አለያም ወያኔ መቼም በምንም ሊያጠፋው የማይችለውን ኢትዮጵያዊነት ለማጥፋት በየግዜው በሚፈጽማቸው ኢ- ሰብአዊ ተግባራት እየታሰሩ እየተደበደቡ እየተገደሉ በአንዱ ሲደርስ ሌላው እያለቀሰ ተራውን እየጠበቀ መኖር፡፡ ሁለተኛው የሚመረጥ ኣራች አይመስለኝም፡፡
ለኢትዮጵያ መንግስትነት መብቃቱ የደደቢት ዓላማውን ሊያስተወው ያልቻለው ወያኔ በኢትዮጵያ መንግሥትነት ስም የያዘውን ሥልጣን የተነሳበትን ዓላማ ለማሳካት የሚያስችለውን ምቹ ሁኔታ ለማመቻቸት መጠቀሚያ ማድረግ የጀመረው ገና ወንበሩ ሳይደላደል እንደነበረ አሌ የሚባል አይደለም፡፡ ይህንንም የቻለውን በብልሀት በዚህ መንገድ ያልሆነለትን ደግሞ በጉልበት ተግባራዊ እያደረገ ከዛሬ ደርሷል፡፡ አሁንም ቀጥሏል፡፡
ወያኔ የደደቢት ውጥኑን ለማሳካት ከተጠቀመባቸው ብልሀቶች አንዱና ዋናው በማር የተለወሰ መርዝ የሆነው ፌዴራላዊ አወቃቀር ነው፡፡ የፌዴራል የመንግሥት ሥርዓትም ሆነ የመሬት አከላለል የአሀዳዊ ሥርዓት ደጋፊ ከሆኑ ሰዎች በስተቀር በአብዛኛው ሰው የሚደገፍ በመሆኑ ወያኔ ከላይ ሲታይ ለሀገርና ለሕዝብ በማሰብ የመረጠው በሚመስል ሁኔታ በኢትዮጵያ ተግባራዊ አንዲሆን በህገ መንግስት እንዲሰፍር ያደረገው ብዙም ተቃውሞ ሳይገጥመው ነበር፡፡ ፌዴራል አወቃቀርን የፈለገው የተነሳበትን ዓላማ ገቢራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟያነት ብሎም ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በማለም አንጂ ለሀገርና ለሕዝብ አስቦ ባለመሆኑ አከላለሉ በቋንቋንና በብሄረሰብ /በጎሳ ላይ ብቻ ተመስርቶ የሚከናወን እንዲሆን የሚያደርግ ሕገ መንግሥት አጸደቀ፡፡ ይህ አዋቃቀር የወያኔን ፍላጎት የሚያሳካ አንጂ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የማይሆን ለመሆኑ የደቡብ ክልል የሚባለውን ማየት ብቻ ይበቃል፡፡ ፌዴራላዊ መንግስትነትን ደግፈው ቋንቋና ብሄርን መስፈርት ያደረገውን አወቃቀር የተቃወሙ የመኖራቸውን ያህል ደጋፊዎችም ስላልታጡ የፌዴራል አወቃቀሩን በህገ መንግሥት ለማስፈርም ሆነ ተግባራዊ ለማድረግ ወያኔ ብዙ አልተቸገረም፡
በመሆኑም በፋኖነት ዘመኑ የትግራይን የቆዳ ስፋት ለማስፋት በሀይል የያዛቸውን የጎንደርና የወሎ ቦታዎች በዚህ የህገ መንግስቱ አንቀጽ መሰረት ከማጽናቱ በተጨማሪ ሲጎመዥባቸው የነበሩ ለም መሬቶችን በሙሉ የትግራይ ክልል ብሎ ወደሰየመው ለመጠቅለል ቻለ፡፡ እንዲህ በብልሀት በህገ መንግሥት ሽፋን ወደ ትግራይ የተከለሉ ዜጎች እኛ ጎንደሬ /አማራ አንጂ ትግሬ አይደለንም ብለው ትግሬ ናችሁ ለመባላቸው የተጠቀሰባቸውን ህገ መንግስት ራሱኑ ለመከራከሪያነት ጠቅሰው ይህን መሰል ጉዳይ የማየት ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ለተሰጠው የፌዴሪሽን ምክር ቤት አቤት እስከ ማለት ቢደርሱም ጩኸታቸው በተኩላ አደባባይ የበግ አቤቱታ አንዲሉ ሆኗል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ወያኔ ሲጠቀምበትና ህዝብ ጥያቄ ሲያነሳ አፈጻጸሙ የተለያየ በመሆኑ ሕግ አለ ብለው በህግ ተማምነው ከጎንደር አዲስ አበባ ዘልቀው አቤት ላሉ ወገኖች ለጥያቄአቸው መልስ ሊያገኝላቸው ቀርቶ ከጥቃት ሊታደጋቸው ባለመቻሉ ዓላማ ፍላጎቱን በብልሀት ካልሆነም በጉልበት ተግባራዊ በሚያደርገው ወያኔ እየታደኑ ነው፡፡ ህገ መንግሥቱ በተግባር የተጻፈበትን ወረቀትና ቀለም ያህል አንኳን ዋጋ የለውም የተባለውም አንዲህ በመሆኑ ነው፡፡
ወያኔ ዓላማውን ተፈጻሚ ለማድረግ አስቀድሞ በብልሀት ብልሀቱ ካላዋጣ በጉልበት ይሄ አልሆን ካለ ደግሞ በህግ መሳሪያነት ጉልበት ከሥርዓት ይሉት ዘዴ የሚጠቀም በመሆኑ ከመነሻው ነገሮችን ለዚሁ ያመቻቻል፡፡ በመሆኑም ወደ ትግራይ ሊጠቀልላቸው ያሰባቸውን ቦታዎች አስመልክቶ በብልሀትም በጉልበትም ምን ማድረግ እንዳለበት ገና ደደቢት ሳለ ነው ያሰበው ያቀደውና የተዘጋጀው፡፡ ይህ እቅዱንም ነው በፋኖነት ዘመኑም ሆነ በመንግሥትነት ግዜው ተግባራዊ ያደረገውና አሁንም እያደረገ ያለው፡፡
ከእነዚህ ስራዎች አንዱና ዋናው ከላይ የተጠቀሰው ቋንቋና ብሄርን መሰረት ያደረገው የፌዴራል አዋቃቀር ሲሆን ሌላው ተቀናሽ ያላቸውን ታጋይ ተጋዳላዮች ቦታው ላይ ማስፈር ነው፡፡ እነዚህ እነ መለስን ቤተመንግስት በማድረስ ተልእኮአቸው የተጠናቀቀና ከታጋይነት ወደ ቀደሞ አራሽነታቸው አንዲመለሱ የተደረጉ ዜጎች በቦታው የሰፈሩት ከነ ጠመንጃቸው በመሆኑ የተሰጣቸውን ለም መሬት አርሰው ከሚያገኙት ጥቅም በላይ ለወያኔ የሚሰጡት ጥቅም ብዙ ነው፡፡ ወሰናችን ተከዜ ነው በማለት የሚያስቸግሩትን እያስፈራሩ ጸጥ ማሰኘት፤ በፍራቻ ለማይበገሩት ደግሞ ጠመንጃቸውን ስራ ላይ ማዋል፡፡ ይህን ደግሞ ሰሞኑን በተካሄደ ሰልፍ ላይ የተሰሙት ታውቁናላችሁ እናሳያችኋላን ወዘተ መፈክሮች በቂ ገላጮች ናቸው፡፡ ሌላው የወያኔ ርምጃ ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ሰዎችን በመውሰድ በወረራ በየዘው መሬት ላይ ማስፈሩ ነው፡፡ ተቃውሞ በርትቶ ትግሉ ገፍቶ በብልሀትም በጉልበትም የማይገታ ከሆነና ወያኔ በመጠባቢቂያነት ወደሚያስበውና አስቀድሞ የተዘጋጀበት ወደሚመስለው ህዝበ ውሳኔ ቢያመራ የተጋዳላዮቹም ሆነ የሰፋሪዎቹ ውሳኔ ምን እንደሚሆን የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
ከሀገር ጥቅም አንጻር ሳይሆን ከራሱ ዓላማ ስኬት አንጻር አርቆ የሚያስበውና የሚሰራው ወያኔ ልብ አማላዩን የፌዴራል ስርዓት ለራሱ ዓላማ ማመቻቻ የተጠቀመበት በመሬት አከላል ብቻም አይደለም፡፡ አንድ ቀን መንግሥት ሊሆንባት የሚያዘጋጃትን ክልል በቀሪው የኢትዮጵያ ሀብት በሁለንተናዊ መልክ ለማሳደግም ተጠቅሞበታል፡፡ የፌዴራል ስርዓት በሚፈቅደውና በህገ መንግስቱም ውስጥ በተጻፈው መሰረት ክልሎች ሙሉ ነጻነት ቢኖራቸው እቅዱን ገቢራዊ ማድረግ እንደማይችል ቀድሞውንም የተረዳውና የዘየደው ወያኔ በአደባባይ የብሄር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራስን የማስተዳደር መብት እስከ መገንጠል ህገ መንግሥታዊ እውቅና እንዳገኘ እየለፈፈ በተግባር ግን የየክልሎቹ ሹማምንት ስሙንና ወንበሩን ከመያዝ የለፈ ሥልጣንም ነጻነትም እንዳይኖራቸው አድርጎ ያልተጻፈ አሀዳዊ ስርዐት እያራመደ የሁሉም ጠቅላይ ገዥ ራሱን አድርጎ ይሾማል ይሽራል ሀብት ይዘርፋል ፡፡
ወያኔ ፍላጎቱን በብልሀት ለመፈጸም እንዲያስችለው በማር የተለወሰ መርዝ ሲያቀርብልን መርዙን በለማየት ለእኩይ አላማው ስኬት ብዙዎች ተባባሪ ሆነዋል ብዙዎችም በዝምታ ተመልክተዋል፡፡ ነገሮች ካለፉ በኋላ መርዙን በማየት የሚሰሙ ጩኸቶችም ሆኑ የሚደረጉ ትግሎች በብልሀት ያሳካውን በጉልበት ለማስጠበቅ በሚወስደው ርምጃ መስዋእትነት እንጂ ድል ሊያስገኙ አልቻሉም፡፡
ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን የተለየ የሚመስል ነገር ይታያል፡፡ ወያኔ በማስተር ፕላን ስም በብልሀት ያሰበው የመሬት ወረራ የገጠመውን ተቃውሞ በጉልበት ሰጥ ለማድረግ ኢሰብአዊ ተግባር ፈጽሞ አልሳካ ሲለው የለመደውን በህግ ሽፋን ጉልበት ከሥርዓት የመጠቀም አካሄድም ሞክሮ ውጤት ባለማግኘቱ ማስተር ፕላኑን ሰርዣለሁ ብሏል፡፡ ይህን ብሎ ግን በባልስልጣኖች አንደበት የሚነገረውም ሆነ በነብሰ ገዳዮቻቸው የሚፈጸመው ድርጊት እንዲሁም ኦህዴድን በወያኔ ታማኞች ለማጠናከር የተያዘው ርምጃ ወያኔዎች እንዴት ያሰብነውን ማሳካት ያቅተናል በሚል አልህ ውስጥ ያሉ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ታክሲ አሽከርካሪዎች ባካሄዱት የአንድ ቀን ስራ ማቆም መንገድ ትራንስፖርት ያወጣውን ደንብ ለሶሰስት ወር አዘግይተነዋል የሚል ምላሽ ተሰምቷል፡፡
ጫካ ሆኖም ሆነ ቤተመንግሥት ተቀምጦ የደደቢት ህልሙን በብልሀትም በጉልበትም ተግባራዊ ሲያደርግ ለኖረው ወያኔ ማስተር ፕላኑን ሰርዣለሁ ማለቱ የመንገድ ሥነ ሥርዓት ደንቡንም ተግባራዊነት ለሶስት ወር አራዝሜአለሁ ማለቱ የህዝብ ትግል ውጤት መሆኑ ባይካድም ወያኔ የባህርይ ለውጥ አምጥቶ ነው ማለት ግን አይቻልም፡፡ እንዲህ በማሰብ መዘናጋት ከተፈጠረ ይህን ውጤት ያስገኘውን ትግል ማክሸፍ ታጋዮችንም ማስበላት ይሆናል፡፡
ወያኔ ከዓላማው ፍንክች ያለበት ግዜ የለም፡፡ቅንጅቶችን ከጸሀይ በታች ባለ ማናቸውም ጉዳይ ለመነጋገር ዝግጁ ነኝ ብሎ ትጥቃቸውን (የህዝብ ሀይል ) ካስፈታ በኋላ እኔ በመረጥኩት አጀንዳና በምለው መንገድ ብቻ ነው መነጋገር የሚቻለው ማለቱ የሚዘነጋ አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም በብልሀትም በጉልበትም ያሰበውን ከማሳካት ወደ ኋላ የማይለው ወያኔ ሸብረክ ያለ የሚመስለው ግዜ ለመግዛት ሁኔታዎችን ለማመቻቸትና ወጥመዱን ለማጥበቅ እንደሆነ በመረዳት በማስመሰያ ድርጊቶች ሳይታለሉና ሳይዘናጉ ለተጨባጭ ለውጥ መታገል ያስፈልጋል፡፡
ወያኔ የደደቢት ህልሙን ለማሳካት ብልሀትን ጉልበትን ጉልበት ከሥርዓትን እንደ ሁኔታው እያማረጠም እያደባለቀም አንደሚጠቀመው ሁሉ በለውጥ ሀይሉ በኩል ለትግሉ ከግብ መድረስ አንድና አንድ መንገድና አማራጭ ብቻ የሚጠቀም ሳይሆን መስዋዕትነቱን ቀላል ድሉን ቅርብ ሊያደርጉ የሚችሉ ግንባር ቀደም ታጋይ አታጋዮችን ከአደጋ የሚከልሉ ወያኔ ጉያ ውስጥ እሳት ማቀጣጠል የሚያስችሉ አማራጭ ስልቶችንና ተግባራዊ የማድረጊያ መንገዶችን መተለም ያስፈልጋል፡፡ በወያኔ ብልሀት መበለጥ፤ በጉልበት ለሚያደርገው መንበርከክ፤ በህግ ሽፋን በሚፈጽመው ውንብድና መታለል እንግዲህ ያበቃ ይመስላል፡፡ቢሆንም ግን ወያኔ እስካሁን ካጠፋው ይልቅ ወደፊት ሊያጠፋው የሚችለው ለበለጠ ተጠያቂነት እንደሚዳርገው ተረድቶ እርቅ የሚፈልግ፤ አድራጎቴን ህዝብ አልወደደውም ብሎ ከደደቢት ህልሙ የሚላቀቅ ሳይሆን ሸብረክ ያለ እየመሰለ የህዝብን ጥያቄ ተቀብያለሁ እያለ በብልሀትም በጉልበትም ዓላማውን ተግባራዊ ለማድረግ ከጥፋት የማይመለስ በመሆኑ ከነጻነት ወዲህ ማዶ የሚኖር መዘናጋት ተራ በተራ መበላትን ያስከትላል ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here