ባለፉት 25 ዐመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ የመጣ ነው ወይ?

0

ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ


ባለፉት 25 ዐመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ የመጣ ነው ወይ?

ባለፉት 25 ዐመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ የመጣ ነው ወይ? ይህንን ጥያቄ መመለስ የምንችለው፣ ከየትኛው ሁኔታ በመነሳት ነው? የምንገመግመው ወይም የምንለካው? የሚለውን ጥያቄ ካስቀመጥንና ለመመለስ የቻልን እንደሆን ብቻ ነው። ሌሎች እጅግ አብስትራክት የሆኑ የጂዲፕ አሰላልና የምርት ጭማሮና ከውጭ የመጣን ልዩ ልዩ ወደ ምርት ውስጥ የሚገቡ በግማሽ የተፈበረኩና የጥሬ-ሀብት ጉዳዮችን ትተን እንዲያው በደፈናው ስንመለከት ከተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል አንጻር፣ ምናልባት 1% ለሚጠጋው የህብረተሰብ ክፍል „የኢኮኖሚ ዕድገት“ መጥቶለታል ማለት ይቻላል። ይህ ዕድገት በትላልቅ ህንጻዎች፣ በሆቴል ቤቶች ስራና ጋጋታ፣ በመንገድ ስራ፣ የስኳርና የቢራ ፋብሪካ የሚገለጽ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከመንግስት ጋር በሺህ ድሮች የተቆላለፉ አየር በአየር ንግድ ውስጥ በመሰማራት፣ የውስጥን ጥሬ-ሀብት በመሸጥ የገቢያቸው መጠን በፍጥነት የተተኮሰ የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ የነዚህ ህብረተሰብ ክፍሎች የፍጆታ አጠቃቀም በከፍተኛ ደረጃ አድጓል። ከውጭ የሚመጣው የቅንጦት ዕቃ የማህበራዊ ስታተሳቸውን ከፍ አድርጎለታል። ይህንና ከዚህ ጋር የተቆላለፈውን ሀብት ጨራሽ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ነው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተብሎ የሚወደስልን። ይህንን ዐይነቱን የኢኮኖሚ ዕድገት በመርከንታሊስቶችም ሆነ በፕሮፌሰር ፍሪድርሽ ሶዲና ፕሮፌሰር ኢሪክ ራይነርት የኢኮኖሚ ቲዎሪ መነፅር ስንመረመረው አዲስ ሀብት የፈጠረ አይደለም። ቲክኖሎጂያዊ ምጥቀትን ያመጣ አይደለም። የውስጥ ገበያ እንዲስፋፋና እንዲዳብር ያደረገና የሚያደርግ አይደለም። ለስራ ፈላጊው ሰፊ ህዝብ የስራ መስክ የከፈተና የሚከፍት አይደለም። የባሰ ጥገኝነትንና፣ ኢኮኖሚያዊ መዝረክረክን ያስከተለና የሚያስከትል ነው። ሀብትን የሚያባክን ነው። በተፈጥሮና በሰው ልጅ ላይ ዘመቻ የከፈተ „የኢኮኖሚ ዕድገት“ ነው። ይህንን ዐይነቱን ዕድገት ጥፋት እንለዋለን። የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል በማባለግ፣ ሰፊውን ህዝብ በማድኸየት አቅመ-ቢስ ያደረገ ነው። እንደሚታወቀው አንድ አገር እንደ አገር የምትከበረው ከሁሉም አንፃር ማደግ ስትችል ነው። ግርማ ሞገስ ያላቸው ከተማዎችና የመኖሪያ ቤቶች ሲሰሩና ለሰፊው ህዝብ ሲዳረሱ ነው። ህዝቡ የመፍጠር ችሎታው ሲዳብር ነው። እንደ አንድ ዜጋ ሲታይና ጠንካራ ህብረተሰብ ለመመስረት ሲችል በእርግጥም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አለ ማለት ይቻላል። ልዩ ልዩ መናፈሻ ቦታዎችና ሲዘጋጁለትና የኬነትና ቤተ-መጻህፍቶች ሲቋቋሙለት ኢኮኖሚው ማደጉ ብቻ ሳይሆን፣ ህዝቡም አዲስ አስተሳሰብ ማዳበር ይችላል። የሰው ልጅ በዳቦ ብቻ አይኖርም፤ ፍቅርና ልዩ ልዩ መንፈሱን የሚያረኩ ነገሮችም ያስፈልጉታል። ከማያስፈልጉ ነገሮች እንዲቆጠብና ውድ ወንድሙን እንደሰው እንዲያይ ከተፈለገ በሳይንስ የተጠና ባህልም መዳበር ከኢኮኖሚው ዕድገት ጋር መያያዝ ያለበት ጉዳይ ነው። የዛሬው በወያኔ አገዛዝና እንዲሁም በኒዎ-ሊበራል ኤክስፐርቶችና አማካሪዎቹ ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመሰረቱ ማጅራት መቺዎችንና ማፊያ መሳዮችን የፈለፈለና ድህነትን ያስፋፋ ነው። በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በሚታተመው በሪፖርተር ላይ የወጣውን ዘገባ መመልከቱ ሁኔታው የቱን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል።

ከዚህ በመነሳት እኛ ኢትዮጵያውያን ምሁር ሆን አልሆን ለምን ዐይነት ሀብረተሰብና ለምን ዐይነት አኮኖሚ ነው? የምንታገለው ብለን መከራከር አለብን። እኛን የሚያሳሰብን የዚህኛው ወይም የዚያኛው ብሄረ-ሰብ ነፃ መውጣትና አለመውጣት አይደለም። እኛን የሚያሳስበን ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው የአርሞው፣ የአማራው፣ የትግሬው፣ የወላይታው፣ የጉራጌው… ወዘተ የኑሮ ሁኔታ ነው። እኛን የሚያሳስበንና አንጀታችንን የሚያቃጥለን ሺህ በሺህ ለአረብ አገሮች በመንግስት የሚሸጡት ልጆቻችንና እህቶቻችን ህይወት ነው። የሚያሳስብን በመንገድ ላይ የሚያድረው፣ ከቆሻሻ እየለቀመ የሚበላው፣ የዕፅ ሱሰኛ እንዲሆን የተገደደው ልጃችን ህይወት ነው። እኛን የሚያስጨንቀን የህዝባችን ኑሮ መጨለሙ ነው። እኛን የሚያሳስበን የአገራችን ውድመትና መቸብቸብ ነው። ህዝቡ እንደ አንድ ዜጋ እንዳይተሳሰር መደረጉ ነው። እኛን የሚያሳስበን ህዝባችን ዕውነተኛ ነፃነቱን እንዳይጎናፀፍና ዕድሉን ወሳኝ እንዳይሆን መደረጉ ነው። በዚህ ዐይነቱ ውጥቅንጡ የወጣ ስርዓት ግለሰብአዊ መብቶች መጣሳቸው ነው የሚያስጨንቀን። ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ መሪ የሌለው መደረጉ ነው ሌት ከቀን እንቅልፍ የነሳን። የሚያሳስበን ያረጀ የብሄረ-ሰብ ጥያቄ ሳይሆን የዘጠና ሚሊዮኑ ህዝብ ዕድል ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከ50ና ከ100 ዐመት በኋላ ኢትዮጵያችን ምን ትመስላለች የሚለው? ነው የሚያሳስበን። የዚኸኛው ወይም የዚያኛው ፓርቲ ለስልጣን መውጣትና መራወጥ አይደለም አንጀታችንን የሚያቃጥለን። ባጭሩ የአገርና የህዝብ ደህንነት፣ ከሁሉም አቅጣጫ ዕድገት አለመኖር፣ ዕድገት እንዳይኖር ከውጭ የተሸረበብን ሴራና በጣም የደከመው ምሁራዊ እንቅስቃሴ ነው እንቅልፍና ዕረፍት የነሳን።

የዛሬው ሁኔታ በዚህ መልክ አፍጦ አግጦ ባለበት ወቅት አንዳንድ ምሁራን ስለተከታታይነት(Sustainable Economic Growth) ስላለው የኢኮኖሚ ዕድገት ይጽፋሉ። በየጊዜው ይህንን በማስመር የሚጽፉት ምሁራን፣ 1ኛ) ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ምን እንደሆነ ለተራው ሰው ሲያስረዱ አይታዩም። 2ኛ) ባለፉት 25 ዐመታት በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ትችታዊ በሆነ መልክ በመመርመርና በመጻፍ አላስተማሩንም። 3ኛ) ዛሬ አገራችን ምድር አፍጦ አግጦ ለሚታየው ድህነትና ረሃብ ዋናው ምክንያት ምን እንደሆነ አልነገሩንም። እንዲያው በደፈናው ብቻ ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ያስፈልጋል እያሉ ነው የሚነግሩን። ይህንን ካላብራሩልን ደግሞ የውር ድንብራችን ነው የምንራመደው ማለት ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ከዚህ ዐይነቱ አባባል የምንረዳው ኢኮኖሚው አድጓል፣ ይሁንና ግን ተከታታይነት የለውም የሚል ድምደማ ነው። በመሰረቱ የተለያየ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊኖር አይችልም። በተለያዩ አገሮች የተለያዩ የህብረተሰብ አወቃቀሮችና አገዛዞች ቢኖሩም፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ዋናው አንቀሳቃሽ ሃይል ፈጠራ፣ ከዚህ የሚፈልቁት ሳይንስና ቴክኖሎጂዎች ናቸው። ከዚህም ባሻገር ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ጉዳይ የቁጥር ብቻ ሳይሆን የዐይነትም ጭምር ነው። እነዚህ ጉዳዮች ደግሞ የግዴታ ከሰው ልጅ የኑሮ መሻሻል ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው። ስለተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት በምናወራበት ጊዜ፣ ስለሪሶርስ አጠቃቀም ጉዳይ፣ ስለ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መፈጠር ጉዳይ፣ ስለ አካባቢ ደህንነት ጉዳይ፣ ስለ ከተማዎችና መንደሮች በደንብ በፕላን መታቀድና መገንባት ጉዳይ፣ ስለ ፍሳሽና ስለቆሻሻ መጣያ ወይም ሪሳይክል ማድረጊያ ጉዳዮች… ወዘተ. ማተት ያስፈልጋል። በተለይም የተፈጥሮን ሀብትና ጫካንም በስነስርዓት መንከባከቡና መጠበቁ የተከታታይ ዕድገት ዋናው ዕምብርት ነው። ንጹህ አየር መተንፈስና ጤንነታችንም ሊጠበቅ የሚችለው የአካባቢያችን ሁኔታ ከሳይንስ አንፃር እየተጠና እንክብካቤ ሲደረግለት ብቻ ነው። በተጨማሪም የወንዞችንና የባህሮችን ህይወት መንከባከቡ እጅግ አስፈላጊ ነው። እንደሚባለው አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ወንዞች የተመረዙና እየደረቁ የሄዱና ህይወትም የሌላቸው ናቸው። ለዚህ ሁሉ በብዙ የስልጣኔ ተመራማሪዎችና የኳንተም ሳይንስ ምሁራን የተደረሰበት ድምዳሜ ለተከታታይ ዕድገት ዋናው ወሳኝ ኃይል ንቃተ-ህሊና( Quantum Consciousness) ነው። በሌላ አነጋገር ዝቅተኛ ንቃተ-ህሊና በሰፈነበት አገር ስለ ተራ ዕድገትም ሆነ ስለ ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት ማውራት አይቻልም።

ስለሆነም ተከታታይነት ስላለው የኢኮኖሚ ዕድገት በምናውራበት ጊዜ፣ 1ኛ) የመንግስትን መኪናና የሚከተለውን ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ መመርመር ያስፈልጋል። ይህ እንቅፋት ሆኖ ከታየ ደግሞ የግዴታ ይህንን መለወጥ ያስፈልጋል። አንድ አገዛዝ እንደፈለገው በራሱ „ሎጂክ“ እየተመራ የአገርን ሀብት ሊመዘብርና ህዝብን ሊያደኸይ አይችልም። መብትም የለውም። 2ኛ) ተከታታይነት ስለሚኖረው የኢኮኖሚ ዕድገት ሲነሳ ወይም ሲጻፍ የግዴታ ስለነፃነትና ስለዲሞክራሲ አስፈላጊነት ማንሳትና መጻፍ ያስፈልጋል። 3ኛ) ተከታታይነት የሚኖረው የኢኮኖሚ ዕድገት የወጭ ኃይሎችን ግፊታዊ ጣልቃ-ገብነት ይቃወመል። በሌላ አነጋገር በዓለም አቀፍ ኮሚኒቲው ግፊት ተግባራዊ የሚሆን ፖሊሲ አንድን አገር የግዴታ መቀመቅ ውስጥ እንደሚከታት ማስተማር ያስፈልጋል። ይህም ማለት በአገራችን ምድር ተከታታይነት የሚኖረው የኢኮኖሚ ዕድገት ተግባራዊ ሊሆን የሚችለውና ህዝባችንም የዕውነተኛ ስልጣኔ ባለቤት የሚሆነው ከዓለም አቀፍ ኮሚኒቲው መዳፍ ስር ሲላቀቅና በከፍተኛ ምሁራዊ ኃይል በግሎባል ካፒታሊዝም አማካይነት በሁሉም አቅጣጫ የሚመጣብንን ግፊት መቋቋም የቻልን እንደሆን ብቻ ነው። መልካም ንባብ !!

LEAVE A REPLY