አባይ ሚዲያ ዜና
ናትናኤል ኃይለማርያም

ባለፈዉ ረቡዕ የሙስሊም ሚልሽያ ቡድን አልሸባብ በወያኔ ወታደሮች ቁጥጥር ስር የነበርችን አንድ ትንሽ ከተማ በቁጥጥሩ ስር ማድረጉን አስታወቀ። ከሶማሌ ደቡብ በኩል የምትገኘዉን ይህንን ከተማ የአፍሪካ ሰላም አስከባሪና የመንግስት ወታደሮች አካባቢዉን ለቀዉ መሔዳቸዉን ተከትሎ የአልሸባብ ሚሊሽያዎች ቦታዉን መቆጣጠራቸዉን ከአካባቢዉ ነዋሪዎችና ከአልሸባብ የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የወያኔዉ ወታደሮች አሚሶን በመባል ከሚታወቀዉ የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ጦር እና ከሶማሌ መንግስት ጦር ጋር በሕብረት በመሆን በዚህ በያዝነዉ አመት የታይግሎን አዉራጃን ለመቆጣጠር ከአልሸባብ ጋር በርካታ ጊዜያት ዉጊያ ማድረጋቸዉን ተከትሎ አልሸባብ በፈጠረዉ ጫና ከተማዋን በእጁ አድርጓል።

አልሸባብ ለኢትዮጵያ ድንበር የሆነችዉን የታይግሎን ከተማ ሲቆጣጠር የኢትዮጵያና የሶማሌ መንግስት ወደ ኋላ በማፈግፈግ የባኮሎ ከተማ ወደ ሆነችዉ ወደ ሁዱሩ መሔዳቸዉ ከስፍራዉ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

በዚህ በያዝነዉ ወር ብቻ አልሸባብ 3 ከተሞችን መቆጣጠሩ ሲታወቅ የአልሸባብ ወታደራዊ ቃል አቀባይ  አብዲያሲስ አቡ ሙሳብ ከቦታዉ እንዳስታወቀዉ የወያኔ ወታደሮች እንደለቀቁ ቦታዉን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረናል በማለት ሲገልጽ አካባቢዉም በመቶዎች በሚቆጠሩ የአልሸባብ ወታደሮች መሞላቷን እና በከተማዉ ዉስጥም የአልሸባብ ባነሮች እየታዩ እንደሆነ ታዉቋል።

የኢትዮጵያም ሆነ የሶማሌ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ምንም ለማለት አልደፈሩም።