ዛሬ የደረስንበት ለመድረስ ብዙ የተጓዝን ቢሆንም ገና እጅግ ብዙ መሄድ የሚያሻን መሆኑን መገንዘብም ይኖርብናል። በዚህ ጎዳና ላይ አንድነትና ፍቅርን የሰበኩና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገው የዘመሩ ከግራና ቀኝ ወከባና የደቦ ጥላቻ ቁም ስቅል ያሳያቸው እንደነበር እናውቃለን። ቀላሉ ነገር ጥልቅና ውስብስብ ሆኖብን ግራ በተጋባ አመለካከት መመካከር ሲገባን መካረርን በመረጡልን ልሂቃን እርስበርሳችን እንድንፈራራና አልፈንም እንድንጠፋፋ ተገፍተን ነበር ።

ኢትዮጵያውያን ግን አለም ከመሰልጠኑ በፊት አብሮነትን መረዳዳትን ከዘርና ጎሳ ባለፈ በፍቅር ስንሰለት ተሳስረው ተጋብተውና አንድ ሆነው መኖርን ያስተማሩ መሆናቸውን ዘንግተን ጠላት በሰፋልን የዘር ከረጢት እንድንገባና የሁዋልዮሽ እንድንሄድ ተገደን ቆይተናል። የዚህ መርዝ ተጎጂው በአብዛኛው ፊደል ቆጥረናል ፖለቲካ ገብቶናል የሚለው የህብረተሰብ ክፍል ነበር/ነው። የዚህ ጽሁፍ መነሻ ወዳጄ እመለከተው ዘንድ የጠቆመኝ የሀኒሻ ሰለሞን የዘፈን ክሊፕ ነበር። https://www.youtube.com/watch?v=WwhFSp1elrk&sns=fbEthiopian singer, Hanisha Solomon

አዎን አደንቃታለሁ ድልድይም ሰንሰለትም ሆና ሁሉን ለማቀራረብ የሞከረችባቸውን ስራዎቿንም አውቃለሁ።ዜማዎችዋ ልብ የሚመስጡ መልዕክቶችዋም አስፈላጊና ወቅታዊ በመሆናቸው የድምፅ ወይም የሙዚቃ ጥራት የአጀብ ብዛትና የመሳሰሉትን የማይሻ በማንም ልብ ሊቀር የሚችል መሆኑንም አውቃለሁ። ይህ ልዩ የሆነብኝና እጅጉን ያስደሰተኝ ግን የመድረኩ አይነትና የታዳሚዎቹ ሁኔታ ነበር። አዳራሹ የኦሮሞ ልጆችና ወዳጆች የታደሙበት ስብሰባ ይመስላል። የማያቸው አርማዎችም የዚህ ምስክር ናቸው። ቢሆንም ቢሆንም ከልብ የመነጨ በክህሎቱም ግሩም በሆነ መልኩ የኦሮሞ ወንድሞችና እህቶች እስክስታ ሲወርዱ ማየት ይህን ያህል ብርቅ ይሆንብኛል ብዬ አላሰብኩም ነበር። አንድነታችን ከልብ የመነጨ በመንፈስ የተቆራኘ መሆኑን የሚመሰክር ሁኔታን ዛሬ ላይ ሆኖ እንደማየት የሚያስደስት ነገር የለም። ወያኔዎች ወይም አናሳ አስተሳሰብ ይዘው በችጋራምነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ የሚያራምዱት በልቶ አይጠረቄ የትግሬ ወሮበሎች የቀመሙት የጥፋት መርዝ እንዴት በዚህ መድረክ ላይ እንደረከሰ ማየትን ያህል የሚያስደስት ነገር ከየት ተገኝቶ? ስሜትን ፈንቅሎ ትከሻን የሚያንቀጠቅጥ እስክስታ ምንጩ ውስጣዊ ነውና አንድነትን ፍንትው አድርጎ ያሳየ መድረክ ነበር።

ምናልባት እኒህ መድረኩን የሞሉ ወንድምና እህቶች እንኳንስ እስክስታ መውረድ አማርኛ መስማት ወይም አማራ ማየት እስከመጥላት የደረሰ የፖለቲካ ስሜት ውስጥ ሆነው ከወገናቸው ጋር ተራርቀው ጠላት በፈረቃ እንዲወቃን እድል ለመስጠት የተገደዱ ሊሆኑ ይችላሉ። ዛሬ ግን ሁኔታው ሁሉ ተቀይሮ ወደ አንድ ጎራ መጥተናል። ለዚህ አስተዋጽኦ ላደረጉ እያደረጉም ላሉ እንደ ሀኒሻ ፀጥታውን ሰብረው ሀሜትና ነቀፋውን ችለው አደባባይ ለወጡ ሁሉ ምስጋና ይገባል።

“…. ወደዱ እንዋደድ አፍቅሩ እንፋቀር…. ድግግም ላይኖረው አንዴ ብቻ ሊኖር… አንድነት ትብብር ፍቅር ነው ቋንቋዬ… ስትል እውነትም እንደ ስምዋ ማር የሆነች የፍቅር አምባሳደር እንደሆነች መመስከር ይቻላል። በእለቱ መድረኩን የሞሉትና ለዚህ ውብ ዜማ ሞገስ የሆኑት ወንድም እህቶችም ሊመሰገኑ ይገባል።

ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ነች ነፃነቷን አስከብራ ሳትንበረከክ የቆመች ታላቅ አገር የምንላት ከሆነ ደግሞ የኦሮሞ ደምና አጥንት ያንን ታላቅነት ቸሯታል። ያንን የራሱ የሆነ አገር ቅኝ ተገዝቼ ነው እንጂ አገሬ አይደለም እስከሚልበት ድረስ ያደረሰው ፖለቲካ አሁን ታሪክ ሆኖ ማነው አገሬን የሚነጥቀኝ? ወደሚል እምቢተኝነት መምጣቱ ታላቅ እመርታ ሲሆን ፖለቲከኞቹን ወደዚህ አቅጣጫ መልሶ ያመጣው ሕዝብም የምንኮራበት ነው።

ታሪክ መቦትረፍ፣ ተራራ መስረቅ፣ ባንክ መዝረፍ፣ ፋብሪካ ነቅሎ መሮጥና ለሊቱን ማጋዝ የችጋራሞች ፖለቲካ ነው። አገሬ ነው ከሚልና ሕዝቡ ወገኔ ነው ከሚል የሚጠበቅ ድርጊት አይደለም። ያንን ሁሉ ክፋት እንደሚሰሩ እየታወቀ ሕዝቡ መሀል ተሸሸገው የሚያስተኩሱና የሚያስገድሉት ላይ እንኳን የከፋ የበቀል እርምጃ የማይወስድና እባካችሁ ሰብሰብ በሉ ብሎ የሚለምን ሆደ ሰፊ ሕዝብ ደግሞ ያኮራል። አሽመድምደን ገድለነዋል ያሉት አማራ ከራሱ አልፎ የወገኑ ደም ደሜ ነው ብሎ የተነሳው በጭንቁ ሰዐት ነበር። ዳግም አንድ ላይሆኑ ተለያይተዋል በማለት የዘር ስም ያለበት መታወቂያ በማደል አማራውን ይጨፈጭፋሉ ተብለው የሚጠበቁት ኦሮሞዎች ታሪክን ለታሪክና ለጊዜ ትተና ዛሬን ሀይላችንን ወደ ጠላታችን የትግሬ ፋሺስቶች እናዞራለን ሲሉ መስማት ኢትዮጵያውነት አንዳች ትልቅ ሀይል ያለው የሕዝብ ቁርኝት መሆኑን ያስተምራል። አሮሞና አማራ አንድ ነን ጠላታችን ወያኔ ብቻ ነው ማለታቸው የአስቸኳይ አዋጅ እስኪለፍፉ ድረስና ፍርሃታቸውን ከማይሸሽጉበት ጥግ እነዳደረሳቸው ተመልክተናል። የነሀኒሻና የመሰል አርቲስቶች ስራ ደግሞ እጅ ለእጅ ተያይዘን አንድንሄድ ያበረታታልና ሙሉ ዘፈኑ በጥሩ ሁኔታ ተዘጋጅቶ መቅረብ ቢችል ደግሞ እጅግ ጥሩ ይሆናል። በዚህ አጋጣሚ ሀኒሻንና አዘጋጆቹን ማመስገን እውዳለሁ። ሀኒሻ አንድነትና ፍቅር መስበክ ከቶውኑ አይሰለቸኝም እንዳልሺው እንደ ቃልሽ ይሁን።

ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር!