የአማራ፣ የኦሮሞና የትግሬ ብሔርተኝነት ልዩነት ምንድን ነው?

አማራ ትናንት፡- የጭቆና፣ የተጠቃሚነትና አማራዊ ውክልና ሁነታ በሚል ርዕስ አቶ ምስጋናው አንዷለም በፌስ ቡክ ገጻቸው ያወጡትን ጽሑፍ እነሆ:
አማራ እንደ ህዝብ የሰው ልጅ የደረሰበት የመንግስት አወቃቀርና አስተዳደር ስልጣኔ ላይ ከሽህ አመታት በፊት የደረሰ ህዝብ ነው፡፡ በፖለቲካዊ አወቃቀር የመጨረሻው ወይም አሁን የምንገኝበት የእድገት ደረጃ መንግስት ይባላል፡፡ ከመንግስት በፊት ባንድ (ጥቂት ቡድን)፣ ትራይብ (ወይም ነገዳዊ አድረጃጀት)፣ ቺፍደም ወይም ከፊል መንግስታዊ አደረጃጀት እና በመጨረሻም ስቴት ወይም መንግስታዊ አደረጃጀት እንደሆነ የአንትሮፖሎጅካዊ ሊቃውን ያስረዳሉ፡፡ በዚህም ረገድ አማራ እንደሴሜቲክና ኩሽቲክ የስልጣኔ ባለቤትነቱ ቀደም ባሉት ሽህ ዘመናት እዚህ የሰው ልጅ የደረሰበት የመጨረሻው አደረጃጀት ላይ እንደደረሰ የሚታወቅ ነው፡፡ ከአክሱም ግዛት መውደቅ ወዲህ ያለውን በጉልህ የሚታወቅ ታሪኩን ስንመረምር እንኳ የአማራ ህዝብ በዳበረ የፖለቲካ አደረጃጀት በመንግስትነት እንደቀጠለ እንረዳለን፡፡

የአማራ ህዝብ ብልጽግናም ሆነ መከራ ከዚሁ የእድገት ደረጃው ጋር የተቆራኘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህ የማህበረ ፖለቲካ የእድገት ደረጃው ለድልም ለውድቀትም ሲያበቃው ቆይቷል፡፡ በአንድ በኩል የመንግስትነት ባህርይ ያለው ህዝብ በመሆኑ ከላይ ከንጉሰ ነገስቱ ጀምሮ እስከታች ጭቃሹምና ምስለኔ ደረሰ በተዋረድ የተዋቀረ በመሆኑ ስርአቱ በቀላሉ የማይፈርስ ጠንካራ ህዝብ ሆኖ ቆቷል፡፡ በሌላ በኩል ይህ አይነት ማህበረ ፖለቲካዊ አደረጃጀት ህዝቡን በተለያዩ የሙያና ውክልና ዘርፎች ሸንሽኖ ስላስቀመጠው ማለትም በንግድ፣ በውትድርና፣ በህግ አስከባሪነት፣ በጥበብ ሰውነት፣ በእምነት አካልነት፣ እና በልዩ ልዩ አንቀጾች ስለከፋፈለው ከገረቤቶቹ የሚነሱበትን ትራይባሊስት ወይም ነገዳዊ ጦርቶች መቋቋም ሲከብደው ቆይቷል፡፡ ከዚህ አይነት የማህበረ ፖለቲካ አደረጃጀት እና ለረዥም ጊዜ ከቆየው የአይሁዳዊነት እና ክርስትና ምልከታ-አለም የሚመነጨው የአማራ ልዩ መታወቂያ የሆነው ሁለንተናዊ ወይም ሁሉን አቀፋዊ ወይም ሁሉ-ልሙዳዊ ባህርይም ለከፋ ጉዳት ሲያጋልጠው ቆይቷል፡፡ ምክንያቱም አማራዊ ንቃተ-ማንነቱን በኢትዮጵያዊ ንቃተ-ማንነት በመቀየሩ እና በእነዚህ በተጠቀሱት ምክንያቶች የተነሳ የጋርዮሻዊ ባህርይውን ለቆ ግለሰባዊ ወይም በራስ-ብቋአዊ ባህርይ ላይ ከደረሰ ቆይቷል፡፡ እንዲህ አይነቱ የማህበረሰብ እድገት በራሱ መልካም ቢሆንም፣ እንዲህ አይነት ማህበረ-ፖለቲካዊ እድገት የሰው ልጅ የመጨረሻ የስልጣኔ ደረጃ መሆኑ አይቀሬ ቢሆንም እና አማራም በዚህ መንገድ እዚህ ላይ መድረሱ እርግጥ ቢሆንም ሁልጊዜ ጥቅም ሲያመጣለት አልታየም፡፡ ምክንያቱም ዙሪያውን አማራው የደረሰበት ማህበረ ፖለቲካዊ እና ምልከታ-አለማዊ ባህርይ ላይ ባልደረሱ ሀይላት በመከበቡ ወይም ዙሪያውን ገና የነገድነት አደረጃጀት ባህርይ ባላቸው ሀይላት በመከበቡ በተደጋጋሚ ለጥቃት ሲጋለጥ ቆይቷል፡፡

በዚህ ረገድ ለምሳሌ በአስራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተከሰተውን የኦሮሞ ወረራ እና ሰፊ የሆነ የዘር ማጥፋት እና የዘር መዋጥ እርምጃ ስንመለከት ለአማራው በኦሮሞ መወረር፣ መጥፋት እና መዋጥ ምክንያት ከላይ የተገለጸው የአደረጃጀቱ ባህርይ ጉልህ ሚና እንደሚወስድ ሰነዶች ያረጋግጣሉ፡፡ ለዚህ ጉዳይ የአይን ምስክር ሆነው ያዩትን ነገር በግእዝ ከትበውት ያለፉትን አባ ባህርይን እንጠቅሳለን፡፡ በነገራችን ላይ አባ ባህርይ የአንትሮፖሎጅ ሳይንስ ከመጀመሩ በፊት በአገራችን የተከሰቱ ብርቅየ አንትሮፖሎጅስት ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ የዛን ጊዜውን ሁኔታ የአዘጋገብ እና የአጠናን እንዲሁም የአጻጻፍና ትንተና ዘዴና ብቃታቸው በአሁኑ ሰአት አንትሮፖሎጅ ከደረሰበት ደረጃ ያልራቀ እና ምጡቅ ነው፡፡ ስለሆነም የአባ ባህርይ መጽሀፍ ተራ ድርሰት ሳይሆን አማራው እንዴት እንደጠፋ እና ኦሮሞ እንዴት አገራችንን እንደቀማ የሚያሳይ ወደአራት መቶ አመታት ያስቆጠረ ጥናታዊ ዘገባ ወይም ሪፖርት ነው፡፡

ወደዚህ ጽሁፍ ቅድመ ነገር ስንገባ አባ ባህርይ አማራው እንዴት እንደተሸነፈ የራሳቸውን ድምዳሜ አስቀምጠዋል፡፡ ይሄውም አማራ በአስር አንቀጽ የተከፈለ እና አጥቂው ክፍል አንዱ አንቀጽ ብቻ መሆኑን ነገር ግን ኦሮሞ እንደዛ አይነት በአንቀጽ የተከፋፈለ ማህበረ-ፖለቲካዊ አደረጃጀት ስላልነበረው ሁሉም አንድ ላይ ያጠቃ ነበር፡፡ ባጭሩ በዚያ ዘመን በአማራና በኦሮሞ መካከል የተካሄደው ጦርነት አንድ ለአስር በሆነ ረድፍ ነው፡፡ አማራው ከዘጠኙ አንቀጾች ለውጊያ ሙያ የተመደቡትን የንጉሱን ወታደሮች ሲያሰልፍ እና ሌላው ዘጠኙ የጦርነቱ ተሳታፊ ሳይሆን ሲቀር በተጻራሪው ኦሮሞው አስር አይነት ክፍልፋይ ሳይኖረው ከአስር አንድ የሆነውን የንጉሱን ጦር እየገጠመ ሲያሸንፈው ቆይቷል፡፡

ይሄ ነገር እንደምን ነው ቢሉ አማራ የደረሰበት የመንግስታዊ ማህበረ-ፖለቲካዊ አደረጃጀት ላይ የደረሰ ማንኛውም ህዝብ አባ ባህርይ እንዳስቀመጡት በአስርና ከዛ በላይ አንቀጾች የመከፋፈሉ ነገር ማህበራዊ ሀቅ ስለሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ የአባ ባህርይን ቃል ለመጥቀስ እና ብዙዎች ሆነን እና የጦር መሳሪችንም ብዙ ሆኖ ሳለ እንዴት በኦሮሞ ተሸነፍን ተብሎ ለሚጠየቀው ጥያቄ “ቁጥራቸን ብዙ ይሁን እንጅ ውጊያ የሚችሉ ጥቂቶቹ፤ ወደውጊያ የማይቀርቡ ብዙዎች ናቸው” ይላሉ፡፡ ለምሳሌ አባ ባህርይ እንዳስቀመጡት በዛን ጊዜ አማራ በአስር ልዩ ልዩ ክፍሎች ይከፈል ነበር፡፡ አንደኛው ክፍል የመነኮሳት ወገን ሲሆን ወደውጊያ የማይገባ ነው፡፡ ሁለተኛው ክፍል የደብተራ ክፍል ሲሆን ወደውጊያ የማይገባ ነው፡፡ ሶስተኛው ክፍል የህግና ፍርድ ሰዎች ሲሆኑ ወደጦርነት የማይገቡ ናቸው፡፡ አራተኛው ክፍል የመኳንንት ሚስቶች አገልጋይ ጀግኖች ሲሆኑ ወደጦርነት አይገቡም የሴቶች ሎሌዎች ነን ይላሉና፡፡ አምስተኛው ክፍል የመሬት ከበርቴና ሽማግሌ ወይም ባለርስት ሲሆኑ ወደውጊያ አይገቡም፡፡ ስድሰተኛው ወገን ገበሬዎች ሲሆኑ ወደውጊያ አይገቡም፡፡ ሰባተኛው ወገን ነጋዴዎች ሲሆኑ ወደውጊያ አይገቡም፡፡ ስምንተኛው ወገን የእደጥበብ ባለሞያዎች ሲሆኑ ወደውጊያ አይገቡም፡፡ ዘጠነኛው ወገን ሙዚቀኞች ማለትም በገና ደርዳሪና አዝማሪዎች ሲሆኑ ወደጦርነት አይገቡም፡፡ አስረኛው ወገን ወታደሮች ሲሆኑ እነሱ ብቻ ሌላውን ዘጠኝ ክፍል የሚከላከሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን አባ ባህርይ እንዳሉት፡- “በእነዚህ ጥቂትነት ምክንያት አገራችን ጠፋች፡፡” አሁንም አባ ባህርይን ለመጥቀስ፡- “ኦሮሞ ግን እነዚህ ያነሳናቸው ዘጠኝ ወገኖች የሉበትም፡፡ ሁሉም ከደቂቅ እስከሊቅ ለውጊያ የሰለጠኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ ያጠፉናል፤ ይፈጁናል፡፡”

ስለሆነም ከላይ በተዘረዘረው ምክንያት የተነሳ አማራ ጠፋ፣ ተዋጠ፣ ተሰለቀጠ፣ አገርና ርስቱን ተቀማ፡፡ ምክንያቱም ኦሮሞዎችም ሆኑ ሌሎች ጎረቤት ነገዶች እንደ ቡድን ሆ ብለው አንድ ላይ ሲያጠቁ አማራ ግን በተናጠል እየተገኘ ሲያልቅ ቆየ፡፡ የዛ የጥንት ልማዳችን ተቀጥላ የሆነው ዛሬ “እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ በዘሬ አልጠራም፣ በአማራነት አልደራጅም” የሚለው ፍልስፍናም ለሌላ ዙር ጥፋት ሲያጋልጠን ቆይቷል፡፡ አሁንም እያጠፋን ነው፡፡ ለዛም መልስ ነው እዚህ መገናኘታችን፡፡ በድሮው ጊዜ አስሩም ወገን ምንም አይነት ልዩነት ሳይኖረው በአንድነት ተዋግቶ ቢሆን ኖሮ ዘሩ አይጠፋም ነበር፤ አገሩ አይወረርም ነበር፣ ዛሬ በራሱ አገር እነደመጻተኛ እየተቆጠረ አይታረድም፣ ወደገደል አይጣልም ነበር፡፡ አሁንም በተለይም ላለፉት አርባ አንድ አመታት አማራውን ለማጥፋት በማሰብ ወደበረሀ የወረዱትን ሰዎች ሁኔታ በማየት ተመሳሳይ አጸፋ ግብረ ሀይል መመለስ ሲኖርብን ጥንት እድንጠፋ ባደረገን አካሄድ ስንጓዝ ቆየን፡፡ ብዙው ወገናችን በኢትዮጵያዊነት ማንነት ስር ተሰልፎ በአማራነቱ የሚደርስበትን በደል አላይም ብሎ አይኑን ጨፍኖ ቆቷል፡፡ እኔ ሰው ብቻ ነኝ፣ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ እኔ ስልጡን ነኝ፣ እኔ ምሁር ነኝ፣ እኔ ሀይማኖተኛ ነኝ፣ እኔ ፖለቲካ አልወድም፣ እኔ በራሴ ፍልስፍና ነው የምመራው ወዘተርፈ የሚሉት ባህርያት እንደ አማራ አንድ ላይ ቆመን በአማራነታችን የገጠመንን ፈተና አማራዊ መልስ ሰጥተን ነጻ እንዳንወጣ አድርጎን ቆይቷል፡፡ ይህ አይነት ባህርያችን በአባ ባህርይ ዘመን የነበረው ባህርያችን ውርስ መሆኑን ለመገንዘብ ከባድ አይደለም፡፡

ካለፈው ታሪካችን ስህተት በመማርም ዛሬ የአማራ ብሄረተኝነትን በመገንባት ላይ እንገኛለን፡፡ አማራን በአማራነት ማሰባሰብ አስፈላጊ የሆነውም ልክ እንደ ትናንቱ ሁሉ ከአስር በተከፋፈለ ሁኔታ በተናጠል እንዳይጠፋ ሁሉም በጋራ እንዲነሳ ነው፡፡ ይህ ሲባል ለአንዳንድ ሰዎች ሁለንተናዊ ባህርያችንን ለውጦ ወደነገዳዊነት መውረድ ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን ስህተት ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የአማራ የወቅቱ ችግር የመውረድ የመውጣት፣ ወይም የመስፋት የመጥበብ ጉዳይ አይደለም፡፡ የወቅቱ የአማራ ችግር የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነው፡፡ አማራ አሁን የሚያደርገው ትግል ለመኖር የሚደረግ ትግል ነው፡፡ መስፋትም ሆነ መጥበብ፣ መውረድም ሆነ ከፍ ማለት አንድ ህዝብ መኖሩን ካረጋገጠ በኋላ በሁለተኛ ደረጃ የሚገባባቸው የቅንጦት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ለቅንጦት ጥያቄዎች መልስ የምንሰጠው ቅንጦት ላይ ስንሆን ብቻ ነው፡፡ አሁን መልስ የምንሰጠው ባለንበት የህልውና ትግል አንጻር ህልውናን እንዴተት ማስጠበቅ አለብን በሚለው ማእቀፍ ነው፡፡ በዛ ላይ እና እያካሄድን ያለው ነገዳዊ ወይም ትራይባሊስት ፖለቲካ አይደለም፡፡ እኛ እያካሄድን ያለነው የአማራ ብሄራዊ ፖለቲካ ነው፡፡ ማለትም ጥያቄያችን የነገድ ጉዳይ ሳይሆን ቀድሞም የነበረውን አማራዊ ብሄራዊ ማንነት እንደገና እዲያብብ በማድረግ በአማራነታችን ለገጠመን ችግር አማራዊ መልስ መስጠት ነው፡፡

የአማራነት እንቅስቃሴያችን ከነገዳዊ ስሜት ከፍ ያለ መሆኑን ለማረጋገጥም በአማራ ውስጥ ያሉ ልዩ ልዩ የባህል ክፍሎች የሚካተቱበት እና እውቅና የሚያገኙበት መሆኑን ማየት እንችላለን፡፡ ስለሆነም የአማራ ብሄራዊ እንቅስቃሴ ግቡ ምሁርና ማይምናኑ፣ ነዳያን እና ባለጸጎቹ፣ አራሾችና ጠቢባን፣ ፈላስፎችና ነጋዴዎች ሁሉም አለምንም ውስጣዊ ክፍልፋይ ተረባርበው ለወቅታዊው ችግር ወቅታዊ ምላሽ ሰጥቶ በቀጣይነትም አማራው አሁን በገጠመው አይነት የጥፋት ጎዳና እንዳይገባ በአማራነቱ ጸንቶ እስከዘመናት ድረስ እንዲቆም ማድረግ ነው፡፡ አሁን የምናደርገው ትናንት አስር ቦታ ተከፋፍለን የተጠቃንበት ታሪክ እንዲስተካከል አንድ ላይ ለመቆም የምናደርገው እንቅስቃሴ ነው፡፡

የአማራ ህዝብ ጨቋኝ ነውን?

የአማራ ህዝብ ጨቋኝ አይደለም፤ ሆኖም አያውቅም፡፡ ከላይ እንደተገለጸው የአማራ ህዝብ የሰው ልጅ በደረሰበት የመጨረሻው ማህበረ-ፖለቲካዊ አደረጃጀት ውስጥ ያለፈ ህዝብ ነው፡፡ በንጉሳዊ መንግስታዊ ስርአት ስር እንደማለፉ ህዝቡ የመንግስታዊ ባህርይ አዳብሯል፡፡ ከዚህ መንግስታዊ ልማድ የሚመነጨው የህዝቡ ባህልም ያለመንግስት ስርአት መኖር የማይችል ሆኖ እንዲቆይ አድርጎታል፡፡ ይህ የአማራው ዋና ባህል የሆነው ማህበረ-ፖለቲካዊ አደረጃጀት ታዲያ የአማራው ብቻ ሆኖ አልቀረም፡፡ በሂደት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ህዝብ ልማድ ለመሆን ሲጣጣር ቆየ እንጅ፡፡ በተለይም ትኩረት ልናደርግበት የሚገባው ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት እንደገና መቆም ከጀመረበት ከዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ጊዜ ወዲህ ያለውን ነው፡፡ በዚህ ንጉስ አማካኝነት ተዳክሞ የነበረው የአማራ ውስጣዊ አንድነት ተመልሶ ጥንት ወደነበረበት የመንግስትነት አስተዳደር ተመለሰ፡፡ ወዲያውም በዳግማዊ አጼ ምኒልክ አማካኝነት ይህ ከአማራው ውስጣዊ አንድነት የመነጨው ሀይል ጥንት የኢትዮጵያ ግዛት የነበሩትን ትናንሽ ከፊል ግዛታዊ (ችፍደም) እና ነገዳዊ (ትራይባሊስት) ህዝቦች እንደገና ወደአንድነት መሰብሰብ አስቻለ፡፡ በዚህም ሂደት አማራው ራሱ ለሽህ ዘመናት የኖረበትን እና ቀደም ብሎም የመላው ኢትዮጵያዊያን ዣንጥላ ስር የነበረውን የመንግስት መዋቅር መልሶ ዘረጋ፡፡ ይሄ ከአማራው ውስጣዊ አንድነት መንጭቶ ለሌሎች የተዳረሰው የመንግስታዊ አወቃቀር እና ስርአት ከአማራው ለሌሎች የተሰጠ ወይም በግድ የተጫነ ሳይሆን አማራው ራሱ በራሱ የሚኖርበት ስርአት ነበር፡፡

ይህ እርምጃ በኋላ እንደገና ለተሰባሰቡት ከፊል መንግስታዊ እና ነገዳዊ ቡድኖች በርካታ ጥቅም አስገኝቷል፡፡ አንደኛውም አማራው በተንቀሳቀሳባቸው ቦታዎች ሁሉ ጎሳ ከጎሳ ጋር የነበሩትን ጦርነቶች አስቁሞ ሰላም አውርዷል፡፡ ይህም አማራ የድሮ ስርአትን ወይም የጋርዮሽ ዘመንን አስቀርቷል ማለት ነው፡፡ እንደ ኦሮሞ ያሉትን መቸም በራሳቸው ሊሰባሰቡ የማይችሉትን ህዝቦች አንድ ላይ አሰባስቧል፡፡ ዛሬ ከ80 በላይ የሆኑትን ነገዶች ከቅኝ ግዛት በመከላከል ዛሬ ለሚኩራሩበት እና መልሰው አማራውን ለሚወጉበት ማንነታቸው መጠበቅ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ዛሬ አማራን እንደጨቋኝ ህዝብ የሚቆጥሩት እና የሚዋጉት የየብሄረሰቦች ወይም ነገዶች ልሂቃን የዘነጉት ነገር እነሱ ሊያሳምኑን እንደሚሞክሩት በ1983 ዓ.ም የተፈጠሩ ሳይሆኑ አማራው በደምና አጥንቱ ጠብቆ ያቆያቸው ናቸው፡፡ ይህ ሲባል ግን አማራውን ያገዙ ከየብሄረሰቡ የተውጣጡ ሀይላት መኖራቸው ሳይዘነጋ ነው፡፡

ይሁንና እነዚህ የየብሄረሰብ ልሂቃን በትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ድርጅት አጋፋሪነት አማራውን የድሮ ስርአት ለማምጣት እነደሚጥር አድርጎ ለማሳየት ሲጥሩ ይታያሉ፡፡ ነገር ግን አማራው የራሳቸው የነበረውን የድሮ ስርአት አጥፍቶ ዘመናዊ ስርአት የገነባ ህዝብ እንጅ የድሮ ስርአት ናፋቂ በሚል ውሀ የማይቋጥር ዘለፋ እንደሚከሰሰው አይደለም፡፡

እውነቱ አማራው የድሮ ስርአት ከተባለ እንኳ የራሱ የነበረውን ዘውዳዊ አገዛዝ በራሱ ልጆች ደም ያስወገደ እና ከዛ የተሻለ ዘመናዊ አስተዳደር ለመገንባት በአያሌው ሲታትር የቆየ ነው፡፡ በ1953 አ.ም ለምሳሌ ንጉሳዊውን ስርአት ለመቀየር እና በህዝብ የሚመረጥ መሪና ስርአት ለመፍጠር እስከመፈንቅለ መንግስት እርምጃ የደረሱት ራሳቸው የአማራ ልጆች ናቸው፡፡ ከዛም ወዲህ የራሱ የአማራው ልጆች ባደረጉት ብርቱ ትግል የዘውዳዊ ስርአት ተገርስሶ ነበር፡፡ ይሁንና የአማራ ልጆች በፈለጉት እና ባቀዱት አቅጣጫ ሊሄድ እድል ያልቀናው አብዮት በወታደሮች ተጠልፎ ለራሱ ለአማራው መጥፊያ ወጥመድነት ውሏል፡፡ ሆኖም ቀድመው የንጉሳዊ ስርአትን አፍርሰው ከዛ የተሻለ ስርአት ለማምጣት ውድ መስዋእትነት የከፈሉት የአማራ ልጀች ጥረት መና አልቀረም ነበር፡፡ ነገር ግን የድሮ ስርአት ልክፍተኛ የሆኑት ድርጅቶች እና ግለሰቦች በመቧደን አማራው ባመቻቸው ሁለንተናዊነትነትን በሚያስተናግደው መደብ ላይ መልሰው የትራይባሊስት ስርአትን ተኩበት፡፡ ስለሆነም በትክክለኛው መስፈርት አገሪቷን ወደድሮ ነገዳዊ ወይም ጎሳዊ ስርአት የዘፈቋት አማሮች ሳይሆኑ እነዚህ የድሮ ስርአት ልክፈተኛ ጎሰኞች ናቸው፡፡

ነገር ግን አይናቸውን በጨው አጥበው አማራው ከመጀመሪያ ጀምሮ ራሱ ሲዋጋው የነበረውን የራሳቸው የሆነውን የድሮ ስርአት ለመመለስ ጥረት እንደሚያደርግ ያስተጋባሉ፡፡ ሆኖም አማራው ያልነበረበትን እና የማያውቀውን የድሮ ስርአት ሊመልስ አይችልም፡፡ ይልቅም ለድሮ ስርአት ቅርብ የሆኑት ራሳቸው በተግባር መልሰውት አገር አያፈራረሱበት ይገኛሉ፡፡

እነዚህ የየብሄረሰቡ ልሂቃን አማራውን በድሮ ስርአት ወኪልነት የሚከሱት አለምክንያት አይደለም፡፡ ራሳቸው የፈጠሩትን የአማራ ብሄራዊ ጨቋኝነት ርእዮተ አለማዊ ድጋፍ ለመስጠት የሚያደርጉት ነው፡፡ የድሮ ስርአትን የአማራ ስርአት አስመስሎ በማቅረብ መልሶ ወደጨቋኝነት ባህሪው ተመልሶ እኛን ሊጨቁነን ነው የሚለውን የበሬ ወለደ ሀሳዊ ርእዮተ አለማዊ እርምጃ እውነት ለማስመሰል ነው፡፡

በመሰረቱ አማራ ጨቋኝ ነውን? በመግቢያችን ላይ አማራ ጨቋኝ አልነበረም፣ ሆኖም አያውቅም ብለናል፡፡ አማራ እንደህዝብ ሌላን ህዝብ ለመጨቆን ሀሳቡም ምክንያትም ኖሮት አያውቅም፡፡ ከራሱ የበቀሉት መሪዎችም አንድም ጊዜ ሌላውን ለመጨቆን እና ለማጥፋት ስልት ነድፈው አልተንቀሳቀሱም፡፡ በአገራችን አንድን ህዝብ ለማጥፋት ሰነድ አዘጋጅቶ ወደትግል የገባ አካል ቢኖር የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ድርጅት ህወሀት ነው፡፡ ሌሎቹም ለምሳሌ እንደኦነግ አይቶቹ አማራውን ለማጥፋት ሰነድ ባይጽፉም እንኳ አማራውን ለማንኛውም ችግር ተጠያቂ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ራሳቸው በፈጠሩት የውሸት ተረት ላይ በመመስረት አማራውን ሲወንጅሉት እና ለማንኛውም ሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጠርሮ አደጋ ተጠያቂ ሲያደርጉት ቆይተዋል፡፡ መብረቅ ለገነጠለው ዛፍ ሳይቀር አማራን ተጠያቂ የሚያደርጉ አካላት ለመሆናቸው ለአራትና አምስት አስርት አመታት የቆየው ስራቸው ምስክር ነው፡፡ አማራውን እንደጨቋኝ እና ቅኝ ገዥ ሀይል አድርገው የሚያቀርቡት የራሳቸውን ህልም ለማሳካት ህልቆ መሳፍርት የሌለው የውሸት ክምር ስለሚያስፈልጋቸው ብቻ ነው፡፡

አማራ አደረገ የሚባለው ነገር መገለጽ ቢኖርበት እንኳ የባህል መስፋፋት በሚለው አውድ መሆን አለበት፡፡ የአማራው ባህል በታሪክ አጋጣሚ የሌሎች ባህል ሆኗል፡፡ ይህ የባህል መስፋፋት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ውስን ለሆኑት የስርአቱ ቁንጮዎች የኢኮኖሚና ፖለቲካ ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ ከዛ በተረፈ ግን መላው አማራ የባህል መስፋፋቱ ምንም ያተረፈለት የለም፡፡

የአማራው የባህል መስፋፋት ቀጥተኛ ጥቅም ያስገኘላቸው ከራሱ ይልቅ ለሌሎች ነው፡፡ አማርኛ ቋንቋን በመናገር በየግዛቱ ሁሉ የንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት በአብዛኛው ከአማራው ውጭ የሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ በፖለቲካዊ ስልጣኑም ቢሆን የአማራ መሪዎች የሚባሉት አካላት ሌላውን ለማስደሰት፣ አገሪቷን የበለጠ ለማስተሳሰር እና አንድነቷን ለማጠናከር በሚል መርህ አማራውን እየገፉ ሌሎችን የስልጣን እና የኢኮኖሚ ባለጸግነትን ሲያጎናጽፉ ነው የቆዩት፡፡ የመሰረተ ልማት ዝርግታቸውን ብንመለከት እንኳ ገዥዎቹ ለበቀሉበት አካባቢ ያደረጉት የተለየ ነገር የለም፡፡ ከዛ ይልቅም ለሌሎች አካባቢዎች የተሻለ ነገር እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡ ስለሆነም በአማራ መሪነት የሚከሰሱት የስርአቱ ቁንጮዎች እንኳን ሌላውን ለመጨቆን የተለየ ስልት ሊነድፉ ይቅርና የራሳቸውን ወገን ተጠቃሚ የሚያደርጉበት አሰራር አልዘረጉም፡፡ የስርአቱ ቁንጮዎች ራሳቸው አማራውን እንደወታደር መመልመያ ክልል ከመቁጠር የዘለለ እይታ አላደረጉበትም፡፡ ከህዝቡ መሀል እየወሰዱ ለአገር ዳር ድንበር መከበር እና ለውስጣዊ የኢትዮጵያ መንግስት መጠናከር ማገዶ ከመሆን የዘለለ እድል አላገኘም፡፡ የአማራ ህዝብ በገፍ በወታደርነት መሰማራት የአማራን ህዝ ጨቋኝነት የሚያሳይ ከሆነማ አሁንም በወያኔ የወረራ አገዛዝ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው የአማራ ወታደር ነው ልንል ነው ማለት ነው፡፡

ዞሮ ዞሮ የአማራውን የባህል መስፋፋት የአማራ ጨቋኝነት እና ቅኝ ገዥነት ማሳያ አድርጎ መውሰድ በጣም ስህተተ እና የሌላው ብሄረሰብ ልሂቃን ባስቸኳይ ማረም ያለባቸው ነገር ነው፡፡ የአማራ ባህል መስፋፋት የአማራን ጨቋኝነት ማሳያ ከሆነማ አሁን በዚህ በምንናገርበት ሰአት አማራው ዘሩ እየጠፋ ነው፡፡ ነገር ግን አገሪቷ የምትተነፍሰው አሁንም በአማራው ባህል ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያ አሁንም በአማራው ባህል ተጽእኖ ስር ናት ማለት ነው፡፡ ከዚህም ተነስተን አማራ አሁንም ጨቋኝ ነው ልንል ነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ያ አይደለም፡፡ የባህል መስፋፋት ጨቋኝነትን ወይም ቅኝ ገዥነትን ያመለክታል ብለው የሚከራከሩ ሰዎች ቆም ብለው የኢትዮጵያን ልዩ ሁኔታ ማጤን ይኖርባቸዋል፡፡ አማራው በጨቋኝነት የሚከሰስበት ስርአት ለአማራው ለራሱ የእግር እሳት እንደነበረ ለማስረዳት ከፍቅር እስከመቃብር የበለጠ የምናቀርበው ነገር የለም፡፡ በፍቅር እስከ መቃብር መጽሀፍ ውስጥ የአብዛኛው ብሄረሰብ ልሂቃን አንብበውታል ተብሎ ይታመናል፡፡ ክቡር ሀዲስ አለማየሁ በምስል ከሳችነት ያቀረቡትን ያንን የአማራ ህይወት ተውኔት አንብበው እንኳ አማራውን በጨቋኝነት ለመክሰስ ከመጣደፍ አለመዳናቸው እጅግ የሚያሳዝን ነው፡፡
የአማራ ባህል በቀላሉ እንዴት ሊስፋፋ ቻለ ከጨቋንነት ጋር የማይዛመድበት ትንተናስ እንደምን ያለ ነው ቢሉ የአማራ ባል በይል አልተስፋፋም፡፡ የአማራ ባህል በቀላሉ ሊስፋፋ የቻለወው ሁሉን አስተናጋጅ መሆኑ እና ቋንቋው በስነጽሁፍ በመታገዙ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ የሚከሰት ነባራዊ ሀቅ ነው፡፡ እናም የባህል መስፋፋት ከጭቆና ጋር ወይም ከቅኝ ገዥነት ጋር አይያያዝም፡፡
እዚህ ላይ አንዳንድ ወገኖቻችን አማራ አልጨቆነም ብሎ ለመከራከር ነገስታቱ አማራ አልነበሩም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ የዚህን አይነት አስተሳሰብ የሚያራምዱ ሰዎች በውስጣቸው አማራ ጨቋኝ ነው የሚለው የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ፍሬ ያፈራባቸው ነው ብሎ መከራከር ይችላል፡፡ ነገስታቱ አማራ አልነበሩም ካልን “አወ ጭቆና ነበረ፣ ነገር ግን አማራ ሳይሆን በአማራ ስም የሚነግዱት ገዥዎች ናቸው የጨቆኑ” የሚል የጎንዮሽ ሙግት ይወልዳል፡፡ ነገር ግን ነገስታቱ አማራ ነበሩ አልነበሩም ወደሚለው ጉንጭ አልፋ ክርክር ዘው ከማለታችን በፊት ጭቆና ነበር ዌስ አልነበረም ብለን መመርመር አለብን፡፡ መልሱ እዚሁ ላይ ነው፡፡ ነገስታቱ አማሮች ነበሩ፡፡ አለቀ ደቀቀ፡፡ ነገር ግን አማራ ቢሆኑም ቅሉ ለአማራው የተለየ አላደረጉም፤ በሌላውም ላይ በአማራው ላይ ሲያደርጉ ከነበረው የተለየ ነገር አላደረጉም፡፡ እነዛ መሪዎች የዘመናቸው ውጤት፣ በዘመኑ የነበረው የስርአት አይነት ወኪሎች ወይም አጄንቶች ነበሩ እንጅ የጭቆና መሳሪያ ሆነ ብለው የፈለሰፉ ጨቋኞች አልነበሩም፡፡ በጊዜው የነበረውን ስርአት ያራምዱ የነበሩ የስርአቱ ቁንጮዎች ናቸው፡፡ በእነሱ ጊዜ የነበረው ትክክለኛ መስመር ደግሞ የዘውዳዊ አገዛዝ ስርአት እና ተያያዥ ዘርፎቹ ናቸው፡፡ ስለሆነም የአማራ ነገስታት ለሶስት ሽህ እና ከዛ በላይ የቀጠለው ስርአት አገልጋዮች እንጅ እነሱ በአማራነታቸው ተሰባስበው ሌላውን ለመጨቆን ስርአት የፈጠሩ አልነበሩም፡፡ ከዚህም ተነስተን አማራ ጨቋኝ ነው የሚለው የጎሳ ፖለቲከኞች የራሳቸውን አጀንዳ ለማስፈጸም የፈጠሩት የሀሰት ክስ ነው ብለን እንደመድማለን፡፡

አማራ ጨቋኝ ነው የሚለው ራስ-ወቀስ ዲስኩር ምንጩ ምንድነው? ፈጣሪውስ ማነው?

የደራሲ በአሉ ግርማን ቃል በመዋስና ወደራሴ ክርክር በመቀየር ልጀምር፡፡ የአማራ ችግር ቀንዱ አገር ውጭ ጅራቱ በአገር ቤት ነው፡፡ በስፋት እንደሚታወቀው ቅኝ ገዥ ሀይላት አላማቸውን ለማሳካት በአማራው ላይ ረዘም ላሉ አመታት በአሳሾቻቸው አማካኝነት ትናት አድርገው እንቅፋቱን ለይተው አውቀውት ነበር፡፡ እርሱም ጠንካራ አማራ ለአላማቸው መሳካት እንቅፋት መሆኑን ነው፡፡ ጠንካራ አማራ ሌላውንም በማስተባበር አላማቸውን የሚያከሽፍ መሆኑን ስላወቁት አማራውን በሌሎች ብሄሮች ማስጠቃት ነበረባቸው፡፡ ለዛም አማራውን የሚያጥላላ፣ የሚዘልፍ ዘመቻ ያካሂዱ ነበር፡፡ በተለይም ኢጣልያ የትግራይ ሰዎችን በመጠቀም ይህንን መሰል አጥፊ ፕሮፓጋንዳ በግንባር ቀደምትነት ስታሰራጭ ነበር፡፡ ናኦድ አምሀ “Chronic Amharophobia & Its Genocidal Cloud!” በሚል መጣጥፉ ላይ ያሰፈረውን የእንግሊዝኛ ጽሁፍ እጠቅሳለሁ፡-
“We can trace roots of the current irrational hate and fear towards ethnic Amhara (Amharophobia) back into the 19th c. Although it had its own domestic genealogy, it was originally cultivated and systematically propagated by aliens, from the West & Middle East. Both parties were/are equally interested in either owning or dismembering Ethiopia to secure their respective national interests in the Red Sea region. Hence, to attain that goal, they must first incapacitate Ethiopia’s creator & natural guardian, the AMHARA! And with such wicked plan; Amharophobia was conceived during the era of “scramble for Africa”.
ደብተራ ፍስሀ አብየዝጊ የተባለ ሰው ከአድዋ ጦርነት በፊት ሮም ውስጥ ሁከት መጽሀፍትን አሳትሟል፡፡ አንደኛው በትግርኛ የተጻፈ “ጦብላሕታ” ሲሆን በዚህ መጽሀፍ ላይ ራሱን ጨምሮ ሶስት የትግራይ ሰዎች በኢጣልያ ጸረ አማራ ፕሮፓጋንዳ ስራ ላይ መጠመዳቸውን ያትታል፡፡ ለምሳሌ ዘካሪያስ የተባለው ጓደኛው በኢጣልያ የፕሮፓጋንዳ ትምህርት ቤት እንደተማረ ይገልጻል፡፡ ራሱ ደብተራ ፍስሀ አብየዝጊ የኢጣልያ የውጭ ጉዳይ መስሪያቤት ቅጥር መስሪቤት ተቀጣሪ ነበር፡፡ ከጦብላሕታ ቀጥሎ “ታሪኽ ኢትዮጵያ” የሚል መጽሀፍ እዛው ሮም ብትግርኛ አሳትሟል፡፡ ይሄኛውን መጽሀፍ በተወሰነ መልኩ አንድ ትግሬ የክፍል ጓደኛየ እየተረጎመልኝ አይቸዋለሁ፡፡ ናኦድ አምሀም ይዘቱን ተንትኖታል፡፡ በውስጡ ከባድ የሆነ የአማራ ጥላቻ እና ማጠልሸት የሚንጸባረቅበት የኢጣልያ የፕሮፓጋንዳ ማሽን ውጤት ነው፡፡ ይህ ሰው ታሪኽ ኢትዮጵያ በሚለው መጽሀፉ ውስጥ ያሰፈረውን የአማራ ጥላቻ ጽሁፍ ከናኦድ አምሀ በመዋስ እጠቅሳለሁ፡- ከአጼ ዮሐንስ ረፍት በኋላ አጼ ምኒልክ ወደትግራይ በዘመቱ ጊዜ እንዲህ ሆነ ብሎ ጽፎአል፡-
“… Some of the troops were not happy … [and] began cursing Tigray as if they came to satisfy her suppliant. Although, the Amhara troops had an intention of eliminating first the people of Agame and then the people of Axum, [however] crossing Agame alone became extraordinarily difficult to them. Then, they [Amharas] kept cursing Tigray. They even lost patience to hear the language [Tigrigna].”

አሁንም እነ ገብረኪዳን ደስታን የመሳሰሉ ደቂቀ ደብተራ ፍስሀ አብየዝጊዎች አማራውን በማጥላላት ስራ ተጠምደዋል፡፡ እነዚህ የጥላቻ አባቶች ራሱን አማራውን እንደሚጠቀሙም የታወቀ ነው፡፡ ናኦድ አምሀ “ከዋለልኝ መኮንን እስከ አለምነው መኮንን” ድረስ የሚጋልቧቸው ፈረሶች አላጡም ይለናል፡፡

ከላይ የተዘረዘረውን በኢጣልያ አማካኝነት በትግራይ ልሂቃን ሲቀነባበር የቆየውን ጸረ አማራ ፕሮፓጋንዳ ሌላ መልክ የሚሰጥ ሌላ አዲስ አለማቀፍ ክስተት ተከሰተ፡፡ በተለምዶ የ60ዎቹ ትውልድ የሚባለው በተለይም የተማሪዎች እንቅስቃሴ እየተባለ የሚገለጸው ክስተት ለአማራ ከባድ መከራን ያመጣውን ያንን ጸረ አማራ ፕሮፓጋንዳ በአዲስ መልክ እንዲቀጥል አድርጎታል፡፡ የማርክሲስም-ሌኒኒዝም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍልስፍና በሌላው አለም ላይ እየተሸነፈ በነበረበት ጊዜ የመጨረሻ ቀብሩን ያደረገው ኢትዮጵያን ነበር፡፡ በተለይ የዚህ ርእዮተ አለም አካል የሆነው የብሄሮች እጣ ፋንታን የሚተነትነው ጉዳይ ቀድሞውንም በአማራ ጥላቻ ተኮትኩተው ያደጉ ልሂቃንን በማገዝ ለአማራ በአይነቱ አዲስ የሆነ ትልቅ መከራን ወለደ፡፡ እነዚህ የአማራ ጥላቻ እርሾ ባለቤት የሆኑት ተማሪዎች የብሄር ጭቆናን እና የመደብ ትግልን ሁኔታ ለመተንተን ወዲያው ያንን ቀድሞ የሚያውቁትን የፈጠራ ፕሮፓጋንዳ ጠቃሚ ሆኖ አገኙት፡፡ አማራ ጨቋኝ ብሄር ነው ለማለት ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ ቀድሞ ከነበራቸው እርሾ ላይ ይሄንን መጤ ርእዮተ አለም ተግባራዊ ለማድረግ ለአማራው አላበሱት፡፡

በተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት ጉልህ እንቅስቃሴ ያደረገው ወለልኝ መኮንን ስለኢትዮጵያ ብሄሮች ሁኑታ ባተተበር መጣጥፉ የአማራን ሞት ርእዮተአለማዊ ሽፋን ሰጥቶ መጥፎ አሻራውን አሳርፎ አልፏል፡፡ የዋለልኝን ጽሁፍ ስናነብ የምናገኘው ነገር በአማራ ጥላቻ ተጀምሮ በጸረ አማራ ትንታኔ የሚደመደም ነው፡፡ በእርግጥ የጽሁፉ መሰረታዊ ጭብጥ ያልበሰለ እና ዋጋ የሌለው ቢሆንም በወቅቱ ቀደም ብሎ የነበረው ጸረ አማራ ስሜት ለማጋጋል እና አማራው በጨቋኝነት ለመወንጀል እንደመስፈንጠሪያ እርካብ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በዋለልኝ ጽሁፍ ላይ አማራ-ወቀስ የሆነ ትርክት በስፋት ይስተዋላል፡፡ ይህም የሚያመለክተው በወቅቱ የነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ውስጡን ለአማራው ጉድጓድ በሚምሱ ጸረ አማራዎች መጠለፉን እና የእንቅስቃሴው አካል የነበሩት አማራ ተማሪዎችም ሳያውቁት ለሌላ ስውር ሀይል የጥፋት መሳሪያ መሆናቸውን ነው፡፡ ለምሳሌ ራሱ ዋለልኝ ለኤርትራዊያን እንቅስቃሴ ትልቅ ድጋፍ ያደርግ ነበር– እዛው ጽሁድ ላይ እንደምንረዳው፡፡ እንዲያውም የጎጃም ገበሬዎችን አመጽ እና የኤርትራዎችን ትግል ለማነጻጸር በመኮረበት ቦታ የጎጃም ገበሬዎች አመጽ የአማራዎች ስለሆነ እንደሚኮራበት የኤርትራው ግን የአማራ ስላልሆነ በስፋት እንደሚወገዝ እየተንገበገበ ጽፏል፡፡ የሚገርመው ለዚህ ድምዳሜው ናሙና የወሰደው የዩነ ቨርሲቲ ተማሪዎችን መሆኑን ስናይ ጸረ አማራነት ከጨቅላነት ጋር ተደማምሮ ያደረሰብንን ጥፋት እንገነዘባለን፡፡ የዛን ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የነበረው የተማሪ ቁጥርና አመለካከቱ በምንም መልኩ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ለመገመት እንደግብአት ሊውል የማይገባው ነበር፡፡
የሆነ ሆኖ ያ ከአድዋ ጦርነት ቀደም ብሎ የተሰራበት አማራ ጠል ዘመቻ በአዲሱ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ፍሬ አፍርቶ የትግራይን ሽፍቶች አማራን ለማጥፋት ተማምለው ጫካ እንዲገቡ እስከማድረግ ደረሰ፡፡ ዛሬ የአማራን ዘር ወደማጥፋት የተሸጋገረው ጸረ አማራ ዘመቻ የአገር ቤት ወኪሎችን በመጠቀም በውጭ ሀይላት የተቀነባበረ እና እግረ መንገዱንም የራሳችንን ልጆች ድጋፍ ያላጣ ነው፡፡ እነ ዋለልኝ መኮንን ሲያራምዱት የነበረው አማራ ኮናኝ ዘመቻ በአብዮቱ ማግስት አማራውን በሁለት ዘርፍ ጠላትነት አጠቃው፡፡ በአንድ ወገን የመደብ ጠላት ተብሎ በደርግና ሌሎች ፓርቲዎች የጥፋት ዘመቻ ተካሄደበት፡፡ የመደብ ጠላት በወቅቱ አነጋገር አማራውን ለማጥቃት እንደመሳሪያ ያገለገለ ዜዴ ነበር፡፡ በሌላ ወገን አማራውን ጨቋኝ ብሄር አድርጎ በጠላትነት ስለፈረጀው ከዛ በኋላ የትግራይ፣ የኤርትራና የኦሮሞ ጽንፈኛ ድርጅቶች አማራውን ለማጥቃት ርእዮተ አለማዊ ድጋፍ አጎናጸፋቸው፡፡ ባጭሩ አማራ የመደብ ጠላት እና ጨቋኝ ብሄር ተብሎ ተመታ፡፡ አሁንም ይህ አማራውን የማጥፋት ዘመቻ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡

ለዚህ ሁሉ ጥፋት መምጣት የአማራው በአማራነት አለመቆም ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ላለፉት 41 አመታት በተለወጠ ፖለቲካዊ አየር ውስጥ ባልተለወጠ ስልት ስንጫወት መቆየታችን ለከባድ ጥፋት ዳርጎናል፡፡ አሁን አማራ የገጠመው ፈተና የስልጣን፣ የተገቢ ውክልና፣ የብልጽግና፣ የእኩልነት፣ የዲሞክራሲና ነጻነት፣ የትምህርትና ወዘተርፈ አይደለም፡፡ የህዝባችን ችግር እነዚሀን ሁሉ አልፎ የህልውና ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በአማራ ሁለንተናዊ አመለካከት እና ግለሰባዊ ማህበረ ባህላዊ እሳቤ ላይ የፋፋው የትግራይ እና የኦሮሞ ብሄረተኞች መልሶ ለመክሰም አንድ ነገር የግድ ያስፈልገዋል፡፡ እሱም እንደ አማራ መነሳሳት፡፡ እንደ አማራ ስንነሳ ሌላውን ለማጥፋት ወይም ሌላውን በመጥላት አይደለም፡፡ ራሳችንን ለማዳን ነው፡፡ ራሳችን ለማዳን ስንነሳ ግን በእኛ ዝንጉነት የፋፋው የትግሬና ኦሮሞ ብሄረተኝነት በራሱ በጨዋታው ህግ ይከስማል፣ ባይከስም እንኳ ይዳከማል፡፡ ያም አብዛኛው አማራ ለሚፈልጋት ኢትዮጵያ አዲስ አይነት የማጠናከሪያ እድልን ይፈጥራል፡፡

መደምደሚያ
በዚህ ሂደት መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ አማራ ብሄረተኝነት ተከላካ ብሄረተኝነት መሆኑን ነው፡፡ የትግራይ ብሄረተኝነት እና የኦሮሞ ብሄረተኝነት አማራን በመጥላት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ማለትም የአማራ ጥላቻ ድቡሽት ላይ የበቀለ አረም ነው ማለት ነው፡፡ የአማራ ብሄረተኝነት ግን ማንንም የማይወነጅል፣ ማንንም ተጠያቂ የማያደርግ፣ በማንም ላይ የበቀል ሀሳብ የሌለው ለአማራው ችግር መፍትሄ ለመስጠት የሚደረግ በጎ እንቅስቃሴ ነው፡፡ እኛ ሌላውን በመጥላት አንበቅልም፡፡ እኛ ራሳችንን በመውደድ ራሳችንን ማዳን ነው አላማችን፡፡ በተጠያቂነት መያዝ ካለብንም ችግሩን በቀጥታ ያደረሱብን ድርጅቶችና የድርጅቶቹ አንቀሳቃሽ ግለሰቦችን ነው፡፡ የአማራነት እንቅስቃሴ ጸረ ህዝብ የሆነ አዝማሚያ ፈጽሞ የለውም፡፡ ለዚህም ማረጋገጫው በየእለቱ በየሚዲው የእኛ ልጆች የሙሏቸውን ማሰስ በቂ ነው፡፡ እልን ያለነው ወደአማራ ብሄረተንነት ተገደን በተከላካይነት መግባታችንን እንጅ ሌላ ድብቅ ወይም ግልጽ አላማ ለማስፈጸም እንዳልሆነ እንዲሰመርበት የግድ ስፈልጋል፡፡

(በሲአትል ስብሰባ ላነብ ሞክሬ ሳልጀምረው ጊዜ አለቀብኝ፡፡ ስለኦሮሞ የቀረበው የክርክር መደገፊያ እንጅ ዋናው ጭብጥ አለመሆኑ ይሰመርበት፡፡ መልካም ንባብ)፡፡

ተጻፈ በምስጋናው አንዱዓለም

#ዳግማዊ_መዐሕድ