ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ዶከተር መረራ ጉዲናና የሪዮው ጀግና አትሌት ሌሊሳ ፈይሳ ለአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ንግግር አደረጉ።

አባይ ሚዲያ ዜና

(ዘርይሁን ሹመቴ)

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፕሬዝደንት ዶከተር መረራ ጉዲና እንዲሁም የሪዮው ጀግና አትሌት ሌሊሳ ፈይሳ በብራሰልስ 30 ጥቅምት 2009ዓም ለአውሮፓ ህብረት ፓርላማ የወያኔ መንግስት በኢትዮጵያውያን ላይ እየፈጸመ ያለውን አምባገነናዊና ኢሰብአዊ ወንጀሎችን በመጥቀስ ንግግር አድርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታን ለተሰባሳቢዎቹ ለማስረዳት ሞክረዋል። ፕሮግራሙን በተሳካ ሁኔታ የመሩት ወይዘሮ አና ጎሜዝ እንደሆኑም ለመረዳት ተችሏል።

ከሶስቱ ተጋባዥ ተናጋሪዎች ውስጥ የሆነው አትሌት ሌሊሳ ፈይሳ የወያኔ መንግስት በንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የሚወስደውን ቅጥ ያጣ የሃይል እርምጃን ለፓርላማው ለመግለጽ ሞክሯል። የሩጫ ሙያዬ በተለያዩ አገራት እየተዘዋወርኩ ወያኔ በአንድ ብሄር ብቻ ሳይሆን በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚፈጽመውን እልቂትና ግድያ ለአለም ለማጋለጥ አስችሎኛል በማለት ለተሰብሳቢው ገልጿል። ይህ ጀግና የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በውስጡ የሰረጸ አትሌት እንዲህ ባለ ትልቅ መድረክ የአንድን ብሄር ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያውያንን ሰቆቃ ለአለም ለማሳወቅ እየጣረ እንደሚገኝም አስረድቷል። በአለም እየተዘዋወረ የሚናገረውም አንድን ብሄር ወክሎ ሳይሆን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ገልጿል። አትሌቱም በማከል የአማራው መሬት ለትግራይ እየተሰጠ የአማራው ህዝብ እንደሚፈናቀል፤ የአዲስ አበባ መሬት እየተገፋ የኦሮሞ ተወላጅ እንደሚፈናቀል፤ በጋምቤላና በሌሎችም ቦታዎች በኢንቨስትመንት ስም ሰዎች እየተፈናቀሉ እንደሆነ ለማስረዳት ችሏል። በተጨማሪም ይህንን የሰዎችን መፈናቀል የሚቃወሙ በወያኔ መንግስት ግድያና እስራት እየተፈጸመባቸው መኖኑንም በንግግሩ ገልጿል። በማጠቃለያውም የአውሮፓ ህብረት ለወያኔ የሚያደርጉትን እርዳታ እንዲያቆሙና ለመብታቸው ከሚታገሉት የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በትብብር እንዲሰሩ ለፓርላማው ጥያቄውን አቅርቧል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና ዶክተር መራራ ጉዲናም የአውሮፓ ህብረት የወያኔ መንግስት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ለሚፈጽመው ወንጀል ተባባሪ ሳይሆን የመፍትሄ አካል እንዲሆን አጽንኦት በመስጠት ንግግራቸውን አድርገዋል። እነዚህ ሁለቱ ተጋባዥ ተናጋሪዎች በበኩላቸው የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያን በአምባገነንነት እየገዛት ባለው የወያኔ መንግስት ላይ ጫና እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። በማጠቃለያም ስለ ቀረበው ገላጻ በፓርላማው በተገኙ አባላት ከፍተኛ ውይይት ከተደረገ በኋላ ወይዘሮ አና ጎሜዝ የሶስቱን ተጋባዦች ንግግር ለአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሃላፊ ለአውሮፓ ካውንስል ፕሬዝዳንት እንዲሁም ለአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት በሪፖርት ተጠናክሮ እንደሚቀርብ ገልጸዋል።