አርብ መስከረም 6 ቀን 2009 ዓ.ም ከጎንደር ከተማ ተነስታ፥ በታች አርማጭሆ ሳንጃ ከተማ ወደ ሚገኘው ቤቷ ስታመራ መንገድ ላይ ያፍኗታል። የሕወሃት ታጣቂዎች ናቸው፣ እንደ ወንበዴ ተደብቀው በማድፈጥ። የክልሉ፣ የዞኑ፣ የወረዳው የመንግስት አካላት አያውቁም። ሕወሃቶች ለክልሉ መንግስት በዚህ አጋጣሚ ያላቸውን ንቀት የገለጹበት ሁኔታ ነው።

ይች እህት ንግሥት ይርጋ ትባላለች። ሕገ መንግስታዊ መብቷና የሰብአዊ ክብሯ ተነፍጎ፣ ምንም ባላጠፋች፤ ሕግ አስከባሪ ነን በሚሉ ወንበዴዎች፣ ጨካኝ አረመኔዎች ፤ ወገኖቻችንን ወደ ሚሰቃዩበት፣ ማእከላዊ ወደ ሚባለው አዲስ አበባ ወደ ሚገኘው የቶርቸር ቻምበር ተወሰደች።

እህታችን ንግስት ሐምሌ 2008 ዓ.ም ላይ ጎንደር ላይ በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ንቅናቄ ላይ ባደረገችው የማስተባበር ተሳትፎ በከተማው ታዋቂነትን ያተረፈች፥ ገና በሃያዎቹ መጀመሪያ የእድሜ ክልል የምትገኝ፥ ምንም ወንጀል የሌለባት ፍትህ ፈላጊ ሴት ናት።

ንግስት ወደ ትግሉ የገባችውና በሕዝብ ዓይን ጎልታ መታየት የጀመረችው፥ የወልቃይት ማንነት ኮሚቴዎችን በሕገ ወጥ መንገድ አፍነው ለመውሰድ በመጡ የወያኔ ታጣቂዎችና በኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የመከላከል እርምጃ ምክንያት ጎንደር ላይ በተቀጣጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ፥ ሰልፍ በመምራትና በማስተባበር ባደረገችው ከፍተኛ እንቅስቃሴ ነበር።

ይህች ወጣት የአማራ ተጋድሎ በመባል የሚታወቀው ሕዝባዊ ንቅናቄን የተቀላቀለችው፣ ቂሊንጦና ቃሊቲ እስር ቤት ጓደኛ ለመጠየቅ ሂዳ ባየችው የወጣት ኢትዮጵያውያን እስረኞች ብዛትና የአማራ እስረኞች ስቃይ፥ በተለይም ከገጠሪቱ ጎንደር ባልሰሩት ወንጄል ታፍነው ተወስደው መዳረሻቸው ሳይታወቅ ለረጅም ጊዜ ያለጠያቂ ሲሰቃዩ ላየቻቸው ወገኖቿ ጩኸትና የመከራ ድምጾች ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ ያጫወተቻቸው የትግል አጋሮቿ ይናገራሉ።

ወጣቷ በአገሯ በምድሯ እግዜር የሰጣትን የመናገር መብት ተጠቀመች። አንገቷን ላለመድፋት ወሰነች። ባርነትን እምቢ አለች። ጎራዴና ጦር ሳትመዝ ጀግንነት ምን ማለት እንደሆነ አሳየች። እነርሱ ግን የለመዱትን የተሸናፊዎች ተግባር ፈጸሙ። አላማቸውን ይችን ወጣት ቅስም ለመስበርና እርሷን ለሌሎች መቀጣጫ ለአምድረግ ነበር። ሆኖም ግን አልተሳካላቸውም። ሚሊዮን ንግስቶች ተፈጥረውል። እርሷም በአካል ወህኒ ብትሂንም በመንፈሷ ግን ነጻነቷን እያወለበለበች ነው።

ትግሉ ይቀጥላል፥ ሕዝብ ያሸንፋል፥