-ጄኔሬተራም ጄኔሬሽን
ካልፎሂያጁ ማስታወሻ የተቀነጨበ
ለጥንቃቄ ሲባል በብእር ስም የተፃፈ
(ከቤኩምሳ ስዩም)
የሆነ የድሮ ዘፈን ትዝ አለኝ:: ዘፈኑ፦
“በጎፈሬው ማህል ፤ሚዶውን ሰክቶ”
አይሂ
“በድልድል ጫንቃው ፤ላይ አልቢኑን አንግቶ”
አይሂ
እያለ ይወርዳል::
የድሮ ጉብል ሲያነጣጥር ፣ሲተኩስ፣ሲመታ ሲገድል ስለሚውል በምን ጊዜ እንደሚያፈቅር አይገባኝም::
የድሮ ሰዎች ያለ ትግል መኖር እንደማይችሉ ለመረዳት የሚፈልግ የጦርነት ዘፈኖችን መስማት አይጠበቅበትም:: የሰርግ ዘፈኖችን ማስታወስ ብቻ በቂ ነው:: አሁን ሰርግን በመሰለ የፍቅር መደረክ ላይ ” አናስገባም ሰርገኛ እደጅ ይተኛ”ብሎ ነገር ፍለጋ ምንድነው:: ይሄ እኮ” የማክበር ሰላ-ምታ-ችንን እያቀረብን ፣ በልጃችን የሰርግ ስነስራት ላይ ያዘጋጀነውን ዱላ እንዲቀምሱልን እንጠይቃለን” የሚል መጥርያ እንደመላክ ነው:: (ማህበረሰቡ ለድብድብ ያለውን ፍቅር ለማወቅ የሚፈልግ ሰው “እስክስታ ምታ፤ ቤት ምታ “የሚሉ ቃላትን መመልከት ይችላል:: የሚገርመው፣”ሰላምታ”በሚለው ቃል ውስጥ ራሱ “ምታ”የሚል ቃል መገኘቱ ነው)
ኮኔክሽን ያላችሁ፤ እንደምናችሁ !! እኔ ጉንፋንና ኮማንድ ፖስቱ ሰንገው ይዘው ያናፍጡኛል:: የድሮ ጉንፋን እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም:: ድሮ ጉንፋን ሲይዘን ፤አንድ ሁለቴ በስሱ አስነጥሰን ፤ይማርህ የሚል ምርቃት ከያልፎሂጁ አፍሰን ፤በዳማ ከሴ የጦዘ ቡን ፤ በባለቅጠሉ ፍንጃል ጨልጠን፤ ያፍንጫችንን ተረፈ ምርት በምሳና ቅጠል ተናፍጠን ፤ “ኖርማል “እንሆን ነበር:: ዘንድሮ ልጄ! ወይ ጉንፋን ከጊዜው ጋር ገግሙዋል::ወይ የመከላከል አቅማችን በጀሶ እንጀራ ምክንያት ተዳክሙዋል:: ከህመሙ በላይ ያዳከመኝ የጠያቂው ምክር ነው::
ምኡዝ ደወለልኝ፤
“ሄሎ”
“አቤት”
“የበውቀቱ ስልክ አይደለም እንዴ?”
“ነው “
“በውቄ ድምፅህ ምን በልቶ ነው ሶስት ኪሎ የጨመረ? ስልክህን ጋሽ ሙላቱ አስታጥቄ ያነሳው መስሎኝ ነበር”
“ጉንፋን ይዞኝ ነው”
“ለምን አጥሚት ነገር አትወስድበትም?”
በለው ምክር! እሺ ያጥሚት እህል አለኝ እንበል፤ በምን አባቴ እንዳፈላለት ፈልጎ ነው? ኤሌክትሪኩ እንደሆነ የጣርያው ፍሬቻ ከሆነ ሰነበተ:: ” መብራት መጣ!”ብለን ከጎረቤቶቻችን ጋር ተቃቅፈን ዘለን ሳንጨርስ ፤ አያ መብራት” ወደ ጂቡቲ ስሄድ እግረመንገዴን አይቻችሁ ልለፍ ብየ ነው”ብሎ እልም ይላል::
በነገራችን ታች፤ በንግሊዝና በኢቶጵያ ትብብር ፣ ከቺቺኒያ እስከ ንግሊዝ ኢምባሲ የሚደርስ በፀሃይ ሀይል የሚሰራ የመንገድ መብራት ተዘርግቶ ነበር::(በትብብሩ ወቅት እንግሊዝ የስራ ማስኪያጃ ፓውንድ ስታዋጣ ፣ ኢትዮጵያ ፀሃይ አዋጥታለች::) የሚገርመው ነገር የመንገዱ መብራት ገና የምርቃቱ ቀን ስለተቃጠለ የምርቃቱ ፕሮግራም የተካሄደው በጄኔሬተር ድጋፍ ነበር:: ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የመብራት ምሶሶዎች ብቸኛ ተግባር አምሺቶ የሚገባን ሰካራም ግንባር መፈንከት ሆኑዋል::
ምክሩ ይቀጥላል፤
“ለምን ባህር ዛፍ አትታጠንበትም?”
“ከታጠንኩ በሁዋላ ባሰብኝ”
” እንዴት ሊሆን ይችላል?”
“ያዲሳባ ባህር ዛፍ ፤ ከስሩ ሽንት እየተሸናበት ስለሚያድግ በጉንፋን ሲማቅቅ የሚኖር ነው::ራሱ የሚታጠነው ነገር ቢያገኝ አይጠላም”
ሌላው ለምን ብርቱካን አትበላም አለኝ::ምክሩን ተቀብየ እዚህ እኛ ሰፈር የሚገኝ ፍራፍሬ ቤት ሄጄ አንድ ኪሎ አስመዘንኩ::ሻጩ ሶስት ብርቱካን መመዘኛው ሰሃን ላይ አስቀምጦ ሲያበቃ ” አንድ ኪሎ ነው”ብሎ ደረቀ::
“ነፍሴ እንዴት ሆኖ ነው ሶስት ፍሬ ብርቱካን አንድኪሎ የሚመዝነው ? በርግጥ ይሄ ነገር ብርቱካን ነው ወይስ የከረንቦላ ድንጋይ? “
አንዱዋ እህቴ “ስፔሻል ሻይ ብጠጣበት ይለቅካል ” አለችኝ :: አልተሳሳተችም:: የሆነ ቦታ ገብቸ ስፔሻል ሻይ ጠጥቸ ሂሳብ ስጠይቅ ስድሳ ሁለትብር ተባልሁ:: ጉንፋን እንደስርቅታ በድንጋጤ እንደሚለቅ ያወቅሁት ያኔ ነው::
ስለድንጋጤ ሲነሳ አንድ ነገር ትዝ አለኝ:: ከሶስት ወር በፊት አንድ ዲያስፖራ ባልንጀራየ ፣ጠርሙስና ናፍጣ
በመጠቀም ቤት ውስጥ ተቀጣጣይ ቦምብ እንዴት መስራት እንደምችል የሚያስረዳ ነገር ኢምቦክስ አረገልኝ:: ” በውቄ፤ አንድ አድማ በታኝ መኪና ስታቃጥል ባልጄዚራ ለማየት ጉዋጉቻለሁ” አለኝ ጉዋዴ:: ኮማንድ ፖስቱ በታወጀ ማግስት ልጁን ብሎክ አረኩት:: ቤቴ ውስጥ የሚገኙትን ጠርሙሶች ሁሉ ጠርጌ ለቆራልዮ ሰጠሁዋቸው::ባጠቃላይ የጠርሙስ ፎቢያ ያዘኝ::
ባለፈው እዚህ ሃያሁለት ወደሚገኘው እውቅ ሊኪየር ሃውስ ጎራ ብየ፤
” እትየ አዛለች ፤ ወይን አለ?”
“አለ”
“በጠርሙስ ነው?”
” ታድያ እንደ ማማ ወተት በላስቲክ ተጠርዞ እንዲቀርብልህ ፈለግህ”?
በዘንድሮ ዘፈን ልሰናበታችሁ፤
በማህደሩ ውስጥ ፤አይፎኑን ሰክቶ
አይሂ
ባለዋይፋይ ሆቴል ፤ግንቡን ተጠግቶ
አይሂ
ላይክ እያዘነበ ፤ለቆንጆ ልጅ ፎቶ
አይሂ
ማርጀት እየቻሉ ፤መኖር እስከመቶ
አይሂ
ማን ሸቤ ይገባል ፤መፈክር ፖስቶ
አይሂ::