አባይ ሚዲያ
ዘርይሁን ሹመቴ

1880ዎቹ እኤአ ሃያላን የነበሩ አውሮፓውያን የተጠናወታቸውን አፍሪካን የመቀራመት አባዜ ለመወጣት እርስ በእርሳቸው ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ ገብተው ነበር። የጨለማ አሃጉር የሚል ስያሜ በመስጠት ህዝቧን በባርነት ሃብቷን በዝርፊያ በመውሰድ ለመክበር የሚያደርጉት ፉክክር ላላስፈለገ ጦርነት እንዳይዳርጋቸው በመስጋት በ1984 እኤአ በበርሊን ኮንፍረንስ አፍሪቃን የመቆራመት ስምምነት ላይ ደረሱ። ይህንን ህልማቸውን በመላው አፍሪቃ እውን ሲያደርጉና የአለምን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማህበረሰባዊ ሂደቶች በቀኝ ግዛት ርእዮተ አለምና ፍልስፍና ሲዘውሩት አንድ አገር ብቻ አልንበረከክ በማለት አስቸገረች። የዚች አገር ንጉስ ብቻ ደንቃራ በመሆን እቅዳቸውን የሚያጨናግፍ ሆኖ ተገኘ። ለባርነት ጉልበታቸውን ያላንበረከኩ፣ ትከሻቸውን ያልሰበሩ፣ ህዝባቸውን በባርነት አረንቋ ከመውደቅ የታደጉ ጥቁር ሰው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ (እምዮ ምኒልክ) በመባል ይታወቃሉ።

እኚህ የጥቁር ህዝብ የነጻነት ተምሳሌት ስመ ገናናው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በታህሳስ 3 ቀን 1903 .. ከዚህ አለም በስጋ ካለፉ 106 ዓመት ሲሆናቸው አባ መላ ኃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ደግሞ ዘጠና አመት ሆናቸው። ዳግማዊ አፄ ምኒልክና አባ መላ በስጋ ካለፉ ወደ አንድ ክፍለ ዘመን የሚጠጋ ዘመን ቢቆጠርም ስለታላቅነታቸውና ስለአሻራቸው ግን ዛሬም ገና አውርተን አልጠገብንም። አፄ ምንሊክ ሀገር የማስተዳደር ጥበብን የተማሩት በአፄ ቴዎድሮስ እጅ ሆነው እድገታቸውን በንጉሡ ቤተመንግስት ማድረግ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ።

የኒዮርክ ታይምስ በ 1909 እ ኤ አ የጋዜጣ እትሙ ላይ ስለ ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ ስለ አስተዳደራቸው እንዲሁም ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ምጣኔያዊ ሁኔታ ዘግቧል። ጋዜጣው ካነሳቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል –

ንጉሱ ኢትዮጵያን ወደ ህገመንግስታዊ የንጉሥ አስተዳደር ለመቀየር ሂደት ላይ መሆኗቸውን፣

የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ወደ 7 ሚልዮን የሚደርስ መሆኑን፣

የአውሮፓውያንን ስልጣኔ ወደሀገራቸው ለማምጣት መጣራቸውን፣ የባርያ ንግድን ለማስቆም መዋጋታቸውንና ነፃ የትምህርት ዕድል ዜጎች እንዲያገኙ መሰረት መጣላቸውን፣

ምንሊክ እራሱ ልዩ ችሎታ ያላቸው ሰው መሆናቸውን። ከችሎታዎቻቸው መካከል የዲፕሎማሲ፣ የፋይናንስ ባለሙያ እና ወታደራዊ ክህሎቶች እንደሚጠቀሱ እና

ይህ የዲፕሎማሲያዊና የወታደራዊ ችሎታቸው የጣልያንን ወረራ ኢትዮጵያ በበላይነት እንድታሸንፍ ያደረጉበት ጥበብ መሆኑን የሚሉትና የመሳሰሉት ይገኙበታል።

ንጉሠ ነገስቱ  ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ካደረጉት  አስፈላጊ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል ባቡር [1893]፣ ስልክ [1882]፣ ፖስታ [1886]፣ ኤሌክትሪክ [1889]፣ አውቶሞቢል [1900]፣ ባህር ዛፍ [1886]፣ የውሃ ቧንቧ [1886]፣ ዘመናዊ ህክምና [1889]፣ ሆስፒታል [1890]፣ የመድሃኒት መሸጫ ሱቆች [1904]፣ ባንክ [1898]፣ ገንዘብ [1886]፣ ማተሚያ [1898]፣ ጋዜጣ [1900]፣ ሆቴል [1898]፣ ፖሊስ ሰራዊት [1901]፣ የፅህፈት መኪና [1887]፣ ሲኒማ [1889]፣ ወፍጮ [1835]፣ ጫማ፣ ድር፣ የሙዚቃ ት/ቤት [1887]፣ የሙዚቃ ሸክላ [1889]፣ ፍል ውሃ [1897]፣ ላስቲክ [1898]፣ ትንባሆ [1900]፣ መንገድ [1896]፣ አራዊት ጥበቃና የጥይት ፋብሪካ [1899]፣ ብስክሌት [1893]፣ ቀይ መስቀል [1889]፣ የሚኒስትሮች ሹመት [1900]፣ ወዘተ. . . ይገኙበታል።

ክብርና ሞገስ የጥቁር ህዝብ ተምሳሌት ለሆኑት ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ!