ጂጂ አባይን የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና ስትል ትገልፀዋለች ለእኔ የእርሷ ግጥሞች አባይን በገለፀችበት መንገድ ብገልፀው ደስ ይለኛል። የማያረጅ ቅላፄ የማይሰለች ግጥም መፃፍ የምትችል በቲፎዞ ሳይሆን በአመከንዮ ከተወያየን አንድ ጂጂን ብቻ ነው የሙዚቃው አምላክ ኤዲቶስ ለኢትዮጵያችን የሰጠን።
አሥር ልጆች ካሉት ቤተሰብ ውስጥ ፈንጥቃ የወጣችው ይህች የቻግኒ ኮከብ ድምጿ የሚናፈቅ ቅኔዋ ለእንደኔ አይነቱ የከተማ ልጅ ተርጓሚ የሚያስፈልገው ጆሮ የሚናፍቀው አይነት ዜማ ለማዜም መጠበብ የማያስፈልጋት በቃ ማይኩን ይዛ ስታወራ ውላ ስታወራ ብታድር የማትሰለች ድንቅ ተፈጥሮ ነች።
በተለይም ናፈቀኝ የሚለው ዘፈኗ የትኛውም የቅኔ መምህር፣ የትኛውም ገጣሚ ነኝ ባይ ሊያስበውና ሊሞክረው የማይችለው የምንግዜም የኢትዮጵያ ሙዚቃ ምርጥ ግጥም ነው፡፡ ዘፈኑ ለብቻው አንድ ፊልም መሆን የሚችል ትልቅ የፈጠራ ውጤት ነው፡፡ እኔ ዘፈኑን ስሰማው ደገኛው ቄስ ሞገስ ተራራውን ገደሉን አቋርጦ ጂጂን የያዘውን አሳልሞ ወደቤት ሲገባ፤ አያና ድማሙ ከእነጂጂ ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው ዋርካ ላይ ተቀምጦ ዋሺንት ሲጫወት ጂጂ ከዋርካው ስር ተቀምጣ አያና ድማሙ አያና ድማሙ እያለች ስትጫወት አባቷ አያ ሽባባው ተነስተሽ ወደቤት ግቢ ብለው ሊገርፏት ሲመጡ ጎረቤታቸው ሆዴ ብላ የምትጠራት አያ ታዴ ጂጂን ከግርፋት ለማዳን አያ ሽባባውን ልመና ዘብ ስትቆም ሆዴ የምትለው ኤሌ ጂጂ ልትገረፍ መሆኑን አይቶ ሆድ ሲብሰው አባቷ አያ ሽባባው ጂጂ ከግርፋት ለመዳን በምታወጣው ድምፅ ተማርከው አለንጋቸውን ጥለው ብድግ አድርገው ሲያቅፏት ሁሉ ይታየኛል።
ለእኔ ይህ ዘፈን እንደርሷ በጥሩ ስነፅሁፍ የሚገልፅ ጠፍቶ እንጂ የብዙ ኢትዮጵያውያንን የልጅነት ህይወት የሚያሳይ ነው። በተለይም ከሀገሩ የወጣ የነጮችን እንሰሳዊ ባህሪይ ተመልክቶ
ናፈቀኝ
ናፈቀኝ የኛ ቤት ጨዋታ
ቁርስ ምሳ እራቱ የምዬ ፈገግታ
ዘመድ አዝማዱ ጨዋታው ሁካታ
አንተዬ የጠላው ቤት ሌላ
የጠጁ ቤት ሌላ
ፋሲካው አልፎ ህዝቡ ጠግቦ ሳይበላ
የመጣው እንግዳ ሰክሮ ሳይጣላ
ናፈቀኝ
ዛሬ በሰው ሀገር ትዝታው ገደለኝ
የሰው ከብት እያየሁ እያንገበገበኝ
የውሃ ዳሪውን የውሃ ፖሊስ በሬዎች የአባቴን በሬዎች የእናቴን መሰሉኝ፡፡
……………………..በማለት እንደጂጂ ነጮቹን የሰው ከብት በማለት ልጅነቱን መናፈቁ አይቀርም። ጂጂ ባለቅኔ ናት እንዳውም የዛሬ ስድስት ወይም ሰባት አመት የባህርዳር ዩኒቨርስቲ የስነጽሑፍ ትምህርት ክፍል ስለግጥሞቿ ባሰራው ጥናት ላይ የጂጂን ግጥም ለማጥናት ተመድበው ይሰሩ የነበሩት የስነጽሑፍ ባለሙያዎች በጂጂ ግጥም አተረጓጐም ላይ ልዩነት መፈጠሩን በወቅቱ አስታውሳለሁ። እኔ ልጅ እያለሁ ባደግኩባቸው አውቶቡስ ተራ፣ ግንፍሌ(አራት ኪሎ) እና ኮተቤ የጂጂን ሙዚቃ የሚከፍቱ ሙዚቃ ቤቶች በመሄድ የጂጂን ድምጽ ስሰማው ይሰማኝ የነበረው ደስታ ወደር የለውም ያኔ ለበጎ ነው ያኔ በድምፇ የወደድኳት ጂጂ አድጌ ግጥሞቿን መገንዘብ ስጀምር ምንኛ የተለየ አእምሮ እንዳላት አስባለሁ። ለአብዛኞቻችን እኔንም ጨምሮ ኢትዮጵያዊ አርቲስት ሲባል መሀይም ከመዝፈን እና ከመጨፈር ውጭ ምንም ማገናዘብ የማይችሉ ፍጥረቶች እንደሆኑ ነው የምናስበው። ጂጂ ግን ልዩ ነች። ጂጂ የኢትዮጵያ የስነጽሑፍ ቅርስ ናት ሲሻት
“አባ ለምን ለምን እኔ
ጀንበር ወጥታ አትገባም ሳልሰራ ኩነኔ” እያለች ፈጣሪዋን መልስ ፍለጋ ትጠይቃዋለች ሲሻት
“ሀይልን በሚሰጠኝ በእግዚአብሔር አምናለሁ
ለስሙ ለክብሩ ቆሜ እዘምራለሁ” በማለት ምስጋናዋን ለፈጣሪ ታቀርባለች በኢትዮጵያ ያለውን የዘረኝነት ልክፍት ስትመለከት “በቃኝ አትለውም ወይ ዘረኛውን መንግሥት” በማለት አብዮታዊ ትሆናለች። ቀጠል አድርጋም
“ዘመን አመጣሽ የዘር በሽታ
መድሐኒት አለው የማታ ማታ
ሀገር በወገን እንዴት ይረታ
ፍቅር በነገር እንዴት ይረታ
ዘር ሳይለያየን ወይ ሐይማኖት
ከጥንት በፍቅር የኖርንባት
እናት ኢትዮጵያ ውዲት ውዲቷ
በጎጆ አያልቅም ሙሽርነቷ ….. እያለች እውነታውን በማፍረጥረጥ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚጣጣሩትን በሙሉ መርዷቸውን ትነግራቸዋለች።
ስለኢትዮጵያ ገጥማ ቅኔ ተቀኝታ የማትጠግበው ጂጂ ኢትዮጵያን እንደልጅ ቁጭ አድርጋ እንዲህ እየተለማመነች ትመክራታለች።
“ኢትዮጵያ አይክፋሽ እናቴ
ምንም ድሃ ብሆን አለው በህይወቴ
ጎትጉቺኝ እስቲ አንቂኝ ከእንቅልፌ
ቤቴን ሳላፀዳ እንዳልቀር ሰንፌ
ቀኔን ሳላሳምረ እንዳልቀር ሰንፌ
………
ክፉ ገዢ መጣ ደጉ ንጉሥ መጣ
ሁሉም ይሄዳሉ እንዳመጣጣቸው ሳቅና ለቅሶሽን አየገዙትምና
አትፍሪ እናት አለም ኑሪልኝ በጤና እያለች ዘለዓለማዊ ሀገር እንጂ ዘለአለማዊ ንጉሥ አለመኖሩን ትናገራለች።
ሰዎች በዚህ ቀውጢ ሰአት በዚህ ኢትዮጵያውያን በየአደባባዩ በሚገደሉበት ወቅት ስለምን ስለአርቲስት ትፅፋለህ ሊሉ እንደሚችሉ አውቃለሁ ሆኖም እየፃፍኩ ያለሁት በችግራችን ወቅት በአንድነት እንድንቆም ስለምታዜመው ጂጂ እጅጋየሁ ሽባባው ነው። ጂጂ አሁን ጤንነቷ በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል ሙሉ ለሙሉ አገግማ በጨለማ ውስጥ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ትልቅ ብርሃን እንደምትሆን እምነቴ ነው ይህ እንዲሆን የምንፈልግ መላው የጂጂ እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ጂጂን አብረን ሆነን አይዞሽ ወገኖችሽ በችግርሽም ሆነ በደስታሽ ከጎንሽ ነን ልንላት ይገባል። ኢትዮጵያ እንደጂጂ አይነት የህዝብ አለኝታ የሆኑ የጥበብ ሰዎች ከምንም ጊዜውም በላይ የሚያስፈልጓት ጊዜ ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያውያንን በጋራ ሊያቆሙ የሚችሉ ኢትዮጵያውያን እየደረሰባቸውን ያለውን በደል በጥሩ ቋንቋ ሊገልፁ የሚችሉ ማገናዘብ የሚችሉ እንደጂጂ አይነት የዘመን ምስክሮች ያስፈልጉናል። ጂጂ የኢትዮጵያ አምላክ ከአንቺ ጋር ይሁን።