አባይ ሚዲያ ዜና በዘርይሁን ሹመቴ

ሪፓርተር ጋዜጣ አቃቤ ህግ በአክትቪስት ንግስት ይርጋና በሌሎች አምስት ተከሳሾች ላይ ያቀረበውን ክስ ዘግቧል።

ጋዜጣው እንዳስነበበን አክትቪስት ንግስት ይርጋ እስከ ካናዳ የሚደርስ መረብ ዘርግታ እንደነበረና በርከት ያለ ገንዘብም ሲመደብላት እንደነበረ አስነብቦናል።

መንግስትን ለመጣል የተቋቋመውን ኮሚቴ በባላይነት በመምራትና የራሷን ግሮሰሪ በአመጽ ትግል ለሚገኙ ቡድኖች ማቆያና መሸሸጊያም ስትጠቀም እንደነበረችም ዘርዝሮልናል።

አገዛዙ በሽብርተኝነት ከፈረጀው ድርጅት አመራሮችም ጋር ግንኙነት እንደነበራትምና ትእዛዝም ስትቀበል እንደነበረም በተጨማሪም አስፍሯል።

ከአክትቪስት ንግስት ይርጋ በተጨማሪ አምስት ተከሳሾችም በትጥቅ ትግል ከሚንቀሳቀስ ድርጅት አመራሮች ግንኙነት በማድረግና ተልእኮ በመቀበልና በማስፈጸም ክስ እንደተወነጀሉ ሪፓርተር አስነብቦናል።

ከዚህ በታች የጋዜጣውን ሙሉ ዘገባ ያገኙታል

በአማራ ክልል በተለይ በሰሜን ጎንደር ከተማ በተለያዩ የዞን ከተሞችና በአዲስ አበባ ጭምር አመፅና ሁከት በማስነሳት፣ የአመፅ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ በማስተባበር ከፍተኛ የሆነ የግልና የመንግሥት ንብረት ላይ ውድመት አድርሳለች የተባለች አንድ ግለሰብ ከሌሎች አምስት ግለሰቦች ጋር የሽብር ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

በቅጽል ስሟ ይርገዱ እንደምትባል የተገለጸችው ንግሥት ይርጋ ተፈራ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ተልዕኮን በመቀበል፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር አባላት የገንዘብ ድጋፍ በመቀበል፣ የተለያየ የጦር መሣሪያ እንዲገዛ በማድረግና በክልሉ በተለያዩ ዞኖችና ከተሞች አመፅና ሁከት እንዲነሳ በማድረግና በመምራት መሳተፏን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡

ግለሰቧ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ቡድን ጋር ግንኙነት ካለው በካናዳ ነዋሪ መሆኑ ከተገለጸው ክንዴ ከሚባለው ግለሰብና በሰሜን ጎንደር ከሚንቀሳቀሰው የቡድኑ አባል ደጀኔ ማሩ ጋር ግንኙነት እንደነበራትም በክሱ ተጠቅሷል፡፡ ሐምሌ 5 ቀን 2008 .. በጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ውስጥ በሚገኘው ደሳለኝ ትምህርት ቤት ውስጥ በተፈጠረው አመፅና ሁከት፣ 20 ከሚሆኑ ወጣቶች ጋር በመግባትና በማስተባበር ሰዎችና ተሽከርካሪዎች እንዳያልፉ መንገድ ከማዘጋቷም በተጨማሪ በአመፁ የተሳተፉ ወጣቶችን በራሷ ግሮሰሪ ውስጥ በማሳደር ከፍተኛ የንብረት ውድመት እንዲደርስ ማድረጓን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አካቷል፡፡

ደጀኔ ማሩ ከተባለ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል ጋር ተገናኝታ በጎንደር ከተማ የተከሰተውን አመፅ መምራት እንዳለባት ከተወያዩ በኋላ ሐምሌ 5 ቀን 2008 .. በጎንደር ከተማ አመጽ የሞቱት አራት ነዋሪዎች መሆናቸውን፣ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ሳይቆስል እንደቆሰለ በማስመሰልና ለመቀስቀሻ በ600 ብር ባነር አሠርታ ሐምሌ 24 ቀን 2008 .. በጎንደር ከተማ ከፍተኛ አመፅ በማስነሳት፣ ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት እንዲወድም ማድረጓን ክሱ ይገልጻል፡፡

መንግሥትን በአመፅ ትግል መጣል እንዳለባቸው በመነጋገርና በመስማማት ሐምሌ 26 ቀን 2008 .. በጎንደር ከተማ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በመሰብሰብና አመፁን የሚያስቀጥሉ 15 ሰዎች ያሉበት ኮሚቴ በመምረጥ ግንባር ቀደም የመሪነት ተሳትፎ እንደነበራትም አክሏል፡፡ ተከሳሿ ኮሚቴው እንዲቋቋም ካደረገች በኋላ ኮሎኔል ደመቀን ለመጠየቅ ጎንደር ማረሚያ ቤት በተገኘችበት ወቅት፣ ኮሎኔሉ ጠንክረው በመደራጀት ሥራቸውን እንዲሠሩ እንደ መከሯትና ከሐምሌ 24 ቀን 2008 .. ጀምሮ ‹‹እቴጌ ጣይቱ›› ብለው እንደሰየሟት ለአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት በስልክ መናገሯን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

በካዳና የሚገኝ የቡድኑ አባል ወደ ተከሳሿ በመደወል የትጥቅ ትግል ለማድረግ ከቆረጠች በውጭ ያሉ የቡድኑ አባላት ከሚያደራጇቸው አባላት ጋር እንደሚያገናኟት፣ አርማጭሆ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱት የቡድኑ አባላት ሰጠኝ አርጋውና ማሩ አረጋ ጋር መገናኘት እንዳለባት፣ በሥሯ የሚገኙ የቡድኑ አባላትን ከላከች ደግሞ እንደ ፕሮጀክት ይዘው ከውጭ ዕርዳታ እንደሚያደርጉላት፣ የጦር መሣሪያ እንደሚያስታጥቋቸውና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን እንደሚያደርጉላት ቃል ተገብቶላት እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ ለቤት ማደሻ በሚል ከካናዳ ከተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ እንደተላከላትም አክሏል፡፡

በለጠ አዱኛ የተባለ ሌላው የጎንደር ከተማ አመፅ አስተባባሪ ለተከሳሿ ነሐሴ 17 ቀን 2008 .. ደውሎላት፣ የቡና ቤት ሴት አለባበስ በመልበስና በየመዝናኛ ቦታዎች በመሄድ ባለሥልጣናትን በወሲብ በማጥመድ የማስገደል ሥራ እንድትሠራ የተሰጣትን ተልዕኮ ለመተግበር እየተንቀሳቀሰችና ፎቶዎችን እያነሳች ለቡድኑ በመላክ ላይ እንደነበረች በክሱ ተገልጿል፡፡

‹‹ትግሉ ከሥርዓቱ ጋር እንጂ ከትግሬ ጋር እንዳልሆነ›› በማስታወቅ ትግሉን ወደ ኋላ ለመመለስ የሚጥርና የሚሞክሩ የሥርዓቱ ተጠቃሚዎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተከሳሿ መናገሯን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ተከሳሿ አመፁን እንድታስቀጥል ከውጭ ተደውሎላት መምህር ኤፍሬም በተባለ ግለሰብ በኩል 108,000 ብር እንደተላከላትም ክሱ አክሏል፡፡

ከንግሥት ይርጋ ጋር ተጠርጥረው የሽብር ተግባር ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው ዓለምነህ ዋሴ ገብረ ማርያም፣ ቴዎድሮስ ተላይ ቁሜ፣ አወቀ አባተ ገበየሁ፣ በላይነህ ዓለምነህ አበጀና ያሬድ ግርማ ኃይሌ (ከአዲስ አበባ) ሲሆኑ፣ በውጭ አገር ከሚገኙ የሽብር ቡድኑ አባልና አመራር ጋር በመነጋገር ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ ለኢሳት ቴሌቪዥን በጎንደር ከተማ ስለተከሰተው አመፅ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት፣ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላትና አመራሮች ጋር በመነጋገር የሽብር ተግባር ለመፈጸም ትጥቅ ከታጠቁ ጋር ግንኙነት በመፍጠር የሽብር ተልዕኮ በመቀበል፣ አመፁን በመምራትና በማስተባበር በግልና በመንግሥት ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በስፋት በክሱ አብራርቷል፡፡ ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1 ሀ እና ለ)38 እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 34 እና 6ን በመተላለፍ ድርጊቱን እንደፈጸሙ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን የሽብር ተግባር ወንጀል ክስ ለማየት ፍርድ ቤቱ ለጥር 23 ቀን 2009 .. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡