በበለሳ የህወሃት/ኢህአዴግ ሰራዊት በታጋዮች ላይ ያደረገው ከበባ ተሰበረ

ሰሞኑን በሰሜን ጎንደር አርባያ ወረዳ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የነጻነት ታጋዮችን በአንድነት በማሰባሰብ የትግል ምክክር ለማድረግ የተጠራውን ስብሰባ ለመክበብ ሙከራ ያደረገው የህወሃት/ኢህአዴግ ሰራዊት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት መበታተኑን ታጋዮች ተናገሩ።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የነጻነት ታጋይ ቴዎድሮስ እንደገለጸው በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች በጋራ በሚወጣ የትግል ስትራቴጂ አገዛዙን ለመግጠም ምክክር ለማድረግ በተጠራ ስብሰባ ላይ ህወሃት መራሹ አገዛዝ አስቀድሞ መረጃ ደርሶት ስለነበር ጦሩን በአካባቢው አሰፍሮ ጠብቋቸዋል።

ይሁን እንጅ በታጋይ ስም ከሚንቀሳቀሱት መካከል በአንደኛው ላይ ጥርጣሬ እንዲያሳርፉ የሚያደርግ ፍንጭ ከስብሰባው በፊት በማግኘታቸው ጥንቃቄ እንዳደረጉና ስብሰባው በተጠራበት አካባቢ ሲደርሱም ያጋጠማቸው ነገር ጥርጣሬያቸው ትክክል እንደነበር እንዳረጋገጠላቸው ታጋይ ቴዎድሮስ ገልጿል።

በእርሱ የሚመራው ሃይል ስትራቴጂክ ቦታ ይዞ ስለነበር ወዲያውኑ ተኩስ በመክፈት በህወሃት ሰራዊት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ በእነሱ ላይ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ከበባውን መስበሩን ገልጿል።

አገዛዙ ወዲያውኑ ተጨማሪ 400 የሚሆኑ ወታደሮችን ቢያመጣም እነሱ ግን ምንም ነገር ሳይደርሰባቸው ከአካባቢው መራቃቸውን ተናግሯል።

የስብሰባው አላማ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የነጻነት ሃይሎችን በአንድ ላይ አቀራርቦ የትግል ስትራቴጂ ለመንደፍ እንደነበር አርበኛ ቴዎድሮስ ገልጿል። የአካባቢው ህዝብ ከለላ ሆኖናል የሚለው አርበኛ ቴዎድሮስ 5 በመቶው የአገዛዙ መረጃ ቢሆንም 95 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ጋር ግን ከእኛ ጋር ሆኖ እየደገፈን ነው  ብሎአል።

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ህዝባዊ ተቃውሞ አገዛዙ በመሳሪያ ሃይል እንደተቆጣጠረው በመገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ ቢለፍፍም ትግሉ ግን በተለያዩ የነጻነት ሃይሎች ተዋቅሮ በመካሄድ ላይ መሆኑን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።