ዘመናዊ ህክምና ፣ ጸበል ፣ ወይም ቃሊቻ ፣ የማይፈውሰው ፈታኝ በሽታ( ወይንእሸት ተክሉ)

በሃገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ በምናየው እይታ ከሆነ ሁለት እጅግ የማይጣጣሙ ታጋዮች ይታያሉ ። እነዚህም አንደኛው የነጻነት ታጋይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የስልጣን ታጋይ ነው ። የነጻነት ታጋዩ በሚገባ በሃገራችን ያለው ችግር የገባውና በትክክልም በወያኔ አስፈጻሚነት በምእራባውያን ገዢነት እየተፈጸመበት ያለውን የከፋፍለህ ግዛ ግፍና መከራ አሽቀንጥሮ ለመጣልና ኢትዮጵያን እንደ ሃገር ሰላም ፣ እኩልነትና ብልጽግና የተሞላባት ሁሉም ብሄርና ብሄረሰብ አለምንም አድሎና መከፋፈል አንድ ሆና ታሪኳን እና ክብሯን ጠብቃ መኖር እንድትችል ያለማሰለስ የሚታገል ሲሆን ፣ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኘው ደግሞ አብዛኛው ወይንም ሁሉም ማለት ይቻላል ለስልጣን የሚታገለው ቡድን የሚገኘው ከሃገር ውጪ በምዕራቡ ዓለምና በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አይሆንም ።

እዚህ ላይ ለመጻፍ የምወደው ስለሁለተኝው ታጋይ ማለትም ዋና አላማው ነጻነትን ማምጣት ሳይሆን ስልጣንን ለመጨበጥ ካለው ጽኑ ምኞት የተነሳ እራሱን ግን ልክ ለህዝብና ለሃገር ተቆርቋሪ አስመስሎ ለሚቀርበው በምዕራቡ ዓለምና በተለያዩ ከኢትዮጵያ ውጪ በሆነ ስፍራ በመደራጀት ከልክ በላይ ለሚጮኸውና ለሚያደነቁረው የህብረተሰብ ክፍል ነው ።

አለመታደል ሆኖ ይህ ከልክ በላይ የሚጮኸውና ሚዲያውን ያጨናነቀው ስመ ታጋይ ክፍል ባብዛኛው የተደራጀው በዘር ወይንም በጎሳ ሲሆን ፣ ጩኸቱም የሚያተኩረው ዛሬ ባለው ህዝብንና አገርን በሚያሳስበው መፍትሄ በሚሻው አገራዊ ጉዳይ ሳይሆን ባልነበረና ባልተፈጸመ ድርጊት ወይም ተደርጓልም ቢባል ከመቶ አመታት በላይ ባስቆጠረና በተረሳ ዛሬ ላይ በማይታይ ፣ በማይጨበጥ ፣ በማይዳሰስ ፣ ተረት ተረት ላይ ሆኖ ያንን እንደ ቀበኛ ከብት እያመነዥጉ ወይ አይውጡት ወይ አይተፉት ለዘመናት እያላመጡ የትግሉ ዋና አስኳል አስመስሎ ለማቅረብና ያንን አንተርሶ ድጋፍ ለማግኘትና ስልጣን ላይ ለመፈናጠጥ የሚደረግ መፍጨርጨር ጆሮ ማጦዝ ከጀመረ ዓመታት ቢያስቆጥርም ዛሬም ትኩስ ሆኖ ትኩሳት እየፈጠረ ነው ።

እነዚህ በዲያስፖራው የተሰገሰጉ ስመ ታጋዮች ተማረም አልተማረም አንዳቸውም የሃገርና የወገን አንገብጋቢው ጥያቄ የገባቸው አይመስሉም ። ቢገባቸውም ከህዝብ ጥያቄ ይልቅ የነሱ የስልጣን ጥማት ስለሚያመዝንባቸው አንገብጋቢውን ጥያቄ ወደኋላ በመግፋት የራሳቸውን የስልጣን መወጣጫ እርከን ያደላድላል ብለው ያመኑበትን ሆኖም ግን ስንዝር እንኳን ያላራመዳቸውን ባዶ መፈክር ይዘው የሚበላውና የሚጠጣው ያጣን ፣ ነጻነት እንደ ሰማይ ቤት የራቀውን ፣ እስራትና ግርፋት የሰለቸውን ፣ መሰደድና መገደል ያንገፈገፈውን ህዝብ “ሚኒሊክ ጡት ቆረጠ” እከሌ መጥቶ ልንጠራበት የማንፈልገውን ስም “…” ብሎ ጠራን ፣ በቃ አኮረፍን ፣ ከፋን ከረፋን ፣ እንገነጠላለን ፣ እናስገነጥላለን ፣ ቁቤ ወይም ሞት ፣ እያሉ ሲያላዝኑ ማስተዋል ከጀመርን ዘመናት አስቆጥረናል ።

እውነት ይነገር ከተባለ ሚኒሊክ ጡት ኣልቆረጠም ፣ አላስቆረጠም ። እሱ የናንተ ባለ ታሪክ ኤርትራዊው ኩታራ ተስፋዬ ገብረ አብ በምርቃና የጻፈላችሁ ነው ። አይ አይደለም እውነት ነው ካላችሁ እውነታው ሌላ ነው ፣ እውነተኛውና አሳዛኙ ታሪክ ያልነበረውና ያልተፈጸመው የጡት ቆረጣው ሳይሆን ፣ ዛሬ ድረስ የሚካሄደው በተበደልን ባዮቹ የሚፈጸመው ዘግናኝ እና ጸያፉ ስራ በጎሳ ምክንያት እርጉዝን ሴት ሆዷን በሳንጃ መቅደድ ፣ አዛውንትን እና አቅመ ደካሞችን ፣ ህጻናትን ከገደል በመወርወርና ከመጨመር ባሻገር ፣ ሚስት ለማግባት ሲባል የወንድን ብልት የሚቆርጠው ማነው? እስቲ ምነው ስለዚህ ዘግናኝ ሁኔታ በሌላው ኢትዮጵያዊ ወይንም በሌላው ብሄር እና ጎሳ አይነሳ? ወይንስ የራስ ሲሆን እንደ መልካም ተግባር መታየት አለበት እየተባልን ነው? ወይንስ “የሹም ዶሮ ስለሆኑ ኩት አትበሏቸው” ነው? ከተናገርንማ ብዙ መናገር ይቻላል ፣ ግን እኛ ሰው አነሰ ፣ ኮሰሰ ፣ ብለን በሱ ደረጃ መውረድ ስለማንፈልግ እዚሁ ላይ ህሊና ላለው የህሊና ወቀሳ ይሁን ብለን ትተነዋል ።

በተጨባጭ ግን ለዚህ ሁሉ መንስኤ የሆነው በራስ ካለመተማመንና እራስን ዝቅ አድርጎ ከማየት የተነሳ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው ። ሌሎችን ይበልጡኛል ብሎ በመገመት ፣ ሌሎች ከኔ የተሻሉ ናቸው በሚል ባፍ የማያምኑት ሆኖም ግን በልብ የሚቀበሉት ፣ አጥንትን ዘልቆ እስኪገባ ድረስ ሊያስተባብሉት ያልተቻለ ጽኑ ህመም እራስን በማሳመን ፣ እውነትን አንሸዋርሬ ነገርን አጣምሜ ካልሆነ በቀር በኔ ግንዛቤና በኔ ችሎታ ከሌሎች ልቄና ደምቄ ልወጣና ልታይ አልችልም ብሎ እራስን በድካም ከማሳመን በመነጨ ወልካፋ ግንዛቤ የሃሰት መዝገብና ዶሴ ይዤ ጥሜን አረካለሁ ከሚል ከንቱ ምኞትና ህልም የተነሳ እንጂ በራሱ የሚተማመንና እራሱን ከሌሎች እኩል ነኝ የሚል ቅን ግንዛቤ ያለው የህብረተሰብ ክፍልም ሆነ ቡድን ይህንን አይተገብርም ። ነገር ግን እነዚህ የስም ታጋዮች የበታችነት ስሜት አይምሮአቸው ላይ እንደ ሸረሪት ድር ስላደራባቸው የሃሰት ቱልቱላ ፈብርከው ለዘመናት ሲያመነዥጉ ይስተዋላል ።

የሚደሰኩሩት ተግባርም ተፈጽሟል ከተባለ ወደኋላ ሄዶ ያንን በላጲስ ማጥፋት ስለማይቻል ከመጥፎ ታሪክ ተምሮ መጥፎው ታሪክ እንዳይደገም መጣር ፣ መስራት ፣ ጥሩ ታሪክ አለ ተብሎ ከታመነ ያንን ለማሳደግ መድከም ሲገባ እንደ ግመል ሽንት ለዘመናት የኋልዮሽ መሄድ የስልጣን ጥመኛውንም አልጠቀመ ፣ ለህዝብና ላገርም ቅንጣት አልፈየደ ። ተጠቃሚ የሆነው ዘረኛውና ጠባቡ ወያኔና ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅላቸው ምዕራባውያን ፣ አረቦች ፣ ቻይኖችና የመሳሰሉት ብቻ ናቸው ። ስለዚህ እነዚህ የታሪክ አመንዣጊና የስልጣን ጥመኞች ፣ ጎሰኞች ፣ የኢትዮጵያን ትንሳኤ እስከዛሬ አዘግይተዋል አሁንም እስከመቼ በዚህ ኋላ ቀር እይታቸው እንደሚያደነቁሩንና ትግሉን እንደሚያጓትቱ ፣ እንደሚያሰላቹን የሚታወቅ ነገር የለም ።

ስለሆነም ፣ ጎሰኝነት ፣ ጠባብነት ፣ የበታችኝነት ስሜት ፣ በራስ አለመተማመን ፣ ዘመናዊ ሃኪም አያድነው ፣ ጸበል አይፈውሰው ፣ ቃሊቻም ሆነ ሌላ ሊያረጋጋው ስለማይቻል ለዚህ መፍት ሄው ይህ የነቀዘው የህብረተሰብ ክፍል መቃብሩ ተምሶ “ሊሞሉበት ነው መረሬ” የሚለው ተዘምሮ ካበቃ በኋላ ብቻ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል ።

      ወይንእሸት ተክሉ