እንኳንም ተወለድ( በወንዴ አዲስ)

አንዱዬ እንኳንም ተወለድክ

እንኳንም የኢትዮጲያ ሆንክ

ፈጣሪ እናትክን ኢትዮጲያን- እጅግ አብዝቶ ቢወዳት

አንተን ካፈሯ ቀምሞ-  ለትንሳኤሽ እነሆ አላት።

ቋያው የቆሰቆስከው- አንድዬ ላይጠፋ ጦፏል

ከባንዶች ብብት ውስጥ ገብቷል

ጠላት እቶን ላይ ተጥዷል

በቅያስህ አእላፍ ተሟል

አባት በሚሉህ አርበኞች- ህልምህ ወደ ድል  አምርቷል

አንዳርጌ እንኳንም ተወለድክ

እንኳንም የኢትዮጲያ ሆንክ

ጌታ እናትክን ኢትዮጲያን- እጅግ አብዝቶ ቢወዳት

ካፈሯ አንተን ቀምሞ – ለትንሳኤሽ እነሆ አላት።

አንዳርጋቸው የኛ ሙሴ- ያለህን ሁሉ ሰውተህ

አባትነትክን እንኳ- ሳይቀር ከልጆችህ ህይወት  ነጥቀህ

አውሮፓ ደህና ሰንብቺ- ቅንጦት ይቅርብኝ ግድ የለም

ላገሬ የምሰስተው- የምነፍጋት አንዳች የለም

አለኝ ቁምነገር ከዱሩ- ካርበኛው አለኝ ቀጠሮ

በቅንጦት የማባክነው- ጊዜ የለኝም ዘንድሮ

ይነጠፍልኝ አጎዛው- በረባሶ አምጡ ለእግሮቼ

ባፍንጫየ ይውጣ ድሎት- እየማቀቁ ህዝቦቼ

ከሸጡ ከተረተሩ- ከፍልሚያው ጎራ እንገናኝ

የእናት አገሬን የኢትዮጲያን- ድምጷን ሰማሁት ስትጠራኝ

ካርበኞች ልጆቼ ጋራ- ጥሪዋን ላደምጥ ቃል አለኝ

ላንቺ ነው ኢትዮጲያ ልላት- ልሰማት ልጄ ስትለኝ

እዛው ነኝ በሀገሬ አፈር- ላልክዳት ኪዳን አለብኝ

ብለህ የቆሰቆስከው- ቋያው ላይጠፋ  ተዛምቷል

ከባንዶች ብብት ውስጥ ገብቷል

ጠላት እቶን ላይ ተጥዷል

በፈለግክ አእላፍ ተሟል

አባት በሚሉህ አርበኞች- ያገርህ ትንሳኤ  ቀርቧል

አንዳርጋቸው ሰምተን ነበረ- ሲሸልሉ ሲፎክሩ

አሰርነው ሲሉ ሳያፍሩ

ማሰር በግረ ሙቅ መስሏቸው

አንዳርጌን እንዳትጨበጥ- ከቶ ማን በነገራቸው።

ጠፍሮ ዘብጢያ መጣል

ጥፍሮችን በጉጠት መንቀል

ሰቆቃን ባይነት መቆለል

ስጋን ባመፃ መበቀል

በበሽታ ማሰቃየት- ካለም እይታ መከለል

ይሆን እንዴ ማሰር ማለት

ባጋሰሶች በባንዶች ቤት

እንዴት ይያዛል አንዳያ- ያውም ከሰንአ ከየመን

ራእዩ ባገሩ መሬት- ሲፈካ ሲያሸት እያየን።

ያን ጀግና ማ ደፍሮ ሊያስር- ያን ያእላፍ

አርበኞች አባት

መንፈሱ ሰፍቶ እንደንጉዳይ- ሲያዘምር

የጀግና መአት

ህዝቦች ደም ስር ውስጥ ከትሞ

ከሚልየኖች ልብ ታትሞ

እንዴት ሆኖ ነው ሚታበት- እንዴት ሆኖ ነው ሚታሰር

ይጠየቅ ድፍን ኢትዮጲያ- ይመስክር ባህርዳር ጎንደር

አንዳርጋቸው መሪያችንነው – እየተባለ ሲፈከር

አንዳርጋቸው ሙሴያችን ነው- እየተባለ ሲዘመር።

አዎ አንዱ መሪይችን ነው- የኢትዮጲያ አምላክ ይመስክር።

 

የኛ ሙሴ እንኳን ተወለድክ

እንኳንም የኢትዮጲያ ሆንክ

ጌታ እናትህን ሲሳሳላት- ፈጣሪ ጦቢያን ሲወዳት

አንተን ካፈሯ ቀምሞ- ለትንሳኤሽ እነሆ አላት።

 

—-

መልካም ልደት ለጀግናው አርበኛ አንዳርጋቸው ፅጌ