ከ500 በላይ የአፍሪቃ ስደተኞች በከፍተኛ ሴኩሪቲ የሚጠበቅን የኤሌትሪክ አጥርን በመስበር ወደ ስፔን ክልል ገቡ። 11 የስፔን ፓሊሶች ተጎድተዋል

አባይ ሚዲያ ዜና በዘርይሁን ሹመቴ

አፍሪቃውያን በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ አውሮፓ የሚያደርጉት ለህይወት እጅግ አደገኛ የሆነ የስደት ጉዞ እየጨመረ እንደሚገኝ ተጠቆመ።

በሰሜናዊ አፍሪቃ የምትገኘው የስፔን ግዛት ወደሆነችው ሲዮታ (Ceuta ) ከ500 በላይ አፍሪቃውያን አደገኛ አጥር ሳይበግራቸው ለመግባት እንደቻሉ ተዘግቧል።

የዚህ አደገኛ አጥር ርዝመት ወደ ስድስት (6) ሜትር እንደሚደርስ የተጠቀሰ ሲሆን ሞሮኮን ከሲዮታ ክልል ለመለየት የተዘረጋም እንደሆነ ታውቋል።

የሲዮታ መንግስት ባለስልጣናት ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለጹት በትንሹ ወደ 500 ስደተኞች ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበትን አደገኛ አጥር በጉልበት ሰብረው ወደ ዚችው የስፓኒሽ ክልል ገብተዋል።

ይህንን አጥር ለማለፍ በተደረገው ግብግብ ሁለት አፍሪቃዊያኖች ተጎድተው ለሆስፒታል መዳረጋቸው ሲገለጸ በአንጻሩ አስራ አንድ (11) የስፔን ፓሊሶች ላይም ጉዳት መድረሱ ታውቋል።

የስፔን ክልል ወደ ሆነችው ሲዮታ ለመግባት ከሞከሩትን አፍሪቃውያን መካከል አብዛኞቹ በአጎራባቿ የሞሮኮ የጸጥታ ሃይሎች ሊገደቡ እንደቻሉም ተነግሯል።

አስቸጋሪውን ውጣ ወረድ አልፈው ወደ ስፔን ክልል ወደ ሆነችው ሲዮታ የጉቡት አፍሪቃውያን  “ነጻነት” (Freedom)የሚል መፈክርን በጉልህ በማሰማት በመንገድ ላይ ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።

በርግጥ አፍሪቃውያኑ አደገኛውን አጥርና ከፍተኛ ጥበቃውን አልፈው እዚሁ ክልል ቢገቡም አውሮፓ ሊያኖራቸው የሚችል የጥገኝነት ፍቃድ የማግኘት ተስፋቸው ግን የመነመነ እንደሆነም ተገልጻል።

ምንአልባት ገሚሶቹ ወደ ሞሮኮ የቀሩት ደግሞ ወደ መጡበት አገራት እንዲመለሱ ሊደረግ እንደሚችል እየተነገረ ነው።