በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሹ መኪና ላይ በተጠመደ ቦምብ ፍንዳታ በትንሹ 34 ሰዎች ተገደሉ። ከ50 በላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል

አባይ ሚዲያ ዜና በዘርይሁን ሹመቴ

በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሹ በመኪና ላይ በተጠመደ ቦምብ ፍንዳታ በትንሹ 34 ሰዎች መሞታቸውንና ከ50 በላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተዘገበ።

እንደ ከተማው ባለስልጣናት ገለጻ መኪናው በቦምቡ የጋየው በከተማዋ ደቡባዊ የማዲና አውራጃ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

መሃመድ አብዱላሂ መሃመድን በዚህ ወር መጀመሪያ አገሪቷን ለመምራት በፕሬዝዳንትነት መረጣቸው ይታወሳል።

ፕሬዝዳንት መሃመድ አብዱላሂ መሃመድ አገሪቷን የማስተዳደር ሃላፊነት ከተረከቡ በሃላ በከተማው እንደዚህ ያለ ከባድ ጥቃት ሲሰነዘር ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነም ተዘግቧል።

ሶቆችና የምግብ መደብሮች በመኪናው ላይ በተጠመደው ቦምብ ፍንዳታ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸውም ታውቋል።

ይህ መጠነ ሰፊ የቦምብ ጥቃት ለብዙ ሰው ህይወት ህልፈትና ለአካል ጉዳት ምክንያት ቢሆንም ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ሰአት ሃላፊነቱን የወሰደ የለም።

አንድ የአልሸባብ ከፍተኛ አመራር ኮማንደር በአዲፕሬዝዳንት ደጋፊዎች ላይ ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው ዛቻ መሰንዘራቸው ይታወሳል።

ለዚህም ይመስላል ለዚህ አሰቃቂ የመኪና ቦምብ ጥቃት አባዛኞች ጣታቸውን በአልሸባብ ድርጅት ላይ እየቀሰሩ የሚገኙት።

ፕሬዝዳንት መሃመድ አብዱላሂ በጥቃቱ የተጎዱትን ሰዎችንና ጥቃቱ የደረሰበትን ቦታ ጎብኝተዋል። ለደረሰው እልቂትም አልሸባብን ተጠያቂ ማድረጋቸውም ታውቋል።

ይህን ጥቃት የፈጸሙትን ለማጋለጥ መረጃ ለሰጠ ወይም ለጠቆመ ፕሬዝዳንቱ የአንድ መቶ ሺህ የአሜሪካ ዶላር (100,000$) የካሳ ሽልማት እንደሚሰጡም አስታውቀዋል።