የህውሃት አገዛዝ የየካቲት 12 የሰማዕታትን ቀን ሆን ብሎ እጅግ በቀዘቀዘ ሁኔታ እንዲከበር ማስደረጉ ተገለጸ

 

አባይ ሚዲያ ዜና በመርጋ ደጀኔ

ተገቢው ክብር ተነፍጎት ለይስሙላ የተከበረው የትላንቱ የየካቲት 12 የሰማዕታት ቀን አከባበር ብዙዎችን አሳዝኗል።

ከአንድ ቀን በፊት የተከበረውን የሕወሃት ምስረታን የሚዘክሩ መፈክሮችና ባንዲራ በሰማዕታት ሐወልቱ ላይ መቀመጣቸው የብዙዎችን ያበሳጨና ልብ የሰበረ እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል።

ይህ የዘንድሮው የየካቲት 12 የሰማእታት ቀን አከባበር በተለይ በግፍ የተጨፈጨፉትን ሰማዕታት የማይመጥን ነው ይላሉ፡፡

የካቲት 11ን የሚዘክሩ ባንዲራዎችና መፈክሮችን በየካቲት 12 ሰማዕታት ሐውልት ላይ ማኖርም አሳዛኝ
እንደነበረ ብዙዎች የተሰበረ ስሜታቸውን ሲገልጹ ተደምጠዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ የመታሰቢያ ስነስርዓቱ አከባበር እየተቀዛቀዘ ቢመጣም የዘንድሮው ደግም እጅጉን አሳዛኝ በሆነ መልኩ በግብር ይውጣና በሩጫ የተካሄደ እንደነበረም ታውቋል።

ፋሺስት ጣልያን የዛሬ 80 ዓመት የካቲት 12 ቀን 1929 ነበር በአዲስ አበባ እና በአካባቢዋ ዘር ከሐይማኖት ሳይለይ ከ30 000 በላይ ኢትዮጵያውያንን የጨፈጨፈው፡፡

ይህንን ጭፍጨፋም ለማስታወስ ፋሺስት ከተወገደ በኋላ ከ1934 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ ሰማዕታቱን በሚዘክረው ሐውልት ስር የመታሰቢያ ስነ ስርዓት ይካሄዳል።

ይህ የየካቲት 12 የሰማእታት ደማቅ ታሪክ አስተማሪነቱ ዘርፈ ብዙ ቢሆንም በአገራችን መልስ ለመስጠት ለከበዱትና አካራካሪ ለሆኑ አንዳንድ ክስተቶች ምላሽ ወይም ማስተማሪያ መሆን ይችል እንደነበረ ኢትዮጵያኖች በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች አስተያየታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።

የዛሬ ስማንያ ዓመት አዲስ አበባ ምን እንደተፈጠረ በታሪክ ወደ ሃላ መለስ ብለን በመቃኘት አሁን ለገጠመን ችግር መፍቻ መፍትሄ ለማግኘት ጥረት መደረግ እንዳለበትም የሚጠቁሙ አስተያየቶች ተበራክተዋል።

የነዚህን ንጹሃን ሰማእታት ታሪክ ማወቅ ፣ ማሳወቅ ፣ ቁምነገሩ እና አንደምታው ችላ እንዳይባል መጠነ ሰፊ ስራ መሰራት እንዳለበትም ተጠቁሟል።