የወርቅ መሸጫ መደብር ተቀጣሪ ኢትዮጵያዊ በአንድ አመት ልጁ ፊት ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ተገደለ

አባይ ሚዲያ ዜና በዘርይሁን ሹመቴ

የቴነሲ ግዛት በሆነችው ሜምፈስ በሚገኝ የወርቅ መሸጫ መደብር ተቀጥሮ የሚሰራ ኢትዮጵያዊ በስለት ተወግቶ መገደሉ ተዘገበ።

ኖሃ አሸኔ በመባል የሚታወቀው ይህ ኢትዮጵያዊ የሶስት ልጆች አባትና የቤተሰብ አስተዳዳሪ እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል።

42 አመቱ ኢትዮጵያዊው ኖሃ አሸኔ በሚሰራበት የወርቅ መሸጫ መደብር ባሳለፍነው ሃሙስ መገደሉ ታውቋል።

የአንድ አመት እድሜ ያለው ልጁ አባቱ በስለት ጀርባው ላይ ተወግቶ ሲገደል አጠገቡ እንደነበረም ተዘግቧል።

ፓሊስ ይህን ህጻን ልጅ ከአባቱ አጠገብ በደም ተነክሮ እንዳገኘው ገልጻል። የኖሃ አሸኔ ግድያ አሰቃቂ ሲሆን የአንድ አመት ህጻን ልጁ ፊት ማስክ ለብሶ ይህን ግድያ የፈጸመው ወንጀለኛ ምን አይነት የአውሬነት ባህሪ እንዳለው ያሳያል።

የአንድ አመቱ ህጻን በዚህ የዘረፋና የግድያ ወንጀል አካላዊ ጉዳት እንዳልደረሰበት ፓሊስ አረጋግጧል።

ይሁን እንጂ በስነ ልቦናውና በአይምሮው ውስጥ ግን ሊለካ የማይችል ውስጣዊ ህመም እንደሚጋረጥበት ሊታወቅ ይገባል።

ይህንን ከአውሬ ያልተናነሰ ድርጊት የፈጸመውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ለማዋል ፓሊስ ፍለጋውን እንደቀጠለ አሳውቋል።

በተጨማሪም ከወርቅ ቤቱ መደብር የተዘረፈ ሃብት ካለም ፓሊስ ምርመራ እያደረገ እንደሆነ መረዳት ተችሏል።

ይህንን ርህራሄ የሌለውን  አረመኔ ወንጀለኛ በተመለከት መረጃ ወይም ጥቆማ ካሎት በዚህ አድራሻና ስልክ ቁጥር Crime Stoppers at (901) 528-CASH በማሳወቅ ትብብሮን ይቻሩ ።

የአባይ ሚዲያ ጠቅላላ አባላት በወንድማችን ህልፈት የተሰማቸውን ሃዘን በመግለጽ ለመላ ቤተሰቡና ወዳጆቹ መጽናናትን እንመኛለን።

በጣም ጥሩ ሰውና ለቤተሰቡ ከፍተኛ ትኩረት ያለው ሰው እንደሆነ ኖሃ አሸኔን የሚያውቁት ሰዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።