በዚህ መንገድ ስለእምየ ሚኒሊክ ላውጋህማ ! (አሌክስ አብርሃም)

0
ከዚህ በመቀጠል  ዳግማዊ ሚኒሊክ ንጉሰ ነገስት ኢትዮጲያ ዘ እምነገደ ይሁዳ ለጦቢያ አገራችን ያስተዋወቋቸቀውን አበይት የስልጣኔ ቱርፋቶች ሞቅ ካለ ርግማን መሰል ስድብ ጋር እናቀርባለን ! ስድቡ ይሄን ሁሉ ስልጣኔ ትቶ የሆነ ያልሆነ ነገር እየለቃቀመ ለሚነጅሰን ነጃሽ ሁሉ መሆኑን ከወዲሁ እያሳሰብን እምየ ሚኒሊክ ለአገራችን አስተዋውቀዋቸው የተዘነጉ ጉዳዮች ካሉ እንዲጨመሩ በአክብሮት እንጠይቃለን !
እየው እንግዲህ አገርህ ኢትዮጲያ ከሚኒሊክ በፊት ከዚህ ከታች የተዘረዘሩትን አበይት ጉዳዮች አታውቃቸውም ……ብታውቃቸውም ደፍሮ ህዝቡ ጋር ባህሉ ጋ ኋላ ቀርነቱ ጋር እየተፋለመ ይበጅሻልና ተቀበይ ያለ መሪ አላጋጠማትም ነበር …ታዲያ እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብህ መይሳው ካሳ የስልጣኔን መብራት ጨለማዋ ምድር ላይ ሲያበራው እምየ ሚኒሊክ በዛ ጭላንጭል እየታገዙ ቦታ ቦታው ላይ ስልጣኔውን እያመጡ ማስቀመጣቸውን ነው ….አልገባህም እንዴ ….የራስህ ጉዳይ ተቀበል እንግዲህ ….
እየው 1901 ዓ.ም. —የምትሳፈጠው ሚኒሊክ ስልጡን ፖሊስ ሰራዊት ለአገርህ አስተዋወቀልህ ….ፖሊስ በዱላው ይዠልጥህና ! ካልዠለጠህ አይገባህም መቸም ! 1900 ዓ.ም.  አባትህ አንተን ሽኮኮ ብሎ  በእግሩ የአስራሰባት ቀን መንገድ  ሲሰጠስጥ   እምየ ሚኒሊክ አውቶሞቢል አስገባልህ ….ወዲያ አውቶሞቢል ይግጭህ ልታስብለኝ ነው አሁን ! ተረጋጋ ከረገምኩህማ በደንብ ነው ባቡር ይግጭህ ብየ አለበለዚያ ሚኒሊክ ባቡር የሚባል ነገር ማስገባቱን ትክዳለሃ !
1899 ዓ.ም.አራዊት ጥበቃ…..አራዊት ይብላህ ወዲያ ! እስቲ አስበው ዛሬ ጌቶችህ ሰው በሚያድኑበት ጊዜ ሚኒሊክ ያኔ ለአራዊት ጥበቃ መስሪያ ቤት ያቋቁም ነበር ! 1900 ዓ.ም ጋዜጣ ተመሰረተ …ይገዝጥህና ያባቴ አምላክ …ጋዜጣ ያኔ ተከፍቶ  ነው ዛሬ ኮማንድ ፖስትህ እያሳደደ የሚዘጋው ! ባንድ ስልክ ሄሎ ዝጉት የሚልልህ …ለነገሩ ስልክም የሚኒሊክ ቱሩፋት ነው ወዳጀ ….ዛሬ ተች ስክሪን ምን ስክሪን የምትለው ….1882 ዓ.ም  ሚኒሊክ ባይገለጥለት ኑሮ ተራራ ጫፍ ላይ ቁመህ ስማ በለው ትላት ነበር !
1898 ዓ.ም ፕላስቲክ …. ዛሬ የታሸገ ውሃ እየተጋትክ ስልጡኝ ነኝ የምትለው ሚኒሊክ ባስገባው የፕላስቲክ ቴክኖሎጅ ነው ….አለበለዚያ መሃል አዲሳባ ላይ ውሃህን በፎሌ ትጋታት ነበር ….ወላ በፍኝህ ለነገሩ በፎሌም ጠጣው በኮዳ የቧንቧ ውሃንም ሚኒሊክ እንዳስገባልህ እንዳትረሳ …..1886 ዓ.ም !!አለበለዚያ ወንዝ ለወንዝ ስትዳክር አተት ይፈጅህ ነበር … አሁን እንደጀመረህ ማለቴ ነው ! እማምላክን !!
1899 ዓ.ም.የጥይት ፋብሪካ…በሚኒሊክ ብሩህ ፍቃድ ተቋቋመ ….ዛሬ የምትፈራውም የምታስፈራራውም በሱ ነው …. ጥይት ይብላህና ልበልህ እንዴ …. 1900 ዓ.ም የሚኒስትሮች ሹመት…. ዛሬ የምትራኮትበት ስልጣን ያኔ ገና ሚኒሊክ ለህዝብ የምትጠቅም ከሆንክ ብሎ ያደራጀልህ ነው ! ይሄ ዛሬ በሱፍና በሚያብረቀርቅ ጫማ እየተጀነነ ታሪክ የሚንድ ሁሉ …ለነገሩ ጫማውንም ያስተዋወቀው ሚኒሊክ ነው ወዳጀ ….1887 ዓ.ም!!
1904 ዓ.ም  የመድሃኒት መሸጫ ሱቆች በሚኒሊክ ለህዝብ ፈውስ ተከፈተ …. እንግዲህ ስለመዳኒት ካወራን አይቀር ‹‹በሽታውን ያልተናገረ መድሃኒት የለውም›› እንዲል ብሂሉ ቆይ አንተ ሚኒሊክ ጋ እንዲህ ያያዘህ በሽታ ምንድነው ወዳጀ ….አይዞህ ተናገር አትፍራ በሽታህን ተናገር ትታከማለህ …ውይ ሳልነግርህ ….ሆስፒታልም በሚኒሊክ ዘመን ነው የተከፈተው ….ከምር !! 1890 ዓ.ም. !!
እና ስታገግም ምርጥ ምሳ …..አለ የሚባል ሆቴል እየተገባበዝን ይሄን ዝባዝንኬ ልዩነታችንን ጥለን አንድነትን የአገር ፍቅርና ስልጣኔን እንጠነስሳለን ….ሆቴል ስል ምን ትዝ አለኝ መሰለህ …..ሆቴልንም ያስጀመረው …..እምየ ሚኒሊክ ነው ! 1898 ዓ.ም!እንደውም ልንገርህ ገንዘብን የብር ኖትን ብትል ባንክን ብትል ሚኒሊክ ነው ቱ ብሎ ቁጥር ቁጥር እያደረገ ያሳየህ ነው የምልህ 1886 ዓ.ም….አለበለዚያማ እስካሁን ሱሪ ለመግዛት አሞሌ ጨው  ተሸክመህ  ነበር ኤድናሞል ቡቲክ ምናምን የምትሄደው….. በሞትኩት …ኤድናሞል ስል ሲኒማው ታወሰኝ ….ጓዴ ሲኒማንም ሚኒሊክ ነው ለካ ያስገባልህ ….ስሪ ዲ ብትል ሰቨን ዲ ….ዲ ነው የጨመረው ሌላ ታምር የለውም አንበሳየ መሰረቱ ሚኒሊክ ነው ! !
     እና ይሄን ሁሉ ነገር አገርህ ላይ ያስገባልህ ሚኒሊክ ነው ….አገሬ የት ነው …ትል ነበር ቅኝ ግዛት ገዝተው ቢወቅሩህ ኑሮ ….ግን ሚኒሊክ ክተት ብሎ አባትህንና አባቴን አሰልፎ ይሄው የምትነታረክባት ሲደላህም የምትንፈላሰስባት አገር አተረፈልህ …..ጓዴ ! ለዛ ነው አድዋ የሚከበረው !! ገባህ አይደል …ካልገባህ ትምህርት ቤት ግባ ….ትምህርት ቤትንም የመሰረተው ሚኒሊክ ነው አልማርም ካላልክ ማለቴ ነው….ሂሂ!