የሒዩመን ራይትስ ወች (HRW) ሕወሐት ለሕዝብ የገባዉን ቃል አጠፈ ሲል ከሰሰ

አባይ ሚዲያ
ናትናኤል ኃይለማርያም

የዓለም አቀፍ የሰዉ ልጆች መብት በምሕፃረ ቃል (HRW) በመባል የሚታወቀዉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የወያኔን ገዥ ቡድን በኢትዮጵያ ስላለዉ የፖለቲካ ዉጥረት እና አለመረጋጋት ለማርገብ የገባዉን ቃል እንደልማዱ መካዱን አጋለጠ።

ሒዩመን ራይትስ ወች በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ቀዳሚ የሆኑት እና በአካባቢዉ ጥናት ያካሔዱት ፍሌክስ ሆርኔ በቅርቡ እንደገለፁት የተቃዋሚ የፖለቲካ መሪ የሆኑትን ዶ/ር መረራ ጉዲናን በፈጠራ ክስ መስርቶ ወደ ወህኒ የጣላቸዉን በመግለጽ እኝህ የ60 ዓመቱ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ አመራር በሃሰት በሽብርተኛ ወንጀል በመክሰስ ማዕከላዊ በሚገኘዉ የማሰቃያ ቦታ ስቃይ እየተቀበሉ እንደሆኑ ገልፆ ከሳቸዉ ጋርም በዚሁ የፈጠራ የሽብርተኛ ክስ የተመሰረተባቸዉ ሌሎች በዉጭ አገር የሚገኙ የተቃዋሚ የሚዲያ ተቋማትና የፖለቲካ ድርጅቶች እንዳሉም አስታዉቋል።

ከነዚህ የዉጭ የሚዲያ ተቋማትና ድርጅቶች ዉስጥ ኢሳት እና የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና በተጨማሪም የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክን ያካተተ እንደሆነ ታዉቋል።

የወያኔዉ ገዢዉ ቡድን ለአገሪቷ ዘላቂ የሆነ ሰላምን ከማምጣት ይልቅ እየወሰዳቸዉ ያሉት እርምጃዎች በምንም መልኩ አግባብ ያልሆነ እንደዉም ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ህጋዊነት በሌለዉ አካሔድ መሰረተ ቢስ ክሶችን በመክሰስ የሰላማዊ ትግል ማካሔጃ መንገዶችን ሙሉ በሙሉ በሚያስብል በማጥበብ ዉጥረቱን የበለጠ እያናረዉ መሆኑንም በዘገባዉ አስፍሯል።

መንግስት የሕዝቡን ጥያቄ የሆነዉን ትክክለኛና መሰረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎችን ምላሽ በመስጠትና በግፍ በየማጎሪያ ቤት ያጎራቸዉን የፖለቲካ መሪዎችና ጋዜጠኞችን በመፍታት ህዝቡም መሰረታዊ የዲሞክራሲ መብቱን እንዲጠቀም በመፍቀድ ፈንታ መንግስት ራሱን በጥልቅ ተሐድሶና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ዉይይት አደርጋለሁ በሚል ከንቱ ዉዳሴ ላይ መሆኑንም ገልጿል።

በተያያዘ ዜናም የወያኔዉ ገዢ ቡድን የሒዩመን ራይትስ ወች በኢትዮጵያ ዉስጥ የተካሔደዉን ሕዝባዊ አመፅ ከጀርባ ሆኖ ይደግፍ ነበር በማለት የከሰሰ ሲሆን ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገ/የሱስ በኦክቶበር 2016 በፃፈዉ ርዕስ ሒዩመን ራይትስ ወች በኢትዮጵያ የሚካሔደዉን አመፅ ያበረታታሉ በአገሪቷም ዉስጥ እሳት እየለኮሱ ናቸዉ በማለት መጻፉን ያስታወሰዉ ሒዩመን ራይስት ወች ዶ/ር ቴድሮስ ለፍሌክስ ሪፖርት ምላሽ በፃፉበት ጊዜ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር በጣም ተባብሶ የገዥዉ ቡድን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ገሐድ ሆኖ እያለ ቴድሮስ ግን ይህን እዉነታ ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልነበሩና ችግሩን ሒዩመን ራይትስ ወች ላይ ለማሳበብ መሞከራቸዉን ሒዩመን ራይትስ ወች በዘገባዉ አስታዉቋል።