የአባይ ግድብ ጠባቂ የሆነ አንድ ም/ሳጅን ፖሊስ ተገደለ

አባይ ሚዲያ ዜና
ናትናኤል ኃይለማርያም

በአባይ ግድብ ጉባ አካባቢ የሚገኘዉ ከአመታት በፊት የተሰራዉ የአባይ ድልድይ ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግለት እንደነበር ሲታወቅ ግድቡን ጠባቂ ከሆኑት የፌደራል ፖሊስ አባል ዉስጥ የም/ሳጂን ማዕረግ ያለዉ በጥበቃ ላይ ተሰማርቶ እያለ ማንነታቸዉ ባልታወቁ ሰዎች ተገሎ መገኘቱ ታዉቋል። ይኽንን ግድያ ማን እንደፈፀመዉና እንዴት እንደ ተገደለም እስከአሁን ድረስ የታወቀ ነገር አለመኖሩ የገዥዉ ሕዉሐት መደብ ዉስጥ ከፍተኛ ፍርሃት ነግሷል።

በአካባቢዉ የግድቡ 6ኛ አመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ ጥብቅ ቁጥጥርና ፍተሻ እየተደረገ እንደሆነም ሲታወቅ ከዚህ ሁሉ ፍተሻ የሳጅኑ መሞት በአካባቢዉ ከፍተኛ ዉጥረትና ድንጋጤ መፍጠሩ የደረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።  በአባይ ግድብ በቅርብ እርቀት ከሚገኙት የሠራተኞች መኖሪያ ካምፕ አንስቶ በአካባቢዉ የሚገኙትን ነዋሪዎች በሙሉ ከፍተኛ ወከባ እና እንግልትም እየደረሰባቸዉ ይገኛል።

ለዚህ ምክንያት ነዉ ተብሎ በገዥዉ የሕዉሐት ቡድን የሚነገረዉ የሻቢያ ተላላኪዎች እና የቤሻንጉል ጉምዝ ሕዝቦች ነፃ አዉጪዎች በአካባቢዉ ሰርገዉ ገብተዋል የሚል ሲሆን ከነዚህ ሰዎች ጋር ምንም አይነት ግኑኝነት የሌላቸዉን ንፁሐን ዜጎችን በማፈን ወደ ማሰቃያ ይዘዋቸዉ እንደሚሔዱም የደረሰን መረጃ ያሳያል።

በቤንሻጉል ጉምዝና በሱዳን ጠረፍ አካባቢ በገዥዉ የሕዉሐት ወታደሮችና በነፃነት ኃይሎች መካከል ከቀናት በፊት የተኩስ ልዉዉጥ እየተደረገ መሆኑን ከስፍራዉ ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል።

በአልመሃል እና በማንኩሻ ታጣቂ ቡድኑን ትደግፋላችሁ እየተባለ በአካባቢዉ በሚኖሩ ነዋሪዎች ላይ የሕዉሐት ቡድን በስፋት እንግልትና ወከባ እየተደረገ መሆኑንና ይኽንንም ተከትሎ በርካታ ሰዎች ታፍሰዉ ወደ ማጎሪያ ቤት መወሰዳቸዉን ከስፍራዉ የደረሰን መረጃ ያሳያል።