የኢሕአዴግ መንግሥት፡-
አጠቃላይ የጤና ምርመራ ያስፈልገዋል
“ሰርቪስ” መደረግ አለበት

በአሁኑ ጊዜ ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲም ሆነ ስልጣን ላይ እንዳለ መንግሥት እያደረገው ያለው እንቅስቃሴ የጤና ጉድለት ምልክቶች እየታዩበት ነው፡፡ እየታዩ ባሉት የጤና ጉድለቶች ወይም የበሽታ ምልክቶች በአግባቡ የተሟላ ምርመራ ተካሂዶባቸው ተገቢውን ሕክምና ካላገኙ ለራሱም፣ ለአካባቢውም፣ ለአገሪቱም ጠንቅ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ወይም ደግሞ በመካኒካል ቋንቋ እንነጋገር ከተባለ ኢሕአዴግ “ሰርቪስ” መደረግ አለበት፡፡ “ለቦሎ” ተብሎ ሳይሆን ሳይዝግና ሳይቆም መሽከርከር እንዲችልና በሌሎች ተሽከርካሪዎችና መንገዶች ላይም ጉዳት እንዳያደርስ ነው፡፡

አጠቃላይ አካሉ ሲታይ የኢሕአዴግ መንግሥት በአንድ ዓይነት ጭንቅላትና የነርቭ ሥርዓት የሚንቀሳቀስ አይመስልም፡፡ አንዱ አካሉ “ነቃ” ያለ እንቅስቃሴ ሲያሳይ፣ ሌላኛው ደግሞ “መደንዘዝ” ያለበት ይታይበታል፡፡ አንዱ አካሉ “የመማሰን” ምልክት ሲያሳይ፣ ሌላው ደግሞ “የማበጥ” ምልክት ይታይበታል፡፡ አንዱ አካሉ ደግሞ “ሲንቀጠቀጥ” ይስተዋላል፡፡ የጤና ሥጋቱ የተፈጠረውም ይህ በየዕለቱ መታየት ስለጀመረ ነው፡፡

አካላቱን አንድ በአንድ እንመርምር ከተባለም ለመሆኑ የኢሕአዴግ መንግሥት ዓይን “ያያል ወይ” የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ በቅርቡ ያሉትን የጎሉ ነገሮች ማየት ሲሳነው እየተስተዋለ ነው፡፡ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ “ማንበብ” ሲያቅተው እየታየ ነው፡፡ ጭራሽ አያይም ተብሎ እንዳይደመደም ደግሞ፣ አልፎ አልፎ ዓይኑ ተከፍቶ ትኩር ብሎ አንድን ነገር ሲያይ ይስተዋላል፡፡ ቢሆንም ግን የተሟላ የዓይን ምርመራና የእይታ ማስተካከያ ሕክምና ያስፈልገዋል፡፡

ጆሮውስ? የኢሕአዴግ ጆሮ ይሰማል? ብዙ ጊዜ አጠገቡ ሆኖ የሚጮህን ሰው ድምጽ እንኳ የሚሰማ አይመስልም፡፡ የአንድ ሰው ጩኸት ብቻ ሳይሆን የብዙ ሕዝብ ጩኸትና ለቅሶ መስማት ሲሳነው ይስተዋላል፡፡ ጭራሽ ጆሮው አይሰማም እንዳይባል ደግሞ አንዳንድ ጊዜ በሹክሹክታና በለሆሳስ የሚነገሩትንም ሲሰማ ይታያል፡፡ የራሱ ንግግሮችና ዘፈኖች ሲሆኑ ደግሞ በልዩ ትኩረትና አድናቆት ሲያዳምጣቸው ይስተዋላል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የራሱንም የሌላውንም ማዳመጥ ያቅተዋል፡፡ ከ”ፍንዳታ” በታች ያለው ድምፅ ሁሉ አልሰማ ሲለውም ያጋጥማል፡፡ የጆሮ ችግሩን ለማወቅና ለመፈወስም ሙሉ ምርመራ ያስፈልገዋል፡፡

አንዳንዴ ለመሆኑ ኢሕአዴግ አለ ወይ? እስኪባል ድረስ የልቡ ምት ፀጥ ሲል ይስተዋላል፡፡ ምቱ ስለቆመ ሕይወት ቆመ እንዳይባል ደግሞ በተወሰነ ጊዜ የደም ግፊቱ ጨምሮ የልብ ምቱ ድው ድው ሲል ከሩቅ የሚሰማበት ጊዜ አለ፡፡ አንዳንዴ የልብ ምቱ ግራፍ ሲታይ ከፍና ዝቅ ማለቱ አሳሳቢ ነው፡፡ “ልበ ሙሉ” ነው ለማለት በጭራሽ አይቻልም፡፡ አሳሳቢ ነውና የተሟላ ምርመራና ሕክምና ያስፈልገዋል፡፡

“የአንጀቱ” ነገርም እንደዚሁ ነው፡፡ አንጀቱ ጤናማ ነው ተብሎ ሲነገርለት የነበረው ኢሕአዴግ እዚህም እዚያም የአንጀት መላላጥ እየታየበት ነው፡፡ “አቃጠለኝ” ሲልም እየተሰማ ነው፡፡

ሆዱም በአጠቃላይ ችግር እየታየበት ነው፡፡ ብዙ ትልና ተውሳክ ሆዱ ውስጥ እንዳሉና ደሙን እየመጠጡት እንደሚገኙ ይነገራል፡፡ እንዲያውም ኢሕአዴግ ትሎችን ተሸክሞ መኖር ይወዳል እየተባለም ይነገራል፡፡ መድኃኒት ሲነገረውና ሲሰጠውም አይወስድም፣ ሊያጠፋቸው አይፈልግም፡፡ በተለይ በተለይ ግን ኢሕአዴግ “ሆደ ሰፊ” ነው እያሉ ሲያሞግሱት የነበሩ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የትርጉም ልዩነት አለው ብለው “ሆደ ሰፊ” መሆኑ ቀርቶ “ሆደ ትልቅ” ሆኗል እያሉ እየወቀሱት ነው፡፡ የሆድ ነገርም ልዩና የተሟላ ምርመራ ያስፈልገዋል፡፡

የኢሕአዴግ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ የሚቆጣጠርና የሚያጣራ ጉበትና ኩላሊት የለውም እየተባለም ይነገራል፡፡ ማሳያ ምልክቶቹም በርካታ ናቸው፡፡ የሚያጣራ ጉበትና ኩላሊት ቢኖረው ኖሮ እንዲህ ባልሆነ ነበር የሚያሰኙ ነገሮች እየበዙ ነው፡፡ ጠጠሮች እዚህም እዚያም እየተፈጠሩ በቀላሉ ፍሰት ሊታይበት የሚገባ ነገር ሥቃይና መከራ ሲያጅበው እየታየና እየተደመጠ ነው፡፡ የሀሞት ከረጢትን በሚመለከትም ሀሞት እንዳለው ባይካድም የሀሞቱ መጠን፣ የከረጢቱ ስፋትና ጥበት አጠያያቂ ሆኗል፡፡ የተሟላ ምርመራ ያስፈልገዋል፡፡

ሳንባ አካባቢም ችግር አለ፡፡ “የመተንፈስ” ችግር እንዳለና “እፍን እፍን” የሚያደርግ በሽታ እንዳለ ግልፅ እየሆነ ነው፡፡ በመተንፈሻ ሥርዓት ዙሪያም ሰርቪስ ያስፈልገዋል፡፡

አፍንጫውም አያሸትም፡፡ አፍንጫው ከሩቁ ያሸታል የሚል እምነት በብዙዎች ዘንድ ነበር፡፡ አሁን ግን ከሩቁ ነገሮችን “ማሽተት” ተስኖታል እያሉ ብዙዎች ማውራት ጀምረዋል፡፡

ምላሱም “የተቆላለፈ” ነው፡፡ የጥርሱ ጤንነትም አይታወቅም፡፡ “አኝኮ ለመዋጥ” እንጂ ለፈገግታ ሥራ ላይ ሲውል አይስተዋልም፡፡ እዚህም የተሟላ ምርመራ ያስፈልጋል፡፡

የኢሕአዴግ ጉልበት፣ ወገብ፣ እግር ጤነኞች ናቸው እየተባለ ይነገርለት ነበር፡፡ እውነትም ነበር፡፡ መጓዝ፣ መሄድ የሚወድ እግር ስላለው ነው መንገድና ድልድይ ሰርቶ የማይታክተው፡፡ ይመሰገናልም፡፡ ነገር ግን ወገቡ መንቋቋት ጀምሯል፡፡ እግሩም እየተላላጠ ነው፡፡ ከመንገድ ብዛት መላላጡ የሚጠበቅ ቢሆንም መላላጥ ያጋጠመኝ ከውጭ በመጣ ጫማ ምክንያትና ከጫማ ጋ መምጣት የነበረበት ካልሲ ስላልተሰጠኝ ነው የሚል ምክንያት በኢሕአዴግ መቅረቡ ግን ቅሬታን አስከትሏል፡፡ የኢሕአዴግ ጭንቅላትም “በውጭ” ያመካኛል ወይ አሰኝቷል፡፡ ልዩ የጤና ምርመራ የሚፈለግበት አንድ አብይ ምክንያትም ይኸው ነው፡፡

እጅና ቅልጥም ዙሪያም ችግር ይታያል፡፡ ዋናው ችግር ተብሎ እየተነገረ ያለው ግን ቅልጥሙ እንዳለ ቢሆንም እጅ ለመስጠት የሚዘረጋ እጅ መሆኑን እያቆመ፣ “ለመቀበል ብቻ” የሚዘረጋ እጅ ሆኗል የሚል ወቀሳ ነው፡፡ እዚህም የተሟላ ምርመራ ያስፈልጋል፡፡

“አንገት የተፈጠረው አዙሮ ለማየት ነው” የተባለለት አንገት በበሽታ ምክንያት አዙሮ ማየቱን አቁሟል፡፡

የኢሕአዴግ መንግሥት በሽታ ብዙ መዘርዘር ይቻላል፡፡ ምልክቶቹን እያዩ ከመገመት ይልቅ የተሟላ ዘመናዊ ምርመራ ማድረጉ ይሻላል እንላለን፡፡ በሽታው ካንሰር ወይስ አንስተኛ በሽታ ነው? በሽታው “አይምሬ” ነው ወይስ የሚፈወስ ነው? በሽታው በመርፌና በኪኒን ይፈወሳል ወይስ ቀዶ ሕክምናን ይጠይቃል? የሚለው የሚታወቀው የተሟላ ምርመራ ሲካሄድ፣ ኢህአዴግም ለምርመራው ፈቃደኛ ሆኖ ሲገኝና ሲቀርብ ነው፡፡ በማያጠራጥር ሁኔታ ግን በርካታ የበሽታ ምልክቶች አሉና ምርመራው በአስቸኳይ ይካሄድ፡፡

ስለ ኢሕአዴግ የጤና ችግር ለማውራት የተገደድነው ለምንድን ነው? የጤና ችግር ያለበት ገዢው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ገዢውም ተቃዋሚውም ችግር አለበት፡፡ ሁሉም የተሟላ ምርመራ እና “ሲቲ ስካን” ያስፈልጋቸዋል፡፡

ሆኖም ግን ስልጣን ላይ ያለ ፓርቲ አገርንና ሕዝብን የመምራት ኃላፊነት ስላለበትና በገዢ ፓርቲ የጤና ችግር ምክንያት ከሰባ ሁለት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ጤናና ኅልውና ለአደጋ ሊጋለጥ ስለሚችልና አሁንም እየተጋለጠ ስለሆነ ነው በመንግሥት ጤና ላይ ያተኮርነው፡፡

ስለሆነም፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ሲባል የተሟላ የጤና ምርመራና ሰርቪስ በአስቸኳይ!

 

Source: Reporter

…………………………………….

Return Back to: ABBAY MEDIA FRONT PAGE

4 COMMENTS

  1. The sickness has spread. There is no cure for it. The only choice EPRDF has is to die agonizing death. This terrible sickness is going to follow EPRDF to its grave and beyond. May god have mercy on its soul.

    FREE BIRTUKAN

  2. As far as I’m Concerned TPLF is Ruling Ethiopia Since 1991—the name EHADEG is te name of THE MASk that TPLF Cover its CRIME or to fool the ppl and to usethem as a rubber Stamp

  3. አገር የሚመራ አገር ወዳድ መቼ ጠፋና ነው፣ ኢሕአዴግን የምንጠጋግነው። ለምን የያዘው በሸታ በዚያው አይወስደውም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here