የብርታኒያ የጦር መኮንን በሰሜን ኬኒያ በታጣቂ ሚሊሻዎች ተገደለ። በድኑን ለማስመለስ የተደረገውም ሙከራ እንዳልተሳካም ተገለጸ

አባይ ሚዲያ ዜና ዘርይሁን ሹመቴ

ለብዙ አመታት የቱሪስት መስብ ሆና የቆየችው በሰሚናዊ ኬኒያ ክልል የምትገኘው ላይኪፒያ የምትባል ቦታ የጎሳ ጦርነትን እያሰተናገደች ከቆየች ወራቶች እንዳለፏት ለማወቅ ተችሏል።

በዚህ ላይኪፒያ የሚኖሩ ህዝቦች በሌሎች ጎሶዎች ተወረው እየተገደሉ እንደሆነም ተዘግቧል። ከወራሪ ጎሳዎች መካከል የማሳይ፣የሳምቦሮ እና የፖኮት ጎሳዎች እንደሚገኙበትም ታውቋል።

እነዚህ ጎሳዎች በሚሊሺያ የተደራጁና ከመንግስት ፋብሪካ የሚመረትን የጦር መሳሪያ በከፍተኛ ደረጃ የታጠቁ መሆናቸው ተረጋግጧል።

በርካታ ኬኔያዊያኖችም በነዚህ ሚሊሻዎች መገደላቸውና መኖሪያቸውን ለቀው መሰደዳቸውም ሲዘገብ እንደነበረ ለመረዳት ተችሏል።

ባሳለፍነው ቅዳሜ ማምሻ እነዚህ ሚሊሻዎች በሰሜናዊ ኬኒያ በወሰዱት የጥቃት እርምጃ ብዛት ያላቸውን ቤቶችን በማቃጠል ሙሉ በሙሉ አውድመዋል።

እነዚህ የተቃጠሉትን መንደሮች ለመመርመር ወደ ቦታው የተጓዘው ትሪስቲያን ቮርስፓይ የተባለ የብርታኒያ የቀድሞ የጦር መኮንን እሁድ እለት በሳምቦሮ ሚሊሻዎች በጥይት ተመትቶ መገደሉ ተረጋግጧል።

ይህ የጎሳ ግጭት እንዲህ ከተፋፋመበት ሶስት ማይሎች እርቀት በሚገኝ ቦታ ወደ 250 የሚሆኑ የኬኒያ መከላከያ ሰራዊት ቢሰፍሩም የጎሳዎቹን ጥቃት ለማስቆም ምንም አይነት ጥረት እያደረጉ እንዳልሆነ የሟች ቤተሰቦች ለሚዲያ ገልጸዋል።

የመኮንኑን በድነ ስጋም በሚሊሺያዎቹ ቁጥጥር ውስጥ ሲሆን ከሚሊሺያዎቹ እጅ ለመውሰድ የተደረጉት ሙከራዎች ውጤታማ እንዳልነበሩም ቤተሰቦቹ እየተናገሩ ይገኛሉ።

ሟች መኮንኑ ከሌሎች ኬኒያዊያን ጋር በመሆን በሰሜናዊ ክልል የሚገኙ የእርሻ መሬቶችንና የቱሪስት መስህብ ቦታዎችን ለአመታት ከወራሪዎች ሲከላከል እንደነበረ አብረውት ሲሰሩ የነበሩት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ይህ የላይኪፒያ ክልል አብዛኞች የብርታኒያውያን ንጉሳውያን ቤተሰቦች ለእረፍትና ከሚመርጧቸው ቦታዎች አንዱ እንደሆነም ዘገባዎች ያመለክታሉ።

የብርታኒያ መንግስት በአፍሪቃ ቀንድና በአከባቢው ለሚያደርጋቸው የሚሊተሪ ወይም የጦር ኦፕሬሽኖች የሚሆኑ ወታደሮችን ከ100 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ በማድረግ በዚሁ ቦታ እንደሚያሰለጥንም  ሪፓርቶች ያሳያሉ።

የኬኒያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ለብዙ ኬኒያዊያን ሞት ሰበብ የሆነውን የዚህን ክልል ግጭት ለማስቆም ምንም ያህል ጥረት አለማድረጋቸው ለከፍተኛ ትችት ዳርጓቸዋል።

ሚሊሻዎቹ ከመንግስት ባለስልጣናትና ከፓርላማ አባላት ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው የሚባል ጥርጣሬ ተበራክቷል። ይህም እውን ከሆነ የሰሜናዊ የኬኒያ ክልል የወደፊት እጣ እጅግ አስጊ ሊሆን ይችላል ተብሏል።

በሚቀጥለው ጥቅምት በኬኒያ ብሄራዊ ምርጫ እንደሚደረግ የወጣው የጌዜ ሰሌዳ ያሳያል።

የ2007 እኤአ ብሄራዊ ምርጫን ተከትሎ በብዙ ኬኒያዊያን ላይ የጭፍጨፋና የግድያ ወንጀል መፈጸሙ ይታወሳል።

በዚህም የዘር ማጥፋት ወንጀል ፕሬዝዳንት ኬኒያታ ለአለም አቀፉ የሄግ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተደረገው ሙከራ በመረጃ አለመሟላት በ2014እኤአ ውድቅ ሊሆን ችሏል።

ፕሬዝዳንት ኬኒያታ የብርታኒያው መኮንን በተገደሉበት በዚህ በሰሜናዊ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት ጣልቃ መግባት ያልፈለጉት ምን አልባት በምርጫው ወቅት አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያመጣባቸው ፈርተው ነው የሚሉ አስተያየቶችም እየተሰነዘሩ ይገኛሉ።

የብርታኒያ መንግስት በበኩሉ በዜጋው መገደል የተሰማውን ሃዘን በመግለጽ የኬኒያ መንግስት ሰላም በክልሉ እንዲሰፍን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።