የወያኔ አገዛዝ አገሪቷን ወደ ዘር ማጥፋትና እርስ በእርስ ጦርነት እየመራት እንደሆነ አንድ የካናዳ የፓርላማ አባል መንግስታቸውን አሳሰቡ (Video)

አባይ ሚዲያ ዜና ዘርይሁን ሹመቴ

የካናዳ ፓርላማ አባል የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያኖች ላይ እየፈጸመ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማስቆም የአገራቸው መንግስት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዳለበት አሳወቁ።

የካናዳ  መንግስት የውጭ እርዳታ በከፍተኛ ደረጃ ከሚለግሳቸው አገሮች መካከል በዋናነት የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ እንደሆነች የፓርላማው አባል ክቡር ቦብ ዚመር ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ስለነገሰው  የፓለቲካ ውጥረት ከእሳቸው በተጨማሪ በአሜሪካም በኮንግረስ ተመራጭ በሆኑት በክሪስ ስሚዝም ለውይይት እንደ አጀንዳ ተነስቶ እንደነበረም ለፓርላማው አባላት አሳውቀዋል።

የካናዳ መንግስት በህውሃት አገዛዝ ላይ ጠንከር ያለ አቋም መያዝ እንዳለበትም የፓርላማው አባል ቦብ ዚመር አስረድተዋል።

የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያኖች ላይ እየፈጸመ ስላለው ልክ ያጣ የመብት ረገጣ መንግስታቸው ስጋቱን በይፋ መግለጽ ብቻ በቂ እንዳልሆነ የጠቀሱት ቦብ ሲመር ይልቁንም እውነተኛ ለውጥና መሻሻል በኢትዮጵያ እንዲመጣ የካናዳ መንግስት ጥረትቱን መቀጠል እንዳለበትም አሳስብዋል።

አገዛዙን የሚተቹ፣ የሚቃወሙ አሊያም የማይደግፉ ኢትዮጵያውያን የሚደርስባቸውን ስቃይ፣  ስደትና እስራት ቦብ ዚመር ለፓርላማው ያስረዱት በፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ላይ የደረሰውን እስራትና ክስ እንደ ምሳሌ በመጥቀስ ነበረ።

የአገዛዙ ታጣቂዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፈኞችን መግደላቸውን እኚህ የፓርላማ አባል ሲናገሩም ተደምጠዋል።

ከኢትጵያ ህዝብ የደረሰበትን ተቃውሞ በሃይል ለመቆጣጠር ባወጣው የስድስት ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ንጹሃን ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውንም አክለው ተናግረዋል።

ከ88 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ይህን የአገዛዙን ግፍና ግድያ በመሸሽ ለስደት እንደተዳረጉም ቦብ ዚመር ለፓርላማው አሳውቀዋል።

የካናዳ መንግስት በኢትዮጵያኖች ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ ለማስቆም ጥረት ካላደረገ የህውሃት አገዛዝ ኢትዮጵያን ወደ ዘር ማጥፋት እና እርስ በእርስ ጦርነት ሊመራት እንደሚችል ቦብ ዚመር አሳስበዋል። 

 ቪዲዮውን ለማየት እዚህ ይጫኑ