አማራ ክልል መምህራን የስራ ማቆም አድማ ጀመሩ

አባይ ሚዲያ ዜና መርጋ ደጀኔ

 
በአማራ ክልል በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች የተጀመረው የመምህራን የስራ ማቆም አድማ እንደቀጠለ ነው ብዛት ያላቸው መምህራን ታስረዋል።
 
ለመንግስት ሰራተኞች የተደረገው ሃገራዊ የደመወዝ ጭማሪ መምህራንን አለማካተቱ ተገቢ አይደለም በማለት የተነሳው የመምህራን የስራ ማቆም አድማ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ በአንዳንድ ወረዳዎች ከሶስት ቀናት በፊት የተጀመረ ሲሆን ተቃውሞውን በሌሎች ወረዳዎች የሚገኙ መምህራን በመቀላቀላቸው በክልሉ በመምህራን ላይ እስራትና ማዋከብ እየደረሰባቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
 
በምዕራብ ጎጃም ዞን በደጋ ዳሞት በቋሪት በደንበጫ በአዴት በጎንጅ ቆለላ ወረዳዎች የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውንና መምህራንም እየታሰሩ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡  በዳጋ ዳሞት ወረዳ ከሃያ በላይ መምህራን በወረዳው ከሚገኙ የተላያዩ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በአዴት ሰባት መምህራን መታሰራቸውን ምንጮች ገልፀዋል፡፡
 
የስራ ማቆም አድማውን በምስራቅ ጎጃም ዞን እነማይ ብቸና እነብሴ ሳር ምድር መርጦ ለማሪያም ስናን ሁለት እጁ እነሴ ሞጣ ወረዳ የሚገኙ መምህራን መቀላቀላቸውንና መምህራንም እየታሰሩ መሆኑን ተሰምቷል፡፡
 
በብቸና ከተማ በላይ ዘለቀ መሰናዶ ትምህርት ቤት መምህራን በጋራ ቃለ ጉባዬ በመያዝ አድማውን ማድረጋቸውንና በመርጦ ለማሪያም 18 መምህራን መታሰራቸውን ሌሎችም ከፍተኛ ማዋከብ እየደረሰባቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
 
በደብረ ወርቅ ከተማ በደብረ ወርቅ 2ኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ ሶስተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን አስካሁን ድረስ አራት ወንድና ሁለት ሴት መምህራን መታሰራቸውን ታውቋል፡፡
 
በተለይ በጎጃምና በጎንደር አንዳንድ መምህራን አድማ አስነስታችኋል በሚል እየታሰሩ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። አድማው ከደሞዝ ማስተካከያ የተያያዘ ነው ቢባልም አጠቃላይ የነጻነት ጥያቄን ያዘለ መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ።