ወያኔ አስመዘገብኩ ያለው የፈጣን እድገት እውነታ የረፒ የቆሻሻ ናዳ ፍንትው አድርጎ እንደሚያሳይ ዘዋሽንግተን ፖስት ዘገበ

አባይ ሚዲያ ዜና ዘርይሁን ሹመቴ

ዘዋሽንግተን ፓስት ጋዜጣ በወያኔ አገዛዝ የምትገኘው አገራችን ኢትዮጵያ በአስጨናቂ መንገድ ላይ እንዳለች ያስነበበው በረፒ ቆሼ መንደር ህይወታቸው ያለፉት ሰዎች በትንሹ 113 መድረሱን በዘገበበት ሪፓርቱ ላይ ነው።

ህዝቡ አገዛዙን በመቃወሙ የደረሰበት ግፍ፣ በእሬቻ አደጋ የደረሰውን እልቂት፣ በቅርቡ የኮሌራ ወረርሽ በአገሪቱ መከሰት፣ እንዲሁም ከአምስት ሚሊዮን በላይ ህዝባችን ለድርቅና ለረሃብ መዳረግ ከ113 ወገናችንን ከቀጠፈው የረፒ ቆሼ አደጋ ጋር በመደመር የኢትዮጵያ አገራችንን ምጥ ዘዋሽንግተን ፓስት በጋዜጣው አስነብቧል።

አገሪቷ በአፍሪቃ በፍጥነት እያደጉ ከሚገኙ አገራት መሰለፏን የዘገበው ይህ ጋዜጣ ይህን እድገት በአፍሪቃ መዲና በሆነችው በአዲስ አበባ በተሰሩት ሰማይ ጠቀስ ፎቆች መገንዘብም እንደሚቻል አስነብቧል።

ልባችንን ሰብሮ ወገናችንን በሞት የቀጠፈው የረፒ ቆሼ ክስተት ግን የወያኔ አገዛዝ አስመዘገብኩ የሚለውን የእድገት ደረጃ ለአለም ፍንትው አድርጎ ያጋለጠ መሆኑን ይህ ጋዜጣ ገልጻል።

ከረፒ የቆሻሻ ክምር ከሚለቃቅሙት ቁሳቁስና ምግብ የእለት ተእለት ኑሯቸውን የሚገፉ እጅግ ብዙ ኢትዮጵያንም በዚችው የአገሪቷን እድገት ትመስክራለች በምትባለው አዲስ አበባ  እንዳሉ ጋዜጣው አስነብቧል።

ለዚህ ወገናችንን ለቀጠፈው የረፒ የቆሻሻ ክምር ናዳ ተጠያቂው አገዛዙ እንደሆነ አምኒስቲ እንተርናሽናል መክሰሱን ዘዋሽንግተን ፓስት በጋዜጣው  አስፍሯል።

የረፒ ቆሻሻን ወደ ሃይል ማመንጫ ለመቀየር የሚደረገው የ120ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ለዚህ አሰቃቂ አደጋ መንስኤ መሆኑ  ከተረጋገጠ የአገዛዙን ምን ያህል አውሬነትና ጨካኝነት እንደሚይሳይ ተገልጿል።

ይህ ፕሮጀክት አገሪቷ የታዳሽ ሃይልን በመጠቀም በ2025እኤአ ወደ መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ካላቸው አገራት ለማሰለፍ ከታቀዱ እቅዶች አንዱ መሆኑን ተዘግቧል።

መላ አገሪቷ ቀርቶ የአፍሪቃ ህብረት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ በመብራትና በሃይል እጦት እንደምትቸገር የዘገበው ዘዋሽንግተን ይህ ችግር አገዛዙ አስመዘገብኩ ካለው የእድገት ደረጃ ምን ያህል ተቃራኒ እንደሆነ ያሳያል ብሏል።

ይህን ፕሮጀክት ለመፈጸም በ2013 እኤአ ውል የተዋዋለው የካምብሪጅ ኢንደስትሪስ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለት ዘዋሽንግተን ፓስት በጋዜጣው አስፍሯል።

በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ ነፍሳቸውን ላጡ ውድ ኢትዮጵያውያን የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን እንመኛለን።

ዘዋሽንግን ፓስትን ሙሉ ሃተታ ይህን ሊንክ በመጫን ያንቡ  The Washington Post