ሴት ልጁ ላይ በአሜሪካ መኖሪያ ቤቱ ውስጥ የግርዛት ተግባር የፈጸመው ኢትዮጵያዊ ወደ አገር እንዲመለስ ተደረገ (deport)

አባይ ሚዲያ ዜና ዘርይሁን ሹመቴ

በአሜሪካ አትላንታ በመኖሪያ አፓርትመንቱ ውስጥ የሁለት አመት ሴት ልጁ ላይ የግርዛት ተግባር የፈጸመው ኢትዮጵያዊ ወደ  አገሩ እንዲመለስ (deport) መደረጉን ተገለጸ።

በ2001እኤአ በመኖሪያ ቤቱ መቀስን በመጠቀም  ሴት ልጁ ላይ  የግርዛት ተግባር የፈጸመው የ41 አመቱ ካሊድ አደም ባሳለፍነው ሰኞ እለት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ መደረጉ ተዘግቧል።

ካሊድ አደም በሴት ልጅ ግርዛት ክስ ወንጀለኛ በመሆን በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያ እንደሆነም ዘ ኒዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አስነብቦናል።

በ2006እኤአ በአሜሪካ በዋለው ችሎት ካሊድ አደም በሴት ልጅ ግርዛት ወንጀል የ10 አመት ጽኑ እስራት ተፈርዶበታል።

ይህን የ10 አመት ጽኑ እስራት ከፈጸመ በሃላ በአሜሪካ የመኖር መብት ተነጥቆት  ወደ አገሩ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ተደርጓል።

የሴት ልጅ ግርዛት በጤና፣ በስነ ልቦናና በማህበራዊ ህይወት እራሱን የቻለ ችግር እንደሚያመጣ ቢታወቅም በተለያዩ የአለማችን አገራት አሁንም ተግባራዊ እንደሚደረግ ጥናቶች ያሳያሉ።

የአለም የጤና ድርጅት ባወጣው ዘገባ መሰረት በ30 አገራት ውስጥ  ከ200ሚሊዮን ሴቶች ላይ ግርዛት እንደተፈጸመባቸው አሳውቋል።

በአፍሪቃ፣ በመካከለኛው ምስራቅና በእስያ ባሉ አገራት የሴት ልጅ ግርዛት ቁጥሩ ከፍተኛ እንደሆነ የጤና ድርጅቱ ባወጣው ሪፓርት ገልጿል።