በረፒ “ቆሼ” የአስክሬን ማውጣት ፍለጋው መቋረጡ ተገለጸ

አባይ ሚዲያ ዜና 

ዘርይሁን ሹመቴ

በአደጋው ህይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 113 እንደደረሰ ቢነገርም የአከባቢው ነዋሪዎች ይህ ቁጥር ወደ 200 እየተጠጋ መሆኑን እየተናገሩ ይገኛሉ።

በቆሻሻው ናዳ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ  የአከባቢው ነዋሪዎች የአስክሬን ፍለጋው ከሃሙስ ጀምሮ  መቀዛቀዙን እንዲሁም በቅርቡ መቋረጡን ገልጸዋል።

የአከባቢው ወጣቶች ይህ የአስክሬን ፍለጋ ተግባር መቋራጥን ተከትሎ በአገዛዙ ላይ ተቃውሞ ለማሰማት በአርብ መጋቢት  8 ቀን 2009ዓም ተሰባስበው እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል።

ይሁን እንጂ ወጣቶቹ በህውሃት መራሹ አገዛዝ ላይ በመሰባሰብ ተቃውሞ ከማድረጋቸው በፊት እንዲበተኑ እንደተደረጉ ታውቋል።

የአገዛዙ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር  ሙላቱ ተሾመ እና የከተማው ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ  ለቀስተኞች በተቀመጡበት ድንኳን በመገኝት እንደጎበኙዋቸው የትንሳኤ ሪዲዮ በዘገባው አስፍሯል።

የአስክሬን ፍለጋው ለጊዜው የተቋረጠው በቅርቡ የተደፉት ቆሻሻዎች መጀመሪያ መነሳት አለባቸው በሚል ብኩን ምክንያት እንደሆነም ነዋሪዎች እየገለጹ ይገኛሉ።

አምንስቲ ኢንተርናሽናል ጨምሮ የአለም አቀፍ ሚዲያዎች የረፒ የቆሻሻ መጣያ ቦታ መሸከም ከሚችለው በላይ እንደነበረ የወያኔ አገዛዝ ቀድሞ ያውቅ እንደነበረ መዘገባቸው ይታወሳል።

ይህንን ከ113 በላይ ኢትዮጵያውያውያንን በሞት የነጠቀንን የረፒ የቆሻሻ ማከማቻ ስፍራን የአገዛዙ ፕሬዝዳንት ሳይጎበኙት መቅረታቸው የአከባቢው ወጣቶችን እንዳስቆጣም ታውቋል።

የከተማው ከንቲባ ፕሬዝዳንቱን ከሸኙ በሃላ የወጣቶቹ ቁጣ ወደ ማይበርደ ተቃውሞ እንዳይሸጋገር በሚል ምክንያት በቦታው በመገኝት ከወጣቶቹ ሲነጋገሩ እንደነበሩም እማኞች ገልጸዋል።

የተቋረጠው የአስክሬን ፍለጋው እንዲቀጥል፣ በፍለጋው ስራ ላይ የሰው ሃይል እንዲጨመር እንዲሁም ሳምንቱን ሙሉ ያለተገቢ መከላከያ የአስክሬን ፍለጋው ላይ ተሰማርተው ለነበሩ የአከባቢው ወጣቶች የነጻ የህክምና አገልግሎት እንዲደረግላቸው ወጣቶቹ ለከንቲባው ጥያቂያቸውን ማቅረባቸውም ተገልጿል።

የአከባቢው ነዋሪዎችን እንደከዚህ በፊቱ አስታዋሽ እንዲያጡ ማድረግ ሳይሆን የስራ እድል በመፍጠር ለወደፊቱ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ወጣቶቹ ለከንቲባው ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ዘዋሽንግተን ፓስት ጋዜጣ የረፒ የቆሻሻ ናዳ አደጋ አስመልክቶ ባወጣው ሃተታ የወያኔ አገዛዝ በ120 ሚሊዮን ዶላር የታዳሽ ሃይል ከረፒ ቆሻሻ ለማምረት ከካምብሪጅ ኢንደስትሪስ ጋር ስምምነት እንደተዋዋለ አስነብቦናል።

በዚህ አደጋ ህይወታቸውን ያጡትን ወገኖቻቸንን በመንግስተ ሰማያት ያኑርልን ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትንና ጥንካሪን ያድልልን።