ባልፈጸመው ወንጀል ለ32አመታት በእስር ሲማቅቅ የነበረ ግለሰብ ነጻ መሆኑ ተረጋግጦ ተፈታ (Video)

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

በ1984እኤአ አንድሩ ዊልሰን በአሜሪካ ሎሳንጀለስ የ21 አመት ወጣትን በተኛበት መኪናው ውስጥ በስለት ወግተህ ገድለሃል ተብሎ በፓሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው።

ወንጀሉ በተፈጸመበት ሰአት የአይን ምስክር ሆና የቀረበችውና አንድሩ ዊልሰን ለ32አመታት ባልፈጸመው ወንጀል እስር ቤት እንዲማቅቅ ያስደረገችው የሟች ፍቅረኛ እንደነበረች ተዘግቧል።

አንድ ሰው  የተከሰሰበትን ወንጀልን እስካልፈጸመ ድረስ ለነጻነቱ እስከ መጨረሻው መታገልና ተስፋ መቁረጥ እንደሌለበት የ62 አመቱ አንድሩ ዊልሰን ይናገራል።

አንድሩ ዊልሰን የሴት ልጁን፣ የልጅ ልጁን እና የእህቱን እጆች ይዞ ከእስር ቤቱ በመውጣት የነጻነት አየርን ዳግም ለመተንፈስ በቅቷል።

ከ32 አመታት በሃላ ነጻ መሆኑ በመረጋገጡና ከእስር በመፈታቱ የተሰማውን ደስታ “ሊገለጽ የማይችል ብሎታል አንድሩ ዊልሰን።

ለዚህ ሁሉ ስቃይ ስለዳረጉት ሰዎች ሲጠየቅ “ያንን ለማሰብም ሆነ በሁኔታው ለመናደድ ጊዜ የለኝም እንዲያውም ያንን በማሰብ የማጠፋውን ሃይል ለቤተሰቤ አውለዋለው”  በማለት የሚያስገርም ምላሽ ሰጥቷል።

በሎሳንጀለስ የሚገኘው የሎዮላ የህግ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች (Loyola Law School) አንድሩ ዊልሰን ወንጀሉን እንዳልፈጸመ ለማረጋገጥ ለ3 አመታት ያህል ሲታገሉ እንደቆዩ ለማወቅ ተችሏል።

የሎዮላ የህግ ተቋም ተማሪዎችን እንደ ባለውለታው ብቻ ሳይሆን እንደ ቤተሰብም እንደሚቆጥራቸው አንድሩ ዊልሰን ተናግሯል።

ለህግ ትምህርት ተቋሙ ያለውን ክብርና ምስጋን የገለጸውም ከእስር ቤት ሲወጣ የተቋሙ አርማ ያለበትን ቲሸርት በመልበስ ነበር።

በቅርቡ 97 እድሜ የሚሞላትንና ለ32አመታት የተለያትን እናቱን በነጻነት ለመጎብኘት ጎዞውን እንደሚያቀናም አንድሩ ዊልሰን ከስካይ ኒውስ ጋር ባደረገው ቃለ መጠየቅ ተናግሯል።

የቃለ መጠይቁን ቪዲዮ ለማየት እዚህ ይጫኑ