በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እስረኞች የረሃብ አድማ እያደረጉ ነው ተባለ /አባይ ሚዲያ /

የኦሮሞ ፈደራሊስት ኮንግረስ አመራር እና አባላት የሆኑት እነ አቶ በቀለ ገርባን እና አቶ ደጀኔ ጣፋ እንዲሁም ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ፤የረሃብ አድማ ላይ ናቸው።

የረሃብ አድማ ለማድረግ እስረኞች የተገደዱበት ዋንኛ ምክንያት ፣ በማርሚያ ቤቱ ውስጥ ለእስረኛ የሚሰጥ መብት ለእነሱ ስለተነፈጋቸው እንደሆነ ቤተሰቦቻቸው ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ለአማርኛ ፕሮግራም በሰጡት ቃል ለማወቅ ተችሏል ።

የረሃብ አድማ ላይ የሚገኙት እስረኞች ፣ማረሚያ ቤቱ መብታቸውን እሲያከብር እና ውሳኔ እስኪሰጣቸው ድረስ ከቤተሰቦቻቸው የሚቀርብላቸው እንዲሁም ከማረሚያ ቤቱ የሚሰጣቸውን ምግብ እንደማይቀበሉ ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል ።

በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ፣ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤት እንዲሁም ለቤተሰቦቻቸው እንደሚገልጹት ከሆነ በማረሚያ ቤት ከፍተኛ የሆነ ኢሰብዓዊ ድርጊት እንደሚፈጸምባቸው በተደጋጋሚ ገልጸዋል ።

በተለይ ፍርድ ቤት በሚቀርብበት ወቅት በአብዛኛውን ጊዜ ለፍርድ ቤት የሚያቀርብት አቤቱታ በማረሚያ ቤት የሚደርስባቸውን እንግልት በተመለከተ ነው።

ይሁን እንጂ ለሚያቀርብት አቤቱታ ተገቢውን ምላሽ ለማግኘት እንዳልተቻላቸው አሁን ድረስ የሚያቀርብት አቤቱታ እንደ ማሳይ መውሰድ ይቻላል።

በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን የክስ መዝገብ ስር የሚገኙ 16 ተከሳሾች አቶ አጋባው ሰጠኝ ጨምሩ ፣ እንዲሁም በእነ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ መዝገብ ሥር ተከሰው የሚገኙ ታሳሪዎች በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንግልት እንደ-ሚደርሳባቸው ፍርድ ቤት በሚቀርብበት ወቅት በተደጋጋሚ አቤቱታ ያሰሙ ነበር።

በተያያዘ ዜና የሆድ ድርቀትን ለመከላከል በወህኒ ቤት ለሚገኙት ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ታዞላቸው ይወስዱት የነበረ Bisacodyl የተባለ መድኃኒት በቂሊንጦ እንዳይወስዱት መደረጋቸው ተሰምቷል፡፡
በቅርቡ የቀዶ ህክምና በማድረግ ወደ ቂሊንጦ ለተመለሱት ዶክተር ፍቅሩ መድኃኒቱን እንዳይወስዱ በቂሊንጦ የተከለከሉበት ምክንያት አስገራሚም አስቂኝም ሆኗል፡፡