አሜሪካ እና እንግሊዝ ከስምንት ሀገራት በሚነሱ በረራዎች ላይ የኤሌክትሮኒክስ እገዳ ጣሉ

 

የአባይ ሚዲያ ዜና መርጋ ደጀኔ

የአሜሪካና የጸጥታ አካላት ከስምንቱ ሃገራት ወደ አሜሪካ የሚጓዙ መንገደኞች ከተንቀሳቃሽ የእጅ ስልካቸው ውጭ ምንም አይነት የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች አብረው ይዘው መጓዝ እንደማችሉ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

 ክልከላው የተጣለው በአብዘኛው ሙስሊም ነዋሪዎች ከሚበዙባቸው ሀገራት በሚነሱ የአውሮፕላን በረራዎች ላይ ሲሆን የእገዳው ምክንያትም ‹‹ሽብርተኝነትን ለመከላከል›› ነው ተብሏል፡፡ ከስምንቱ ሀገራት ወደ አሜሪካ የሚጓዙ መንገደኞች ወደ አውሮፕላን ሲገቡ ታብሌት ፎቶ ካሜራ ላፕቶፕ ዘመናዊ ጌም መጫዎቻዎች የዲቪዲ ማጫዎቻዎችን እና መሰል የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን መያዝ እንደማይችሉ ተነግሯል፡፡

ከሽብር ጥቃት ስጋት ጋር በተገናኘ የተወሰደው ነው የተባለው ይኸው እገዳ በግብፅ ኩዌት ኳታር ሞሮኮ ዮርዳኖስ፣ ሳውዲ አረቢያ እና በተባበሩት አረብ ኤመሬት የሚገኙ 10 አየር ማረፊያ ጣቢያዎች ላይ ተግባራዊ መደረጉ ታውቋል።

ክልከላው ከላይ የተጠቀሱትን የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ያካተተ ቢሆንም እንደ ሞባይል እና የህክምና መሳሪያዎች ያሉ ቁሶችን እንደማይጨምር የገለጸው ዘገባው እገዳውም ከዛሬ ጀምሮ በሚደረጉ በረራዎች ላይ ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምር አክሎ ገልጿል፡፡


የዩናይትድ ስቴትስ የሀገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት በጉዳዩ ላይ ሲያሰላልስል መቆየቱን የገለጸ ሲሆን በመጨረሻም እገዳው ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኑን ገልጿል፡፡ የሽብር ጥቃት የሚፈጽሙ ሰዎች እንዲህ ያሉ መሳሪያዎችን እንደሚጠቀሙም የደህንነት መስሪያ ቤቱ ተናግሯል፡፡ ‹‹እንደ ላፕቶፕ ያሉ ቁሶች አውሮፕላኑን ሊያጋዩ የሚችሉ ቦንቦችን መደበቅ ይችላሉ፡፡›› ሲልም መስሪያ ቤቱ አክሎ ገልጿል፡፡ 

አሜሪካ የወሰደችውን ዕርምጃ ተከትሎ የብሪታኒያ መንግስት ተመሳሳይ እገዳን ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑን ቢቢሲ ማክስኞ ምሽት ዘግቧል። ይሁንና የብሪታኒያ የጸጥታ ሃላፊዎች እገዳውን በተመለከተ በቅርቡ ማብራሪያን ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የዜና አውታሩ አመልክቷል።

የቱርክ መንግስት በበኩሉ አሜሪካ የወሰደችው ዕርምጃ የተሳሳተ ነው በሚል ማስተካከያ እንዲደረግ ጥያቄን ማቅረቡን ቢቢሲ በዘገባው አስነብቧል። የግብፅ አየር መንገድ በበኩሉ ዕርምጃውን ከአርብ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ባለፈው አመት በሶማሊያ በአንድ የመንገደኞች አውሮፕላን ላይ በላፕቶፕ ኮምፒውተር ላይ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል። የአሜሪካ የደህንነት ባለስልጣናት የሽብር ድርጊትን የሚፈጽሙ አካላት ተመሳሳይ ስልት የመጠቀም እቅድ እንዳላቸው መረጃ መኖሩን ገልጸዋል።