አርበኞች ግንቦት ሰባት ዳግም ጥቃት መሰንዘሩ ታወቀ

አባይ ሚዲያ ዜና
መርጋ ደጀኔ
 
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ታጋዮች መጋቢት 12 ቀን በሰሜን ጎንደር ዞን በወገራ ወረዳ በሚገኝ አንድ የፓሊስ ፅ/ቤት ላይ ጥቃት መፈጸማቸው ተሰማ።
 
ከጎንደር 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ ከተማ ሌሊት ወደ 7 ፡18 ገደማ የግንባሩ ወታደሮች ዘልቀው በመግባት የከተማው ፖሊስ ፅ/ቤት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሱ ተነግሯል።
 
በከተማው ለ45 ደቂቃ የቆየ የተኩስ ልውውጥ መሰማቱም ተገልጿል። ይህ የተኩስ ልውውጥ የተካሄደው በአርበኞች ግንቦት 7 ወታደሮች መካከልና በከተማው በፀጥታ ስራ ላይ ተሰማርተው በሚገኙት የመከላከያ  የፀረ ሽምቅ ሚሊሻ እንዲሁም መደበኛ ፖሊስ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
 
በዚህ ጥቃት ከወያኔ በኩል 3 ወታደሮች እንደተመቱ ታውቋል። 2ቱ ወዲያውኑ ሲሞቱ አንደኛው ሆስፒታል ገብቶ የህክምና እርዳታ ቢደረግለትም መትረፍ ባለመቻሉ ዛሬ ህይወቱ ሊያልፍ እንደቻለም ተነግሯል። ወያኔ በዚህ ውጊያ  የበላይነት የተነጠቀው እነዚህ የነጻነት ሃይሎች ጥቃቱን ካደረሱ በኋላ በማፈግፈግ ራሳቸውን ከወያኔ ወታደሮች እይታ በመደበቃቸው እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።
 
በዚህ በነጻነት ሃይሎች ድርጊት  የተበሳጨው የዞኑ ኮማድ ፖስት በ12/07/09 ዓም ስብሰባ በመጥራት የከተማውን ፖሊስ አዛዥ፣በወቅቱ የፀረ ሽምቅ ጋንታ አመራር እና የመከላከያ የቡድን አመራር የነበሩትን ግለሰቦች ከስራ በማገድ እንዲታሰሩ ማስደረጉ ታውቋል።
 
ሌሎች አመራሮችም በከተማው ከፍተኛ ተኩስ ሲደረግ ከቤትና ከካምፕ ወጥተው ማገዝ ሲገባቸው ይህን ባለማድረጋቸው ከሀላፊነት ታግደዋል።
ይህን ዘመቻ ያደረጉት የአርበኞች ግንቦት ሰባት ታጋዮች ግዳጃቸውን ጨርሰው ወደ ቦታቸው በሰላም እንደተመለሱም ተዘግቧል።