በጀርመን የመራሂተ መንግስት አንጌላ መርክል ፓርቲ በምርጫ ድል ቀናው

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

በጀርመን ማርች 26 ቀን 2017እኤአ ሳርላንድ በምትባል ግዛት በተደረገ ምርጫ የመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፓርቲ ድል እንደቀናው ተዘገበ።

በደቡብ ምእራብ ጀርመን የምትገኘው ይህች የሳርላንድ ግዛት ለአንድ ሚሊዮን ጀርመናዊያውያን መኖሪያ ስትሆን ለፈረንሳይና ለሉግዘምበርግ አገራት አጎራባች ናት።

በዛሬው የምርጫ ውጤት የካንስለር አንጌላ መርክል ፓርቲ የሆነው የክሪስቲያን ዲሞክራቲክ ህብረት (CDU) 41ከመቶ በማስመዝገብ እንዳሸነፈ ተዘግቧል።

የአዉሮጳ ኅብረት ምክር ቤት የቀድሞው ፕሬዝደንት በሆኑት በማርቲን ሹልስ የሚመራው የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (SPD) በዚህ ምርጫ 29.5% የሚሆን ድምጽ ለማግኘት እንደቻለ ታውቋል።

ለከፍተኛ የቴክኖሎጂ ምርት እንደማግኔት እየተቆጠረች ያለች ይህች ክልል ከምርጫው በፊት የምትተዳደረው በሁለቱ ግዙፍ ፓርቲዎች (SPD) እና (CDU) በተመሰረተ ጥምር መንግስት እንደሆነም መረዳት ተችሏል።

በስደተኛ ፓሊሲያቸው ከፍተኛ ትችት ለማስተናገድ የተገደዱት ካንስለር አንጌላ መርክል ፓርቲያቸው በሳርላንድ ምርጫ ማሸነፉ ከፍተኛ እፎይታ ይሰጣቸዋል ተብሏል።

ከሴምተምበሩ ጠቅላላ ምርጫ በፊት በሌሎች ሁለት ግዛቶችም እንዲሁ ምርጫ እንደሚደረግ ሪፓርቶች ያሳያሉ።