ታላቁ የደቡብ አፍሪቃ የነጻነትና የጸረ አፓርታይድ ታጋይ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

ከኔልሰን ማንዴላ ጋር የአፓርታይድን ስርአት ለመጣል የታገሉት አክቲቪስት አህመድ ካትራዳ በ87 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት መለየታቸው ተዘገበ።

የነጻነት ታጋዩ አህመድ ካትራዳ በጆሃንስበርግ ሆስፒታል የጭንቅላት ቀዶ ጥገና እንደተደረገላቸውና ለጥቂት ቀናት ታመው እንደነበረ ለመረዳት ተችሏል።

በ1964 እኤአ የዘረኛውን የአፓርታይድን ስርአት በሃይል ለመጣል ተንቀሳቅሳችኋል በሚል ክስ አህመድ ካትድራ  ከኔልሰን ማንዴላ ጋር የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው እንደነበረም ይታወቃል።

ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ለታጋዩ አህመድ ካትራዳ ክብር በመላው ደቡብ አፍሪቃ የአገሪቷ ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለወብ ትእዛዝ አስተላልፈዋል።

እኚህ የነጻነት ታጋይ በአፓርታይድ አገዛዝ ከ26 አመታት በላይ ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፤ 18 አመታትን በሮቢን ደሴት ከኔልሰን ማንዴላ ጋር እኩልነትን፣ ፍትህንና ዲሞክራሲን ለማምጣት ታስረዋል።

ዊኒ ማንዴላ እና የሰላም ኖቬል ተሸላሚው ሎሬት ዴዝሞን ቱቱ በጸረ አፓርታይድ ታጋዩ አህመድ  ካትራዳ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል።

የአፓርታይድ አገዛዝ በ1964 በእነ ኔልሰን ማንዴላ ክስ የእድሜ ልክ እስራት ካከናነባቸው ስምንት ውድ የደቡብ አፍሪቃ የነጻነት ታጋዮች  መካከል አሁን በህይወት የቀሩት ሁለት ብቻ መሆናቸውም ለማወቅ ተችሏል።