(ክፍል አንድ)

አስራ ሰባት አመት በበረሃ የተመላለሰው ህወሃት/ኢህአዴግ የተራበውን ስልጣን በእጁ ካደረገበት 1983 ዓ.ም ወዲህ በሃገራችን ሁለመና የናኘው የጎሳ ፖለቲካ አሁን አሁን ‘መጨረሻችን ምን ይሆን?’ የሚያስብል አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ጎረቤት ሱማሌን ዝንጀሮ ያየው ክምር ያስመሰለው፣ ደቡብ ሱዳንን የዋይታ ምድር ያደረገው፣ ሩዋንዳን ከልብ የማይወጣ ፀፀት ያሸከመው የጎሳ ፖለቲካ እኛም ቤት አግድም እያደገ ነው፡፡የጎሳ ፖለቲካችን አግድም አደግነት በገለጫው ብዙ ነው፡፡

አያት ቅድም አያቶቻችን ኢትዮጵያ የተባለችውን ሃገር ከነክብሯ ለመጭው ትውልድ ለማስረከ ያደረጉትን ከአእምሮ በላይ የሆነ ክቡር እና ድንቅ መስዕትነት ማቃለል፣ማሳነስ፣ ማጣጣል ወይም ሌላ ትርጉም መስጠት የጎሳ ፖለቲካችን አግድም አደግነት ሁነኛ መገለጫ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ ተጠራርቶ ለሃገሩ ነፃነት ሲል የሞት ገበያ ላይ የዋለበትን የአድዋ ድል በማክበር ፋንታ የጎሳ ፖለቲካ የለከፋቸው የእኛ ወንድም እህቶች የራሳቸውን አሞሌ ሊያቃልሉ ይታጠቃሉ፡፡ግማሾቹ ‘የአድዋ ድል ከሁለት ጨቋኝ አንዱን የመምረጥ ጉዞ ነበር እንጅ የኢትዮጵያ ህዝብ የነፃነት ጣዕምገብቶት ያደረገው አልነበረም’ ሲሉ ሌሎቹ ‘የአድዋ ድል ባይኖር ኖሮ ኤርትራዊያን ሆድ ብሷቸው አይገነጠሉም ነበር’ ይላሉ፡፡ሌላው የባሰበት ደግሞ ‘የአድዋ ድል የአፄ ምኒልክን ጨቋኝነት የጋረደ ክፉ ጥላ ነው’ ባይ ነው፡፡

የጎሳ ፖለቲካችን አግድም ማደግ ሌላ መገለጫ ብዙ ዋጋ የተከፈለበትን ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ቀላል እና ርካሽ በሆነ የማህበራዊ ሚዲያ ሆይ ሆይታ ብቻ ድምጥማጡን ለማጥፋት ከንቱ መፋተር ነው፡፡ ብዙዎች የሞቱለትን፣ እልፎች በኢህአዴግ እስር ቤት አሳር መከራ የሚያዩለትን ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ማጓጠጥ፣ ዋጋውን ማቃለል፣ አመጣጡን አኮስሶ የፈረደበት የአማራ ህዝብ ብቻ ንብረት ማድረግ ከጀማሪ የማህበራዊ ሚዲያ ፖለቲከኛ እስከ ፕሮፌሰር ተብየ የኦሮሞ አክራሪ ብሄርተኞች የሚላዘን የማይቀየር ችኮ ሙዚቃ እየሆነ መጥቷል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን መጥላትም ሆነ መካድ የማንኛውም ግለሰብ መብት ሆኖ ሳለ ‘ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም’ ማለት ግን ‘እኔ ያልሆንኩት እና ያልወደድኩት ነገር ህልውና የለውም’ እንደማለት ያለ ራስን ያለመግዛት ምልክት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ቆምኩለት የሚሉትን ጎሳ ማንነት በተመለከተ አሉታዊ ለመሰላቸው ነገር ሁሉ እንደሚታመሙት እንደዛው እነሱ በኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ላይ ክፉ ደግ ሳይመርጡ አፋቸውን ሲያላቅቁ ራሱን ከኢትዮጵያዊ ዜግነት ብቻ ጋር ያጋመደውን ዜጋ ሁሉ እንደሚያሳምሙ ማወቅ አለባቸው፡፡ የስሜት ፈረስ በጋለባቸው ቁጥር በኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ላይ የመደንፋት መብቱ እንደሌላቸውም ማወቅ አለባቸው፡፡እስከ ሽበት ሽምግልና የተማሩት ትምህርት ሌላው ቢቀር ይህን ሊገልፅላቸው ግድ ነው፡፡

ረዘም ያለ ዘመን እንደማስቆጠሩ ቆምኩለት ለሚለው የኦሮሞ ህዝብ ይህ ነው የሚባል ተግባራዊ ነጥብ ማስቆጠር ያልቻለው የኦሮሞ ብሄርተኞች እንቅስቃሴ የተሳካለት ነገር ቢኖር ማናቸውንም የመገናኛ ዘዴዎች ተጠቅሞ ጩኽት ማበርከቱ ላይ ነው፡፡ የጩኽቱ ማድመቂያ ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ላይ ያለው የብዙሃንነት ነገር ነው፡፡ ተግባር

ይበልጥ በሚሰምርባት በዚች አለም ተግባሩ ላይ እምብዛም የሆኑት የኦሮሞ ብሄር ፖለቲካ አቀንቃኞች ‘ብዙሃን ነን’ የሚለውን ትርክታቸውን ተንተርሰው ብዙ ይተልማሉ፡፡ መገንጠሉን ይሞክራሉ! ለዚህም ቻርተር ከትበው ወገናችን ያሉትን ብቻ ታዳሚ ያደረጉ፣ አስገራሚ ንግግር የተደረገባቸው ተከታታይ ዝግ ስብሰባዎች ያደርጉ ይዘው ነበር፡፡

የእነዚህ ስብሰባዎቹ ተፈጥሮ፣የተብላሉባቸው ሃሳቦች፣የመግለጫዎቹ ይዘት የብሄር ፖለቲካችን አካሄድ የደረሰበትን እንዳይሆን የሆነ ጉዞ አመላካች ነበሩ፡፡ በስደት ላይ ያሉ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ብቻ ተሰብስበው ‘ኢትዮጵያን አፈራርሰን የኦሮሚያ ሪፐብሊክን እንገነባለን፤ የኦሮሚያን ሪፐብሊክ መገንቢያው ብቸኛው ወለልለም የኢትዮጵያ ፍርስራሽ ነው’ ተብሎ ሲታዎጅ ‘በሃገርቤት ያለውም ሆነ በስደት ያለ ነገር ግን በስብሰባው ያልታደመ ኢትዮጵያዊነቱን የሚወድ ኦሮሞ የለም ወይ?’ ብሎ ለማሰብ የጎሳ ፖለቲካው አግድም አደግነት አይፈቅድም፡፡ በዘሁ ጉደኛ ስብሰባ በአይን የሚታይ ወታደር በሌለበት፣ስለትጥቅ ትግል ቀደም ብሎ ባልተነሳበት ሁኔታ ባለ አራት ወታደራዊ እዝ ጣቢያዎችም እንደሚዋቀሩ ታውጆ፣ ለሰላማዊ ትግል የሚታሰር የሚፈታውን ኦቦ በቀለ ገርባን የወታደራዊ እዞቹ ራስ አድርጎ ሲሾም ቢያንስ በኢህአዴግ እስርቤት ላለው አቶ በቀለ ገርባ ሌላ የክስ አንቀፅ ማዋጣት እንደሆነ ለማሰብ የጎሳ ፖለቲካችን ደመነፍሳዊ ሩጫ ስክነት አይሰጥም፡፡ ተግባሩ ላይ ቄሱም ዝም መፅሃፉም ዝም ሆነ እንጅ በዛ ሰሞን ‘ኦሮሚያ የራሷ ወታደራዊ ሃይል ኖሯት ነው ከሌሎች ኢትየጵያዊያን ጋር መነጋገር ያለባት፤ሌሎቹን ክልሎችም የምንመክረው ይህንኑ ነው’ ብሎ ነበር የወታደራዊ እዙ ምክትል ተደርጎ የተሰየመው አቶ ጃዋር መሐመድ፡፡

የ “ብዙሃን” እና “ታላቅ ህዝብነት” ተረክ

የኦሮሞ ብሄርተኘነትን የሚያቀነቅኑ ልሂቃን ፍላጎት ለዘብ ሲል ኦሮሞ የገነነባት ኢትዮጵያን መመስረት አለያም ኦሮሚያን ገንጥሎ የኦሮሚያ ሪፐብሊክን መመስረት እንደሆነ ከንግግራቸው መረዳት ቀላል ነው፡፡ የዚህ ክርክር መነሾ አንድም የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሲበደል ኖሯል የሚል ሲሆን ሌላም የኦሮሞ ህዝብ በሃገሪቱ የሚይዘው የቁጥር ብዙህነት እና በክልሉ ይገኛል የተባለው ግዙፍ የተፈጥሮ ሃብት ነገር ነው፡፡እነዚህ ክርክሮች ጥያቄ አያጣቸውም፡፡

የኦሮሞ ዘውጌ ብሄርተኝነት አቀንቃኝ ልሂቃን የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያለው ድርሻ መበደል የበዛበት እንደሆነ እርግጠኞች በመሆናቸው የቂም ፖለቲካ በማፋፋሙ ላይ ይበረታሉ፡፡ የሰፈነባቸው የተበዳይነት ስነልቦና በራሳቸው በኩል እንደ እምቦቃቅላ ህፃን ሁሉም እንዲያባብላቸው የመፈለግን ዝንባሌ ሲያላብሳቸው በሌላው ላይ(በተለይ በኢትዮጵያ ብሄርተኝነት አቀንቃኞች ላይ) ደግሞ የፈለጉትን ክፉ ደግ የመናገር መብት ያላቸው አድርጎ እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያለው ድርሻ መበደል ብቻ ነው የሚሉ አሳቢዎች ይህንኑ ባይተዋርነታቸውን የሚደግፍላቸው ከሚመስላቸው ቦታ እመር ብለው ታሪክን ይተርካሉና የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ወራሪ ሆኖ የቆየበትን ዘመን ባላየ ያልፉታል፡፡ይህ እንደዋዛ የሚያልፉት የታሪክ እውነታ ግን አሁን ብዙሃን ነን ለሚለው ተረካቸው መሰረት የጣለ በመሆኑ እነሱ እንደሚፈልጉት በሽፍንፍን መታለፍ የሌበት ነገር ነው፡፡

የኦሮሞ ህዝብ የሰፈረበት መሬት የኢትዮጵያን አብዛኛ ክፍል የሚይዝ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ክልሉ የያዘው የተፈጥሮ ሃብትም አያሌ እንደሆነ ተናግረው ‘ታላቅ ህዝብ ነንና

የኢትዮጵያን ሁለመና መዘወር አለብን’ ለሚሉ የኦሮሞ መብት አቀንቃኞች መቅረብ ያለበት ወሳኝ ጥያቄ እድሜ አለሙን ሲበደል ኖረ የሚሉት የኦሮሞ ህዝብ አሁን የሚኖርበትን ሰፊና ለም መሬት የያዘው እንዴት ነው? የሚለው ነው፡፡ መልሱ የታወቀ ቢሆንም ለመድገም ያህል በመካከለኛው ዘመን ማብቂያ አካባቢ በኦሮሞ ማህበረሰብ ዘንድ በተከሰተው የህዝብ ቁጥር መጨመር የተነሳ የኦሮሞ ህዝብ ሃይልን ተጠቅሞ በተለያየ አቅጣጫ ባደረገው በግዝፈቱ በአፍሪካ ጭምር በሚነሳ መስፋፋት ነው፡፡ በመስፋፋት የተያዘን መሬት ይዘውት እንደ ተወለዱት የአካል ክፍል የራስ ብቻ አድርጎ፤መሬቱ በያዘው የተፈጥሮ ሃብት ሲኩራሩ፣ ‘ብዙሃንነት ያለኝ በመሆኔ የሃገሪቱን ሁለመና ካልዘወርኩ እገነጠላለሁ’ ሲባል ታሪክን ወደኋላ ቆጥሮ የኦሮሞ ህዝብ ወደዚህ መሬት ከመስፋፋቱ በፊት መሬቱ ላይ እንኖር ነበር የሚሉ ሌሎች ህዝቦች ክርክር ቢያነሱ ለመልሱ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡

ሌላው ጉዳይ የኦሮሞ ህዝብ በመስፋፋት የያዘው መሬት የራሱ ንብረት ነው የሚሉ የኦሮሞ ብሄርተኝነት አቀንቃኞች የኦሮሞ ህዝብ በመካከለኛው ዘመን እንዳደረገው ባለ መስፋፋትም ሆነ በተለያየ መንገድ ኦሮሚያ ላይ ሰፍረው የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ህዝቦችን ሲፈልጉ የሚያፈናቅሉ ሲሻቸውም ወደ ገደል የሚወረውሩ የመሆናቸው ነገር ነው፡፡ መስፋፋት ባለቤትነትን ካጎናፀፈና የኦሮሞን ህዝብ በመስፋፋት የያዘው መሬት ባለቤት ዳደረገው ከኦሮሞ ሌላ ኦሮሚያ ላይ የሰፈረ ህዝብ የሰፈረበት አካባቢ ባለቤት የማይሆነው ለምንድን ነው?! በኦሮሚያ መገንጠል አለመገንጠል፤በኦሮሞ ልሂቃን የኢትዮጵያን ፖለቲካ በዋናነት የመዘወር አለመዘወር ለተተኪ አምባገነንነት ወንበር በመቋመጥ ዙሪያ ያለው ሃሳብ ሳይደመጥ እንዲጨፈለቅ የሚፈረድበት በየትኛው ዳኛ ነው?! ኦሮምኛ ሳይናገር በኦሮሚያ ክልል መገኘቱ ብቻ ወንጀል ሆኖ ወደገደል ያስወረወረው፣ ኮሽ ባለ ቁጥር ስጋት የሚወርሰው ባይትዋር የመሆኑ ነገር እንደትክክል የሚወሰደውስ እንዴት ባለ ፍርድ ነው?!

እዚህ ላይ ትልቅ ሃቅ ይፋለሳል! የኦሮሞ ህዝብ በታሪክ አጋጣሚ በሃይል ተስፋፍቶ በሰፈረበት ለም መሬት ላይ ከተፈጥሮ ቱርፋት ላይ እየተጠቀመ፣ እንዳሻው እያመረተ መኖሩ አልበቃ ብሎ መሬቱን እስከመገንጠል መብት እንዳለው የሚከራከሩ ሰዎች ለሌላ ብሄር ሲሆን ኦሮሚያ ላይ ሰፍሮ መኖርን እንኳን ሊከለክሉ ሲቃጣቸው ሚዛናዊነታቸውን ያጣሉና በሌላው ብሄር ዘንድ እንደ ስጋት ቢቆጠሩ አይገርምም፡፡አሁን አሁን ልጆቻቸው በኦሮሚያ ክልል ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ሲመደቡ የሚያለቅሱ ወላጆች እየበረከቱ የመጡት ለዚሁ ነው፡፡ ‘ኦሮሞ ሲሞት ሌላው ለምን ዝም ይላል?’ ለሚለው ጥያቄ ግማሽ መልስ ያለውም እዚሁ አሳቤ ውስጥ ነው፡፡

የኦሮሞ ብሄርተኝነት አቀንቃኝ ዜጎች መበደል ስነልቦና ለራስ በማዘኑ ላይ ብቻ አቁሞ አስቀርቷቸው ይሄን ሁሉ ሃቅ ተረጋግተው በሚዛናዊ የህሊና ፍርድ እንዳያዩት ሳያደርግ አልቀረም፡፡ ለዚህም ቢሆን ወሳኙ ነጥብ ፊውዳሊዝም ለረዥም ዘመን ተንሰራፍቶ በኖረባት፣የሰብዐዊ መብት እና የዲሞክራሲ ጉዳይ ድሮ ቀርቶ ዘንድሮ ውሃው ባልሞቀባት ሃገር ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተበደለ ማነው? የሚለው ነው፡፡የበደል ውድድር ሚዛን ይውጣ ከተባለ ደግሞ ሁሉም የጎሳ ፖለቲከኛ የመጣበት ጎሳ መዓት እንደወረደበት አድርጎ ማሰቡ አይቀሬ ነው፡፡ በጋራ ወደፊት ለመራመድ የድሮው የበደል ዶሴ ክብደት ቅለት መጣራት ካለበት ሌላው ህዝብም የኦሮሞ ህዝብ ሲስፋፋ አደረሰብኝ የሚለውን በደል ለመስማት የመዘጋጀት እርጋታ ያስፈልጋል፡፡እዚህ ስክነት ላይ ከተደረሰ ደግሞ አፄ ምኒልክ የሚብጠለጠሉበትና ኢትዮጵያ ተሰርታ ያለቀችበት የተስፋፊነት ወንጀል በመካከለኛው

ዘመን ገንፍሎ ሃገሪቱን አጥለቅልቆ በነበረው የኦሮሞ ህዝብ ቤትም እንዳለ ለማዎቅ ይቻላል፡፡ጦርነት እና መጋደል የኦሮሞን ህዝብ ጨምሮ ሁሉም ተስፋፊ የሚያደርገው ልማድ እንጅ አፄ ምኒልክ እና ወታደሮቻቸው ብቻ የኦሮሞን ህዝብ መከራ ለማሳየት አቅደው ያደረጉት ነገር እንዳልሆነ ለመረዳት ስክነት ይጠይቅ ይሆናል እንጅ ይሄን ያህ ውስብስብ ነገር አይደለም፡፡

ሁለተኛው የኦሮሞ ብሄርተኝነት አቀንቃኞች ክርክር የኦሮሞ ህዝብ ቁጥር ብዙ በመሆኑ ወደፊት የምትመሰረተዋ ኢትዮጵያ የኦሮሞ ህዝብን ጥቅም ያስቀደመች መሆን አለባት የሚለው ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ቁጥር ብዛት የማይካድ ሆኖ ሳለ በዚህ አውድ ብዙሃንነት የተተረጎመበት መንገድ ከዘመናዊው የዲሞክራሲ መርህ እሳቤ አንፃር ሲገመገም ስህተት ያዘለ ነው፡፡ አሁን አለማችን በደረሰችበት የስልጣኔ ደረጃ ሳቢያ የተወሳሰበውን ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ፣ፖለቲካዊ ስንክሳር አቻቻይ በሆነ ሁኔታ ለማስኬድ ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ዘይቤ ፍፁም ነው ባይባልም ተሻይ እንደሆነ የሚያከራክር ነገር አይደለም፡፡በዲሞክራሲያዊ የፖለቲካዊ ዘይቤ ብዙሃንነት የሚበየነው ተመሳሳይ ቋንቋን በመናገር ሳይሆን ተቀራራቢ ሃሳብን በመጋራት ነው፡፡ በሌላ አባባል የብዙሃንነትን ግዝፈት የሚያገኙ ሰዎች በልበልቦናቸው መርምረው በያዙት አቋም እና በተስማሙበት ሃሳብ ምስስል/ቅርርብ እንጅ መርጠው ባልተወለዱበት ፣አውጥተው አውርደው እንሁን ብለው ባልሆኑት የብሄር ተመሳሳይነት አይደለም፡፡

ሳይንሳዊ እና ዘመናዊ በሆነው የዲሞክራሲያዊ አሰራር እሳቤ መሰረት ቋሚ ብዙህነት የሚባል ነገር አለመኖሩ ሌላው የኦሮሞ ዘውጌ ፖለቲከኞችን የብዙሃንነት ክርክር አፍራሽ እሳቤ ነው፡፡ በአንድ ሃሳብ ላይ ተስማምተው ለተወሰነ ሃሳብ ሲሆን ብዙሃን በመሆን ሃሳባቸው ገዥ ሃሳብ እንዲሆን ያደረጉ ሰዎች በሌላ ሃሳብ ላይ ሊለያዩ ስለሚችሉ የቀደመው ብዙሃንነታቸው ፈራሽ ይሆናልና የሰዎች ብዙሃንነት እንደሃሳቦች ተለዋዋጭነት የሚወሰን እንጅ ቋሚነት ያለው ነገር አይደለም፡፡ ስለሆነም ሰዎች አንድ አይነት ቋንቋ ስለተናገሩ ብቻ ሁሌ በአንድ ልብ አስበው በአንድ አፍ የሚያወሩ የዘላለም ማህበርተኞች አድርጎ ማሰቡ የሚያፈነግጠው ከዲሞክራሲያዊ እሳቤ ብቻ ሳይሆን ከሰው ልጅ ተፈጥሮም፤አሁን አለማችን ከደረሰችበትሁለንተናዊ ውስብስቦሽ አንፃር የሰውልጅ ማንነት እና ፍላጎት ከሚነሳበት በርካታነት ጭምር ነው፡፡ እንዲህ በተወሳሰበች አለም የሰዎችን የማንነት ክር በበረከተበት ዘመን አንዷን የማንነት ክር(ቋንቋን) ብቻ ስቦ አውጥቶ ከአቅሟ በላይ የሁሉ ነገር ወሳኝ ማድረግ ልክፍት የዘውግ ፖለቲከኞ ወደ ስልጣን መንደርደሪያ መንገድ ካልሆነ አዟዙሮ የማሰብ ችግር ይሆናል፡፡

የቁጥር ብዛትን ተንተርሶ ትልቅ ህዝብ ነን የሚለው በአብዛኛው በአማራ እና በኦሮሞ ዘውግ ፖለቲከኖች ዘንድ የሚደጋገመው ተረክም ከመሰረታዊ የዲሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብቶች ጋር ጠብ ያለው ንግግር ነው፡፡ ትልቁን ፖለቲከኛ ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ ብዙ ፖለቲከኞች የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ ፋንታ በጎ ለማድረግ ሲሉ በሚያነሱት ምክረሃሳብ የሚያነሳሱት የአማራ፣የኦሮሞ እና የትግሬ የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኖች ሊያደርጉት ስለሚገባ ነገር ነው፡፡ አማራና ኦሮሞ በዛው በመከረኛ ብዙ ቁጥርነት ነው ቢባል እንኳን የትግራይ ልሂቃን ደግሞ ጠብመንጃ አንግተው አንጋች ማበርከታቸው ከብዙ ቁጥርነት ታስቦላቸው መሰለኝ በሶስተኝነት መነሳት ያለበት ባለ ብዙ ቁጥሩ የሶማሌ ህዝብ ተዘሎ እነሱ የተተኩት! ይህ አስተሳሰብ አንድም ለኢትዮያዊነቱ ብዙ ያዋጣውን አሁንም በኢትዮጵያ ላይ ክፉ ሲያወራ የማይሰማውን የአፋር፣የደቡብ፣ የጋምቤላ ወዘተ ህዝቦች ከምንም ያልቆጠረ ክፉ አግላይ አስተሳሰብ ከመሆኑ የተነሳ እነዚህ ሰዎች ይህን

ምክረሃሳብ ሲሰሙ ምን ይሰማቸዋል ተብሎ ተዟዙሮ ያልታሰበበት ግንፍልተኛ እና እብሪተኛ አካሄድ ነው፡፡ ሁለተኛው የዚህ እሳቤ ችግር እራሱን ከማንም ዘውግ ጋር የማይፈትል፣ከፍ ሲል ሰው ነኝ ዝቅ ሲል ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚቆጥረውን ዜጋ በምድር ላይ ያልተፈጠረ የሚያስመስል አንድ ስማቸውን የረሳሁት ፈረንጅ በአንድ ወቅት ትዝብታቸውን ሲያስቀምጡ “ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካ ጎሳ ነው፤ ጎሳ ደግሞ ቋንቋ ነው” ያሉትን የሚያጠናክር አስተሳሰብ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ፖለቲካ ዘር እና ቋንቋ ብቻ አይለም! ይልቅስ በሃሳብ ላይ የቆመ እልፍ ያለ ፖለቲካ እሩቅ ያስኬዳልና እርሱ ለኛ ያስፈልገናል! ለወደፊቷ ኢትዮጵያም የሚበጀው ይሄው ነው፡፡

ፀሀፊውን ለማግኘት – meskiduye99@gmail.com