የደቡብ ኮሪያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት በስልጣን መባለግና በሙስና ቅሌት በቁጥጥር ስር ዋሉ

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

በደቡብ ኮሪያ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ለመሆን የበቁት ፓርክ ጉን ሄ (Ms Park Geun-hye) በሙስና ቅሌት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታወቀ።

በማርች 10 ቀን 2017 እኤአ ከሙስና ቅሌት ጋር በተያያዘ ክስ ፕሬዝዳንት ፓርክ ጉን ሄ (Ms Park Geun-hye) ከስልጣናቸው እንዲወገዱ መደረጉ ይታወሳል።

ፓርክ ጉን ሄ  (Ms Park Geun-hye) ስልጣናቸውን መከታ  በማድረግ የተለያዩ ግዙፍ ኩፓንያዎች በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ለቅርብ ጋደኛቸው  በጉቦ መልክ እንዲሰጡ አስደርገዋል ተብለው ተከሰዋል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት የቀድሞው ፐሬዝዳንት በዚህ ሙስና ቅሌት ውስጥ የተዘፈቁት የቅርብ ጋደኛቸው በፓለቲካው አለም ለዋሉላቸው ውለታ ምላሽ እንደሆነም ተነግሯል።

የአለማችን ግዙፉ ሳምሰንግ ኩፓንያም ከኚሁ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የሙስና ቅሌት ጋር ስሙ ተያይዛል። ሳምሰንግ ኩፓንያ  ወደ 38 ሚሊዮን ዶላር  ለተከሳሽ የቅርብ ጋደኛ ጉቦ እንደሰጠ ሪፓርቶች ያሳያሉ። 

በስልጣን መባለግን ጨምሮ የአገሪቷንና የመንግስትን ሚስጥር በማባከን ክስ ፍርድ ቤቱ የቀድሞው ፕሬዝዳንቷ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ትእዛዛ አስተላልፏል።  

ፓርክ ጉን ሄ  (Ms Park Geun-hye) በደቡብ ኮሪያ ታሪክ በወንጀል ክስ ከስልጣናቸው ከተወገዱ ፕሬዝዳንቶች ውስጥ ሶስተኛ መሆናቸውም ሪፓርቶች ያሳያሉ።

በቀረበባቸው ክሶች በፍርድ ቤት ውሳኔ እስከሚያገኙ ድረስ ተካሳሽዋ በእስር እንደሚቆዩም ለማወቅ ተችሏል።