የኢትዮጵያን መንግስት በመቃወም በጀርመን ፍራንክፈርት ጎዳናዎች የእግር ጉዞ ፕሮግራም ተደረገ (Video)

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ
የተቋውሞውን ቪዲዮ ለማየት ይህንን ሊንክ ይጫኑ

https://www.youtube.com/watch?v=PpjuLNG2DWM

በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የህውሃት አገዛዝ በህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ጭቆናና የመብት ረገጣ በመቃወም የእግር ጎዞፕሮግራም ማድረጋቸው ታወቀ።

በዚህ በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ዛሬ አፕሪል 1 ቀን 2017 እኤአ የተካሄደው የእግር ጎዞ ፕሮግራም አላማው በስልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ አገዛዝ በህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ኢሰብአዊ ድርጊቶች ለምእራባውያኑ በጥልቀት ማሳወቅ እንደነበረም ለመረዳት ተችሏል።

የእግር ጎዞ ታዳሚዎች የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ እያውለበለቡ የተለያዩ  መፈክሮችን በማንገብ በፍራንክፈርት ጎዳና ተቋውሟቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።

ጥቁር ልብስ ለብሰው በቅርቡ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው ቦታ በደረሰው የቆሻሻ ናዳ አደጋ ህይወታቸውን ያጡትን ከ110 በላይ ዜጎቻችንንም ዘክረዋል።

ኢትዮጵያውያን በአገዛዙ የሚደርስባቸውን ግፍ፣ ግድያና የመብት ረገጣ የሚያስረዳ በራሪ ወረቀት በጀርመንኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተዘጋጅቶ ለጀርመናዊያንና ለጎብኚዎች መበተኑን ተገልጿል።

የጀርመን መንግስት የህውሃት አገዛዝ በመላው ኢትዮጵያኖች ላያ እየፈጸመ ያለውን አረመናዊና ኢዲሞክራሲ ድርጊቶች እያየ ከአገዛዙ ጋር የሚያደርገውን ትብብር ቆም ብሎ እንዲያስብበት በዚሁ የእግር ጎዞ ላይ ተጠይቋል።

ከምስራቅ አፍሪቃ ወደ አውሮፓ የሚፈልሱትን ስደተኞች ለማስቆም በሚል ሰበብ የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ መንግስት በንጹሃን ህዝቦች ላይ የሚያደርሰውን ግድያ፣ እስራትና የመብት ረገጣ እያየ እንዳላየ መሆን እንደሌለበትም ለማሳወቅ ጥረት እንደተደረም ለማወቅ ተችሏል።

በኦሮምያ፣ በአማራ፣ በጋምቤላ፣ በኮንሶ እንዲሁም በአዲስ አበባ በአስቸኩዋይ ጊዜ አዋጁ ሰበብ የኢትዮጵያ አምባገነናዊ መንግስት የወሰደውን የግድያና የጅምላ እስራቶችን ለጀርመናዊያኖች ለማስረዳት እንደተሞከረም ተዘግቧል።

ይህ የተቋውሞ የእግር ጎዞ የተጠናቀቀው በስልጣን ላይ ባለው መንግስት በግፍ የተገደሉትን፣ የታሰሩትን ንጹሃን ወገኖቻችንና በቅርቡ በቆሻሻ ናዳ በሞት የተነጠቅናቸውን ኢትዮጵያኖችን በማሰብ በተደረገ የጸሎትና የሻማ ማብራት ዝግጅት ነበረ።