ባለፈው ፣ተጠባባቂ ፓስተር ገመቹ ቸርች ካልወሰድኩህ ሞቸ እገኛለሁ አለኝ፤

” በውቄ እግዜርን ፍለጋ ላይ ነኝ ትል የለ?! ታድያ እግዜርን የምትፈልገው ረከቦት ጎዳና ዳር ቆመህ የሴቶችን ዳሌ በማወዳደር ነውን? ተው ተመከር ተው! አለም አላፊ ነው፤ መልክ ረጋፊ ነው፤”ብሎ ተከዘ::

እኔም መልሼ፤”ስማ! አለም አቃፊ ነው:: መልካችን ሰልፊ ነው:: ችግራችን ሰፊ ነው፤ ጭቆና ተላላፊ ነው:: መንግስት ተጋፊ ነው:: ዛሬ ብርቱ ቢመስልም ነገ ረጋፊ ነው:: እኔን ያስጨነቀኝ የኑሮ ጥፊ ነው”እያልኩ ልቀጥል ስል ደንግጦ አስቆመኝ:: ገመቹ ወደ መንግስተ ሰማይ እንጂ ወደ ቂሊንጦ የመግባት እቅድ የለውም::

በመጨረሻ፣ እሺ ብየ፣ ባቅራቢያችን ወደሚገኘው “ቡበጥ የቅርወ” ወደ ተባለ ቸርች ሄድን:: ለመጀመርያ ጊዜ ፣ በቸርችና በቤተክስያን መሃል ያለው ልዩነት ገባኝ:: ቤትክስያን ማለት ፣ ልክ እንደ ማንኩሳ ሚካኤል ያለ፣ ፍጥረት ሲነጋጋ ጀምሮ የኖሩ በሚመስሉ ሾላ ዛፎች የታጀበ፣በጉልላቱ ዙርያ፣ የሚያንጎላጁ ርግቦች የሰፈሩበት ፣የከርቤ መአዛ ያለው ንፋስ የሚነፍስበት፣ በዝጌር መኖር ባታምን እንኳ፣ ተፈጥሮን ለማድነቅ የምትጎበኘው ቦታ ሲሆን፣ ቸርች ማለት ግን በላብ በትንፋሽና በድምፅ የተሞላ ትልቅ አዳራሽ ማለት ኑሯል::

ደግነቱ፣ እኔና ገመቹ ስብከት ተጠናቆ የፈውስ ፕሮግራም ሊጀመር ሲል ነው የደረስን::

ድንገት ፊቴን ወደ መድረክ ሳቃና ፣ ያየሁትን ማመን አቃተኝ:: መድረክ ላይ ማይክ ጨብጦ የቆመው የቀድሞ መምህሬ ሻረው መሆኑን መቀበል ከበደኝ::

“እንዴ!? ይሄ ሰውየ እኮ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የለየለት ኢአማኒ ነበር:: እኔና ጉዋደኞቼን ከቤተ እምነት ያስኮበለለን ይሄ ሰውየ እንዴት ፓስተር ሊሆን ቻለ?” አልኩ ወደ ገመቹ ዙሬ፤

“አሁን አመለጠ! ከሰይጣን አሰራር አመለጠ! የኔ ጌታ ምን ይሳነዋል?! ገና ብዙ እናያለን” አለ ገመቹ ፣የትንሽ ልጅ ብርድልብስ የሚያክል ፎጣ አውጥቶ በደስታ እንባ የረጠበ አይኑን እያበሰ፤

“ያይን ህመም ያለባችሁ፣ ጆሮ አችሁን የሚያስቸግራችሁ፣ አፍንጫችሁን የሚያፍናችሁ ፣ የጉሮሮ እብጠት የሚያሰቃያችሁ አንዴ ተነሱ” አለ ፓስተር ፤ ሻረው::

ያዳራሹ ግማሽ የሚያህል ህዝብ ወንበር እያተራመሰ ተነሳ።
ህም !! እንዲህ ቁመን ስንሄድ ሰው እንመስላለን እንጂ ፣አንድ ሁለት ቡለን የጎደለው ማሽን ነን እኮ! ብየ ተከዝኩ::

“ወደ መድረኩ ውጡ”

ወደ መድረክ ለመውጣት በተደረገው እሽቅድድም አንድ አራት ሰዎች ወደቁ::

“እግዲህ እናንተ…፤ እዚህ ቦሌ መድሃኒያለም አካባቢ ደረጃውን የጠበቀ ፣ካንገት በላይ ክሊኒክ ተከፍቱዋል:: እዛ ብቅ ብላችሁ ብትታዩ ጠቃሚ ነው እላለሁ፤ አመሰግናለሁ:: “አለ ፓስተር ፣ማለቴ ..ዳስተር ሻረው::

ዞር ስል ገመቹ አጠገቤ አልተገኘም::