ከነገ ባሻገርን በቅርብ እርቀት (ለጠቅላላ ግንዛቤ)

ከነገ ባሻገርን በቅርብ እርቀት ( በመስቀሉ አየለ)

እንደ ጎግል ትንበያ በሚቀጥሉት ጥቂት አስርተ አመታት ውስጥ የሰው ልጅ ዛሬ ላይ ቆሞ ሊያስበው በማይችለው ደረጃ ፕላኔታችን እንደ ካልሲ ተገልብጣ ሌላ መልክ ይኖራታል። በአጭሩ አሁን ሳይንስ ፊክሽን የሚመስሉት ጉድ ትንግርት የሆኑ ነገሮች ሁሉ ሳይንስ ይሆናሉ።

ከሁለት አመት ቦሃላ ኬብል የሚባል ነገር በሰፊው ወደ መቃብር የሚወርድበት ሁሉም ነገር ዋየር-ለስ (wireless) የሚሆንበት አመት ሲሆን የ “3D” ቴክኖሎጅን በመጠቀም የሰው ልጆችንን ዋና ዋና የሰውነት ሆድ እቃዎች ወይንም ኦርጋን በይፋ በማምረት በገበያ ሸልፍ ላይ መደርደር የሚጀመርበት የመጨረሻው መጀምሪያ ይሆናል ብለዋል።

እንደ ነጮቹ አቆጣጠር በ2020 ዓም ላይ ሰማኒያ አምስት በመቶ የሚሆነው የአለማችን ህዝብ የኢንተርኔት ተጠቃሚ የሚሆን ሲሆን በ2024 ገበያ ላይ የሚቀርቡ መኪኖች በሙሉ ማይክሮ ችፕስ የተገጠመላቸው እንደሚሆኑም ስምምነት ላይ ተደርሷል። አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስን በተመለከተ በ 2030 ዓም ከሰው አእምሮ ጋር በመጣመር (integrated) በይፋ የኑሮ ዘዴያችን አካል ይሆናል።ይኽም ማለት አርቲፊሻል ኢንተሎጀንስ ችፕሱን በሰው ልጆች ጭንቅላት ውስጥ በማስገባት፣ ኒውዮኮርቴክስ ከተባለው የአንጎላችን ክፍል ጋር ብሎም ከአይክላውድ ( i-cloud ) ጋር በማገናኘት ምንም ነገር ማስታወስ ሳያስፈልገን ማናቸውንም በጎግል ውስጥ ያለ ተዝቆ የማያልቀው እውቀት ተጠቃሚ የምንሆንበት ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ነው።

እንደ ዝርዝር ዘገባው የሰው ልጅ እስካሁን መፍትሄ ያላገኘላቸውን ገዳይ (deadly) በሽታዎች በሙሉ በ2035 ዓም ላይ በቁጥጥር ስር በማዋል ሳይንስ “በሽታ ወይንም ስጋ ደዌ” በተባለ የሰው ልጅ ታሪካዊ ጠላት ላይ ይነግሳል።

አሁን ባለው ፍጥነት ሲሰላ በ 2040 ዓም ላይ የሰው ልጅ ቁጥር ወደ አስራ ሁለት ቢሊዮን የሚጠጋ ሲሆንበ 2050 ዓ ም ላይ ለፕላኔታችን እራሱን የቻለ ቫን አለን ቤልት በመገንባት መሬትን ከአስትሮይዶች ጥቃት ለመከላከል የሚያስችለው አቅም ይፈጥራል።
ይኽ የአሁን ትንብያ ከሃያ አመት በፊት ከነበረው ቅድመ ትንበያ ጋር ሲነጻጸር በ 20 አመት ላይ ግማሽ ያህሉ ጫካዎች ሙሉ ለሙሉ ከምድረ ገጽ እንደሚጠፉ፤ አለም በከፍተኛ እረሃብ፣ የአየር ብክለት፣ ድርቅና የጎርፍ ማጥለቅለቅ እንደምትጠቃ እና በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን አጋሽ ላይ ከስድስት መቶ ሚሊዮን በላይ ሰዎች አደገኛ በሆነ ድርቅ ሰለባ እንደሚሆኑ ነበር የገለጠው።