“አጥሚት በገንፎ ይደገፋል” ከንገረኝ እንግዲህ ማንም ነኝ

0

[email protected]

“ስድስት ወር ሙሉ እንቅልፍ ዝር ሳይልብኝ እንዴት መኖር እችላለሁ?” በማለት ከተጋደመበት አልጋ ላይ ፍንጥር ብሎ ተነሳ:: ቀና ሲል የተጨማደደ ምርጊት ፊቱ ከመኝታ ቤቱ መልበሻ መስታወት ጋር ተፋጧል። ወትሮም ልምጭ የሚመስለው የፊቱ ገጽታ እንደ አባጨጓሬ በጺም ተሸፍኗል። ከመቅጽበት ገጽታው ልውጥውጥ ብሎ ራሱኑ አጨንቁሮ ሲመለከተው “ምን ታየኛለህ!” በማለት ምስሉ ላይ አፈጠጠበት። በመስታወት ውስጥ በህይወት የመኖር ትርጉሙ አልገባው አለ። ከሞላው ጎጆ አውጥቶ ፌስ-ቡክ በረሃ ያስገባውን ምክንያት ተመለከተ። እንደተለመደው የመንፈቅ ድርጊቱና የህሊና ጥያቄዎቹ ቀስረው ያዙት። በእንቅልፍ እጦት ምክንያት እንደ ደረቀ ሸንበቆ የሚንቋቋ ወገቡን በእጁ ደገፈ። ዝልፍልፍ ያሉ እግሮቹን ለመዘረጋጋት እየሞከረ አልጋውን ዞር ብሎ ተመለከተ።
ተስፋ በቆረጠ አንደበት፣
“መኝታዬ እንኳን የጭንቀቴ እንጉርጉሮ ያቃልልኛል ብልም መጽናናት አላገኘሁም። ይልቁንስ እንቅልፍ የማላገኝበት የድካምና የሃዘን ሌሊት ሆነብኝ። ፊቴም ከተስፋ እጦት ምክንያት ገረጣ።ለካንስ ተስፋ ለመንፈስ ብቻ ሳይሆን ለስጋ ጥንካሬም ፍቱን መድሐኒት ነው። ተስፋ ሳጣ እውነትን ገደልኳት። የህሊናዬ መዳጨት ተክለ- ሰውነቴን የቦና ጥጃ አስመሰለው። ከቀን ወደ ቀን ገጽታዬ አጥሚትና ሙቅ የምሰራበት የወይዘሮ “ምነውሸዋ” ድስት አስመሰለኝ። ወይኔ! እኔ የአማራ ተነስ! ተቀመጥ መሪ…ወይኔ! እኔ የአዲስ አበባ ልጅ!” በማለት እየተናገረ ኮስሞቲክስ የተደረደረበትን መልበሻ በጡጫ ደበደበ። ጭንቅላቱን ቁልቁል በመስደድ ከእንጨቱ ጋር ደጋግሞ አላተመ። ከድሮው በመቶ እጥፍ ፈሪና ድንጉጥ እየሆነ መሄዱ ይበልጥ አናደደው። የንዴቱ ጥላ ከፊቱ ላይ ውልብ አለበት። አይኖቹን ጨፈነ። ማታ ማታ እንደ ጅብ ተጠራርተው የሚረባረቡበትን የአሁኑ የትግል አጋሮቹን አሰበ
ለጥቂት ጊዜ ዝም አለ።
ትንሽ ቆይቶ ደስ አለው።
ደስያለው አንዳንድ ወዳጆቹ ለቁመናውና ጢሙ ድጋፍ በመሆናቸው ነበር። ከነጻነት ታጋዩ ቼጉቬራ ጋር መልኩ እንደሚመሳሰል ስለነገሩት ነበር። የተቀሩት ደግሞ ሰሞኑን በትግራይ አሉላ አባነጋ ት/ቤት ከተለጠፈው የመለስ ዜናዊ ፎቶ ጋር ሊያዛምዱት ሞክረዋል። እንደ ተክሌ ይሻው አይነት የመላኩ ተፈራ ወዳጆችና የፕሮፌሰር አስራት ጠላቶች ደግሞ “የአዲሲቷ አማራ ቦልሼቪኩ መሪያችን ምስል” በማለት አወድሰውታል። በሞረሽ “የመተካካት ፖሊሲ” መሰረት በአዲሱ የፈረንጆች አመት ሊ/መንበርነቱን እንደሚሰጡት ቃል ገብተዋል። ወጣቱ አክቲቪስት የተክሌ ይሻውን ንግግር እያስታወሰ “ቃል የእምነት እዳ ነው!” በማለት ተናገረ። የእሱ ፎቶ በቼጉቬራና መለስ ዜናዊ ፎቶ ጋር ተዛምዶ መነሳቱ ብርታት እንደሚሰጠው አሰበ።

ይህም ሆኖ በአእምሮ ውስጥ ከሚንከላወሰው ጩኸትና ቱማታ በቀላሉ ሊላቀቅ ስላልቻለ ሩብ ደርዘን የእንቅልፍ ኪኒና ከብልቃጥ አውጥቶ አፍ ውስጥ ሞጀረው። ለህዝብ ያበረከተው የግጥም መድብል መቅድም ላይ “ማንም ነኝ” በማለት ራሱን የገለጸበት አባባል በአይነ ህሊናው መጣበት። አፍታም ሳይቆይ መድሐኒቱን ከሰውነቱ ለማውረድ ውሃ ፍለጋ ወደ ማእድ ቤት መጓዝ ጀመረ። ሁለት እርምጃ ሳይጓዝ ቤቱ ወለል ላይ የተደፋው አጥሚት አዳልጦት መሬቱ ላይ በግንባሩ ተደፋ። አወዳደቁ መጥፎ ስለነበር ግንባርና ከንፈሩ መለስተኛ ስንጥቃት ደርሶበት ደሙ ወለሉ ላይ ፈሰሰ። በተጨማሪም የግራ እጁ ጡንቻ ላይም ምድጃ ላይ የተዳጠው የአጥሚት ብረት ድስት አቃጥሎታል:: አለም ጨልማ ታየችው።
በወደቀበት ተቀምጦ ለማስታወስ ሲሞክር ለካስ ለመንፈስ ጭንቀት የሚወስደውን ትራንኳላይዘር እና አንቲዲፕሬሳንት መድሐኒት አልወሰደም። የጡንቻዎቹ መወጣጠር፣ የልብ ምቱ መጨመር፣ የራስና የደረት ህመም የተሰማው ሰሞኑን ሰአቱን ጠብቆ ባለመዋጡ መሆኑን ተገነዘበ። ዘወትር የሚጎበኛት ሳይካትሪስት መዳኒቱን እያቆራረጠ ከወሰደ ምን አይነት ምልክቶችን ሊያሳይ እንደሚቻል የነገረችውን ለማስታወስ ሞከረ። ተስፋ መቁረጥ፤ እንቅልፍ ማጣት፤ እራስን እንዳስፈላጊው ፍጡር በማየት የመገለል ስሜት መሰማት፤ የወሲብ ፍላጎት መቀነስ፤ ከፍተኛ የጥፋተኝነት ስሜት መሰማት፤ ሊገለጽ የማይችል “አልቅስ አልቅስ” የሚል ስሜት መኖር፤ ራስን አለመቆጣጠር፣ መቅበዝበዝና ራስን ለማጥፋት ማሰብ…የመሳሰሉትን እንደሆነ የእጁን ጣቶች እየቆጠረ አስታወሰ። ከእነዚህ ምልክቶች ውስጥ ስንቶቹ በእሱ ላይ የሚታዩ እንደሆነ ዘረዘረ። ሰማንያ በመቶ የሚሆኑት ሳይወድ ጨምድደው በቀኝ ግዛት ይዘውታል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ለጭንቀቱና ስጋቱ ማስታገሻ የሚወስደው ዲያዝፓም መድሃኒት ሌሎች መዘዞችን ይዞበት መጥቷል። የመርሳት በሽታ። ትላንትና የጻፈውንና የተናገረውን የመርሳት በሽታ!!-…በቅርብ ቀን አንድ በኢንተርኔት የሚተላለፍ “አዲስ ድምጽ” የሚባል ሚዲያ ትላንትና የጻፈውን ሲጠይቀው ምን አይነት ምላሽ እንደሰጠ አስታወሰ። “ረስቼዋለሁ” ብሎ በድፍረት ከመናገር ይልቅ ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ “ጌታዬ ባለጌ ነህ! ጌታዬ ባለጌ ነህ” ማለቱ ለራሱ አሸማቀቀው። ባለፉት ጥቂት ወራቶች ውስጥ ምን ያህል የአማራን ስም እየጠራ ኢትዮጵያዊነትን እንዳላጥላላና አንድነትና ኢትዮጵያዊነትን የሚሰብኩትን ሁሉ ጸረ አማራ እንደሆኑ አድርጎ እንዳላደነቆረን ሁሉ ከናካቴው ርስት አድርጎት ብላቴናው ከሰሞኑ “ኢትዮጵያ” በማለት የለቀቀውን ነጠላ ዜማ “ለዘረኞችና በዘውግ ለተለከፉ መድሀኒት እንደሆነ” እነደውም “ሲዲው በፋርማሲ ሁሉ መሸጥ እንደሚገባው” በፌስቡክ ገጹ ላይ ሲሰብከን ጣቶቹን አላደናቀፋቸውም::

ወጣቱ “የአማራ ተነሳ! ተቀመጥ አክቲቪስት” እንደምንም ከወደቀበት ተፍጨርጭሮ በመነሳት ፊቱን ታጠበ። ስንጥቃቱን በአልኮል አከመ። ግንባርና ከንፈሩን በፕላስተር ዘለግ አድርጎ ለጠፈ። ምንም እንኳን ከውስጡ ጋር የሚታገለው ፍርሀት እንደ ወባ ቢያንቀጠቅጠውም ለከፈተው የጦር አውድማ እና አዛዥ ለሆነበት ክፍለ-ጦር የስራ ምልክት ሆኖ እንዲያግዘው እንደ ምንም ትንፋሹን ለሰከንድ ዋጥ አድርጎና ፊቱን ውሀ ውስጥ እንደገባ ጋቢ ጭምድድ አድርጎ አኮሰታትሮ ጀግና ለመምሰል ፎቶ ተነሳ። ባለ ሶስት እይታውን (3D) ፎቶ አሰማምሮ በፌስቡክ ላይ ለጠፈው። ይህ ሁሉ እልህ አስጨራሽ ስራ ሰርቶ የገባበት ንዴት አልበርድ ስላለ በድቅድቅ ለሊት ጮክ ብሎ ዛቻና መፈክር ቀላቅሎ አሰማ። ጥሎበት ዛቻ፣ መፈክርና ግጥም ድምጽን ከፍ አድርጎ ማሰማት ይወዳል።

“የጠላቶቼን ሞት ሳላቃርብ ከሞትኩኝ ሞቴ አንድ ሞት ሳይሆን አስር ሞት ይሁን!! ህልሜን ማሳካት ካቃተኝ እኔ የወንዶች ወንድ: የ40 ሚሊዮን አማራ ወኪል! የሺ ሰው ግምት የወደፊቱ ሞረሽ ሊ/መንበር መባሉ ይቅር!…ወይኔ የኮከብ ልጅ! …በያዝኩት ብእር ድንጋይ ጨምቄ ውሃ የማጠጣ።… በቀጭኑ አንደበቴ “ጌታዬ” እያልኩ በሬ አስወልጄ ወተት የማሳልብ!!….ወይኔ የኮከብ ልጅ!…የመርካቶ ሰባተኛ እና የጣሊያን ሰፈር አራዳ!!” በማለት አቅራራ። ከዚህ ቀደም በድሮ አድናቂዎቹ ዘንድ ቆሞ ያሰማውን ግጥም በቃሉ ወረደበት። ሲያጠቃልል “አማራ ወይም ሞት!” በማለት ግራ እጁን ወደላይ አወጣ። የጎጃሙ ቆምጬ አምባው ትዝ ብሎት የመፈክር እጅ ቅያሪ አደረገ። ከግራ ወደ ቀኝ። የተበላሸ አካሄድ መስተካከል ስላለበት ቀኝ እጁን ለመፈክር አውጥቶ “አማራ ወይም ሞት!” በማለት ፎከረ። “አባት ሀገር አማራ ወይም ሞት!” በማለት ደገመው።
ለጥቂት ጊዜ ዝም አለ።
ትንሽ ቆይቶ ደስ አለው።

ደስ ያለው ምክንያት አውደ- ጦርነት በተከፈተ የፌስቡክ በረሃ ጦርነት ድል እየተቀዳጀ መሔዱ ነበር። የተከታዮቹ፣ የሼሩ፣ የላይኩና ኮሜንቱ ቁጥር ከእለት ተእለት እየጨመረ ሔዷል። አዋጊ ኮማንደር በመሆን አውደ-ጦርነቱን በከፈተ በጥቂት ወራት ውስጥ በአንደኛው አካውንቱ 44ሺህ ተከታዮች፣ በሌላኛው አካውንቱ 89ሺህ ላይከሮችና በሶስተኛው አካውንት 10ሺህ ተከታዮች አፍርቷል። ይፋ ባላደረጋቸው አካውንቶች ባለሁለት አሀዝ እድገት አሳይቷል። እርግጥ አንዳንድ ጊዜ ከቀልቡ መሆኑ ሲያቅተው በድብቅ አካውንቱ በሚሰጠው ምላሽ ማንነቱ በቀላሉ ሊደረስበት መቻሉንም ተመልክቷል።

ከዚህ በተጨማሪ ላይክ፣ ሼርና ኮሜንት የሚያደርገው ከመጣጥፍ ይዘት አንጻር ከፍና ዝቅ ሲል ተመልክቷል። ግንቦት ሰባትን ኢሳትንና እንዲሁም ለኢትዮጵያ ደማቸውን ሰጥተው የራሳቸውን እዳ የከፈሉትን ከሰደበ በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። የቁም ግራፏም እየተምዘገዘገ ወደ ሰማየሰማያት ይነጉዳል። የፌስቡክ የበረሃ ትግሉም ይግማል። ብርሃን የሚፈሩት የፌስቡክ የጨለማ እጆች በንዴት ውስጥ ሆነው ጸጉራቸውን ይነጫሉ። የተፈበረከ አዳዲስና የፌስቡኩን ሰማይና ምድር የሚያናውጥ መረጃ ይዘው ይመጣሉ። አስተውሎት በጎደለው ስሜታዊ ዝንባሌ ወጣቱን ጠሃፊ ለማስደሰት ይጥራሉ። የአንዳንዶቹ ሰዎች ከልክ ያለፈ ሙገሳ ከጊዜያዊ ጭንቀቱ ይገላግለዋል። “ወንዝ አይፈሬ ጥለት” የሆነ ይመስለዋል።

ይህም ሆኖ የፌስቡክ በረሃ አርበኛው ወጣት ቅር የሚሉት ነገሮች አሉ። ለምሳሌ በፍልሚያው ሜዳ ከሚሳተፉና ላይክ ከሚያደርጉት ተከታዮች ውስጥ ዘጠና ዘጠኝ ፐርሰንቱን አያውቃቸውም። እርግጥ የወያኔ የፊስቡክ አመራሮችና አባላት ከአስር ዘጠኙ እንደሚሆኑ በጥናት ደርሶበታል። እሱ ለሚጽፈው ከፋፋይ፣ ዘረኛ፣ ክብረ-ነክና ሁሉንም ሰው በጠላትነት የሚፈርጁ መጣጥፍ የፊት መስመር ሰርተው እርስ በራስ እየተቃረኑ ሲፏከቱ የሚውሉት እነሱ መሆናቸው በደንብ ገብቶታል።

ከእነዚህ የወያኔ የፊስቡክ አባላት ውስጥ ከፊሎቹ ከሂትለር አስበልጠው ያጀግኑታል። ዘረኝነቱን ከሱ ተቀብለው የበለጠ ይዘሩታል:: ሞት የማይፈራ አማራዊ ጀግና እንደሆነ ይገልጡለታል። የሰሜኑን ኮከብ መነሻ ሃሳብ ይበልጥ በመለጠጥ “ትግሬ በሙሉ የአማራ ጠላት ነው፤ ግንቦት7 የአማራ አመራር የለውም፤ ሌንጮ ለታና ብርሃኑ ነጋ አማራን ረግጠው ለመግዛት ያስባሉ፤ ኢሳት የአማራን ስም ሳይጠራ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ሸዋ የሚለው ጸረ- አማራ ስለሆነ ነው…“ በማለት ያጫጩሁታል።
አስተያየታቸውን ሲጨርሱ ደግሞ “አማራ ተነሳ! አማራ ንቃ!” የሚል ሃሽታግ ያሳርፋሉ። የሰሜኑን ኮከብ እስከ ማምለክ እንደሚሄዱና ነጻ የሚወጡት በእሱ መንገድ ብቻ መሆኑን ይፋ ያደርጋሉ። ከወጣቱ ጠሀፊ ሃሳብ በተቃራኒ ያለውን ሙልጭ አድርገው በመሳደብ የእንግዴ ልጅ እንደሆነ ይገልጻሉ። ወያኔ የወደቀ እንጨት በመሆኑ ምሳሩን እሱ ላይ ከማድረግ ይልቅ በአማራው ጠላት በአርበኞች ግንቦት 7 ላይ መሆን እንደሚገባው ምክር ይሰጣሉ። በሚሰጡት ምክር ልቡን ያቆሙታል።

የተቀሩት የወያኔ የፌስቡክ ሰራዊት አባላት ከወጣቱ የአማራ ተነስ! ተቀመጥ! መሪ ተጻራሪ በመሆን “አማራ እንዳያንሰራራ አድርገን ከቀበርነው ቆየን፤ ተልባ ቢንጫጫ በአንድ ሙቀጫ፤ አማራ የሚባል ማንነት የለም፤ የጎንደር ኢሰፓ አመራር፣ የመላኩ ተፈራ የስራ ባልደረባና የሰርቶ አደር ጋዜጣ አዘጋጅ የነበረው ተክሌ ይሻው ለታሪክ ፍርድ ይቅረብ!!፤ ሞረሽ ከተክሌ ይሻው ውጭ አባላት የሉትም” የሚሉ ጭቅጭቆችን ያስቀጥላሉ። በማጠቃለያቸው የአማራውን ህዝብ ለመርገጥና የትንኝ ያህል ክብደት እንደማይሰጡት ለማሳየት ይሞክራሉ።

እርግጥ በሁለት የወያኔ የፌስቡክ ሰራዊት አባላት መካከል በሚካሄደው ቅጥፈታዊ የቦካ ጠብ ተቃዋሚውም በንዴት ኣንደሚጨምሩ የሰሜኑ ኮከብ ተመልክቷል። አንዳንዶቹ ወደ ቀልቡ እንዲመለስ ምክር ቢጤ የሚሰጡና ሽንፍላውን ሊያጥቡለት ሲሯሯጡ ተመልክቷል። ሌሎቹ የሰሜኑ ኮከብ ዘመድና ጓደኛ ካለው “ሰባት ጸበል” መመታት እንዳለበት የምራቸውን የጻፉትን አንብቦ ትክክለኛነቱን በውስጡ አረጋግጧል። “ምክራቸው ጥሩ ነበር። ነገር ግን ሽንኮራም ሆነ ደብረሊባኖስ ለመሄድ ድርድሩ ማለቅ ይኖርበታል” በማለት ተናገረ።

“ወጣቱ ጠሀፊ” የሙት ሙቱን ወደ ማቀዝቀዣው በመሄድ ወለል አድርጎ ከፈተው። የፍሪጁ ሽታ ደስ አላለውም። እንደዚህም ሆኖ ባዶ ነው። ጠላቱ ይደንግጥ ክው ብሎ ቀረ። ቆሌው ተገፈፈ። በማቀዝቀዣ ውስጥ አመሻሽ ላይ ከሰራው “የማሪያም ምሳ” እና “ሙቅ” ውጪ ምንም ነገር የለም። አይኑን በፍሪጅ አይን ላይ ከወዲያ ወዲህ ቢያቁለጨልጭ ጠብ የሚል ነገር አጣ። የታጠፈ አንጀቱ እርር ኩምትር አለ።
ለጥቂት ጊዜ ዝም አለ።
ትንሽ ቆይቶ ደስ አለው።
“ወይኔ እኔ የአማራ ተነሳ! ተቀመጥ መሪ!…ወይኔ እኔ የሰሜኑ ኮከብ…ዝናር የሌለው ነፍጠኛ፣ አለንጋ የሌለው ፈረሰኛ ሆንኩ?” እስከመቼ የበላሁበትን ወጭት እየሰበርኩ እኖራለሁ?”…እስከመቼ የሰላም እንቅልፍ ሳልተኛ እኖራለሁ?….እስከመቼ በህሊና ጸጸት እየተገረፍኩ ቀንና ሌቱን እገፋለሁ? በማለት በውስጡ ተናገረ::

አፍታም ሳይቆይ ወትሮ በተለያየ ጊዜ ሲያከብርቻው ከነበሩት ግለሰቦች መካከል እንደ አንደኛው ሰውየ የተጎናጸፈው ዝና ለእሱም እንዲሆን የሚመኘው ጓደኛው በውስጥ መስመር መጥቶ “እጸድቅ ብዬ ባዝላት ተንጠልጥላ ቀረች፤ ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ፤ ባንድ ራስ ሁለት ምላስ” በማለት በተለያየ ጊዜ የጻፈለት ትዝ አለው። እንዲሁም ሌሎች ወዳጆቹ የነበሩትም ለእጅና ምላሱ ልጓም ካላበጀለት ከሌላው ቀርቶ ከራሱ ጋር ታርቆ መኖር እንደማይችል በተደጋጋሚ አስጠንቅቀውታል። ይሔ አጓጉል ድፍረቱና መንታ ምላሱ አንድ ቀን እንደሚያዋርደው ነግረውታል። “እኔ” ከሚል በሽታ መላቀቅ ካልቻለ የራሱን ነብስ ሊያጠፋ እንደሚችል መክረውታል። በሳንሆዜ የምገኙ የኪነ-ጥበብ ሙያተኞችንም በተለያየ መንገድ ወያኔን የሚታገሉ ሰዎች በመከፋፈል “እከሌ ወያኔ ነው!” በማለት የሚጽፈውን እንዲያቆም ምክር ቢጤ ለግሰውታል።

ይህም ሆኖ የሰሜኑ ኮከብ ምክሩን ሊቀበል አልቻለም። የደብተራ ባህሪውም ተግሳጽና ምክር ለመቀበል አይፈቅድለትም። ለሁሉም ግልጽ እንደሆነው ደብተራ ጊዜያዊ ፈውስ ማምጣት ሲያቅተው ደንበኞቹን መግደል ይጀምራል። በርግጥ ሚስጥረ- ስላሴ ሲገፈፍ መጀመሪያ አደገኛ ጠላት የሚሆኑት ከራሳቸው ጋር ነው። የአምላክነት ስሜቱ ሲጠፋባቸው እንደ እብድ ያደርጋቸዋል። መንፈሰ ቁጡና ብስጩ ይሆናሉ። በዚህ ምክንያት የሰዎች ስቃይና ጭንቀት ለእነሱ የሐሴት ምንጭ ነው።
የሰሜኑ ኮከብ የደብተራ ስራ እየሰራ መኖሩ አበሳጨው።

ወጣቱ “የአማራ ተነሳ! ተቀመጥ! አክቲቪስት” ጠረጴዛውን በቡጢ እየደበደበ “ለምን መረጋጋት አልቻልኩም? መንፈሴ ለምን ይረበሻል? ለምን በሃሳብ ማእበል እንገላታለሁ? ለምን ሁሉም ሰው እንደ ጠላት ይመለከተኛል? ለምን ህዝቡ እንደ በረሃ ንብ ከቦ አሳሬን ያስቆጥረኛል? ለምን ራሴን የቁም እስረኛ አደረኩ? ለምን ዘላለም ማተቤን እየበጠስኩ እኖራለሁ? በህልሜም በውኔም እነሱን መሆን የምፈልጋቸው ሰዎች ለምን ናቁኝ?” በማለት ተናገረ። በሚያነሳና በሚጥለው ሃሳብ በቀላሉ መላቀቅ አልቻለም። ለዚህ የእብደት ህይወት የተዳረገውን የፌስቡክ ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ ፈልጎ በማግኘት ንከሰው ንከሰው አሰኘው። የፈረንጁን ምስል ወደ አእምሮ እያመጣ በጥላቻ አይኑ ተመለከተው። ተስፋ ቆርጦ ወንበሩ ላይ ተመቻችቶ ተቀመጠ። በስለላ አንደበት የቀኝ እጁን በማውጣት “አባት ሀገር አማራ ወይም ሞት!” በማለት መፈክር አሰማ።
ለጥቂት ጊዜ ዝም አለ።
ትንሽ ቆይቶ ደስ አለው።
ደስ ያለው ምክንያት መንፈሱ የተረበሸው፣ በሃሳብ ማእከል የሚንገላታው፣ ራሱን የቁም እስረኛ ያደረገውና ማተቡን የበጠሰው እሱ ብቻ አለመሆኑን ሲገነዘብ ነበር። ደስ ያለው ምክንያት በአሁን ሰአት በአጠገቡ ያሉት የትግል አጋሮቹ እንኳን ዲግሪ ከሶስተኛ ክፍል መዝለል ያልቻሉ መኖራቸውን ማወቅ ነው። መቼም ጠላቶቹ የጋራ ናቸውና በመደበኛ ትምህርት ሶስተኛ ክፍል ያልተሻገረ እየተመለከቱ ዲግሪህን ለፌስቡክ በረሃው ለጥፈህ አሳይ አይሉትም። በጥራዝ ነጠቅነት ከቃረሙት አንዳንድ እንግሊዘኛ በቀር አንድ መጽሀፍ ጨርሰው ያላነበቡት አጠገቡ ተኮልኩለው እሱን የትምህርት ማስረጃ መጠየቅ በማንም አእምሮ ሊመጣ የሚችል አይደለም። ተገቢም አይደለም። ቢሆንም ግን ከጠላቶቹ ሐሜት ለመዳን የትምህርት ማስረጃውን በይፋ ቢለጥፈው ይጠቅመው ይሆናል ኣንጂ አይጎዳውም። አለበለዚያም ፕሮፌሰር ጄኔራል ሳሞራ የኑስን በምሳሌ እያነሳ “ትምህርት ምን ያደርጋል?” የሚል ግጥም ቢጽፍ ይሻለዋል።

“ወጣቱ የአማራ ተነሳ! ተራመድ! መሪ” በድቅድቅ ለሊት በሩን ከፍቶ መውጣት ፈለገ። የሳንሆዜ ገደል- ማሚቴ ጋር ሄዶ በመጮህ የውስጡን ጭንቀት በደብተራ ሰይፉ ቆራርጦ ሊጥለው ፈለገ። በእሳት ሰንሰለት አስሮ ወደ ጥልቁ የፓስፊክ ውቅያኖስ ሊጥለው አሰበ። በአንድ ጊዜ የተሰረቀው የልቡ ደስታ ተመለሰለት። ሸክሙ የወረደ ያህል ተሰማው። ይሁን እንጂ ሀሴቱ ብዙም መቆየት አልቻለም። ገና ወደ በሩ ጋር ሲሄዱ ሌላኛው የሳንሆዜ የፌስቡክ አናብስት ትዝ አለው። ዮኒ ማኛ!። ባለፈው ጊዜ ዮኒ ማኛ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደሰጠው አስታወሰ። “የሳንሆዜ ደርቢ” በእሱና ዮኒ ማኛ መካከል እንዲካሄድ ድፍን የፌስቡክ በረሃ አርበኛ በጠየቀው መሰረት ዮኒ ማኛ ፍላጎቱን ማሳየቱ አስደነገጠው። “ማንያውቃል የደርቢ ግጥሚያው ሳይደርስ ከጓሮ ተደብቆ ድንገተና ጥቃት ሊያደርስብኝ ይችላል” በማለት ለራሱ ተናገረ። የዮኒ ማኛን ማሳሰቢያ መለስ ብሎ ለማስታወስ ሞከረ። ገና የቦክስ ግጥሚያው ሳይደረግ በአጥሚት ብረትድስት የተቃጠለውና በገንፎ ዱቄት የተሰራ ዘነዘና የሚመስለው ክንዱና እንዲሁም በአጠቃላይ መላ ሰውነቱ ዛለ። ሆዱን ሞረሞረው። ለካስ ማታ ወስፋቱ በመዘጋቱ ምክያንት ያሞቀሞቀውን አጥሚት ብቻ ጠጥቶ ነበር ወደ አልጋው የሄደው።
***
ከለሊቱ ዘጠኝ ሰአት ሆነ ::
“ወጣቱ ጠሀፊ” በተለይ መጨረሻ ላይ በየጊዜው ክህደት መፈጠሙና ማህተበ ቢስ በመሆኑ እንዲሁም በትላንት ወዳጆቹ መናቁ እጅግ ከነከነው። ትላንትናን በአይነ ህሊናው እንዲመለከት አደረገው። በአፍላ የስደት ዘመኑ ከየአቅጣጫው የጎረፈለትን አድናቆትና ምስጋና እንዴት አሳብጦት እንደነበር ትውስ አለው። ትላልቆቹ ኢትዮጵያውያን ፊት ለፊቱ መጡ። “ሰው እንጂ ህዝብ አላጣሽም” በሚል ርእስ ዛሬ በሚሰድባቸው ሰዎች ጥረት የታተመለት የግጥም መድብል የጀርባ ሽፋን ላይ አስተያየት የሰጡ ሁለት ምርጥ ኢትዮጵያውያን ህሊናውን ወረሩት። አንጋፋዋ አርቲስት “ከኢትዮጵያዊነት በታች መጥበብ አይችልም ስሜቴ” የሚለውን የግጥም ርእስ መነሻ አድርጋ የጣፈችውና እንደእሱ አይነት ወጣቶች እንዲበራከቱ ምኞቷን ለመግለጽ ያፈሰሰችው የብእር ቀለም ትዝ አለው። የመድረኩ ፈርጥ ደግሞ “ያልኖረበትን ዘመን የመረመረ፣ ከእድሜው በላይ የተጨነቀ” በማለት ያቀረበለት ምስጋና ጭንቅላቱን መታው። ካቀረቀረበት ቀና ለማለት ሲፈልግ ደግሞ በጣም ክብርና ፍቅርን በተደጋጋሚ በግጥምና በሌላ ጽሁፍ ሲለግሰው የነበረው ብላቴና እፊቱ ላይ ድቅን አለበት፡ ከሰሞኑ “ኢትዮጵያ” በሚል ስም በለቀቀው የነጠላ ዜማ “ እንኳን ሰማይ ላይ ባንዲራሽን አይቶ: ኢትዮጵያ ሲባል ማን ዝም ይላል ሰምቶ” በማለት አንድ አመት ሙሉ እንቅልፍና ወዳጅ አጥቶ የጮሀበትን “የአማራ ተነስ ተቀመጥ” መፈክር በኡዚ ጥይት እንደተመታች ወፍ ብትንትኑን አውጥቶበታል:: ዛሬ የጠበበበትን ደረጃ እያየ ትላትና “አርበ-ሰፊ ነኝ! ወጣትነት ዛሬም ኢትዮጵያዊነት” በማለት በኢትዮጵያ ፍቅር ታምሜ ልሞት ነው ብሎ በአደባባይ መደስኮሩ አሳፈረው።

ዛሬ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሁለት አንጋፋ አርቲስቶች አጠገቡ ያሉ አይመስለኝም። ገና ስሙ ሲጠራ እንደሚቀፋቸው ከሩቅ ሆኖ መገመት ይቻላል። የበይነ-መረብ የውጊያ አምድ ከፍቶ የሚያሰማውን ሽለላና ፉከራ ያዳምጣሉ ብዬም አልገምትም። በየጊዜው ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በጎደለው ሁኔታ እየፈበረከ የሚያወጣቸው ለአንደበት የሚከብዱ ቃላት ጤንነቱን እንዲጠራጠሩ እንደሚያደርጋቸው ጠንቋይ መቀለብ አያሻውም። በእርግጥም ወጣቱ ጠሀፊ የሚያሳየው የተቅነዘነዘና ቅጥ ያጣ የተናዳፊነት ዘይቤ ከጤና መታወክ የሚመጣ እንጂ ከሌላ ሊሆን አይችልም። እናም ዛሬ ከማድነቅ ባሻገር ከሚያመልካቸው ሰዎች መካከል ሁለቱ አንጋፋ የመድረክ ሰዎች ከጎኑ እንደሌሉ አሁንም ከሩቅ ሆኖ መገመት ይቻላል። ከፓስፊክ ውቅያኖስ አጠገብ ሆኖ የቅርቡን ማወቅ ባይቻልም።
ለጥቂት ጊዜ ዝም አለ።
ትንሽ ቆይቶ ደስ አለው።
ከንፈሩን ከፍቶ ፈገግ አለ። በጣምም ደስ አለው። ፈገግ ያለው ምንም እንኳን ሁለቱ የመድረኮቹ ፈርጦች እንደሚጠየፉት ቢጠበቅም አጠገቡ ሌሎች የሚደግፉት ሰዎች አለማጣቱ ነበር። እነ ዘጠኝ ስድብ ጎራሽ ሊዲያ ዘ-ወልቃይት እና ፊልድ ማርሻል ተክሌ ይሻው ሁለቱን አንጋፋ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ተክተዋል። ዘጠኝ ጎራሿ ሊዲያ ዘ-ወልቃይት እንኳን ለቆሽማናው ጠሀፊ ቀርቶ ለዘጠኝ ኮምታራዎች የማታንስ የወጣላት ተሳዳቢ እንደሆነች ጠንቅቆ ያውቃል። ጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋውም ሌሎችን ቀድሞ ማክበር ብቻ ሳይሆን ማምለክ የሚቃጣውን ነገር ግን ዛሬ የእሱን የቀንና ሌሊት የፌስቡክ የዘለፋና የአሉባልታ አለንጋ የሚቀምሱትን ጋዜጤኞችን ተክቶለታል። እንደውም ጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋውን አዲሱ የፈረንጆች አመት “ምርጥ የፊስቡክ አክቲቪስት” በማለት የደረጃ ምደባ ሊሰራለት አስቧል:: አፍታም ሳይቆይ እጁን ዘርግቶ “የጥፋት ዘመን” በሚል ርእስ ሙሉቀን ያሳተመውን መጽሀፍ ከመደርደሪያው ላይ አንስቶ ማገላበጥ ጀመረ።

“ወጣቱ ጠሀፊ” ከተቀመጠበት በደመ-ነብስ ብድግ አለ። ከግጥም መድብሉ ውስጥ “ሰው እንጂ ህዝብ አላጣሽም” እና “ንገረኝ እንግዲህ” የሚለውን ክፍል አወጣ። “ነገረኝ እንግዲህ” የሚለው የግጥም ክፍል የጉም ሽንትነቱን በሰነዶች ስለገለጠለት በደመ-ነብስ ገነጠለው። ሌላ ሰው ሳይነግረው የራሱ ልበ-ህሊና ስለማንነቱ ስለነገረው በአንድ ጊዜ ከንፈሩና እጁ ተንቀጠቀጠ። አይኑ ያለእረፍት ተርገበገበ። ተነስተህ ብረር፣ ብረር የሚል ስሜት አደረበት። ግን ደግሞ በድቅድቅ ለሊት ወዴት ይሄዳል። እንደምንም ጥርሱን ነክሶ “ሰው እንጂ ህዝብ አላጣሽም” ከሚለው ክፍል ላይ የከተበውን ለይቶ አወጣ። ጮክ ብሎ ከፊል ግጥሙን አነበነበ።
የኔ ስሜት ለዘር ድግስ
ለዘር ወጣወጥ በድን ነው
ከኢትዮጵያዊነት በታች መጥበብ አይችልም ስሜቴ
አርበ-ሰፊ ነው ቆዳዬ ማደሪያ የሆነው ለትብቴ።
“የሰሜኑ ኮከብ! ወደ መኝታው ለመሄድ እየተነሳ ከሰአታት በፊት ለፌስቡክ የጦር አውድማ አባላቶቹ የጻፈው መልእክት ትዝ አለው። የወዳጅና የጠላት ሰራዊት መልእክቱን ምን ያህል እንደተረዱት ለማወቅ ጉጉት አደረበት። የተደራጀው ክፍለ-ጦር ምን ያህል ላይክ እና ሼር እንዳደረገው መቆጣጠር እንዳለበት አሰበ። የተሰጡትን አስተያየቶች ለማንበብ እንደ ወትሮው ቋመጠ። ሃሳቡን ተከትሎ የወገን ጦር በወሰደው ስምሪት ምን ያህል የጠላት ሃይል አከርካሪው እንደተመታ፤ አሊያም አፈግፍጎ እንደሆነው መረጃውን ማጠናቀር እንደሚገባው ተገነዘበ። ስልኩን እየነካካ ትዝ ሲለው ሳምንታዊው “የአማራ ንቃ! አማራ ተነሳ!” የንቅናቄ ኮሚቴ መሪዎች የሚሰበሰቡትና ሪፖርት የሚያዳምጡበት ቀን ነው። ይህ የደለንቲ ስብስብ የሆነ ንቅናቄ በስትራቴጂክ ጉዳዮች ማሰብና ማቀድ ስለማይችል በእለቱ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ያውቃል።

በትክክልም ስለ ስትራቴጂና ታክቲክ ከማሰብ በፊት ራእይ ይቀድማል። ራእይ ለመንደፍ ደግሞ የትላንት፣ የዛሬና የነገን ሁኔታ መመርመር የሚያስችል የትምህርት ዝግጅትና እውቀት ያስፈልጋል። እንዲህ አይነት እውቀት ደግሞ እንደተለመደው አዋቂ መስሎ ለመታየት ከሚደረግ ከቃላትና ጥቅስ ድርደራ፣ ከደብተራ አይነት አነብናቢነትና ደጋሚነት መላቀቅ ይጠይቃል። “በሽታውን ያወቀ መድሀኒት አያጣም” እንደሚባለው የራስን ማንነትና ችግሮች ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል። ማፈራረስ፣ ልዩነትን ማስፋት ቀላል መሆኑን ተረድቶ በመተማመንና መከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነትን ለመመስረት መትጋትን ይጠይቃል። በታታኝ፣ አንዱን ከፍ ሌላውን ዝቅ ከሚያደርግ ቀኖናዊ አመለካከት ተላቆ የእርቅና የመቻቻል እሴቶችን የሚገነባ እውቀት ያስፈልጋል። ከመሰሪነት፣ ራስን ብቻ ከማስቀደምና እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ የሚል አስተሳሰብ በመላቀቅ በጋራ መስራት አማራጭ የሌለው መሆኑን ማወቅ ይጠይቃል።

እርግጥም በፊልድ ማርሻል ተክሌ ይሻው የሚመራው ንቅናቄ ቤተክርስቲያን እንዴት አድርጌ ልሰነጣጥቅ ከሚል በስቴፕለር ከተበሳ ወረቀት ቀዳዳ አይነት ጠባብ አስተሳሰብ ወጥቶ የስትራቴጂና ታክቲክ እንዴት ሊያስብ ይችላል?…በርግጥም የሞረሹ ፊተውራሪ የስኳር በሽተኛ በሆነ ቄስ ላይ ሁለት ቀን በር ዘግቶ ህይወት እንዲጠፋ ሙከራ ከማድረግ ተሸጋግሮ እንዴት ስለሁለንተናዊ የጋራ እይታ ያለው ራእይ ሊታሰበው ይችላል?…እውነትም የመላኩ ተፈራ የስራ ጓድ እየረገጡ ከመግዛት አስተሳሰብ ወጥቶ እንዴት ዲሞክራሲያዊ ባህል እንዲጎለብት ያደርጋል?…በትክክልም ራሱን “ከመሸ ነጋ” ማላቀቅ ያልቻለ ሰው እንዴት ብሎ ግልጽ ግቦችንና ቅደም ተከተሎችን አውጥቶ ሊንቀሳቀስ ይችላል?…በርግጥም የሚሰሩ ሰዎችን ማዋከብ፣ መዝለፍና ማንጓጠጥ ባህሉ ያደረገ ሰው በምን መመዘኛ ውጤታማ ስራ ለሚሰሩ ተገቢውን እውቅና ሊሰጥ ይችላል?…በአጠቃላይ ራሱ አባል ራሱ ስራ አስፈጻሚ ራሱ ገንዘብ ያዢ ራሱ ኦዲተር ራሱ የህዝብ ግንኝነት ራሱ ጸሀፊ እና እራሱ ሊቀመንበር የሆነበትን ብቸኛ ግለሰባዊ ድርጅት የሆነውን ሞረሽን እንደ ዶሮ እንቁላል ታቅፎ የተቀመጠ ግለሰብ እንዴት አድርጎ ነው ከሌሎች ጋር አብሮ ስለሚሰራበት ሁለተናዊ ድርጅት ማሰብ የሚችለው? ሀቅ ሀቁን ለመናገር ሞረሽን በፖለቲካ ድርጅት ሳይሆን በበጎ አድራጎት አድራጎት አደራጅቶና የኑሮው መሰረት አድርጎ የሚንቀሳቀስ መሪ እንዴት አድርጎ ተተኪን ስለማፍራት ሊያስብ ይችላል??

“የሰሜኑ ኮከብ” ከተክሌ ይሻው ጋር ያደረገውን መቀናጆ እያሰበ “በሬ ካራጁ ይውላል” በማለት ተናገረ። መቀናጆው የፊጋና ያረጀ በሬ አይነት ሆኖ ተሰማው። የመቀናጆው መነሻ ስሜትና የመጨረሻው መዳረሻ የጠላቴ ጠላት በሚል ብሂልና ማጠቃለያውም እርስ በራስ የመበላላት እሳተ ጎመራ የሚያስነሳ እንደሆነ ከወዲሁ ደመ-ነብሱ ነግሮታል። ተክሌ ይሻው የአማራን ፖለቲካ ከጨበጠ ውጤቱ የዜሮ ድምር ፖለቲካ እንደሚሆን ገብቶታል። አጥፍቶ መጥፋት የሚታይበት “አብዮታዊ እርምጃ” ይሆናል።

ያም ሆነ ይህ “የአማራ ተነሳ! ተቀመጥ! መሪ” ለንቅናቄው ኮሚቴ አባላት የፌስቡክ በረሃውን አውድማ ሪፖርት ማቅረብ እንዳለበት ተነግሮታል። በጥያቄም ሊያጣድፉት እንደሚችሉ ተገንዝቧል። በተለይም “ዘጠኝ ስድብ ጎራሽ ሊዲያ ዘ-ወልቃይት (ዘ-ቁጭራ) **አማራ”፥ “ተጋዳሊት ርስቴ”፣ “ኮለኔል መሳፍንት ባዘዘው እንቢተኛው”፣ “የቤተ-አማራ ህልፍኝ ከልካይ”፣ “አስር አለቃ አያሌው መንበር” “አምሓራ ለዘላለም አምሓራ ነው”፣ “ቀናበል አማራ አማራነቴ ኩራቴ”፣ “የአማራ ልጅ ቲጂ”፣ “አጼ ቴዎድሮስ ዘጎንደር አማራ ሳተናው”፣ “ኤደን የመይሳው ልጅ”፣ “የወሎ ልጅ ቆንጆ”፣ “የዞማ አምሃራዊት”፣ “በቀለ ውቤ አርበኛው”፣ “Amhara first”፣ “ አባት ሐገር አማራ”፡ “ አጎት ሐገር አማራ” ወዘተ በጦር አውድማ በረሃ በድጋፍ ሰጪነት ስለማይጠፋ ፋታ እንደማይሰጡት ገብቶታል። ፊልድ ማርሻል ተክሌ ይሻው የፊስቡክ የጦርነት አውድማ “ፌስ ቡክ-101” ኮርሱን ስላልጨረሰ ብዙም አያስቸግረውም።

ከንቅናቄው አመራር ግላዊ ምልከታ ወጥቶ ስለ ወከሉት የህብረተሰብ ክፍልና አባላት ሲያስብ ድንጋጤ ወረረው። በአማራው ስም እንደ አሸን የፈሉትን ድርጅቶች ጣቱን ከፍና ዝቅ እያደረገ መቁጠር ጀመረ። “ቤተ-አማራ”፣ “አማራ መድሕን”፣ “ቤተ-አማራ መድሕን”፣ “ዳግማዊ መአሕድ”፣ “አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (የውጭ)”፣ “የአማራ ወጣቶች የጋራ ንቅናቄ”፣ “የአማራ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ”፣ “ልሳነ ግፉአን የወልቃይት ማህበረሰብ”፣ “ሞረሽ ወገኔ የአማራ ድርጅት”፣ “ጎንደር ህብረት”፣ “ጎጃም ህብረት”፣ “ወሎ ህብረት”፣ “ሸዋ ህብረት”፣ “ብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ”፣ “አማራ ተጋድሎ”፣ “ከፋኝ”…ቆጥሮ መጨረስ አቃተው። ከእነዚህ ሁሉ እንደ አሸን የፈሉ ድርጅቶች እሱን እንደ አባላቸው የሚወስዱ ስለመኖራቸው ጥርጣሬ ገባው። “የአማራ ህዝብ ፍላጎት አንድ ከሆነ እንደ ቅርጫ ስጋ የተከፋፈሉ ድርጅቶች ለምን ያስፈልጋሉ?” የሚል ጥያቄ ውስጡን ወረረው። ስንቶቹ ሀቀኛ፤ ስንቶቹ በወያኔ የተደራጁ፤ ስንቶቹ ውስጥ ወያኔ ወኪል እንዳስቀመጠና ስንቶቹ መሬት የወረደ ስራ እንደሚሰሩ፣ ስንቶቹ ወያኔን ከስልጣን አባረው ስልጣኑን ለመያዝ የተነሱ መሆናቸውን ማወቅ ተሳነው። ግንባሩን በመዳፉ መላልሶ እየደበደበ “በአብዮት ወቅት እብዶችና ወፈፌዎች ይበራከታሉ!” በማለት ቭላድሚር ኢልች ሌኒን ተናገረ የተባለውን አስታወሰ። በተጫማው የወፈፌ መነጽር ሌሎች እብዶችን ተመለከተ። ሁለት ፍሬ አንቲድፕሬሳንት ኪኒና አውጥቶ በደረቁ ቃመ። መድሀኒቱ ደረቱን እየፋቀው ሲሄድ የተሰማውን ህመም እንደምንም ተቋቁሞ “አማራ ወይም ሞት!” በማለት በቀኝ እጁ መፈክር አሰማ።
***
ከለሊቱ ዘጠኝ ከሩብ::

“ወጣቱ ጠሀፊ” በጣም ከፋው:: ከልጅነት እስከ እውቀት እንደ አዲሱ ቴዲ አፍሮ ነጠላ ዘፈን “ኢትዮጵያ” “ኢትዮጵያ” እንዳላለ አሁን ኢትዮጵያን ለካራ ማቅረቡ አሳዘነው። “የሶስት ሺህ ዘመን የደም ያጥንት፤ የሻራ ምልክት” በማለት እየዘመረና አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ አላማን እያወደሰ በታሪክ መስታወት ማየት አለመቻሉ አናደደው። “ኢትዮጵያዊነት እንዲቀጥል ኢትዮጵያ መኖር አለባት” ብሎ መናገር የሚከብደው ጊዜ ሲመጣበት እጅግ ተበሳጨ::“የዛሬው ትግል ማጠንጠኛ በመጀመሪያ ኢትዮጵያን ማዳን ሲሆን እያንዳንዱ ለሁሉም፤ ሁሉም ለእያንዳንዱ ህልውና” የመታገያ ስልት መንቀሳቀስ አለብን ብለው ከሚጎተጉቱት የቀድሞ ጓደኞቹ መነጋገር እንደማይችል በርግጠኝነት መገመት ችሏል።

እናም ከዚህ በኋላ ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ጋር ፎቶ ለመነሳት የሰማዩን ጋሪ ቲኬት ቆርጦ ከካሊፎርኒያ ዳላስ ቴክሳስ መጓዝ አይቻልም። መቼም ከኢትዮጵያዊነት በታች ወርዶ ከፕሮፌሰር አጠገብ መቆም የድመት ያህል ክብር ላይገኝ ይችላል። እቅፍ አድርጎ ግንባርና ጭንቅላት መሳምማ ፈጽሞ የሚቻል አይደለም። መቆጣጠር ቢያቅት እንኳን የውስጥ ብሶትን በእንባ መግለጽ አይቻልም:: ወጣቱ “የአማራ ተነስ! ተቀመጥ!” አክቲቪስት መጀመሪያ አማራነቴ የሚለው አገላለጽ ፕሮፌሰሩ አጥብቀው እንደሚጠየፉት ያውቃል:: ፈልጓቸው የሄደ ጊዜ እንደነገሩት በስማ በለው ሰምቻለሁ። እንደ ወያኔ በህዝብ መካከል ጥላቻን፣ አለመተማመንና የጠላትነት መንፈስን ከሚነዛ አነጋገርና ጽሁፍ እንዲቆጠብ መክረውታል። ከዚህ በፊት አስቦበት የማያውቀው ጉዳይ ስለሆነ “እሺ ጌታዬ!” በማለት ምክራቸውን ተቀበለ። አጠገባቸው ቁጭ ብሎ መጽሃፋቸውን አስፈረመ። ለፌስቡክ የበረሃው ትግል የሚያግዘው ባለ ሁለት እይታ (2D) ፎቶ ተነሳ። ዳላስ ቴክሳስን ሳይሻገር ለጠፈው። ግዛቱን ለቆ ሳይሄድ ብዙ ላይኮች፣ ሼሮችና ኮሜንቶች አስተናገደ። ይሁን ኣንጂ ከወደዱት፣ ከተጋሩትና አስተያየቶቻቸውን ከጻፉት ተከታዮቹ ከዘጠና አምስት በመቶ በላይ “ስም የለሽ” እና የወያኔ የፌስቡክ ሰራዊት አባላት መሆናቸውን ስለሚያውቅ ቅር አለው።

ወጣቱ “የአማራ ተነሳ! አክቲቪስት ቀጥሎ ልቡን የነሳው ሁኔታ ያጋጠመው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ሌሎች ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና ምስጉን ጋዜጠኞችን ሲያስብ ነበር። በተለያየ ጊዜ ሎጥሏጣ እየሆነ እነዚህን ሰዎች እረፍት ያሳጣውን ሲያስታውስ ሰውነቱ ተኮማተረ። ፎቶ ተነስቶ ለመለጠፍ የነበረውን ጉጉት ወደ ኋላ መለስ ብሎ ሲያስበው ራሱን መቆጣጠር አቃተው። እሱ ሄደባቸው እንጂ እነሱ አልመጡበትም። እሱ ተራ በተራ ፎቶ እየተነሳ ለጠፈ እንጂ እነሱ በእሱ ገጽላይ መለጠፋቸውም ትዝ አይላቸውም። እነሱ የግጥም ችሎታቸውን እንዲያጎለብት ከማበረታታት አልፈው መድብሉን እንዲያሳትም ድጋፍ አደረጉለት እንጂ እዳሪ የነካው እንጨት አላደረጉትም።

እሱ የአርበኞቹ የከፍተኛ ትምህርት ምኩራብ መውጣት እያደነቀ እንዲሁም የራሱን የጭንቅላት ባዶነት እየወቀሰ ይናገራል እንጂ እነሱ ምንም አይሉትም። ዲግሪ ስለሌለው አክብሮታቸውን ዝቅ አላደረጉም። እሱ “በድን ነኝ! ሬሳ ነኝ! ምንም ነኝ!” እያለ ራሱን ሲወቅስ፤ እነሱ ተጨማሪ ከማድረግ ተቆጥበው የነጻነት ጥማትና የአላማ ጽናት እንዲኖረው ያበረታቱታል። ከአንድነት ዲሞክራሲና እኩልነት ሃዲድ ውጭ እንዳይወጣ ይመክሩታል። እሱ በህዝብ ፊት ግለሰቦችን እንዴት እንደሚዘረጥጥ ሲያወራ፣ እነሱ ህልማቸው የሆነውን ኢትዮጵያን ስለማዳን ይነግሩታል። ነጻነት በተግባር እርምጃ እንጂ በብእር ቀለም በመዘርጠጥና ማዋረድ እንደማይመጣ ያስተምሩታል። በመሬት ላይ የሚካሄደው ትግል የድርሻውን እንዲወጣ ከፈለገ “በግጥም “ብዙ ስራዎችን መስራት እንደሚችል ጠቆም እንዳደረጉት በቅርበት አውቃለሁ። ወጣቱ ጠሃፊ ተፈጥሮአዊ ባህሪ እየተቀየረበት ያለውን እርስ በርሱ የሚደባደብ ተቃሮኖ አስተሳሰብ መውጣት ካልቻለ መድረስ ራሱ ገፍትሮ እንደሚጥለው ቁጭ አድርገው ነግረውታል። በተለይ ከሁለት አመት በፊት በሳንሆዜ በተካሄደው የኢትዮጵያ ኣግር ኳስ ውድድር ወቅት ከ20 ያላነሰ የአርበኞቹ ደጋፊዎች ለእራት በተሰበሰቡበት ተራ በተራ እንደነበረ ሰምቼአለው። “ኣባክህን! በኢትዮጵያ ባህል የወንድ ተቀጣሪ አስለቃሽ አልተለመደምና ስራውን አቁም!” ብለው መክረውት ነበር።

“ወጣቱ የአማራ ተነስ! ተቀመጥ! መሪ” ንዴቱና ግራ መጋባቱ እየጨመረ ሄደ። እንደ ውሃ ላይ ኩበት ተንሳስፎ መቅረቱ ወለል ብሎ ታየው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ውስጣዊና ድብቅ ባህሪው ገንፍሎ መውጣቱና ከመቅጽበት መታወቁ ጎዳው። ስሜቱን ሰከን ማድረግ አቅቶት ዘወትር ላይና ታች መላጋቱ እንዲሁም ተለይቼ ልታይ ባይነቱ የበለጠ እየጋመ መሄድ አናደደው። ቁጣና ንዴቱን ለማስተላለፍ የተቀመጠበትን ጠረጴዛ ደጋግሞ ደበደበ። ለብዙ ደቂቃ ቆዘመ። የታጋይነት ምልክት የሆነው ጺሙን እያሻሸ ትካዜውን ቀጠለ።
ለጥቂት ጊዜ ዝም አለ።
ትንሽ ቆይቶ ደስ አለው።
ደስታ የተሰማው ከላይ ያስታወሳቸውን አርበኞችና ምሁራን የሚተኩለት ሰዎች አጠገቡ በማግኘቱ ነበር። ከደስታው ብዛት ማእረግ ጨምሮላቸዋል:: እነዚህም “ፊልድ ማርሻል ጸሀፊ ተውኔት ተክሌ ይሻው”፣ “ሜ/ጄኔራል ርስቴ ተስፋይ” እና “ተራማጅ ብርሃኑ ዳምጤ(አባመላ)” ነበሩ። በእርግጥ የድርጅቱን ማህተም በኪሱ ይዞ የሚዞረው ፊልድ ማርሻል አመኔታ የሚጣልበት ባይሆንም ለጊዜያዊ ሆይሆይታ የሚያንስ አይደለም። የሰሜኑ ኮከብ ፊልድ ማርሻሉን “ስንት አባላት አሉህ?፣ የምትሰበስበውን ገንዘብ ምንድነው የምታደርገው?፣ መሬት ላይ የወረደና በአንተ በቀጥታ የሚመራ ስንት ሰራዊት አለህ?፣… የሞረሽ አመራርና ምክርቤት አለወይ?…በመደበኛነት መቼ ይሰበሰባል?፣…የአመራር ምርጫ እንዴት ይካሄዳል?…በቀድሞው የአብዮት ጠባቂ ደምስ በለጠ እየተካሄደ ያለው ዩ ቲዊብ ላይ የሚለቀቀው የአማራ ድምጽ ሬድዮ በርግጥ ከኢንተኔት ተሻግሮ በአጭር ወይንም በረጅም ሞገድ ኢትዮጵያ ይደርሳል ወይ?” በማለት መጠየቅ እስካልጀመረ ድረስ ለአጭር ጊዜ አብሮ ለመዝለቅ አያዳግተውም። የሰሜኑ ኮከብ ወደኋላ ሄዶ ፊልድ ማርሻሉን “ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ መአድን በመሰረቱ ሰአት ምንድነው ያደረካቸው?” ብሎ እስካላፋጠጠ ድረስ ሳይከፋ መኖር ይችላል። በፌስቡክ የበረሃ ግንባር ለፊልድ ማርሻሉ ቁጭ ብድግ እስካለ ድረስ “ጌታዬ!” እያለ መኖር ይችላል።

እርግጥ ከፊልድ ማርሻሉ ጋር መቆየት በጣም አደገኛ እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል። በአጭር ጊዜ ውስጥ የሞረሽን አክሊልን ማእተብ እስካልነጠቀው ድረስ ማርሻሉ ሰው በማጥፋት የሚስተካከለው የለም። ድፍን የጎንደር ህዝብ “የእግዜር ታናሽ ወንድም” በማለት የሚጠራውን መላኩ ተፈራ በቁጭት ባስታወሰ ቁጥር ረዳቱ የነበረውን ተክሌ ይሻውን ሲጠቅሱ በአይኑ በብረቱ ተመልክቷል። ወጣቱ የአማራ ተነስ! ተቀመጥ! መሪ አስኳላ እያለ ፕሮፌሰር አስራት መላው አማራን ሲያቋቁሙ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲሳለቅባቸው ሰምቷል። ይባስ ብሎም ሰውየው ከልደቱ አያሌው ጋር በማሴር መአድን ለማዳከም ኤዴፓ የሚባል ፓርቲ መስርቶ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ያውቃል። በወቅቱ ፊልድ ማርሻሉ በሚያደርገው ቅስቀሳ “ከኢትዮጵያ በታች መጥበብ አልችልም!” እያለ መፈክር ሲያሰማ ተመልክቷል። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ፕሮፌሰር አስራትን ተስፋ የሚያስቅርጡ ሃሳቦች ሲሰነዝር እንደነበር የተመለከተው ነው። እኔም ለዚህ አባባል የህይወት ምስክር ነኝ።

ይህ ብቻ አይደለም። ወጣቱ የአማራ ተነስ! ተቀመጥ! መሪ በአሜሪካን የስደት እግሩ ከረገጠበት ቀን ጀምሮ ስለ ፊልድ ማርሻሉ የሰማቸው በርካታ ነገሮች አሉ። በተለይም የሰሜኑ ኮከብ “የኢህአፓ ወጣቶች ክንፍ አመራር” በነበረ ሰአት ስለ ተክሌ ይሻው ወንጀሎች ቋቅ እስኪለው አዳምጧል። ተክሌ ይሻው የመላኩ ተፈራ የቀኝ እጅ በመሆን የጎንደር ወጣቶችን በኢህአፓ ስም እንደ ቅጠል የማርገፍ ስራ ሰርቷል። ለብዙዎች ግልጥ ኣንደሆነው ተክሌ ይሻው የሰርቶ አደር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በነበረ ሰአት መላኩ ተፈራ፣ አሊ ሙሳ፣ ጌታቸው ሺበሺ…ወዘተ የፈጸሙትን ግድያ “ለአገሪቱና አብዮቱ ደህንነት” ሲባል የተወሰደ አብዮታዊ እርምጃ እንደሆነ አሞካሽቶ ጽፏል። የትግራይ ክፍለሀገር የኢሰፓ አንደኛ ጸሃፊ በነበረ ሰአት ህይወቱን ለአብዮቱ የሰጠ እንደሆነና አብዮታዊ እርምጃው ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ምክሩን ለግሷል። በዚህ ምክንያት ከአዋቂ እስከ ልጅ፤ ከምሁር እስከ ገበሬ፤ ከቄስ እስከ ሼኪ ጎንደር ያፈራቻቸው ዜጎች አገር ጥለው ተሰደዱ። አንዳንድ የጎንደር ቀዬዎች ሰው-አልባ ሆኑ። በተቃራኒው የአህቱንና የአጎቱን ልጆች እንደገደለ በመኩራራት ለጎንደር ህዝብ ሲናገር የነበረው መላኩ ተፈራ እና ተክሌ ይሻው እየተገናኙ የውስኪ ብርጭቆአቸውን ያጋጩ ጀመር። የጎንደር እምባ ላይደርቅ ፈሰሰ።
መላኩ ተፈራ የእግዜር ታናሽ ወንድም፣
የዛሬን ማርልኝ የነገን አልወልድም።
“ወጣቱ ጠሀፊ” ተክሌ ይሻውን በህሊናው እየሳለ “ታዲያ ይሄ ልጋጋም ሰውዬ እንዴት ሊታመን ይችላል ፕሮፌሰር አስራትን ያንጓጠጠና የሰደበ ሰው ለእኔ እንዴት ሊመለስ ይችላል?” በማለት ተናገረ። አስከትሎም “እኔንስ አንገቴ ላይ የወፍጮ ድንጋይ አንጠልጥሎ ወደ ጥልቅ ባህር ቢወረውረኝ ማን ያድነኛል?” በማለት ራሱን ጠየቀ። በፍርሃቱ ላይ ፍርሃት ጨመረበት። የውጭውን ሲኖዶስና በተለይ በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውን ታላቁን የቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክርስትያን “ፎገራ እና ወገራ” ብሎ ለሁለት ለመሰንጠቅ ጥረት እንደሚያደርገው ሁሉ የሰሜኑን ኮከብ አርባ አራት ቦታ እንዳይሰነጣጥቀው ፈራ። የፊልድ ማርሻሉ አጋፋሪ ከሆኑት ውስጥ በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ነዋሪ የሆነው የቀድሞ የአኢወማ ጸሃፊና የደርግ አብዮት ጠባቂ ገራፊ የነበረው ምርጫው ስንሻውና በኮሎራዶ ተራሮች መሽጎ የሚኖረው ደምስ በለጠ በዋዛ ሊታዩ የማይችሉ ሰዎች እንደሆኑ አሰበ። አሜሪካም እግሩ ከረገጠበት ጊዜ ጀምሮ ስለ ምርጫውና ደምስ የቀን ጅብነት ብዙ ሰምቷል፡ ሁለቱም ከመሬት ስር ተቆፍረውና ተፈቅፍቀው ለምግብነት እንደሚያገለግሉት ካሮትና ድንች የሚያመሳስላቸው እንደ ብዙ ነገር አለ:: ሁለቱም የቀድሞ የደርግ አብዮት ጠባቂዎች የነበሩና በኢህአፓ ስም ብዙ ለግላጋ ወጣቶችን የገረፉ ያስገረፉ ያሳሰሩና ያስገደሉ ናቸው ሁለቱም በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ነዋሪ የነበሩና በጋዜጠኝነት ስም የተቃዋሚ የድጋፍ ስብስቦችን ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ቆዳ ጭምር ገፈው የቀረጠፉ ናቸው:: ሁለቱም የተቃዋሚው አንድነት ሲያዩ አይናቸው ደም የሚለብስና ማንኛውንም ነገር ተጠቅመው አንድነትን እንደ ንፋስ እንደነካው ገለባ የሚበታትኑ ናቸው።

ምርጫው ስንሻው ለፓለቲካ ትግል ድጋፍ: ለድርቅ እና ለሌሎች ህዝባዊና ማህበራዊ ጉዳዮች በተለያየ ጊዜ የተሰበሰን በብዙ ሺህ ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ቅርጥፍ አድርጎ የበላ ግለሰብ መሆኑን “ወጣቱ ጠሀፊ” አልሰማም ለማለት ያዳግታል: እንደዚሁም ከህዝብ በዘረፈው ገንዘብ በከፈተው ቤተክርስትያን ከምእመናን የሚዋጣን አስራትና እርጥባን ገንዘብ ብቻ ሳይሆን እድሜያቸው ከገፋ አዛውንት እናቶችን እቁብ እንሰብስብ ብሎ ገንዘባቸውን የውሀ ሽታ ያደረገ ቁጭ በሉ መሆኑን ጸሀይ የሞቀው ሀቅ መሆኑን ያውቃል:፡ ምርጫው የደርግ ስርአት ተገርስሶ ከወደቀ በኋላ ለጥቂት ወራቶች በወያኔ የቁም እስረኛ ሆኖ በነበረበት ወቅት በአዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ ከወንድሙ ጋር ይኖርበት የነበረውን የቀበሌ ቤት በብአድን አባላቶች ድጋፍ በድብቅ ከሃገር ከመውጣቱ ጥቂት ቀናቶች በፊት ቁልፉን ለሁለት ግለሰቦች የሸጠና ወንድሙን ያለ ጨረቃ ቤት ያስቀረ ለማንም የማይመለስ ነብሰ በላ መሆኑን ድብን አድርጎ ያውቃል:: የፊልድ ማርሻሉ የቀድሞ የስራ ባልደረባ እና የቀድሞ አብዮት ጠባቂ የኢንተሬኔት የአማራው ድምጽ ሬድዮ አዘጋጅ ደምስ በለጠ በደርግ ግዜ ባሳየው የላቀ አስተዋጽኦ ራሽያ ከመላኩ በፊት ያስለቀሳቸው የሽሮ ሜዳ አካባቢ ወጣቶች የነበሩ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ዛሬም ድረስ ስሙን ሲሰሙ እንደሚያንቀጠቅጣቸው አልሰማም ማለት አይቻልም:: “እነዚህን ከጨካኝ አውሬ የከፋ የሰው ጨካኞች፣ በንጹሃን የአማራ ደም እጃቸውን የተለቃለቁ” በማለት ለራሱ ተናገረ። አስከትሎም “የፈሩት ይደርሳል፣ የጠሉት ይወርሳል” በማለት አንጎራጎረ። አፍንጫው ጋር ያለች ብስጭቱ ተመልሳ መጣች።

ተጋዳሊት ርስቴ ተስፋየም ቢሆን ለጊዜያዊ መሸሸጊያ ተስማሚ ናት። እርግጥም ዳንዴሞዋ ታጋይ በቃርሚያና በጥራዝ ነጠቅ የሰበሰባቸውን እንግሊዘኛ የማድነቅ ግዴታ አለበት። የርስቴ ንግግር የቋንቋ ውበትም ሆነ የሃሳብ ብስለት የሌለው ደካማና ደንገርጋራ መሆኑን ቢመለከትም አፉን በዚፕ ማሰር ይኖርበታል። የርስቴ የትግል አቅጣጫ የወያኔን ህገ-መንግስት የተቀበለ እና ለህገ-መንግስቱ ተገዥ እንደሆነ አምኖ ሊቀበል ይገባል። ለወጣቱ አማራ ተነስ! ተቀመጥ! መሪ ለመቀበል ቢከብድም ዳንዴዋ ታጋይ ርስቴ “ፖለቲካ ጎበዝ ናቸው” በማለት የምታደንቀውን ወያኔ ማድነቅም ግድ የሚልበት ጊዜ ሊመጣ እንደሚችል ተገንዝቧል። ተወደደም ተጠላ ከርስቴ ለመቆየት ህሊናውን “የመስዋእት ጠቦት” ማድረግ ይኖርበታል።.በርግጥም ጠለቅ ያሉ ኪነ-ጥበባዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ሃይማኖታዊ ፍልስፍናዎችና መላምቶችን መነጋገር ጥቁር ድንጋይ ላይ ውሃ የማፍሰስ ያህል ስለሚሆን የሚሞክር አይደለም። እንዴት ከባድ ነው?…እግር ከወርች ከመታሰር በምን ይሻላል?…በቁመና ከመሞት በምን ይበልጣል?…

ከሁሉም በላይ ካዳንዴዋ ርስቴ ጋር መግባባት የሚከብደው የእለት ስራዎችን መስራትና ማሰብ የምትፈልገው በጋራ ወንፈል እና ወፈራ መልኩ ነው። ለእያንዳንዱ እርምጃዋ “አንቺ እኮ ከሴቶች ሁሉ የተለየሽ ነሽ!” የሚል ወሮታና ብድር ካልቀረበላት ታኮርፋለች። ለስራዋ እውቅና የተሰጣት አይመስላትም። አንዳንዴም አፍ አውጥታ “ማእሬ ለምንታይ ልፍንቲቴን ሀበኒ?” በማለት ቅሬታዋን ታሰማለች። የመጀመሪያው ሰሞን ለሰሜኑ ኮከብ ቋንቋዋ ግራ ገብቶት የደስታ ተክለወልድን የአማርኛ መዝገበ ቃላት እስከ ማገላበጥ ደርሶ ነበር። ሊያገኘውም አልቻለም። ለካስ ወንፈል እና ወፈራ የሰሜኑ ኮከብ አጥብቆ የሚወደው የትግርኛ ቃላት ነው።

ከዚህ በተጨማሪም የዳንዴዋ የፖለቲካ አቋም ደፋርነት እና ቀጥተኛ መሆን አስደንግጦታል። ሴትየዋ በፈረንጆቹ አዲስ አመት “የአመቱ ደፋር ሴት! እንድባል ልፍንታዬን ስራልኝ!” የሚል ትእዛዝ መስተላለፏ ይበልጥ ጭንቀት ለቀቀበት። በሰሜኑ ኮከብ የፌስቡክ በረሃ ላይ “የአመቱ ደፋር ሴት! ታጋይ ርስቴ” ለማለት መዘጋጀቱ መንፈሳዊ ሽብርና አካላዊ ሰቆቃ ሆነበት። በእሱ አእምሮ ውስጥ ትላልቅ የሚላቸውን ሰዎች በበሬ ወለደ አሉባልታ ሲያንጓጥጥ ከርሞ “የ3ኛ-ጨ” ክፍል ተማሪዋን “ደፋር! “ለማለት መድፈሩ ራሱን መልሶ አሳፈረው። ሳያስበው “ይቺ ገልቱ ግፍንት ሴት መቼ ይሆን ከአናቴ ላይ የምትወርደው?…ይቺ ግራ ቀኝ ረጋጭ ውንግርግርና ውሽልሽል ወርዳ አዋረደችኝ!…ይቺ አመዳማ ነጭ ዝንጀሮ እኔንም ቁር የመታው እንዳሞድ አደረገችኝ” በማለት እየሰቀጠጠው ተናገረ። እጆቹ ባላቦት መንፈጭፈጭ ጀመረ።

ታጋይ ርስቴ ጭንብል ያጠለቀች ተዋንያን መስላ ታየችው። ብአዴን በተጠና እና በተቀነባበረ ሁኔታ የላካት ኣንደሆነ ተጠራጠረ። በጭንቅላቱ መልሶ መላልሶ “እኛ በህገ-መንግስቱ ጥላ ስር ሆነን ነው የምንታገለው። ብአዴን አማራ ክልልን እንዲያስተዳድር እንፈልጋለን። ወልቃይትን ለወልቃይቴ ከተመለሱለት ህዝቡ ትጥቁን እንዲፈታ እናደርጋለን። ይሄን ማድረግ ወያኔ ከቻለ ኢትዮጵያን እንዲመራ እንፈቅዳለን” በማለት በሚዲያ የተናገረችውን አስታወሰ። ውስጡ በብሽቀት ቅጥል እርር ድብን ኩርምት አለ። ብርጭቆውን አንስቶ በእንጥፍጣፊ የቀረችውን አጥሚት ቸለሰበት። “3ኛጨ” የሚለው ተመልሶ መጣበት።

መልኳን አሳምራ እንደ ቴክሳስ ፈረስ
ሶስተኛ ክፍል ናት እስከ ዛሬ ድረስ::
ወጣቱ ጠሃፊ አፍና አፍንጫውን ጠረገና በጥልቅ ሀዘን ውስጥ ተውጦ “ በዝች ውሽልሽል ሴት ምክንያት የበለጠ ኣንቅልፍ አልወስድ አለኝ። ምን እንደነካኝ አላውቅም። አሁን አሁን ባዶነት እየተሰማኝ ነው። ጋደም ብዬ በሰመመንና ህልም የማያቸው ሰዎች የማከብራቸውና እነሱን መሆን የምመኛቸው ሆነዋል። ከነጭ ዝንጀሮዋ ጋር በመሆን የተሳደብኩት መልሶ እንደ እሾህ ወጋኝ” በማለት ተናገረ። ዋነኛ የትግል መሳሪያ የሆነውን ዘመናዊ ስልክ ከፍቶ ታጋይ ርስቴ በበርሃ ስንዘፍነው ነበር ብላ የሰጠችውን ግጥም መጻፍ ጀመረ።
ጎበዝ ተሓሕት ተጋዳላይ ትግራይ
አርኪብላ በሎ ንዚ – ሃሻ አምሃራይ።
ለጥቂት ጊዜ ዝም አለ።
ትንሽ ቆይቶ ከፋው።
ትንሽ ቆይቶ ደስ አለው።
“ወጣቱ ጠሀፊ” በመጨረሻ የደስታው ምንጭ የሆነው ከብርሃኑ ዳምጤ(አባመላ) ጋር ሽርክና መፍጠሩ ነው። አበው ሲተርቱ “ሳይደግስ አይጣላም” ይሉ የለ። የመርካቶ ውቃቢ ምስጋኒታ ይድረሰው። እንደ እውነቱ ከሆነ ከአባመላ ብዙ ልምድ መውሰድ እንደሚቻል አስቀድሞ ገብቶታል። ሰውየው የሚከተለው የ”ዳይናሚዝም ፍልስፍና” ለሰሜኑ ኮከብ እንደ ትምህርት ሊቀሰም የሚችል ነው። “ተራማጅነቱም” ቢሆን ከታጋይ ርስቴ ጋር ተደምሮ ህገ-መንግስቱን (የወያኔ ፕሮግራምን) እስከተቀበለ ድረስ ከብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ጋር የመደራደር አቅም ሊፈጥር ይችላል። ከታጋይ ርስቴ የቅርብ ወዳጅና አበልጅ ከሆነው ጠቅ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር መረጃ ሊለዋወጥ ይችላል። በቤተ-አማራ የውስጥ አርበኛ በሆነው ፕሬዝዳንት ገጹ አንዳርጋቸው የገንዘብ ድጋፍ ሊያገኝ ይችላል። የቀድሞ ባሏና የልጇ አባት ከሆነ የወያኔ ጄኔራል ጋር ወዳጅ ሊሆን የሚችልበት እድል ፈጥሮለታል። ታዲያ ከዚህ በላይ ዳይናሚዝምና ተራማጅነት ከየት ይመጣል?…በድጋሚ ምስጋኒታ ለተጋዳሊት ርስቴ ተስፋይ!!

“ወጣቱ የአማራ ተነስ! ተቀመጥ! መሪ” ስለ ፊልድ ማርሻሉ፣ ሌ/ጄኔራሏና አባመላ ማሰቡና ከአጠገቡ እንዳሉ ማወቁ ከፍተኛ ደስታ ፈጠረለት። ለረጅም ሰአት በፓልቶኩ አስገብቶ ስላስተናገደው ምስጋና አቀረበለት። “እውነትም የመርካቶ አራዳ ይግደለኝ!” በማለት በውስጡ ተናገረ። የአባመላ ጠንካራ ጎን ፊትለፊቱ ተደቀነ። አንዳንዶች “የዳይናሚዝም ፍልስፍናን በማሳጣት በቀጥታም ሆነ በዙሪያ ጥምጥም መሄዳቸው ትክክል እንዳልነበረ ተገነዘበ። “መሽቶ በነጋ ቁጥር መገላበጥ የማይችሉበት አድሓሪያን ናቸው” በማለት በውስጡ ተናገረ።

በደስታ ብዛት ጠረጴዛውን ላይ ያለውን ኮምፒውተር አውጥቶ የፌስቡክ በረሃውን ሲመለከት ያልጠበቀውን ነገር ተመለከተ። ከጠላቶቹ አንዱ የሰሜኑ ኮከብ ለአባመላ የገጠመለትን “ይገርማል!” የሚለውን ግጥም ለጥፎታል። መጥፎ ገጠመኝ!…በአንድ ጊዜ በጦርነቱ የተሸነፈ ያህል ተሰማው። በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆኖ “ይገርማል!” የሚለውን ግጥም ለመስማት የኮምፒውተሩን ቁልፍ ተጫነ።

ወጣቱ ጠሃፊ “ይገርማል!” በማለት “መታሰቢያነቱን ለአባመላና አይነቶቹ ይሁንልኝ” በማለት የጻፈውን ግጥም ሰምቶ መጨረስ አቃተው። በተለይም

የእድሜውን ግማሽ እዳሪ ሲወጣ፣
የግማሹን ፓልቶክ ላይ ጀግኖ ሲቆጣ፣
የግማሹን ግማሽ ኢያጎን ተላብሶ፣
ሲያቃጥር ሲያቃጥር ሃምሳ ቀለም ለብሶ።
የሚለውን ስንኝ እየዘገነነው አዳመጠ።
ሁሉንም ሳያጠቃልል የኮምፒውተሩን መውጫ በመጫን ዘጋው። አንቲዲፐሬሳንት መድሀኒቱን ባለመውሰዱ “አልቅስ አልቅስ” የሚል ስሜት ተሰማው። በአእምሮው ውስጥ ራሱን የማጥፋት ዝንባሌ ተጫነው። እያደረገ ያለው ነገር በሙሉ ወንጀል ሆኖ ተሰማው። ራሱን በማጥፋት በሙታን ተርታ ከመመደቡ በፊት “ለአማራ ተነሳ! ተቀመጥ!” የፌስቡክ ሰራዊት አባላት ኑዛዜ መጻፍ ፈለገ። ፊልድ ማርሻል ተክሌ ይሻውን፣ ተጋዳሊት ርስቴና ዘጠኝ ጎራሽ ሊዲያ ዘ- ወልቃይትን በኑዛዜው ማካተት እንዳለበት ተገነዘበ። ራሱን ከሰዋ በኋላ የ”አማራ ተነሳ!ተቀመጥ!” ገድል ሲጻፍ መሪዎቹ እንዳይረሱት የሚማጸንበት እንዲሆን ፈለገ። በቀብሩ ስነ-ስርአት ላይ በሚነበቡት ጀግንነታዊ ታሪክ ውስጥ “አማራ ወይም ሞት! ሩጫዬን ጨርሻለሁ!” የሚል ማሳረጊያ እንዲጨመርበት ፍላጎቱን አሳየ። ሀሳቡን ሲጨርስ ፈገግ አለ።
ለጥቂት ጊዜ ዝም አለ።
ትንሽ ቆይቶ ከፋው።
ወደ መኝታው ሔደ።
***
** ቁጭራ በአዲስ አበባ ከአንዋር መስኪድ በላይ ወደ ጎጃም በረንዳ በሚያወስደው መንገድ ላይ የሚገኝ ሰፈር ሲሆን: አካባቢው ብዙ በሴተኛ አዳሪነት የሚተዳደሩ እህቶቻችን የሚገኙበት ሲሆን እንደ ብዙው በአዲስ አበባ ውስጥ እንደሚገኙ የድሀ ሰፈሮች ሁሉ ግለሰቦችን እርስ በእርስ ሲሰዳደቡ ማየት የተለመደ አካባቢ ሲሆን: “ሊዲያ ዘ-ቁጭራ” ብለው በፌስቡክ ቅጽል ስሟን ያወጡላት ግለሰብ ሰለቸኝ ደከመኝ ሳትል ቀንና ሌሊት የፌስቡክን ሬከርድ በስድብና በአሽሙር ከሰበሩ ጥቂት አናብስት እንስቶች መካከል አንዷ በመሆኗ ነው:: ከዚህም የተነሳ ምንም እንኳን በብዙዎች ዘንድ በስድብ አንቆርቋሪነቷ እውቅናን ብታተርፍም በሌላ በኩል ደግሞ አድናቂዎቻ “የአማራ ፈርጥ” እያሉ ያንቆላፕስዋታል።