የስብሃት ነፍስ (አብዮት ሙላቱ)

የስብሃት ነፍስ (አብዮት ሙላቱ)

የመቂ ልጅ ነኝ። ኮሌጅ በጥሼ ስራ ስጀምር ማረፊያዬ አዲስ አበባ እንዲሆን አብዝቼ እመኝ ነበር። የምኞቴ ሰበቡ አዲስ አበቤ መሆን አይደለም። መቂ ምናድርጋኝ? አዲስ አበባን እሚያስናፍቀኝ ጋሽ ስብሃት ነበር።

መጽሀፎቹን አንብቤ ወድጄዋለሁ። ጋሽ ስብሃት እንዲህ አለ። ጋሽ ስብሃት እንዲያ አለ። በወሬ የደረሰኝ “ስብሃት አለ” እርሱ ካለው በላይ ነፍሴን ያጡዘው ነበር። ይህ የጦዘው ስብሃትን የማግኘት ጉጉት መርገብ የሚችለው ደግሞ ያው ሰውዬው በሚኖርበት ከተማ ተገኝቶ ሰውዬው በዋለው ስፍራ መዋል ነው መፍትሔው።ልቤም የሚነግረኝ ይሄንኑ ነበር። ሂድ ስብሃትለአብን አግኘው። እናም ጋሽ ስብሃትን ባሰብኩ ጊዜ ሸገር መኖር ህልሜ ነበር። ስብሃትን ከማውቀው በላይ እንዳውቀው ዘነበ ወላ ደግሞ ማስታወሻን ሰጠኝና ሰውዬውን የሴት ያህል አፈቅረው ጀመረ። እንዲያውም ዩንቨርሲቲ እያለሁ “ስቤ” የተባለ ቅጥያ ላንዳንዶቻችን ከአንዳንድ አሽሟጣጭ ተበርክቶልን እንደነበር አስታውሳለሁ። “ስብሃታዊያን” እንደማለት ነገር ነው ስቤ። ስብሃታዊያን ብባል እንኳንና ያኔ ዛሬም በስተርጅና ደስታዬን አልችለውም።ተገኝቶ ነው፤የስብሃት ደቀ መዝሙር መሆን። በርግጥ አሺሽ የነፋንና ጫት የቃመን ፣ ካቲካላ የጠጣንና ራሱን ያዝረከረከን እንዲሁም ሴት አብዝቶ ያየን ወጠጤ ሁላ ከስብሃት ማመሳሰል ሰብሃትን አለማወቅ ነው።

እኔ ያኔ ከብዙ ሱስ፣ ከትንሽ ግጥም፣ ከጥቂት ንባብ ፣ ከብዙ ዕብደትና ለሴትና ለስብሃት ከነበረኝ የተትረፈረፈ ፍቅር በቀር ምንም ያልነበረኝ “ጀዝባ” ነበርኩ። ለዚያ ነው “ተገኝቶ ነው!” ማለቴ። ጀዝባ የሚለው ቃል ለስድብ ያደላ ትርጉም ያለው ቢሆንም ለዚያ ዘመን ዓለማያ ዮንቨርሲቲ ለክብር የተጠጋ ማዕረግ ብጤ ነበር። በነገራችሁ ላይ ይህ ሁሉ ሲሆን ሰውዬውን በፎቶ ካልሆነ በቀር በድምጽም በምስልም አላውቀውም ነበር-ስብሃትን። ያኔ የክፍላገር ልጅ መሆን ችግሩ ይሄ ነበር፤ ክፍለሐገር መረጃ ይነፍግሃል። የመረጃ ዕጥረት አዲስ አበቤ መሆንን ያስመኛል። ለሌላ አይደለም፤ ስብሃትን ፍለጋ ብቻ።
አዲሳባን በኑሮ ሲያይዋት
ዳርዳሯ አበባ መሀሏ እሳት
መሆኗ በተለይ ዛሬ በደንብ ገብቶኛል።
ቡና እየተጠራራህ በቡና ቁርስ ብቻ ሆድህን እምትሞላ መቂ ምን ጎደላት? መቂ የሚጎድላት library እና ስብሃት ነበር። በርግጥ ዋናው ነገር ነው የጎደለን። ዛሬም መቂ መጸሀፍት መሸጫ መደብርና ቤተ መጸሀፍት የሏትም። መቂዎች ይሄ ፀረ ዕውቀት አያዋጣም። የተመካችሁበት ሽንኩርትና ቲማቲም ምች ይመታዋል። ለልጆቻችሁ ከሽንኩርት ማሳ ይልቅ ዕውቀት ለማውረስ ቸኩሉ።

ስብሃትን የማየት ዕድል አመለጠኝ

ኮሌጅ ከመበጠሴ በፊት አዲስ አበባ የመምጣት ዕድል አገኘሁ። የዓለማያ ዩንቨርሲቲ የስነ ጽሁፍ ክበብ በቡሽኪን አዳራሽ አዘጋጅቶት ለነበረው ፕሮግራም ግጥም ይዤ እንድቀርብ ወዳጄ መሀመድ ሰልማን ጥሪ አቀረበልኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ የፑሽኪን መድረክ ላይ እና የሸገር እምብርት ላይ ቆምኩ። ፑሽኪንን ወደድኩት። “የዝሆን ልፊያ” የሚለውን ግጥሜን አቅርቤ ተሰናበትኩት።

ዝሆን በጠገበ ቁንጣኑን ሊያስታግስ ከዝሆን ቢላፋ፤
ስንት ሳር ወደመ ፍቅር አገኝ ብሎ ከቤቱ የወጣ
ስንት ጉንዳን ጠፋ፤
ስንት ሚጢጢ ነፍስ እንደ ወጣ ቀረ ዝሆን በተላፋ።

(በነገራችሁ ላይ “ዝሆኖች ተጣልተው ሰበሩት ድንበሩን” ከሚለው የቴዲ የ97 ዓ.ም ዝነኛ ዘፈን የኔ ግጥም የአንድ አመት ታላቁ ነው።ከኔም ከቴዲም ግጥም ይልቅ ደግሞ የህዝብ ተረት ዘላለም ታላቅ ነው። ከዚያ ነውና የተቀዳው ሀሳቡ።ብትፈልጉ አብዮተኛዋን ሶልያና ሽመልስን ጠይቋት ትነግራችኀለች። የቴዲ ዘፈን ሲወጣ “አንተ… የቴዲን ዘፈን ሰማኸው..ዝሆኖች ተጣልተው የሚለውን?” በስልክ የነገረችኝ እሷ ራሷ ናት፤ ማርያምን)
እምብርቷ ላይ ቁሜ ሸገርን ደግሞ ናቅኋት። በክፍላገር ጎዳና ሀሳቡን ጥሎ ካንዱ ቀበሌ ወደ ሌላ እንቅፋት እንኳ ሳያደናቅፈው መመላለስ ለለመደ ለኔ አይነቱ ሰው የአዲስ አበባ ውክቢያ ከእብድ ጋር እንደ መሯሯጥ ያህል ትርፉ ድካም ብቻ ነበር። እናም በፍጥነት ከሸገር ሸሸሁ። ጋሽ ስብሃትንም ሳላየው ወጣሁ። በወቅቱ ከኛ ሰፈር በቅርጽም ባሰፋፈርም እምብዛም ከማይለየው የወዳጄ ኪዳኔ መካሻ ቤተሰቦች ዘንድ አየር ጤና አዳሬን አድርጌ ጤናዬን ይዤ ወደ መቂ ተመለስኩ። ጋሽ ስብሃትን ለማየት የነበረኝ የመጀመሪያው ዕድል አመለጠኝ። ጊዜው አልደረሰም ማለት ነው አልኩ ለራሴ።

ስብሃትን በብዥታ አየሁት

ሰው የምላሱን ፍሬ ይበላል። አዲስ አበባን ተመኘሁ።አዲስ አበባ መኖር ጀመርኩ።ወደ ጋሽ ስብሃት ከተማ ቀረብኩ። 22 አካባቢ ከተምኩ። ስብሃት ይሉት ፈላስማ ግን 22 አካባቢ የለም። አዲስ አበባ ሰፊ ነው። ጊዜው እስኪደርስ በኑሬዬ ቀጠልኩ። ጊዜ እራሱ ስብሃትለአብን ያለሁበት ድረስ ያመጣል ብዬ ያ ቀን እስኪደርስ ወደ ስራዬና ሱሴ ተመለስኩ። ከስራ መልስ ጫቴን መጻፌን… እቀረጥፋለሁ። ሲመሽ ወደ መሸታ ቤት አዘግማለሁ። ኮማሪት እያየሁ አነጋለሁ። ሲነጋ ስራ ከሌለኝ የዘሪሁን ህንጻ ፊት ለፊት ካለው የታክሲ መጫኛና ማውረጃ አንዲት ድንጋይ ላይ ተጎልቼ የተሳፋሪ ቂጥ የወራጅ ፊት እየገመገምኩ እውልና ፀሀይ ሲበረታ ገለምሶዬን ሸክፌ ወደ ጎጆዬ እገባለሁ። ስብሃትን ሳላየው አንድ አመት አለፈ።ሁለተኛው አመት ተደገመ። ከፍቅር ይልቅ ሱስ ክንዱ የበረታ መሆኑ የተገለጠልኝ ስብሃት አዲስ አበባ አንድ የሆነ ጥግ ለገባው ህይወት ላልገባው ሞት እያደለ መሽቶ እንደሚነጋ እያወኩ ስብሃትን ፍለጋ ከ22 መውጣት ሲሳነኝ ነው።
በሶስተኛ ዓመት ከለታት ባንዱ ቅዳሜ እዚያው ድንጋይ ላይ ቂጥና ፊት እያየሁ ሳለ ሌላ ታክሲ ፊቱን ወደ አብዮት አደባባይ መልሶ ቆመ።እመኪናው ሆድ አንድ ሶስት ሰዎች ይቁነጠነጣሉ። ሴቶች ናቸው። ጥሎብኝ ከሰው መካከል ቀድሜ እማየው ሴት ነው። ከሴት ገላ ቀድሜ እማየው ቂጥና ጡት ነው። ወደ መኪናው ሆድ በመግባት ላይ ያለ ያፈነደደ ቂጥ አየሁ። የወንድ ነው። በንዴት “ምናባቱ ይኼ…ሌላ ተካሲ ጠፍቶ ነው ?” ብዬ ዐይኔን ከቂጡ ነቅዬ ወደ ጋቢና ወረወርኩት። አሁንም ወንድ አጋጠመኝ። አንዳንድ ቀን እንዲህ ነው። እንደ ቂጥና ፊት ይገለባበጣል። ከወንድ ቂጥ ያመለጠ ዐይን ምነኛ ዕድለቢስ ቢሆን ሰላላ የወንድ እጅ ላይ ያርፋል? ሰላላው እጅ ገቢናውን ተደግፏል። ከወንድ ቂጥ የወንድ እጁ ይሻላል ብዬ እዚያው ጋቢና ቆየሁ። የሰውዬውን ሰላላ እጅ ተከትዬ ወደ ፊቱ በረርኩ። የተንዠረገገ ነጭ ጺም ጠይም ፊት ላይ ተመለከትኩ። እማውቀው ፊት መሰለኝና ደነገጥኩ። ሊያውም የቅርብ ሰው አፈጠጥኩ። ሰውዬው ከኔ ጎን ወዳለ አቅጣጫ ይመለከታል። ነጭ በጥቁር ቀለም የተወሰወሰ ባርኔጣ አጥልቋል። ለሰውዬው ከጺሙ ጋር ሞገስ የሰጠው ባርኔጣውንም አውቀዋለሁ። ከራሴ ጋር ማውራት ጀመርኩ”እንዴ ይሄ ሰውዬ ስብሃት አይደለም’ዴ? ነው እንጂ…። በስብሃት ስም ተመዝግበው የደረሱኝ ፎቶዎች ሁሉ ይህን ሰውዬ ነው የሚመስሉት። ይሄ ሰው ስብሃት ካልሆነ ሌላ ስብሃት የለም…” እያልኩ እያወራሁ ሳለ የሞቀ ፈገግታ የሽማግሌው ገጽ ላይ ተመለከትኩ። ለማነው ይሄ ሁሉ ፈገግታ ብዬ ዐይን ብከተል አጠገቤ አንዲት ቆንጆ ቆማለች። የሽማግሌው ዐይን ቆንጆዋ ላይ ነበር። ለካስ ያ ሁሉ ፈገግታ ለውበት ነበር የተበረከተው…? እንደገና ከእንቅልፍ እንደመባነን ነቃሁ”እንዴ ይኼ ሰውዬ ስብሃት ነው” ብዬ ከተጎለትኩበት ስነሳ ታክሲውም አብሮኝ ተነሳ። ስብሃት እጁን ሳልነካው አለፈኝ። ለሁለተኛ ጊዜ አመለጠኝ። ይበልጥ እየቀረብኩት ለመሆኔ ግን ልቤ ነግሮኛል። ስብሃት የጠቆመኝን ቆንጆ ተሳልሜ ወደተለመደው ጎጆ አቀናሁ።

ስብሃት 22 መጣ

ስብሃትን አብዝቼ እንደምወደው የሚያውቅ ወዳጄ እዮብ እሸቱ “ስብሃት ዛሬ ከኛ ጋር በቱርክ ይውላል” ሲል በስልክ አበሰረኝ(በዚያ ዘመን ቱርክ ለተወሰኑ ወዳጆች መገናኛችን ነበር)። እንደዚያች ቀን ምን እንደማደርግ ግራ የገባኝ ቀን የለም። ስብሃትን ባገኝ ብዬ ሳስብ ለመጠየቅ የመዘገብኳቸው ብዙ ጥያቄዎች የት እንደገቡ ሳላውቅ ከልቤም ከአዕምሮዬም ተሰወሩ። ስብሃት መጣ። በአንድ ቤት ውስጥ አብረን ዋልን። ስብሃትን አግኝቼ እስክንለያይ ቃል መተንፈስ አቅቶኝ መሸ። እሱ ሲያወራ እኔ ስሰማ ዋልን። መሸ። ተለያየን። ያ ታክሲ ውስጥ ያየሁት ስብሃት እሱ ራሱ ነበር አብሮኝ የዋለው። ደስ አለኝ።

ጋሽ ስብሃት ቤቴ መጣ

ወዳጆቼ እዮብ እሸቱ፣ ተስፋዬ እና ፍትህአወቅ የወንደወሰን ስብሃትን ቤቴ ድረስ ይዘውልኝ መጡ። ጋሼ ያኔ መታመም ጀምሮ ነበር። የሚወሳስደውን ወስዶ እንኳ የሆነ የተጫነውን ነገር ማራገፍ ስለተጫነው መጀመሪያ መተኛትን መረጠ። አልጋዬ ላይ ጋደም አለ(የዛሬውን አያድርገውና ያኔ አልጋ ነበረኝ፤ኤልያስ ተስፋዬ ያወረሰኝ። እኔም በተራ አወረስኩት)። ከእንቅልፉ ነቃ። ሽንት ቤት በድጋፍ ወሰድኩት። ጋሼ እኔ ቤት ሲመጣ ስጋው በጣም ተዳክሞ ነበር። በራሱ አቅም ከተቀመጠበት ቦታ መነሳት አይችልም ነበርና ሱሪውን አስታጠኩት። አዕምሮው ግን ንቁ ነበር። ኪዳኔ መካሻ ግጥም አቀረበ። እኔ ግጥም አቀረብኩ። ጋሽ ስብሃት ግጥም ይወዳል። አንዱ ግጥም ያልቅና እንደ ገና ሌላ እንድናነብለት ሲጠይቀን ሌላ ስናነብለት ፈረንጅ እያጣቀስ ሲያሞካሸን ዋልን። ስብሃት ማድነቅ ይችላል። ስብሃት ጭንቅላቱን እየወዘወዘ፣ግንባሩን በመዳፉ እየደቃ ካደነቃቸው ግጥሞቼ አንዷ ይህቺ ናት፡-
የግዜ ጥይት
ገዳይ ሰው አላውቅም ሰውማ ጥይት ነው
ካፈር የተሰራ
እንኳንስ ሊገድል ለራሱም ሸክላ ነው
ድንገት ተሰባሪ የጭቃ ተራራ
ተራራ ለመናድ ዓልሞ ሊመታ ምላጭ የሚስበው
የጭቃው ባለቤት እግዜር የኛ ጌታ ባለክላሹ ነው

ስብሃት ቤቴ የመጣ ለት ቤቴ የፑሽኪን አዳራሽ ሚናን ተረክባ ዋለች።
“ብሽቅ” የምትለውን ቃል ከስብሃት አንደበት የሰሙ እኚያ ሰዎች የእውነት ብሽቅ ስለሆኑ መሆን አለበት። ስብሃት ነቄ ነው። መሽቶ ምናምን ስንቀማምስ ብዙ ጥያቄ አነሳሁለት። ስለአሺሽ እና የሚጥል በሽታ፣ ስለነቄ ትውልድ፣ ስለቴዲ ፣ ሰለ ሀና፣ ስለ እምነት…ደስ እያለው በፈገግታ ታጅቦ ጥያቄዎቼን መለሰልኝ። ስብሃት ቴዲ አፍሮን ይወደዋል። ለምን መሰላችሁ ነቄ ካልሆንክ ቴዲ አፍሮን ልትወደው አትችልም። ነቄ ማፍቀር እንጂ መጥላት አይችልም። የስብሃት ነፍስ ፍቅር እንጂ ጥላቻን አታውቅም። ስብሃት ነቄ ነው። ቴዲም ነቄ ነው። እርግጠኛ ነኝ ቴዲም ስብሃትን አብዝቶ ይወደዋል። ለመጥላት መሰልጠን ይኖርብሃል። ለመጥላት ጥላቻን መማር ይኖርብሃል። ለማፍረስም እንደዚያው። ነቄ ይገነባል እንጂ ለማፍረስ አይበረታም።

በስተመጨረሻም ስብሃት እንዲህ አለኝ”ልባርግ…ከዚህ በኀላ እዚህ ቤት ብቀር ባንተ ነው” እጁን ወደ ኪሱ ከተተ። የስልክ ቁጥር የተጻፈበት ብጫቂ ወረቀት እየዘረጋልኝ”የማናጀሬ የኩኩሻ ስልክ ነው። በማንኛውም ቀን ready ነን” ከተሟላ ፈገግታ ጋር አቀበለኝ። እኔም ከአስራ ሶስት አመት በፊት ለግጥም መጻፊያ እንዲሆነኝ ገኒ(ዓለማያ) የሰጠችኝ ማስታወሻ ደብተር ላይ ስልኩን እንደ ግጥም መዘገብኩት። ስልክ አልባ ነበርኩ ያኔ። ስብሃትን ከዚያ ቀን በኀላ አላየሁትም። ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት ፈገግታ ግን አብሮኝ ይኖራል። ጋሼ እንዲህ ተቀኝቶ ነበር፡-

እግዜር እራሱን በደለ
አመስጋኙን እየገደለ

ጋሼ እንኳን ተወለድክልን
ሚያዚያ 27-