የህወሃታውያን መሰነጣጠቅ ምንጭና መንስኤ [ክፍል 1 በወንድወሰን ተክሉ]

በህወሃት መንደር ሰልስታይ[3ኛው]እንፍሽፍሽ ስለመፈጠሩ፧?
የህወሃታውያን መሰነጣጠቅ ምንጭና መንስኤ [ክፍል1በወንድወሰን ተክሉ]

መነሻ አንድ-የህወሃት መሰነጣጠቅ።

የህዋታውያን መንደር በውስጣዊ ጭንቀት እርሰበርስ መጠቃቃት እና ብሎም እርሰበርስ ተጠላልፈው አሸናፊ ቁንጮ ለመሆን ፍትጊያና ፍልሚያ ቀልጧል። ሰላማዊ እሚመስለው የህወሃት አመራር በክፍተኛ ውስጣዊ ማእበልና ወጀብ መናጥ ከጀመረ ሰንብቷል።
በሸሪያዓ ሕግና ባህል የተጋቡ ባልና ሚስቶች መካከል ለፍቺ የሚያበቃ ችግር ሲከሰትና ብሎም ችግሩ እልባት አጥቶ ለመፋታት እሚያደርስ ደረጃ ላይ ሲደርስ ባልና ሚስቱ እሚፋቱበት የፍቺ ሂደትና ደንብ ከተቀረው ባህልና ሂደት በእጅጉ የተለየ ሆኖ እናያለን። ባልየው ሚስቱን በሸሪዓ ፈትቼሻለሁ ብሎና ኒካውንም ቀዶ ግን ፈትቼሻለሁ ካላት ሴት ጋር በአንድ ቤት ውስጥ ተለያይተው ግን ሳይለያዩ ለወራትና ብሎም ለመፋታት ምክንያት የሆናቸው ጉዳይ እልባት አድጎ መልሶ ሚስቱ የማድረግ ሁኔታ እንዳለ እንረዳለን። እናም በህግ ተፋተው ግን አብረው ለወራት የሚኖሩ ባልና ሚስቶችን ሁኔታ ብታዩና ብትሰሙ የተፋቱ ወይስ ያልተፋቱ ባልና ሚስቶች ልትሏቸው ነው?

የህዋታውያን ውሳጣዊ ክፍፍልና መሰነጣጠቅ ለእኛ በሕዋታውያን ዘንድ እንደሰብጀክት ለምንቆጠር ኢትዮጵያውያን ያልተነገረ፣ ያልታወቀና ይፋ ያልሆነ ግን እርሰበርስ የነበራቸውን ድርጅታዊ አንድነት፣ የስልጣን ተዋረድና ጥምረትን አፍርሰውና በጣጥሰው ያሉ ስለመሆናቸው ከውስጣቸውና ከአከባቢያቸው እያፈተለኩ ያሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ፍቺያቸውን በአንዱ አሸናፊነትና ጠቅላይነት በሚደመድሙበት ወቅት አሸናፊው [የሚያሸንፍ ካለ]ብቅ ብሎ የተሸናፊውን ሀጢያት እየተናዘዘ በመደስኩር ይፋ ሲያደርግ ብቻ ነው እኛ ልናውቅ የምንችለው። የህዋታውያን ክፍፍል ዛሬ እዚያ ደረጃ ላይ አልደረሰምና ለግዜው ተፋተው ግን በአንድ ቤት አብረው እንደሚኖሩት ሙስሊም ባልና ሚስቶች አብረው የሚመሩ መስለውን እየታዩን እንደሆነ እያየን ነው።

ለመሆኑ-እንዴትና በምንስ ምክንያት ነው ሊከፋፈሉ የበቁት ወይም ለመከፋፈል የሚበቁት? እንዴትስ ሆኖ ነው የህወሃት ካድሬዎች ይህንን ክፍፍል 3ኛው እንፍሽፍሽ ነው በሚል ፍርሃት ሊገልጹት የቻሉት? እንፍሽፍሽ በህወሃት ታሪክ ውስጥ ታጋይ ሌላውን አቻ ታጋይ እያጠፋና እየዋጠ የመጡበት ታሪካቸው ስም ነው። ያኔ ገና በደደቢት በረሃ ሳሉ ውስጣዊ ልዩነቶችን የፈቱበት መምቻ ስም ነው። ብዙዎችንም ከትግሉ ጎራ እየነጠሉ የቀበሩበት እርምጃ እንፍሽፍሽ እያሉ ይጠሩታል። የ1993[2001] ክፍፍልንም ደም አልባው እንፍሽፍሽ እያሉ ታጋዮቹ ይገልጹታል። ዛሬ በህወሃት ውስጥ አንደኛው ወገን ሌላኛውን ወገን ሙሰኝነት፣ በስልጣን አላግባብ መጠቀምና የመሳሰሉት መምቻ ዱላዎች እየመዘዘ አንዱ አንዱን ሊመታበት እጥቅም ላይ ሲያውል እየተስተዋለ ነው። በህወሃት የቅጣት በትር ለመመታት ሙሰኝነት፤ በስልጣን አላግባብ መጠቀም እና ስልጣንን ተገን አድርጎ ባላንጣን ማጥቃት ምክንያት ሆኖ አያውቅም። በፖለቲካው ቅኝት መጋዝ የቻለ ታጋይና ባለስልጣን ፍጹማዊ የማይገሰስ ያለመከሰስ መብትን የተጎናጸፈ ሆኖ ያሻውን እያደረገ ሳለ ድንገት የተጠያቂነት ጉዳይ እሚቀርብበት ክስተት የተጠያቂው ፖለቲካዊ ቅኝት ተለውጦ ሲገኝ ብቻ እንደሆነ ይታወቃል። ሙሰኛን እና ሙሰኝነት መመርመር አለበት የሚለው የዛሬው የህወሃት መራሹ ስርዓት ድምጽ የክፍፍሉን ጎራ የእርሰበርስ መጠቃቃትን ፍትጊያ የምናይበት ተግባር እንጂ ፍትሃዊነትን የምንሰማበት ሂደት ሆኖ አይደለም።

መነሻ ሁለት-የመሰነጣጠቁ ዋና አስካልና መንስኤው።

የ2015ቱ አገር አቀፍ ምርጫ ማግስት መቶ በመቶ አሸንፌያለሁ በሚል እውጃ ከበርቻቻውን በአደባባይ ሲያጣጥፉ በድርጅታዊ ደረጃ ግን ውጥረት፣ጭንቀትና ቅስቀሳ ተጣጡፎ ነበር የሰነበተው። ህወሃታውያን በደሳለኝ ሃይለማርያም ቀጣይነት እና የለም መቀጠል የለበትም በሚሉ ሰዎች ከፍተኛ ንትርክና ጭቅጭቅ ተፈጥሮ ነበር። ማለትም የመለስን ሌጋሲ ደጋፊዎችና የለም አሻንጉሊቱ ይበቃዋል እኛው እራሳችን መሪነቱን መያዝ አለብን በሚሉ ከመለስ ሌጋሲ ይልቅ የራሳቸውን ሌጋሲን የመገንባት ርሃብና ምኞት ባሸነፋቸው ሃይሎች መካከል ልዩነት ተከስቶ ነበር። በጄኔራሎች የሚመራው ፈርጣማ ሃይል ጥቂት የሲቪል ባለስልጣናትን እና በጣት የሚቆጠሩ ወሳኝ የድርጅቱን ባለንብረቶችን ይዘው በደሳለኝ ቀጣይነት ጎራ ሲሰለፉ ሌሎቹ ደግሞ በተለይም ብቃቱ እያለን ያለአግባብ በአቶ መለስ ጥላ ስር ተጋርደናል የሚል እምነት ያላቸው በጸረ ደሳለኝ ይቀጥል ጎራ ተሰልፈው ተጠዛጠዙ። የህይል ሚዛኑ ወደ ጄኔራሎቹ ጎራ አመዘነና በደሳለኝ ኮንዶምነት መምራት የጀመረው ሃይል ዳግም ደሳለኝን ለጠ/ሚ/ርነትበውስጣዊ ተቃውሞ እንደታጀበ ሊያበቃ ቻለ።

5ኛው የህወሃት ምርጫ ልክ በ5ኛ ወሩ የህልውናውን ስር መንግሎ የሚነቅል ክስተት በኖቭምበር 2015 በኦሮማይታ ከተማ ጊንጪ ህዝባዊ አመጽ ፈነዳ። ብዙም ሳይቆይ በመላ ኦሮሚያ ተጥለቅልቆ ውስጡ ያልረጋውን ህወሃት መንግስት ይንጠው ጀመር። በሁኔታው ለመጠቀም ወታደሩ ክፍል በኮንደሙ ደሳለኝ ሃይለማርያም ተጥቅሞ ኦሮሚያን በ8ት ጄኔራሎች እዝ ስር በማዋል የስልጣን ባላንጣውን የሚያዳክምበትን እርምጃ መተግበር ጀመረ። ቢሮክራሲውን እና በህወሃት ውስጥ ወሳኝ ስልጣን ያላቸውን ቁንጮዎችን ያሰለፈው ክፍል በደህንነት ሃይሉ በመጠቀም የአጸፋ እርምጃ መውሰዱን ተያያዘው። ህዝባዊው አመጽም ተባብሶ በአማራ ግዛት በተዛመተበት ወቅት የህዋታውያን መንደር የእርሰበርስ ክፍፍላቸውን አምቀው ለመፍትሄ ሲሉ በአንድ ላይ በአማጺው ህዝብ ላይ ለመረባረብ ተስማምተው ለምክር ተቀመጡ። ምክክሩም በሁለት ደረጃ የተከፈለ ነበር። አንደኛው በህወሃት ቁልፍ ሰዎች፣ ጄኔራሎችና የህወሃት ነፍስ አባቶች ብቻ የተካሄድ ምክክር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በተመረጡ የህወሃት ወሳኝ ሰዎች ዋና ሰብሳቢነት የህዝባዊው አመጽ የተቀጣጠለባቸውን የአማራውን እና ኦሮሞ ክልል ባለስልጣናትን መርጠው እንዲሳተፉ ያደረጉበት ዝግ ምክክር ነበር።

ህወሃት በብቸኝነት በር ዘግቶ በደረገው ምክክር ላይ ዛሬ በተለያየ ጎራ ተከፋፍለው ያሉት የህወሃት አመራሮች በአጠቃላይ በጋራ የተስማሙበት ድምዳሜ፦
1ኛ-ሕዝባዊው አመጽ በአጠቃላይ የህወሃትን ብሎም የትግራይን ህዝብ ጥቅምና ህልውናን በከፍተኛ አደጋ ላይ የጣለ አመጽ ስለመሆኑ
2ኛ-የሁለቱን ክልሎች ትብብራዊ መሳይ አመጽን ወደ ሁለንተናዊ የጋራ አመጽና ትግል እንዳይቀየር ነጣጥሎና የተፈለገውን ሃይል ተጥቅሞ መጨፍለቅና መደፍጠጥ እንደሚያስፈልግ።
3ኛ-የሕዝባዊው አመጽም ዋንኛ ምክንያት በመርህ ደረጃ የውስጣዊ ችግር ውጤት ሳይሆን የውጫዊ ህይል ውጤት መሆኑን በጋራ የተስማሙበት ነበር።
ሆኖም እነዚህ ዛሬ በተለያየ ጎራ ተከፋፍለው ያሉት የህወሃት ከፍተኛ አመራሮች በእነዚህ 3ት መሰረታዊ ነገሮች ልይ የተስማሙ ሆነው ሳለ ያልተስማሙበት ወሳኝ ነጥብም ይዘው ነበር የተገኙት።

ያልተስማሙባቸው ነጥቦችም።
1ኛ-የተፈጠረውን ህዝባዊ አመጽ በማያዳግም ሁኔታ-በተለይም የትግራይን ሕዝብ የወደፊት ህልውናን ከስጋት ግርዶሽ የነጻ ለማድረግ በመፍትሄነት በቀረቡ የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ።
2ኛ-የአገራዊው አመጽ መናኸሪያና መፍለቂያ በሆኑት 2ቱ ክልሎች የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ላይ በሚወሰደው እርምጃ ላይ
3ኛ-አጠቃላይ ሁኔታውን በማን መሪነት ስር ይፈጸም በሚለው ነጥብ ላይ ባለመስማማት የሀሳብ ልዩነት ይዘው ተገኙ። ከዚህ ምክክር በኋላ-አንደኛው የህወሃት ክፍል በድርጅታቸውና በትግራይ ህዝብ ላይ ከፍተኛ አደጋ የፈጠረው ህዝባዊው አመጽ መንስኤ ቀደም ሲል በደፈናው ውጫዊ ሃይል ውጤት ነው ብሎ የተቀበለውን ሃሳብ በመጣል የህዝባዊው ዓመጽ መንስኤ ውስጣዊ ነው የሚል የጸና አዲስ አቋም ይዞ ብቅ ይላል።

በወቅቱ [ይህ አቋም በተንጸባረቀበት ወቅት ማለት ነው] የቢሾፍቱ ጭፍጨፋ በተፈጸመ ማግስት በተነሳ ታላቅ ህዝባዊ ነውጥ ቁጣ በሰበታና በሌሎችም ስፍራ ባሉ ኢንደስትሪዎች ላይ ከፍተኛ ሕዝባዊ ጥቃት በተፈጸመ ማግስት ሲሆን -የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ወታደራዊው ክፍል ተጽእኖ አድራጊነት ያወጁበት ወቅት ነበር።

መጀመሪያ በኦሮሚያ ጊንጪ ከተማ ፈንድቶ አጠቃላይ ኦሮሚያን ያጥለቀለቀው ህዝባዊው አመጽ -በአማራ ክልል-በኮንሶ-በደቡብ ክልሎች በተስፋፋበት ወቅት ሌት ተቀን በመመክር ላይ ያሉት የህወሃት አስኳሎች በማያዳግም ሁኔታ ለሁለት የተከፈሉበት ሁኔታን ፈጠረ። የሀሳብና አቃም ልዩነት የታየበት ነጥብም የትግራይን ህልውና በሚመለከት ነበር።
ድርጅቱ በውስጣዊ ጭንቀትና ውጥረት ተሞልቶ ሌት ተቀን በምክክር እሚነታረክበት አጀንዳ-የትግራይን ህዝብ የወደፊት ህልውና የሚያረጋግጥ መፍትሄ ዛሬውኑ በማያዳግምሁኔታ መውሰድ አለብን በሚለው አቋም ላይ ሲሆን አጠቃላይ አመራሩ በሀሳቡ ላይ ተስማምቶ ግን መውሰድ አለበት በተባለው መፍትሄ ላይ ግን ለመስማማት ሳይችሉ ይቀራሉ።

መነሻ ሶስት-ህወሃትን የሰነጠቀው የትግራይ አጀንዳ።

ህወሃት ዛሬ ያልተለያየ ግን የተሰነጣጠቀ ገዢ ሃይል ነው። ክፍፍሉ የህዝባዊው አገር አቀፍ አመጽ ቢሆንም በዋነኝነት ግን የትግራይ ጉዳይ ሆኖ ተግኝታል። ጄኔራሎቹ-ወ/ሮ አዜብ መስፍንን ይዘው ደሳለኝ ሃይለማርያምን መጋረጃ በማድረግና በጄኔራል ሳሞራ የኑስ መሪነት ለትግራይ ህዝብ የህልውና ስጋት ፍቱን መፍትሔ አለን በማለት ያዘጋጁትን የትግራይን አድን እርምጃ ለመውሰድ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቀው ይገኛሉ። በሌላ ወገን በደህንነቱ ጌታቸው አሰፋ መሪነት ግን በእነ ዓባይ ጸሃዪ ስብሃት ነጋ፣ ወርቅነህ ገበየው መሪነት የሚመራው ወገን ደግሞ እኔ ነኝ ለትግራይ ህዝብ የሚጠቅም የተሻለ አማራጭ መፍትሄ ያለኝ በሚል ጽኑ አቋሙ የሙጢኝ እንዳለ ይታያል።
ሁለቱም ወገኖች የህወሃት ብሎም የትግራይ ህዝብ ህልውና አደጋ ላይ ነው በሚለው እሳቤ ይስማማሉ። የጄኔራሎቹ ቡድን የችግሩ መንስኤ ውስጣዊ ሳይሆን በውጫዊ ህይል የመጣ ነው ብሎ ያምናል። ውጫዊ ህይል ሲል-በኤርትራ ማእከልነት የህወሃትን ህልውና የሚፈታተን ጸረ ህወሃት ሃይል ተፈጥሮ ደርጅቷል ብሎ ያምናል። የህዝባዊው አመጽም ዋና መሃንዲስና ቀያሽ ይህኛው ኤርትራን መደራጃው አድርጎ የተደራጀው የተቃውሞ ሃይል ጡንቻውን የሚያፈረጥምበትን ዓባይን መነሻ ያደረገው የአከባቢው ጂኦፖለቲካን እንደ ማስወንጨፊያ ሮኬት ይመለከተዋል። የግብጽ በአፍሪካ ቀንድ ተስፋፊነት፣ በኤርትራ ቀይ ባህር በእነ ኳታርና ሳኡዲ ዓረቢያ ሃይሎች እጅ መውደቅ ለትግራይ ህዝብ ከታች ከኢትዮጵያ ህዝብ በተነሳ እሳት ከላይ ከሻእቢያ ጋር በተፈጠረ እሳት መውጪያ በሌለው ግን ጠላት በሚሆኑት ሃይሎች ከበባ ስር እንደወደቀ በመቁጠር ይህንን ከበባ ሙሉ በሙሉ መክበቡን ቀጥሎ ቀለበት እስኪያበጅ ድረስ መጠበቅ የለብኝም በሚል እርምጃ ሊወስድ ወስኗል።

የጄኔራሎቹ ስብስብ-የትግራይ ችግር የኤርትራን ችግር በመፍታት መሰረት ያለው መፍትሄ ማምጣት ይቻላል ብሎ ደምድሟል። በሰሜን ያለውን ተጎራባች ከጸረ-ትግራይ ሃይል እጅ ፈልቅቆ ማውጣት ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገውና ለወሳኙ የታላቂቷ ትግራይን ራእይ የሚያስፈጽም ነው ብለው ዓምነውበታል።

ጄኔራል ሳሞራ የኑስ በደህንነቱ አሰፋ ጌታቸው ክፉኛ የተናቀ ግን ውስጡ የቆሰለ ወታደር ነው፡፣ መለስ ልክ የደሳለኝ ሃይለማርያምን የጀርባ ባዶ ታሪክ አጥንቶ ለኮንዶምነት እንደመለመለው ሁሉ-ሳሞራ የኑስም ከትግራይ አናሳ ቢኒዓሚር ተወላጅነቱ በህወሃት ውስጥ ለስልጣን መሰላል የማያበቃ ባዶ ስለሆነ እንደማያሰጋ አይቶና መልምሎ ነው የጦር ሃይሎች ኤታማዦርነቱን ቦታ ሊሰጠው የቻለው። ሳሞራ የጀርባ ድጋፍ የሌለው [በራሱ ተነስቶ አንቱ ለማስባል የሚያበቃ ድጋፍ አለመኖር ማለት ነው]የተናቀ ሆኖ ሳለ በባለ ውለታው አቶ መለስ ዜናዊ ውለታ ለታላቅ ቦታ የበቃ በመሆኑ እድሜ ልኩን የመለስ አምላኪ እና ውለታ መላሽ ወታደር እንደሆነ ይታወቃል። ሳሞራ የኑስ ደሳለኝን እና በስሩ ያሉትን ጄኔራሎች ያዛል፡ የመለስ ሚስት ከኋላ ሆና ሁሉንም ሳሞራ የኑስን፣ ደሳለኝ ሃይለማርያምን እና ግሩፑን በበላይነት ታዛለች። መለስ ከመሞቱ በፊት ለዓመታት ሳሞራ የኑስን በምንሊክ ቤተመንግስት ውስጥ ለ24 ሰዓት ከአጠገቡ በማደርግ ከአዜብ መስፍን ፊት ለፊት ኢንዶክትሪኔሽን ሲያጠምቀው የከረመ ሰው ነው። ሳሞራ በአዜብ በኩል የማቹን መለስ ትእዛዝ ተቀባይና ጠባቂ ሳይሆን በግሉ ለግል ስልጣኑ ተነሳስቶ የክፍፍሉ መሪ ነኝ ቢል ኖሮ 24ሰዓት ባልሞላ ግዜ ውስጥ ዘብጥያ ሲወርድ በታየ ነበር።

ዛሬ ትልቁ የሀይል ሚዛን ይዞ ህወሃትን እየሰነጠቀ ያለው የጄኔራል ሳሞራ የሀይል ምንጭና መንስኤ በሚስቱ ውስጥ የተቀመጠው የመለስ ዓላማና ስልጣን ብቻ ነው። ይህን ሀይል የሚቃወመው የእነ ዓባይ ጸሃዪ ክፍል ህወሃትን እና የትግራይን ህልውና ለከፍተኛ አደጋ የጠላው ህዝባዊው አመጽ መንስኤ ውስጣዊ ነው ነው ብሎ የተሻሻለ አቋም ይዞ የተገኘው ክፍል ነው።
የጄኔራሎቹ ክፍል-ኤርትራን መሰረት ያደረገውን የተቃዋሚ ሀይልና ብሎም የግብጽን ሀይል እየጠነከረ መምጣትን እንዲሁ በዝምታ እደጃችን ድረስ እስኪደርሱ ቁጭ ብለን መጠበቅ የለብንም ባይ ነው። በቀደሞ ማጥቃት [55]በኤርትራ ያለውን ጸረ-ህወሃት ሃይል መደምሰስ ይኖርብናል ብሎ ባመነበት የመፍትሄ እርምጃ ላይ የደህንነቱ ግሩፕ አልተቀበለውም።

የእነ ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ክፍል በኤርትራ ያለውን ህይል መመታት አለበት በሚል ውሳኔ ላይ የደረስነው ከሻእቢያ ጋር ያደረግነው ምስጢራዊ ድርድር ተቀባይነት ባለማግኘቱ የተነሳ ከሀይል እርምጃ በስተቀር ሌላ አማራጭ አጥተናል የሚል አቋም ይዘዋል።
ህወሃት መራሹ ስርዓት ለሕዝብ ይፋ ያልሆነ ድርድር ከሻእቢያ ጋር በተከታታይ አካሄዶ ሊሳካለት እንዳልቻለ ነው እሚታወቀው። በጌታቸው አሰፋ ጋር የተሰለፉት እነ ዓባዪ ጸሃዪ እና ስብሃት ነጋ ክፍል ለሻእቢያ የሚሰጠው ተስጥቶ ከባድመ ጭምር ማለት ነው አሰብን በመመለስ ለትግራይ ሰለማዊ ቀጠና ለመፍጥር የሚፈልጉ ሲሆን ይህን ዓላማቸውን ለመተግበር የሀይል እርምጃ መውሰድ የለብንም ብለው ያምናሉ።
ይህንንም ለማድረግ መንግስታዊ ስልጣንን-ማለትም-የጠ/ሚሩን ቢሮ፣ ፓርላማውን፣ ወታደሩን እና ቢሮክራሲውን በእኛ ቁጥጥር ስር መዋል አለበት በሚል አቋም አገር አቀፉ ህዝባዊ አመጽ ምንጭና መንስኤው ውጫዊ ሃይል ሳይሆን ውስጣዊ ችግር ነው የሚል እድምታ ይዘው ተነስተዋል። የህዝባዊው አመጽ መንስኤ ውስጣዊ ችግር ውጤት ነው ሲሉ የሀይለ ማርያም ደሳለኝን ግብረሃይል አመራር ተጠያቂ በማድረግ የብቃት ማነስና መምራት ያለመቻልን መደምደሚያ በማድረግ ስልጣኑን መቆጣጠር አለብን ባዮች ናቸው። በዚህ የትግራይን ህልውና አድን ዘመቻቸው ላይ የአመራር ስልጣኑ በእኛ ስር መሆን አለበት የለም በእኛ ነው መሆን ያለበት በሚል ሲከፋፈሉ በሁለቱም በኩል አንዱ አንዱን ለመምታት ሙሰኝነትን፣ እና በስልጣን መባለግን እየመዘዙ ሊጠቃቁበት ሲጥሩም እየታየ ነው። ሂደቱም በዘረፋውና በሙስኝነቱ የአንበሳውን ድርሻ ያላቸው የህወሃት ቁልፍ ሰዎች እራሳቸውን ለማዳን ሲሉ የሁለቱን ሀይሎች በገለልተኝነት ለማየትና ወደ አሸናፊው ለመቀላቀል በማድባት ጥበቃ ላይ እንዲገኙ በማድረጉ 3ኛ ተሰንጣቂ ቢያስመስላቸውም ድርጅቱ ግን በሁለት ወሳኝ አንጃዎች መካከል እንደተክፈለ ነው ማወቅ የተቻለው።

ጠቅለል አድርገን ስናየው-በሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ ተመልምሎና ተኮትኩቶ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሙሉ ጄኔራል የተደረገው ሳሞራ የኑስ ሙሉ ታማኝነቱን ለሟች መለስ ት/ት በማድረግ ለወ/ሮ አዜብ መስፍን ታዛዥ በመሆን በተራው የጠ/ሚሩን ቤሮ ደሳለኝ ሃይለማርያምን ስልጣን በመቆጣጠር በአገሪቷ ላይ አሁን የፈላጭ ቆራጭነትን ሚና እየተጫወተ ሲሆን ዋና ዓላማውም የትግራይን ህዝብ ህልውና እና ሁለንተናዊ የበላይነትን [በፖለቲካው፣በኢኮኖሚ፣ በጂኦግራፊያዊ ይዞታ]ለማረጋገጥ-የኢትዮጵያን ህዝብ በጸረ-ሻእቢያና ግብጽ ላይ አስተባብሮ ኤርትራን ሙሉ በሙሉ በመውረር የትግራይ ጥገኛ መንግስትን አስመራ ላይ መስርቶ ለረዥሙ ግዜ የትግራይ ትግሪኛ መንግስት [የአግዓዚያን ግዛትን]ምስረታ መሰረት መጣል በማለት ወስናል። ሻእቢያንም ለመምታት አስተባብሮ ከተጠቀመና በአስመራም የትግራይ ጥገኛ መንግስት ካቋቋመ በኋላ ትግራይ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን ጥገኝነት በጥሶ በትግራይ ትግሪኛ መንግስት ዘመኑን ለመግፋት ወስኗል።
[በቅርቡ አቶ ደሳለኝ ሃይለማርያም የትግራይ ህዝብ ችግር የሚፈታው የኤርትራ ችግር ሲፈታ ነው ያለ ሲሆን ከወራት በፊት ደግሞ የሻእቢያን ስርዓት ለመደምሰስ ልንዘምት ነውም ብሎ እንደነበር አይዘነጋም]

ሁለተኛው ሃይል በእነ ጌታቸው አሰፋ፣ዓባይ ጸሃዪ እና መሰሎቹ የሚንቀሳቀሰው ክፍል በበኩሉ የጄኔራሉን የኋላ ታሪካ [በትግራይ አናሳው ቢኒአሚር ጎሳ ተወላጅነቱ] የተነሳ መንግስታዊው የስራ አስፈጻሚ አመራር በጄኔራሉ ስር ሊውል አይገባም በሚል የጸና አቋም የተሰባሰቡ ናቸው። እራሱ ጌታቸው አሰፋ ጄኔራል ሳሞራ የኑስን በከፍተኛ ንቀትና አልታዘዝ ባይነት ቢያስተናግደውም አቶ መለስ በህይወት እያለ በከፍተኛ ደረጃ ሲናቅ የነበረና በተሰጠውም ስልጣን በአግባቡ እንዳይጠቀም የተደረገ ሰው ነበር። መለስ ጌታቸው አሰፋን አቅመቢስ ለማድረግ በራሱ ሚ/ርነት በሚመራው የደህንነት ጽ/ቤት ውስጥ የጌታቸውን የበታች ሹም ሪፖርት እንዲያደርግለት በማድረግና በማግለል ሲበደል የነበረ ሰው ነው። ዛሬ እንደ እሱ በመለስ ፊት የተነሱ የህወሃት ቁልፍ ሰዎችን ተቀላቅሎ በመለስ ስለተሾመ ብቻ በአቅመቢሱ ደሳለኝ ህይለማርያም እና ከኋላው በሚያዙት እነ ሳሞራ የኑስ አዜብ መስፍን፣ ዓባይ ወልዱ ትእዛዝ አንመራም በሚል የገነኑ ሆነዋል። የትግራይን አድን ዘመቻም እኛ ነን መምራት ያለብን በሚል መንግስታዊ ስልጣንን ለመቆጣጠር እየተፋለሙ ይገኛሉ።

[በዚህ ክፍፍል የአገራችን ቀጣይ እጣፈንታ ምን ሊሆን ይችላል? ማንስ አሸናፊ ሆኖ ሊወጣ ይችላል? ማንም ያሸንፍ ማን ለኛ ለኢትዮጵያውያን የሚያመጣው ፋይዳና ጉዳትስ ምንድነው? የሚለውን ነጥብ እመልስበታለሁ]-