የደህንነቱ መ/ቤት በአዲስ አበባ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሽብር ጥቃት ለማድረስ ማሴሩ ተሰማ

0

ባለፉት ወራት ውስጥ በጎንደርና በባህር ዳር ከአገዛዙ ጋር ቅርበት ባላቸው አካላት ላይ ያነጣጠሩ ተከታታይ ፍንዳታዎች ሲደርሱ ቆይተዋል።

በጎንደር ከተማ በጥቂት ወራት ውስጥ ከአስር በላይ ፍንዳታዎች የተፈፀሙ ሲሆን በእንግዶች ማረፊያ ሆቴል ላይ በደረሰ ፍንዳታ አንድ የውጭ ሃገር ዜጋን ጨምሮ አምስት ሰዎች እንደተጎዱ በወቅቱ መዘገባችን ይታወሳል።

እንዲሁ በባህር ዳርም ጃሽን ቢራ “ባላገሩ” በሚል ስያሜ ለገበያ ያቀረበውን ቢራ ለማስተዋወቅ በተጠራው የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ በፈነዳ ቦንብ ምክንያት አንድ ከሥርዓቱ ጋር ቀረቤታያለው ሰው ሕይወት ሲያልፍ በአራት የፓሊስ አባላት ላይ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰ ይታወቃል።
የፍንዳታዎቹ ተከታታይነት፤ በጥንቃቄ የተጠኑና የታለሙ መሆናቸው እና የጎንደርና የባህርዳር ነዋሪዎች ለፍንዳታ ፈፃሚዎቹ በጎ ስሜት ያላቸው መሆኑ የአገዛዙን የደህንነት መሥሪያ ቤት በእጅጉ ያሣሰበ መሆኑን የውስጥ መረጃዎች አመልክተዋል።
በመሆኑም በሥርዓቱ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቆም ወይም የሕዝቡን ስሜት ለማስቀየር መወሰድ በሚገባቸው እርምዳዎች ላይ ምክክር ሲደረግበት መቆየቱን ከደህንነቱ መሥሪያ ቤት የሾለከው መረጃ ያመለክታል።

በዚሁ የሴራ ስብሰባ ላይ ለደህንነት መሥሪያ ቤቱ ስጋት መባባስ ውጫዊ ምክንያቶችም መኖራቸው በስፋት ተነስቷል። የአሜሪካና የእንግሊዝ ኤምባሲዎች ለዜጎቻቸው ባወጧቸው መግለጫዎች ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እንዳይንቀሳቀሱ የጉዞ ማስጠንቀቂያዎች ሰጥተዋል።

የአገዛዙ የደህንነቱ መሥሪያ ቤት ወደፊትም አዲስ አበባም ተመሳሳይ ጥቃት ሊደርስባት ይችላል የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱን የጠቀሱት ምንጮች በስብሰባው ላይ ለዚህ በመፍትሄነት ከቀረቡት አስተያየቶች አንዱ የደህንነቱ መሥሪያ ቤት አዲስ አበባ ውስጥ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ቦምብ በማፈንዳት እና ሰላማዊ ዜጎችን በመፍጀት በአርበኞች ግንቦት 7 ላይ ማላከክ ነው መባሉን ይገልጻሉ። በመሆኑም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዘወትር እንቅስቃሴዓቸው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መረጃ አቅራቢዎቹ አሣስበዋል።

አገዛዙ እንዲህ ዓይነት ድምዳሜ ላይ የደረሰው ዛሬ በጎንደርና በጎጃም የሚታየው ሕዝባዊ አመጽ ነገ አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ መላው ኢትዮጵያ እንደሚሰራጭ ስለሚያውቅ ነው ያሉት አንድ ከፍተኛ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር የአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ከሽብርተኛው የህወሓት አገዛዝ ራሱን እንዲጠብቅና ለተባበረችና ፍትህ ለሰፈነባት ኢትዮጵያ ከድርጅታቸው ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።